በፉፉ ሞጆ
እንዲህ ዓይነት ሙያዊ ጭብጦች ዙርያ ጽሑፍ አቅርባችሁ ዓለም ዓቀፋዊ ኅትመት ለምሳሌ ጆርናሎች (Journals) ላይ ይታተምልኝ ብትሉ፣ ምን አዲስ ዕውቀት አለውና ይሏችኋል፡፡ ገንዘብ ከፍላችሁ ያሳተማችሁት የገዛ አገራችሁን ጽሑፍ እንደገና ከፍላችሁ የምታነቡባቸው ዓለም አቀፍ ጆርናሎች፣ እንዲህ ያለ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለው ጉዳይ ከፍላችሁም ቢሆን አያውጡላችሁም፡፡ አገራዊ የሆኑ የራሳችንን ልሳኖች ልጠቀም ብትሉ ደግሞ የሉንም ማለት ይቀላል፡፡ ጋዜጦቻችንም ቢሆኑ ሲበዛ ሙያዊ ጉዳይ ነው ይሉና ዞር ያደርጉታል፡፡ ወደ ባለቤት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ብትልኩት አጀንዳቸው እስካልሆነ ዞር ብለው አያዩትም (ምን አገባን ዓይነት ነገር)፡፡ ወይም በራሳቸው መንገድ አጥንተውና ሰንደው አያሳውቁንም፡፡ ወደ አባባና ጋሼ ጋ ብትሰዱት፣ ስለማየታቸው ይቅርና ስለመድረሱ እንኳን የምታረጋግጡበት መንገድ የለም፡፡ ችግሩ መሠረታዊ ነውና የልማት ዕቅዶቻችን ውስጥ መታየቱን ይቀጥላል፡፡ በመሀል አገሪቱ እየተጎዳች ነው፡፡ ለነገሩ እኮ በየትኛውም ደረጃ፣ በየትኛውም ትምህርት ቤት ስለጉዳዩ መማሬን እንኳን አላስታውስም፡፡ የጨነቀ ዕለት እንዲሉ የጋዜጣ ዓምደኛ አደረገን፡፡ ይሁንና ግን በተቃራኒው፣ ዓለም አቀፋዊ ጆርናሎች ላይ ካሳተምኩዋቸው በርካታ ጽሑፎች ይልቅ፣ በጋዜጣ ያወጣሁት አንድና ሁለት ዘገባ ከፍተኛ አንባቢና ምላሽ ሲያገኝ፣ ለውጥ ሲፈጥር በመታዘቤ ይሁን አልኩ፡፡ ሳይደግስ አይጣላም ነው ነገሩ፡፡ በነገራችን ላይ ሬዲዮቻችንና ጋዜጦቻችን ለምሳሌ ሪፖርተር ለምን መስኖ ልማት፣ ግብርናና አርብቶ አደር ዓይነት ዓምድ እንደማይኖራቸው ይገርመኛል፡፡ መሠረት እንደሆኑ አይታወቅ ይሆን? ፋይዳቸው ከሌላው አንሶ ነውን? በግራ ጎኔ ነው እንዴ የተነሳሁት፣ ተነጫነጭኩኝ እኮ… የምትነጫነጭበት አያሳጣህ (ምርቃት እኮ ነው)፡፡
ወደ ርዕሰ ጉዳያችን ስመለስ ይህ መጣጥፍ ‹‹በእኔ የምለው›› ዓምድ ሥር ያለ መስኖ ንቁ ተሳትፎ፣ የአሥር ዓመቱ ዕቅድ ግቡን አይመታም (https://www.ethiopianreporter.com/111887/) በሚል ከዚህ በፊት በወጣሁት ጽሑፌ በግርድፉ ነካክቼው ያለፍኩ ቢሆንም፣ እጅግ ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ ለማብራራትና በማኅደርነት ለማስቀመጥ ፈለግኩኝና ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ሙያዊ ክርክሮችን ከቆሰቆሰልን ይበቃናል፡፡ የበፊቱ መጣጥፍ ቀጣይ አድርጋችሁ ውሰዱት፡፡
ስለመስኖ ልማት አገራዊ ፋይዳ መናገር አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡ የመስኖ ልማትን መገንባት ብዙ ገንዘብ፣ መሬት፣ የማኅበረሰብ ተሳትፎ፣ ውኃ፣ ኃይል፣ ወዘተ ይጠይቃል፡፡ እጅግ ሲበዛ ውድ መሠረተ ልማት ቢሆንም፣ የአገር ህልውና እንደመሆኑ ብዙ ወጪ ይጠይቃል ብሎ ገሸሽ ማድረግ ፍፁም አይቻልም፡፡ ባይሆን በልካችን መገንባት እንችል ዘንድ ግልጽ ባለ መረጃ ሊደገፍ ይገባዋል፡፡ ከልኩ ካለፈ ብዙ ገንዘብ ይፈጅብናል፡፡ ከሚፈለገው በታች ከሆነም ደግሞ የሚፈለገውን አገራዊ ድጋፍ መወጣት አይችልምና የዚህ መጣጥፍ ዓላማ፣ ለመሆኑ ኢትዮጵያ ምን ያህል በመስኖ የለማ መሬት ያስፈልጋታል? ለየትኞቹ የሰብል ዓይነቶች ቅድሚያ መስጠት አለብን? በምን መጠን ልናለማ ይገባናል? መነሻ መርሆዎቻችን ምን መሆን አለባቸው? እንዴት ይወሰናል? ወይም ይሠላል? ወዘተ. ጉዳዮችን ማሳያ የምትሆን ፍንጭ ለመወርወር ሲሆን፣ ከኃዛዊ መረጃዎች ጋር እያዛመድኩ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ የጋዜጣ ዓምድ ነውና መጣጥፉ በተቻለ መጠን ድርቅ ያለና አሰልቺ እንዳይሆንባችሁ ጥረት አደርጋለሁ፣ እሞክራለሁ፡፡
አንድ ገበሬ እህል የሚያመርተው ለቤተሰቡ የሆድ ፍጆታ ሲሆን፣ ከተረፈው ብቻ ወደ ገበያ ያወጣል፡፡ በምግብ ራስን ችሎ ከተቻለ ገቢ ለማግኘት፣ እንደ ቤተሰብ ከተመለከትነው የአገሮችም ሆነ የእያንዳንዱ ማኅበረሰብ የህልውና መሠረት በምግብ ራስን መቻል ስለሆነ፣ የምግብ ሰብሎችን ማምረትና እንስሳት ዕርባታ የግብርና ተቀዳሚ ግብ ይሆናሉ፡፡ ቀጥታ ለአገር ውስጥ ገበያ የሚቀርቡ ሰብሎችም ሆኑ እንስሳት፣ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ውጤቶች በሙሉ አገር ውስጥ እስከተመገብናቸው ድረስ በምግብ ራስን መቻል በሚለው ግብ ሥር የሚቀመጡ ናቸው፡፡ የተረፉት ነው እንግዲህ ለአገር ውስጥና ውጭ ገበያ የምናቀርባቸው፡፡ ለአገር ውስጥ ገበያ ካልን ደግሞ ምግብ ላልሆኑ ኢንዱስትሪዎችና ለእንስሳት መኖነት የሚውሉ ናቸው፡፡ ወደ ውጭ የሚላኩትን እንዲሁ ለምግብነት፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለእንስሳት መኖ፣ ወዘተ ግልጋሎት ይጠቀሙባቸው ዘንድ በሽያጭ እንልክላቸዋለን ማለት ነው፡፡ መስኖ በምግብ ራስን መቻል፣ ለአገር ውስጥ ገበያና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ሰብሎችን ለማምረት ያገለግለናል፡፡ እንደ መነሻ በምግብ ራስን መቻል በሚለው ግብና በሰብሎች ላይ ብቻ አተኩራለሁ፡፡
አንደኛ በምግብ ራስን መቻል ማለት አገሪቱ በምድሯ አቅፋ ለምታኖራቸው ሕዝቦችና እንስሳት በቂ ሰብልና መኖ እያፈራች የመቀለብ ብቃቷን ያመለክተናል፡፡ ሁሉም ኅብረተሰብ የሚያስፈልገውን የምግብ ዓይነትና መጠን በአገር ውስጥ ማምረት መቻል ነው፡፡ ሥሌቱን ብዙ ውስብስብ ጉዳዮችን እንደ መያዙ፣ ነገሮችን ግልጽ ለማድረግና ለማቅለል ሲባል ብዙ ብዙ ታሳቢዎችን መሠረት ማድረጉ አይቀርም፡፡
ሁለተኛ አንድ ሰው በቂ ምግብ አገኘ የሚባለው ምንና ምን ያህል ቢመገብ ነው? የሚለው ቀላል መሳይ ግን ውስብስብ ጥያቄ ላይ ከስምምነት መድረስ ግድ ይለናል፣ ቁልፍ ስለሆነ፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ኢትዮጵያን የሚወክል የጋራ ድምዳሜ አልነበረንም፡፡ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (Ethiopian Public Health Institute, 2022-Food-Based Dietary Guidelines of Ethiopia) አንድ ዕድሜው ሁለትና ከዚያ በላይ የሆነ ኢትዮጵያዊ ሊከተል የሚገባውን የምግብ ሥርዓት በተመለከተ፣ አመጋገባችንንና ዓለም አቀፍ የምግብ ድርጅት (FAO) መርሆችን መሠረት አድርጎ በቅርቡ ባሳተመው መመርያ ውስጥ የተዘረዘረው የሚያግባባን ይመስለኛል፡፡ አማራጭስ አለን እንዴ? በሚከተለው ሠንጠረዥ 1 ውስጥ ቀርቧል፡፡
ሰንጠረዥ 1 ቁልፍና ወሳኝ ሆኖ ስላገኘሁት ሙሉውን አቀረብኩት፡፡ ለየትኛውም የልማት ዘርፍ፣ የምርምር ሥራ፣ ለማስተማሪያነት፣ ለቀበሌ ሱቅ ኃላፊ፣ ለመሐንዲስ፣ ለሐኪም፣ ለኢኮኖሚስት፣ ለፖለቲከኛ፣ ለነጋዴ፣ ለባለ ኢንዱስትሪ፣ ለገበሬ፣ ለውጭ ባለሀብት፣ ለሚኒስትር፣ ለፕሬዚዳንት፣ ለአገር፣ ለአኅጉር፣ ወዘተ. መነሻ መሠረት ሆኖ የሚያገለግል ነው፡፡ ያለዚህ መረጃ ለሕዝብና ማኅበረሰብ አገልግሎት ተብሎ ሊታቀድ ወይም የሚታቀድ ነገር የለም፡፡ ቀደምት የልማት ዕቅዶቻችን በሌላ አገር መረጃዎች ላይ የተንጠለጠሉ በመሆናቸው፣ ለቀጣይ ሥራና ለሌሎችም ተደራሽ እንዲሆን ማቅረቡን መረጥኩ፡፡ የአመጋገብ ሁኔታዎች ላይ ልዩነት ሊኖር ይችላልና ማመሳከር ጥሩ ነው፡፡
ሰንጠረዥ 1 ዕድሜው ሁለትና ከዚያ በላይ የሆነ ኢትዮጵያዊ በየቀኑ እንዲመገብ የሚመከረው የምግብ ዓይነትና መጠን (ከሰነዱ የተሰበሰቡ፣ ትርጉም የጸሐፊው) ነው፡፡
ሰንጠረዥ 1
የምግብ ዓይነት |
ለአንድ ሰው በቀን የተመከረ መጠን፣ ግራም |
ለስሌት የተወሰደ መጠን፣ ግራም |
ለአንድ ሰው በዓመት የሚያስፈልገው፣ ኪሎ ግራም |
ምሳሌ ሰብሎችና ምግቦች |
በአገራችን የአመጋገብ ዘይቤ |
ብራ አገዳ እህሎች (Grains, white roots and tubers) |
570 (400-650) |
500 |
182.5 |
ስንዴ፣ በቆሎ፣ ጤፍ፣ ካሳቫ |
1 እንጀራ ወይም 1 ከግማሽ ዳቦ (ሶስት ጊዜ) |
ጥራጥሬዎች (Pulses) |
90 (80-115) |
90 |
33 |
ቦሎቄ፣ አኩሪ አተር፣ ሽንብራ፣ ምስር |
አንድ ጭልፋ ሽሮ |
የዘይት ፍሬዎች ምሳሌ ለውዝ (Nuts and seeds) |
15 (10-20) |
15 |
5.5 |
ጥጥ፣ ሱፍ፣ ለውዝ፣ ሰሊጥ |
1 ማንኪያ ሱፍ ፍትፍት (ሁለት ጊዜ) |
ፍራፍሬ (Fruits) |
150 (100-160) |
150 |
55 |
ብርቱካን፣ ሙዝ፣ ፓፓያ፣ ማንጎ፣ አቮካዶ |
1 ሙዝ ወይም ማንጎ |
አትክልት (Vegetables) |
130 (100-140) |
130 |
48 |
ቲማቲም ሽንኩርት፣ ጥቅል ጎመን |
1 ጭልፋ አትክልት |
ስኳር (sugar) |
15 (10-31) |
15 |
5.5 |
ሽንኮራ አገዳ፣ ስኳር ድንች፣ ከረሜላ፣ ጣፋጭ መጠጦች |
1 ብርጭቆ ሻይ |
ከተክል የሚገኙ ምግቦች ንዑስ ድምር |
|
900 |
|
|
|
ከእንስሳት የሚገኙ እንደ ወተት ያሉ (Milk and dairy foods) |
250 (200-400) |
250 |
90 |
አይብ እርጎ፣ ወተት |
1 ብርጭቆ ወተት |
እንቁላልና ስጋ (Meat and eggs) |
30 (20-50) |
30 |
10 |
አሳ፣ እንቁላል፣ ስጋ |
1 እንቁላል ወይም 1 ጭልፋ ጥብስ |
ቅባትና ዘይት (Fats and oils) |
15 (10-17) |
15 |
5.5 |
ቅቤ |
1 ማንኪያ ቅቤ |
ጨው (Salt) |
0-3 |
2 |
0.75 |
|
|
ከእንስሳት የሚገኙ ምግቦች ንዑስ ድምር |
|
297 |
|
|
|
ጠቅላላ ድምር |
|
1197 |
|
|
|
ነገርን ነገር ያነሳዋልና፣ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዴሚ በ1989 ዓ.ም. ያሳተመው የሳይንስና የቴክኖሎጂ መዝገበ ቃላት፣ በእንግሊዝኛ ‹‹Cereals›› የሚባሉትን ሰብሎች ብራ አገዳ እህሎች፣ ‹‹Legumes›› የሚባሉትን አበባ አዝርዕት፣ እንዲሁም ‹‹Pulses›› የምንላቸውን ደግሞ አበባ እህል ጥራጥሬ በሚል ይተረጉማቸዋል፡፡
ሰንጠረዥ 1 ላይ እንደሚታየው ከአጠቃላይ ፍላጎት ውስጥ፣ ከተክሎች የሚገኘው ምግብ በደምሳሳው 75 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን፣ ከእነዚህ ተክሎች መካከል ደግሞ የእህልና ጥራጥሬ ሰብሎች 56 እና 10 በመቶ፣ እንዲሁም ፍራፍሬና አትክልት ደግሞ 17 እና 14 በመቶ ድርሻ በቅደም ተከተል አላቸው፡፡ የስኳር (ሸንኮራ አገዳ) ድርሻ ሁለት ከመቶ ብቻ ነው፡፡
በምግብ ራስን መቻልን እንደ ግብ ካስቀመጥን፣ የዝናብም ሆነ የመስኖ ማሳዎቻችን ላይ የምናበቅላቸው ሰብሎች ስብጥርና ሽፋን ይህንን የምርት ድርሻ መከተል አለበት እላለሁ፡፡ ለምሳሌ ከዚህ ቀደም በወጣ የሸንኮራ አገዳ መስኖ መሬት ሥሌት መጣጥፍ ላይ (https://www.ethiopianreporter.com/74582/) 10 እና 7.5 ኪሎ ግራም ስኳር በዓመት ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ ከላይ የሚያሳየን ግን 5.5 ኪሎ ግራም ነው፡፡ ስለዚህ መልማት ይኖርበታል ተብሎ የተሠላው መሬት ስፋት በ50 እና 25 በመቶ ይቀንሳል ማለት ነው፡፡ ይህ የሚያሳየን በሰንጠረዡ ውስጥ የተዘረዘሩት የምግብ ፍላጎት መጠን መረጃዎች እጅግ ወሳኝ መሆናቸውን ነው፡፡
ይሁን እንጂ አንድ ሰብል የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች ውስጥ ተመድቦ ሊገኝ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ሽንኩርት፣ ሽሮ ወጥና አትክልቶች ውስጥ ተመድቦ እናገኘዋለን፡፡ ከእያንዳንዱ ሰብል የሚፈለገውን መጠን ለየምግብ ዓይነቶቹ በአግባቡ ማከፋፈሉ የመስኖ መሬት ስፋት ግመታ ሥሌታችንን የሚያቀል ቢሆንም ቅሉ፣ ሥራው ግን ውስብስብ ነው፡፡ የአገራችን ማኅበረሰብ የአመጋገብ ሥርዓት ብዝኃነት (ለምሳሌ በርካታ የፆም ቀናት መኖራቸው)፣ የምግብ ዓይነቶቹና ምግቦቹ የሚዘጋጁበት ሰብሎች ብዛትና ስብጥር ጉዳዩን የበለጠ ያወሳስቡታል፡፡
ሦስተኛ የዕድሜና የአመጋገብ ስብጥሩ፣ የሕዝብ ብዛት ቆጠራው ጉዳይ፣ ወዘተ. በርካታ ነገሮችን የሚያስጎለጉል ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን የ2006 ዓ.ም. ዘገባን መሠረት አድርገን፣ በ2015 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሕዝብ 105 ሚሊዮን አካባቢ ይደርሳል (110 ሚሊዮንን ተጠቅሜያለሁ) ብለን በአጭሩ እንለፈው፡፡
አራተኛ ከመስኖ ልማት አንፃር ከላይ የተዘረዘሩትን የምግብ ዓይነቶች የሚወክሉ የእህል ዓይነቶች የትኞቹ ናቸው? የሚለውን መወሰንም እንዲሁ አሻሚ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እጅግ በርካታ በዝናብ ሊለሙ የሚችሉ የሰብል ዓይነቶች ያላት እንደ መሆኑ መጠን፣ ሁሉንም ወደ ሥሌት ማስገባት ነገር ማወሳሰብ ነውና በመስኖ ጭምር መልማት የሚችሉ ግን ወካይ የሆኑትን መምረጥ ያስፈልገናል፡፡ ነገሩን ለማቅለል (ነገርን ማቅለል ከማወሳሰብ የበለጠ ይከብዳል እንዲሉ) በቆሎ፣ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ጥጥ፣ አኩሪ አተር፣ ለውዝ፣ ብርቱካን፣ አቮካዶ፣ ቲማቲም፣ ሽንኩርትና ሽንኮራ አገዳ ወካይ ናቸው ብለናል፡፡ ምን በወጣኝ የሚል ካለ ደግሞ የራሱን ሰብል መምረጥ ወይም ለሁሉም ማሥላት መብቱ ነው፡፡
አምስተኛ የተመረጡት ሰብሎች አማካይ ምርታማነት እንዴት ይወሰን? የሚለው ጥያቄ መፍትሔ ሊያገኝ ይገባል፡፡ ምክንያቱም አሥር ከመቶ የምትሆን የቁጥር መዛነፍ፣ አሥር በመቶ የመስኖ መሬት ልዩነት ታስከትላለችና፡፡ በዝናብ የሚገኘውን ወይስ የመስኖ ምርታማነት፣ በገበሬው ዘንድ የሚታየውን ወይም በሳይንሳዊ መንገድ አልምተው የሚያገኙትን፣ ወይስ የውጭ አገር መረጃ እንጠቀም? ሁሉም ይቅርብንና የአሥር ዓመቱ የግብርናው ዘርፍ ዕቅድ ሰነድ ውስጥ የተጠቀሱትን የምርታማነት አኃዞች አማካያቸውን እንውስድና፣ በሰነዱ ውስጥ ላልተጠቀሱ ሰብሎች ደግሞ ከሌሎች የጥናትና የመስክ ዘገባዎች እየለቀምን አማካያቸውን እንይዛለን ማለት ነው፡፡
ስድስተኛ በመስኖ መልማት ያለበት የእህል ምርትና የመሬት ሽፋን ምን ያህል እንደሆነ የሚወስነው ግን ማን ነው? የሚለው ጥያቄም የራስ ምታት እኮ ነው፡፡ የሰብል ባለሙያ ወይስ የመስኖ መሐንዲስ? ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የወረዳ ኃላፊ፣ የክልል ፕሬዚዳንት፣ አስተማሪ፣ የቀበሌ ኮሜቴ፣ ወዘተ. ማን ነው? እነዚህ በሙሉ የመወሰን ሥልጣን የላቸውም፡፡ ወሳኞቹ የዝናብ እርሻችሁ (ግብርናችሁ)፣ የሕዝብና የገበያ ፍላጎታችሁ ናቸው፡፡ በዝናብ እያመረትን ያለነው ምርት በቂ ነው ብንል እንኳን፣ ዘላቂና አስተማማኝ ግን አይደለም፡፡ የአገራችን የመስኖ ልማት አስፈላጊነት ማጠንጠኛ ዕሳቤው፣ ተደጋጋሚው ድርቅና የዝናብ አለመስተካከል የፈጠረውን ክፍተት የመሙላት ብሎም ዘላቂ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ከፍ ሲል ደግሞ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ማግኘት ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የሥሌታችን መነሻ ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚከሰተው ድርቅም ይሁን የዝናብ አለመስተካከል በአማካይ 35 በመቶና ከዚያ በላይ የምርት መቀነስና ውድመት እንደሚያስከትል ጥናቶች የሚያመላክቱ በመሆኑ፣ ሲቀጥል ደግሞ በርካታ ጥናቶች በዓለም ላይ ከሚታረሰው አጠቃላይ የእርሻ መሬት ውስጥ 20 በመቶ የሚሆነው በመስኖ የሚለማ ሲሆን፣ 40 በመቶ የሚሆነውን የዓለም ሕዝብ ምግብ ፍላጎት ይሸፍናል ይሉናል፡፡ ስለዚህ የአገራችን መስኖ የአጠቃላይ አገራዊ የምግብ ሰብል ፍላጎት መጠንን ከ30 እስከ 40 በመቶ ቢሸፍን አልንና እኛ በአማካይ 35 በመቶ የሚለውን ተጠቀምን፡፡ ለምሳሌ በቻይና የመስኖና የዝናብ እርሻ መሬቶች እኩል በእኩል ቢሆኑም ቅሉ፣ ከ75 በመቶ በላይ የምግብ ሰብል ፍላጎቷን የምታሟላው ከመስኖ መሆኑን ለታዘበ እንዲህ ያለ ተስፈኛ ዕቅድ ማስቀመጥም ይቻላል፡፡ እኔ ግን የእስካሁኗን አገሬን ስለማወቃት እፈራለሁ፡፡ ምን ያህል ማልማት እንዳለብን ለመወሰን፣ አሁን ምን ያህል መሬት በመስኖ እያለማን ነው ተብሎ ከተጠየቀም፣ ምን ያደርግልናል ይህ እኮ ዓመታዊ ዕቅድ የምናወጣበት ወይም የሩብ ዓመት ሪፖርት አይደለም፡፡ የፈለገ ካለ በኋላ ላይ መረጃ አሰባስቦና ቆጥሮ ማቀናነስ ይችላል፡፡
ሰባተኛ የመስኖ እርሻ እንደ ዝናብ እርሻ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ አይመረትም፡፡ አካባቢውና የሰብሉ ዓይነት በፈቀደልን መጠን እስከ ሁለት ጊዜ ማምረት እንችላለን (በአጋጣሚ ካልሆነ በስተቀር በዘላቂነት በዓመት ሦስት ጊዜ ለማምረት ተፈጥሮ ትፈቅድ ይሆን?)፡፡ ዝናብ አጠር አካባቢዎች ላይ ቶሎ የሚደርሱ ሰብሎች መስኖን በመጠቀም በዓመት ሁለት ጊዜ ይመረታሉ፡፡ ዝናብ በቂ በሆነባቸው አካባቢዎች ደግሞ ሌሎቹ ሰብሎች በዓመት አንድ ጊዜ በመስኖ ይመረታሉ፡፡ ዝናብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ግን መስኖ አያስፈልግም፡፡ በሚከተለው ሰንጠረዥ ውስጥ፣ መስኖን ብቻ ታሳቢ አድርገን ፍራፍሬዎችና ሸንኮራ አገዳ በዓመት አንድ ጊዜ፣ ጥጥና ለውዝ ደግሞ በሁለት ዓመት ሦስት ጊዜ፣ ሌሎቹን ሰብሎች ግን በዓመት ሁለት ጊዜ ማምረት ከቻልን በሚል ዕሳቤ የሚያስፈልገንን የመስኖ ምርትና የእርሻ ስፋት ለማሥላት ሞከርን፡፡ ሁሉንም ሰብሎች ማካተቱ ለጋዜጣ አይመችምና (የአገሪቱ ተቆጥሮ የማያልቅ የሰብል ዓይነቶችን መታዘብ ይቻላል) የተመረጡ ሰብሎችን አማካይ ምርታማነትን እንጠቀማለን፡፡
ሠንጠረዥ 2. የተመረጡ የሰብል ዓይነቶች ምርታማነት፣ ከመስኖ የሚጠበቅ ጠቅላላ ምርትና
ወካይ የሰብል ዓይነቶች |
ሕዝብ ብዛት |
ለአንድ ሰው በዓመት የሚያስፈልገው ኪሎ ግራም |
የሚያስፈልግ ጠቅላላ ምርት በኩንታል |
ከመስኖ እርሻ የሚጠበቅ ምርት (35 ከመቶ) በኩንታል |
አማካይ ምርታማነት ኩንታል በሔክታር |
በየዓመቱ መታጨድ ያለበት የመስኖ ማሳ በሔክታር |
የሚያስፈልግ የመስኖ ማሳ ስፋት በሔክታር |
ሌሎች ተጨማሪ ሰብሎች |
በቆሎ፣ ስንዴና ጤፍ |
110,000,000 |
182.5 |
200,750,000.0 |
70,262,500.0 |
35 |
2,007,500.0 |
1,003,750.0 |
ካሳቫ፣ ሩዝ፣ ገብስ፣ ማሽላ፣ ዳጉሳ፣ ሥራ ሥር ሰብሎች |
ቦሎቄ፣ አኩሪ አተር |
110,000,000 |
33 |
|
12,705,000.0 |
12 |
1,058,750.0 |
529,375.0 |
ሽንብራ፣ ምስር፣ አተር |
ጥጥና ለውዝ |
110,000,000 |
5.5 |
6,050,000.0 |
2,117,500.0 |
25 |
84,700.0 |
56,466.67 |
ሱፍ፣ ሰሊጥ |
ፍራፍሬ (ብርቱካንና አቮካዶ) |
110,000,000 |
55 |
60,500,000.0 |
21,175,000.0 |
250 |
84,700.0 |
84,700.0 |
ሙዝ፣ ፓፓያ፣ ማንጎ፣ መንደሪን፣ ዘይቱን |
አትክልት (ቲማቲምና ሽንኩርት) |
110,000,000 |
48 |
52,800,000.0 |
18,480,000.0 |
250 |
73,920.0 |
36,960.0 |
ካሮት፣ ጎመን ጥቅል ጎመን፣ ድንች፣ ቃሪያ፣ ሰላጣ፣ አደንጓሬ |
ሸንኮራ አገዳ |
110,000,000 |
5.5 |
6,050,000.0 |
2,117,500 |
1300 |
1,628.8 |
42,307.7 |
ስኳር ድንች |
ድምር |
|
329.50 |
362,450,000 |
126,857,500 |
|
3,311,199 |
1,753,559 |
|
ቀደም ሲል እንደተገለጸው ምርታማነትን ማሳደግ ጠቀሜታው የጎላ ስለመሆኑ እንደማሳየታችን፣ ከዚህ በተጨማሪም የመስኖ እርሻ ውጤታማነት የተመሠረተው በምርት ድግግሞሽ ላይ ስለመሆኑ ጭምር ሊሰመርበት ይገባል፡፡ መስኖ እየተጠቀምን በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የምናመርት ከሆነ፣ 3.3 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ያስፈልገናል፡፡ አዋሽ ተፋሰስ ውስጥ የተሰበሰበ መረጃ እንደሚያሳየው በመስኖ ማሳ ላይ ያለው የምርት ድግግሞሽ 125 በመቶ ብቻ ሲሆን፣ ይህንን መሠረት አድርገን ካሠላነው በአገራችን እስከ 2.68 ሚሊዮን ሔክታር የሚደርስ በመስኖ የሚለማ እርሻ ያስፈልገናል፡፡ ይሁን እንጂ ከሰንጠረዥ እንደምንረዳው ከላይ በተገለጸው የምርት ድግግሞሽ አኳያ ግን፣ 1.75 ሚሊዮን ሔክታር ማሳ ብቻ ለምግብ ሰብሎች ማዋል ይጠበቅብናል ማለት ነው፡፡ የምርት ድግግሞሽን በመጨመር ብቻ ቢያንስ ከአንድ ሚሊዮን እስከ 1.5 ሚሊዮን ሔክታር የሚደርስ የመስኖ መሠረተ ልማት ዝርጋታ ወይም ግንባታን እናስቀራለን ማለት ነው፡፡ በብር ቢሠላ እኮ በጣም በትንሹ ከ250 ቢሊዮን ብር በላይ ነው (250 ሺሕ ብር በሔክታር አማካይ የግንባታ ወጪ ሒሳብ)፡፡
ስምንተኛ ሌላው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ደግሞ ምን ያህል የመስኖ መሬት በየትኞቹ ሰብሎች መሸፈን ይኖርበታል የሚለው ነው፡፡ በሰንጠረዥ 2 እንደሚታየው ከሆነ በበቆሎ፣ በስንዴና በጤፍ ዓይነት ሰብሎች በአንድ ላይ፣ እንዲሁም በቦሎቄና በአኩሪ አተር መሰል ጥራጥሬ ሰብሎች በአንድነት መሸፈን ያለበት የመስኖ ማሳ ሽፋን፣ ከአጠቃላዩ 1.75 ሚሊዮን ሔክታር 57 እና 30 በመቶ ድርሻ በቅደም ተከተል ይይዛሉ፡፡ ድምራቸው ወደ 90 በመቶ አካባቢ መሆኑ ነው፡፡
እስከ 65 በመቶ የሚደርሰውን የምግብ ፍላጎትን የሚሸፍኑት እነዚህ የሰብል ዓይነቶች (ስንዴ፣ በቆሎ፣ ጤፍ፣ እንዲሁም ቦሎቄና አኩሪ አተር) እስከ 90 በመቶ የመስኖ እርሻ ሽፋን ይፈልጋሉ ማለት ነው፡፡ ቻይና 90 በመቶ የሚደርሰው የመስኖ እርሻዎቿን በእነዚህ ሰብሎች እንደምትሸፍን ስንገነዘብ፣ የሥሌታችንን እውነታ ያረጋግጥልናል፡፡ ለምግብነት የሚፈለገውን ስኳር ለማግኘት በሸንኮራ አገዳ መሸፈን ያለበት የመስኖ መሬት ድርሻ ከአጠቃላዩ ሁለት በመቶ ብቻ ሲሆን፣ ይህም 42,000 ሔክታር አካባቢ ይደርሳል፡፡ አሁን ግን 72,000 ሔክታር አካባቢ ለስኳር ልማት የዋለ በመስኖ የሚለማ የሸንኮራ አገዳ እርሻ አለን፡፡
እስኪ ደግሞ በአንድ የምግብ መደብ ሥር የሚገኙትን ስንዴ፣ በቆሎ፣ ጤፍ፣ ሩዝ፣ ገብስ፣ ማሽላ፣ ዳጉሳ፣ ካሳቫና ሌሎች ሥራ ሥር ሰብሎችን ለይተን እንመልከት፡፡ አንድ ኢትዮጵያው እነዚህን ሰብሎች ይመገባል ብለን እናስብና፣ በሰንጠረዥ 1 ከተጠቀሰው 182.5 ኪሎ ግራም በዓመት ላይ የእያንዳንዱ ሰብል ድርሻ ምን ያህል እንደሆነ የሚያውቅ አለ? በአኃዝ ማስቀመጥ ይቻል ይሆን? ግድ የላችሁም ለጊዜው ከበቆሎና ስንዴ በስተቀር የሌሎቹን ሰብሎች ፍላጎት ከዝናብ እርሻ ማሟላት ስለምንችል፣ ከመስኖ ልማት አንፃር አንድ እንጀራን ወይም አንድ ከግማሽ ዳቦን እንደሚወክሉ አስበን በቆሎና ስንዴን ወስደን ነገሩን እናቅለው እስኪ፡፡
በቆሎ እንጀራን፣ ስንዴ ደግሞ ዳቦን ይወክላል እንበልና አንድ ሰው በዓመት ምን ያህል እንጀራና ዳቦ ይበላል? ምን ያህል ሰው እንጀራ ወይም ዳቦ ተመጋቢ ነው ታድያ? ምን ያህሉ የአገራችን ሰው እንጀራ ወይም ዳቦ ተመጋቢ ነው ታድያ? ዝርዝር መረጃ እንደሚያስፈልግ ያስገነዝበናል፡፡ የተጋነነ ቢሆንም ቅሉ እኩል፣ እኩል ሕዝብና የአመጋገብ ዘይቤ እንያዝላቸው፡፡
ሰንጠረዥ 2 ላይ ለሥሌት የተጠቀምነው አማካይ ምርታማነት 35 ኩንታል በሔክታር ሲሆን፣ በዓመት ሁለት ጊዜ ካመረትን ለበቆሎም ሆነ ለስንዴ ለእያንዳንዳቸው ወደ 0.5 ሚሊዮን ሔክታር (በድምሩ 1 ሚሊዮን ሔክታር ሲሆን፣ 70 ሚሊዮን ኩንታል ምርት) የሚደርስ የመስኖ ማሳ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ይሁንና የበቆሎ አማካይ ምርታማት 50 ኩንታል የስንዴ ደግሞ 40 ኩንታል አካባቢ በሔክታር ከወሰድን ግን፣ የሚያስፈልገን የመስኖ እርሻ ስፋት 0.35 እና 0.44 ሚሊዮን ሔክታር በቅደም ተከተል ይሆናል ማለት ነው፡፡ አንድ ጊዜ ብቻ የምናመርት ከሆነ ግን 0.7 እና 0.88 ሚሊዮን ሔክታር ማለት ነው፡፡ ከላይ የዘረዘርናቸውን ታሳቢዎች መሠረት አድርገን፣ በዚህ ዓመት ከ1.3 ሚሊዮን ሔክታር የመስኖ መሬት ላይ (ሁለት ጊዜ ካመረትን 0.65 ሚሊዮን ሔክታር ይሆናል)፡፡
65 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት (50 ኩንታል በሔክታር ሒሳብ) ለማግኘት ዕቅድ መያዛችንን በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተነግሮናልና ምን ያህል ትርፍ ምርት እናገኛለን? ለአገር ውስጥ ፍጆታ ከመስኖ 35 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠበቅ በመሆኑ፣ በትንሹ እስከ 30 ሚሊዮን ኩንታል ትርፍ የስንዴ ምርት ይኖረናል፡፡ እንግዲህ 30 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ወደ ውጭ ለመላክ ወይም ኤክስፖርት ለማድረግ መዘጋጀት አለብን ማለት ነው፡፡
በዝናብ ይገኛል ከተባለው 100 ሚሊዮን ኩንታል (የተሳሳትኩ አይመስለኝም ካልሆነ አስተካክሉት) ጋር የምርት መጠኑ 165 ሚሊዮን ኩንታል ሲሆን፣ ግማሹ ሕዝብ ስንዴ ብቻ ይመገባል በሚለው ዕሳቤ አጠቃላይ ፍላጎቱ ወደ 100 ሚሊዮን ኩንታል ይደርሳል፡፡ እንግዲያውስ እጅግ በተጋነነ ፍላጎት ላይ እንኳን ተመሥርቶም፣ ወደ 65 ሚሊዮን ኩንታል ትርፍ ስንዴ ይኖረናልና ወደ ገበያ ለማውጣት በቶሎ መዘጋጀት ያለብን ይመስለኛል፡፡
በአጠቃላይ ምንም እንኳን ብዙ የማርያም መንገድ እየጠየቅን፣ ሰበቦችና ታሳቢዎችን እየደረደርንም ቢሆን አገራችን ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ትችል ዘንድ፣ እንዲሁም መስኖ የሚገባውን ሚና በአግባቡ እንዲወጣ ምን ያህል መሬት ማልማት እንደሚኖርብን የመወሰን ውጣ ውረድን በምሳሌ ለማሳየት ሞከርን፡፡ ይህ መጣጥፍ አመላካች እንጂ የመጨረሻው ውሳኔ የቀረበበት እንዳልሆነ ልትገነዘቡ ይገባል፡፡ ስለሆነም የሚከተሉት ነጥቦች አስፈላጊነት ላይ ሁሉም አፅንኦት እንዲሰጥ አደራ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ የመጀመሪያው፣ የሕዝባችንን የአመጋገብ ባህሪይ ዘርዝሮ ማስቀመጥን በተመለከተ (የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ያሳተመው ሰነድ፣ የአገራችንን የአመጋገብ ባህሪያትን ለምሳሌ የሚፆመውን ማኅበረሰብ በዕድሜ ጭምር ከፋፍሎ የምግብ ፍላጎት መጠኑን ያስቀምጣል፡፡ ከመረጃ መረብ ላይ አውርዳችሁ ብታዩት ጥሩ ነው ብዬ እመክራለሁ)፡፡ ሁለተኛው የምግብ ፍላጎት መጠኑንና አስፈላጊ የሆኑትን የምግብ ሰብሎች ለይቶ ማስቀመጥ፣ ሦስተኛ በመስኖና በዝናብ የምናመርታቸውን ሰብሎች ዓይነት፣ ስብጥርና ፍላጎት መጠንን፣ እንዲሁም የእርሻ መሬቶቹን ቁርኝት በተመለከተ በግልጽ መለየት፣ አራተኛ የሰብሎችን ምርታማነት በዝርዝር ማስቀመጥ፣ በተለይ ደግሞ ምርታማነትንና የምርት ድግግሞሽ የማሻሻል ሥራ ላይ ልንረባረብ እንደሚገባን ሲሆን፣ የሁሉም ጉዳዮች ማጠንጠኛው ግን የመረጃ ክፍተት እንደመሆኑ የተደራጀ ተደራሽ በየወቅቱ የሚታደስ አስተማማኝ አገራዊ የግብርና ልማት መረጃ ቋት የመዘርጋት አስፈላጊነት ይሆናል፡፡ ሰበብ ያስደረደረኝ እኮ የመረጃ ክፍተት ነው፡፡
ይህን ደረቅ መጣጥፍ እዚህ ድረስ ዘልቆ ያነበበ የጉዳዩን አሳሳቢነት ተረድቷልና እያመሠገንኩኝ፣ በሚቀጥሉት መልመጃ አራት ዓይነት የቤት ሥራ ጥያቄዎች ልለያችሁ፡፡ ጥያቄ አንድ የእንስሳት መኖ በመስኖ ይለማል እንዴ ካላችሁ እንክት በደንብ ነዋ ካልኩ በኋላ፣ ታዲያ ምን ያህል መልማት አለበት? ሁለት ከአገር ውስጥ ፍጆታ አልፈን ወደ ውጭ እንላክ ብለን ካቀድን መጠኑን እንዴት እንወስናለን? ሦስት እስካሁን በመስኖ እያመረትን ያለውን የሰብል ዓይነትና ስብጥር፣ የምርትና የማሳ ስፋት፣ ወዘተ. በተመለከተ አገራዊ መረጃዎችን ፈልጋችሁና አሰባስባችሁ፣ ከተዘረዘረው አንፃር አስተያየቶቻችሁን አካፍሉን፡፡ ተወያዩበት (ድሮ መልመጃ አምስት ሥር የሚቀመጡ ጥያቄዎችን አይመስልም?)፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የመስኖ መሐንዲስ ተመራማሪ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር፣ በመስኖ ዲዛይንና ቁጥጥር በርካታ ጽሑፎችን ያበረከቱና በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን እየሠሩ ሲሆን፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡