Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርት‹‹ፌዴሬሽኑ ያወጣውን መመርያ ለውይይት ያቀረበው በጠቅላላ ጉባዔ ካፀደቀ በኋላ ነው›› አሠልጣኝ አቶ...

‹‹ፌዴሬሽኑ ያወጣውን መመርያ ለውይይት ያቀረበው በጠቅላላ ጉባዔ ካፀደቀ በኋላ ነው›› አሠልጣኝ አቶ ተሰማ አብሺሮ

ቀን:

የዘመኑ አትሌቲክስ በቴክኖሎጂና በሳይንሳዊ መንገድ እየታገዘ አጀማመሩ ላይ የነበረው የማጠናቀቂያ ሰዓት እየተሻሻለ መምጣት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ የሥልጠናው ሒደት በተለያዩ የሥልጠና ሥልቶችና ሥልጠና በሚሰጡ ድርጅቶች እየታገዘ፣ በውድድሮች ላይ ሪከርዶች እንዲሰበሩ አስችሏል፡፡ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ከትራክ ይልቅ ወደ ከጎዳና ውድድሮች ፊታቸውን አዙረዋል፡፡ በአትሌቶች መካከል ካለው ፉክክር በዘለለ፣ የትጥቅ አምራቾች ጭምር አዲስ የመሮጫ ጫማ ይፋ ለማድረግ ውድድር ውስጥ ከገቡ ሰነባብተዋል፡፡ አትሌቶች ከትራክ ወደ ማራቶን ውድድሮች የሚሸጋገሩበት ሒደት ተቀይሮ፣ ቀጥታ ወደ ጎዳና ውድድሮች መሸጋገር ጀምረዋል፡፡ ዓለም አቀፍ የጎዳና ውድድሮች የሚያሰናዱ አገሮች ለአሸናፊ አትሌቶች የሚከፍሉት ገንዘብ ጨምሯል፡፡ የዘመናዊ አትሌቲክስ ውድድር ላይ ተካፋይ የሆኑት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በማዘወተሪያ ሥፍራ ዕጦት እየተፈተኑም ቢሆን በተለያዩ መድረኮች  እየተካፈሉ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ አትሌቶች ጀርባ ያሉት አሠልጣኞች ሚናም የጎላ መሆኑ ዕሙን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ስኬታማ አሠልጣኞች መካከል አንዱ የሆኑት አሠልጣኝ ተሰማ አብሽሮ ከ100 በላይ ሠልጣኞችን በማሠልጠን ላይ ይገኛሉ፡፡ ስለአጠቃላይ ወቅታዊ አትሌቲክስ ሁኔታ በተመለከተ ዳዊት ቶሎሳ ከአሠልጣኝ ተሰማ አብሺሮ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ እንቅስቃሴና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ያለበት ደረጃ ምን ይመስላል?

አቶ ተሰማ አትሌቲክስ ያለበት ሁኔታ አዳዲስ ክብረ ወሰኖች እየተሰበሩ፣ ፈጣን ሰዓት እየተመዘገበና እየተሻሻለ ነው፡፡ ይህንን ያደረገው ሳይንሱ ነው፡፡ ከ20 ዓመታት በፊት የነበሩ ነገሮች አብዛኛዎቹ ተቀያይረዋል፡፡ ውድድሮቹ ሳይንትፊክ መንገዶችን ተከትለው እየተከናወኑ ነው፡፡ አዲዲስ ጫማዎች መጥተዋል፡፡ እንዲሁም ዘመናዊ የልምምድ መንገዶች ተፈጥረዋል፡፡ የሌላው ዓለም አትሌቲክስ ተለውጧል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ግን ተለውጧል ማለት ይከብዳል፡፡

- Advertisement -

ሪፖርተር፡- የዓለም አቀፍ አትሌቲክሱ ያለበት ሁኔታ ተለውጧል ካልን፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከሌላው እኩል አልተለወጠም ማለት እንዴት ይቻላል?

አቶ ተሰማ፡- የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከሌላው ዓለም አትሌቲክስ አንፃር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ የማዘውተሪያ ሥፍራ ቅንጡት እየሆነ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ወክለው በዓለም ሻምፒዮናና ኦሊምፒክ ላይ የሚካፈሉ አትሌቶች የመለማመጃ ትራክ እንኳን የላቸውም፡፡ አትሌቶቹ ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት ሲያደርጉ እንኳን አንድ ለእናቱ የሆነው የኢትዮጵያ ስፖርት አካዴሚ ትራክ ሲጠቀሙ የነበረው በፈረቃ ነበር፡፡ ለማራቶን ዝግጅትም አብዛኛውን ልምምድ የምናደርገው በሰንዳፋና በሰበታ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ አትሌቶች እየተጎዱ ነው፡፡ የመኪና አደጋ እያጋጠማቸው ነው፡፡ በማዘውተሪያ ዕጦት ምክንያት አትሌቶችን እያፈራን ነው ማለት አይቻልም፡፡ ይኼ ማለት ተተኪ አትሌቶችን ማፍራት አይቻልም ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ከዚህ በፊት በትራክ ውድድሮች ላይ ያሳካናቸውን ውጤቶች፣ ከዚህ በኋላ እናመጣቸዋለን ማለት ይከብዳል፡፡ በአትሌቲክሱ ቀጣይነት ያለውን ውጤት ለማምጣት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በርካታ ትራኮችን መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ሌላው በቂ የሆነ የአትሌቲክስ ባለሙያ የለንም፡፡ አሁን ላይ የዓለም አትሌቲክስ ባለበት ደረጃ፣ እኛ የተሟላ ነገር አለን ማለት አይቻልም፡፡

ሪፖርተር፡- ከኢትዮጵያ አትሌቶች ጋር ከሚፎካከሩ አገሮች መካከል ኬንያ ትጠቀሳለች፡፡ ኢትዮጵያ ያላሟላችው፣ በአንፃሩ ኬንያ የምትሻልበት መሠረታዊ ንፅፅር ምንድነው?

አቶ ተሰማ፡- ኢትዮጵያ ከማን ጋር ተወዳደራለች? በኢትዮጵያ ውስጥ ለአትሌቲክሱ ተሟልቷል ሊባል የሚችለው ነገር ለውድድር የሚቀርብ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ከኢትዮጵያ አትሌቶች ጋር የምትፎካከረው ኬንያ፣ በየመንደሩ የመሮጫ ትራክ ወይም ልምምድ ማድረጊያ የአሸዋ ትራክ አላት፡፡ የኬንያ ስፖርት ኮሚሽን አትሌቲክሱ ላይ ኢንቨስት ያደረገው ከኢትዮጵያ በጣም ይልቃል፡፡ በኬንያ፣ ናይሮቢና በኤልዶሬት ያላቸውን ትራክና የልምምድ ሥፍራ ተመልክቻለሁ፡፡ ለውድድርና ለልምምድ የተለያዩ ሥፍራዎችን አሰናድተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ ያላት ውጤትና የተሟላላት መሠረተ ልማት ተመጣጣኝ አይደለም፡፡ ጂቡቲ በአትሌቲክስ ተሳትፎ እምብዛም ነች፡፡ ግን ሁለት የመለማመጃ ትራክ አላት፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ከሌሎቹ አንፃር በጣም ወደ ኋላ የቀረች ነች፡፡ በኢትዮጵያ ከተለያዩ የክልል ከተሞች የተወጣጡ በርካታ ድንቅ አትሌቶች ተመልክተናል፡፡ እነዚህ አትሌቶች ግን ስኬታማ የሆኑት፣ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ተሟልቶላቸው አይደለም፡፡ ስለዚህ የምንጓጓለትን አትሌቲክስ በስኬት እንዲቀጥል፣ በአትሌቲክስ መሠረተ ልማት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ይኖርብናል፡፡

ሪፖርተር፡- በርካታ አትሌቶች በትራክ ላይ ቆይታ ሳያደርጉ፣ በቀጥታ ወደ ማራቶን ውድድር ሲገቡ መመልከት እየተለመደ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ምንድነው?

አቶ ተሰማ፡- አንድ አትሌት ወደ ሩጫ ሲመጣ ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ታሳቢ አድርጎ ነው፡፡ አንደኛው አገሩን ወክሎ በሚሳተፍባቸው ውድድሮች ላይ አገሩን ለማሳወቅ፣ ሁለተኛው ራሱን ለማሳወቅና ሦስተኛው የገንዘብ አቅም ለመፍጠር ነው፡፡ በወቅታዊው ሁኔታ በትራክ ውድድር ላይ ስኬታማ ሆነው የቆሙለትን ዓላማ የሚያሳኩት ጥቂቶች ናቸው፡፡ ጥቂት ውጤታማ አትሌቶች ብቻ ናቸው ተከፋይ የሚሆኑት፡፡ አምስተኛና ስድስተኛ ደረጃን ይዘው ያጠናቀቁ አትሌቶች ምንም ዓይነት ገንዘብ ሊያገኙ አይችሉም፡፡ አብዛኛዎቹ ሽልማት ያላቸው ውድድሮች ወደ ጎዳና መጥተዋል፡፡ ለምሳሌ በግማሽ ማራቶን፣ በማራቶን፣ እንዲሁም በጎዳና ውድድሮች ላይ የሚካፈሉ ተሳታፊዎች እያንዳንዳቸው ክፍያ ይከፍላሉ፡፡ ከዚያ የሚሰበሰበው ገንዘብ ለአትሌቶች እንደ ደረጃቸው ይከፈላቸዋል፡፡ አንድ አትሌት በትራክ ውድድር ተካፋይ ለመሆን እነ ለተሰንበት ግደይ፣ ጉዳፍ ፀጋዬና ሰለሞን ባረጋ የደረሱበት ደረጃ መድረስ ግድ ይለዋል፡፡ እዚያ ደረጃ ለመድረስ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች የልምምድ ትራክ ዕጦት ፈተና ይሆንበታል፡፡ በዚህም ምክንያት አሠልጣኞች አትሌቶች ቀጥታ ወደ ማራቶን ከመግባታቸው በፊት፣ በትራክ ላይ አሳልፈው ወደ ጎዳና ውድድሮች እንዲገቡ ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ አትሌቶች ቀጥታ ወደ ጎዳና ውድድር ለማሳተፍ ይገደዳሉ፡፡ ሌላው የጎዳና ውድድሮችን የሚያዘጋጁት የዓለም አገሮች፣ በማራቶን ውድድር ወቅት ከተሞቻቸው በቀጥታ በቴሌቪዥን እንዲታዩላቸው ፍላጎት ስላላቸው ከፍተኛ ገንዘብ ይከፍላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ከጊዜ ወደ ጊዜ የማራቶን ሰዓቶች በፍጥነት እየተሻሻሉ ሲመጡ እየተመለከትን ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በዘንድሮ የበርሊን ማራቶን ኬንያዊው ኤሎድ ኪፕቾጌ ክንዱ ላይ ያደረገው ተለጣፊ ችብስ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር፡፡ በአጠቃላይ የጎዳና ሩጫ ሰዓቶች በፍጥነት መሻሻል ምን አዲስ ነገር እየፈጠረ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ተሰማ፡- የማራቶን ፈጣን ሰዓት የጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ 2፡12:11 ነበር፡፡ በሒደት በበላይነህ ዴንሳሞ፣ ፖልቴርጋት፣ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ እንዲሁም ኤሎድ ኪፕቾጌ እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ በየጊዜው የመሮጫ ጫማ እየተሻሻለ መጥቷል፣ በዚያው ልክ ደግሞ ጫማውን የሚያመርቱ ካምፓኒዎች ስፖንሰር ያደረጓቸው አትሌቶች እንዲያሸንፉ በመፈለጋቸው ፉክክር ውስጥ ገብተዋል፡፡ ስለዚህ ጫማዎች ላይ እየተሠሩ ያሉ ማሻሻያዎች የረቀቁና ሳይንሳዊ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ይኼም አትሌቶች ምንም ነገር እንዳይሰማቸውና በምቾት እንዲሮጡ አስችሏቸዋል፡፡ የኪፕቾጌ በዘንድሮ የበርሊን ማራቶን ወቅት እጁ ላይ አድርጎት የነበረው ‹‹ቺብስ››፣ አሜሪካ አገር ባለ የሕክምና ተቋም አንድ ሰው በ42 ኪሎ ሜትር … ምን ያህል የስኳር መጠን ያቃጥላል? ምን ያህል ካሎሪ ያቃጥላል? እንዲሁም ምን ያህል ውኃ ሊጠቀም ይችላል? የሚለውን ለማጥናት የተጠቀመው ነበር፡፡ ይኼ ድርጅት መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገና በጤና ዙሪያ ጥናት የሚሠራ ሲሆን፣ በርካታ ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድሮችን በዋነኛነት ስፖንሰር ያደርጋል፡፡ በዚህም ሥሌት መሠረት አትሌቱ ያወጣውን የካሎሪ መጠን እንዴትና በምን መጠን መተካት አለበት? የሚለውን መልስ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡ አትሌቱም የፈጀውን አቅም ለማወቅና የአመጋገብ ሥርዓቱ ላይ እንዲያሻሻል ይረዳዋል፡፡ ስለዚህ ነባራዊ ሁኔታዎች በሳይንሳዊ ጥናት መደገፋቸውንና ምቹ ጫማዎች መምጣታቸው ሰዓቶች በፍጥነት እንዲሻሻሉ አስችሏቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በርካታ አትሌቶች እርስዎ ሥር ከመሠልጠናቸው ባሻገር፣ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ተቋማት ጋር በቅንጅት እንዲሠሩ ተደርጓል፡፡ አትሌቶቹ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ተቀናጅተው እንዲሠሩ የሚደረግበትን ሒደት ቢያብራሩልኝ?

አቶ ተሰማ፡- በእኔ ሥር ከ800 ሜትር እስከ ማራቶን ርቀቶች እየሠለጠኑ የሚገኙ ከ100 በላይ አትሌቶች አሉ፡፡ አትሌቶቹን ከአገር አቋራጭ፣ ከወጣቶች ውድድር፣ እንዲሁም የአትሌቶችን ተክለ ሰውነትና እንቅስቃሴን በመመልከት የተመለመሉ ናቸው፡፡ ለአትሌቶቹ ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ አትሌቶቹን የሚያጓጉዙ አውቶብሶች፣ የአትሌቶቹን ጉዳይ የሚያስፈጽሙ የቢሮ ሠራተኞች፣ የአትሌቶችን የቪዛ ጉዳይ የሚያስፈጽሙና የማሳጅ ሥራን የሚሠሩ ሠራተኞች አሉን፡፡ ከዚህ ባሻገር ከአትሌቶቹ ጋር የሚኖረን ስምምነት፣ አትሌቶቹ በውጭ አገር ውድድር ላይ ተሳትፈው ከሚያገኙት ገንዘብ 15 በመቶ ለማኔጅመንት በሚከፍሉት ክፍያ መሠረት ነው፡፡ መቀመጫውን ኔዘርላንድ ያደረገው ግሎባል ስፖርት ኮሙዩኒኬሽን 15 በመቶ ክፍያ ቆርጦ፣ በሥሩ ለሚገኙ 70 ሠራተኞች ክፍያ ይፈጽማል፡፡ እኔ ከሠራተኞቹ አንደኛው ስለሆንኩ ከሚገኘው ድርሻ ላይ ለአገልግሎት ደመወዝ ይከፍለኛል፡፡ ይኼ ድርጅት ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ለተሰንበት ግደይ፣ ኪፕቾጌና አልማዝ አያና የመሳሰሉትን አትሌቶች ሲያስተዳድር የቆየ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የግሎባል ስፖርት ኮሙዩኒኬሽንና የ‹‹ኢኤንኤን›› ሩጫ ሚና ምንድነው?

አቶ ተሰማ፡- ድርጅቱ በተለያዩ አገሮች አሠልጣኞች ያሉት ሲሆን፣ አትሌቶችን የመለምላል፣ አትሌቶቹ ለውድድር ብቁ እስኪሆኑና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ እንዲካፈሉ ሙሉ ወጪ ችሎ ዕድሎችን ያመቻቻል፣ አትሌቱ ገንዘብ ማግኘት ሲጀምር ከተገኘው ገንዘብ ላይ 15 በመቶውን ይቆርጣል፡፡ ሌላው አትሌቶች ጉዳት ሲያጋጥማቸው አስፈላጊውን ወጪ ሸፍኖ ያሳክማል፡፡ በተጨማሪም ከትጥቅ አምራቹ ‹ናይኪ› ጋር ተዋውሎ ትጥቃቸውን ያሟላል፡፡ ‹‹ኢኤንኤን›› ሩጫ የግሎባል ስፖርት ኮሙዩኒኬሽን አንደኛው አጋር ሲሆን የአትሌቶች የመድን ድርጅት ነው፡፡ ይኼ ተቋም አትሌቶች ጉዳት ሲገጥማቸው ሕክምናቸውን ከመሸፈን በዘለለ፣ አዳዲስ አትሌቶች ሲመጡ ለኪሳቸው የሚሆን ገንዘብ ያመቻቻል፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ለአትሌቶች ውድድር ማመቻቸት ማስመዝገብና የትራንስፖርት ወጪዎችን ይሸፍናሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ‹ከብሔራዊ ቡድን አትሌቶችና አሠልጣኞች ምርጫ፣ እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ አዲስ መመርያ ይፋ አድርጓል፡፡ በመመርያው ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?

አቶ ተሰማ– መመርያዎች በተለያዩ ጊዜያት ይወጣሉ፡፡ አብዛኛውን መመርያዎች ሲወጡ የተወሰነ ቡድንን (ግሩፕን) ብቻ የሚጠቅሙ ሆነው ነው የሚወጡት፡፡ ለምሳሌ አሠልጣኝን በተመለከተ በልምድ ከፍተኛ ደረጃ የደረሱ አሉ፡፡ ሌላው ደግሞ በአንፃሩ በትምህርት ከፍተኛ ደረጃ የሚደርሱም አሉ፡፡ ሆኖም ሁለቱም መገምገም ያለባቸው በዓለም ሻምፒዮን፣ እንዲሁም በኦሊምፒክ ባመጡት ውጤት መሠረት መሆን አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ መመርያው በይበልጥ የትምህርት ወረቀት ያላቸውን የሚጠቅም ነው፡፡ በአንፃሩ ከዚህ ቀደም የትምህርት ወረቀት ያላቸው አሠልጣኞች በተለያዩ ጊዜያት ዕድል አግኝተው ውጤታማ መሆን የቻሉ በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ ለምሳሌ ስድስት አትሌቶች የተሰጠው አሠልጣኝ ከአምስቱ አንዱን ብቻ ውጤታማ ካደረገ፣ ሌሎቹስ የት ደረሱ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ በልምድ ሪከርድ መስበር የቻሉ አሠልጣኞች አሉ፡፡ ስለዚህ መመርያው ልምድ ያካበቱ አሠልጣኞችን የሚያገል ነው፡፡ ስለዚህ መመርያው ሲተገበር ግራና ቀኙን ተመልክቶና አጢኖ መሆን ይኖርበታል፡፡ የብሔራዊ አትሌቶችን ምርጫ በተመለከተ በግልጽ ያልተቀመጡ ነጥቦች አሉ፡፡ ለምሳሌ የዓለም ዘርፍ የኋላዋ በኦሪገኑ የዓለም ሻምፒዮና መመረጥ አለባት ስንል፣ አንድ ማራቶን ብቻ ነው የተካፈለችው ተብሎ ሳትመረጥ ቀረች፡፡ ስለዚህ በመመርያው ላይ ‹‹በአንድ ውድድር ላይ የተካፈለ አይመረጥም›› የሚል ግልጽ የሆነ ነጥብ መቀመጥ አለበት፡፡ በተጨማሪም መመርያውን ወደ ውይይት ያመጡት በጠቅላላ ጉባዔ ካፀደቁ በኋላ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከልምምድ ቦታ ዕጦት ባሻገር በሥልጠና ሒደት ላይ ፈታኝ የሆነባቸው ጉዳይ ምንድነው? 

አቶ ተሰማ፡- በሥልጠና ሒደት በጣም ፈታኝና አስቸጋሪ እየሆነብን የመጣው ጉዳይ፣ ወንድ አትሌቶች በሴት አትሌቶች ላይ መመርኮዝ መጀመራቸው ነው፡፡ ሴት አትሌቶች በባሎቻቸው የሚደርስባቸው ጫና ፈተና እየሆነብን ነው፡፡ እንደዚህ ስንል ሁሉም ባሎች ጫና እየፈጠሩብን ነው ማለት አይደለም፡፡ ሆኖም አንዳንድ የሴት አትሌቶች ባሎች፣ አትሌቶቹን በፈለግነው መንገድ እንዳናሠለጥናቸው ጫና እያደረጉብን ነው፡፡ ወንዱን አትሌት በሴቷ አትሌት መንገድ እንዲሠራ ስትነግረው ፈቃደኛ አለመሆኑ ይታያል፡፡ ሌላው የማዘውተሪያ ሥፍራ ነው፡፡ የዕለት ከዕለት የሥልጠና መርሐ ግብር ካወጣን በኋላ፣ የምንሠራበት ቦታ ስናጣ ሁሉንም ዝግጅት ያበላሽብናል፡፡ ለምሳሌ ሱልልታ ባለው የቀነኒሳ የመሮጫ ትራክ ላይ ልምምድ እናድርግ ብንል፣ ለ100 አትሌቶች በሳምንት ሁለት ጊዜ መክፈል ከባድ ነው፡፡ ሌላው ችግር ኦሊምፒክና ዓለም ዋንጫ ሲደርስ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን መካከል ያለው ውዝግብ ነው፡፡ እነዚህ ውድድሮች ሲቃረቡ የሚሰጡ ውሳኔዎች ለኦሊምፒክ አትሌት ያበቃን አሠልጣኝ፣ እንዲሁም አትሌቱን ሳይቀር የሚሰብር ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...