Wednesday, May 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዳሸን ባንክ ከታክስ በፊት 3.8 ቢሊዮን ብር አተረፈ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዳሸን ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ጠቅላላ የሀብት መጠኑን ከአንድ መቶ ቢሊዮን ብር በላይ ማሳደግ መቻሉንና በዓመቱ መጨረሻም ከታክስ በፊት ከ3.8 ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፉን አስታወቀ፡፡ 

በኢትዮጵያ ውስጥ ቀዳሚ ከሚባሉ የግል ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው ዳሸን ባንክ በ2014 መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የሀብት መጠኑን 117 ቢሊዮን ብር ማድረስ መቻሉ የሀብት መጠናቸውን ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ ከቻሉ ሦስት ባንኮች መካከል አንዱ አድርጎታል፡፡  

ባንኩ ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የቀረበው የባንኩ ሪፖርት እንደሚያመላክተው የሀብት መጠኑ ከዓምናው በ23.7 በመቶ በመጨመር 117 ቢሊዮን ብር ደርሷል። በ2013 የሒሳብ ዓመት የባንኩ ጠቅላላ የሀብት መጠኑ 94 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን ፣ በ2014 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ጭማሪ ማሳየቱን አመልክቷል፡፡ 

ዳሸን ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ያገኘው ትርፍ በኢንዱስትሪው ካሉ የግል ባንኮች ሁለኛው ከፍተኛ ትርፍ ሆኖ ተመዝግቧል። ባንኩ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 3.8 ቢሊዮን ብር ትርፍ አግኝቷል፣ ይህም በ2013 ዓ.ም. ካስመዘገበው 2.4 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ1.4 ቢሊዮን ብር ብልጫ ወይም ከ56 በመቶ በላይ ነው፡፡

የትርፍ መጠኑ ዕድገት የባንኩ ባለአክሲዮኖች የትርፍ ክፍፍል ድርሻ (ዲቪደንድ) እንዲጨምር ያስቻለ እንደሆነም የባንኩ ሪፖርት ያመለክታል።

በዚህም መሠረት የባንኩ ባለአክሲዮኖች በአንድ የአክሲዮን መጠን (አንድ ሺሕ ብር ዋጋ) የሚያገኙት የትርፍ ድርሻ 532 ብር አንደሚሆን ይህም በ2013 የሒሳብ ዓመት ካገኙት 471 ብር የትርፍ ድርሻ ጋር ሲነፃፀር የ61 ብር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ 

የባንኩን የ2014 የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለጠቅላላ ጉባዔው ያቀረቡት የዳሸን ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዱላ መኮንን ባንካቸው የሥራ አፈጻጸም መልካም ቢሆንም የተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በርካታ ተግዳሮቶች የተስተዋሉበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ 

ከውጭ የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት፣ ከአገር ውስጥ ደግሞ የቀጠለው ግጭትና በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች የተከሰተው ድርቅ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል፡፡  

የአገሪቱ ባንኮች መንግስት የዋጋ ንረትንና የኢኮኖሚ አሻጥርን ለመከላከል፣ ምርት ወደ ውጭ ገበያ የሚልኩ አካላትን ለማበረታታትና የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያን ለማሳደግ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ዕርምጃዎችን በወሰደበት ሁኔታ ውስጥ ሆነው ለመሥራት የተገደዱበት ዓመት እንደበር የቦርድ ሰብሳቢው ተናግረዋል፡፡ 

የተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት አዳዲስ ባንኮች ወደ ኢንዱስትሪው የተቀላቀሉበትና ባንክ ያልሆኑ ድርጅቶችም ወደ ፋይናንስ አገልግሎት የገቡበት መሆኑን ጠቅሰው ይኸው በዘርፉ ያለውን ፉክክር ይበልጥ እንደሚያሳድገውና ከፊት ለፊቱ ብዙ የሚጠብቀው ውድድር መኖሩንም ገልጸዋል። እንዲህ ያሉ ተግዳሮቶችና ውድድሩን ጠንከር ያደረጉ አዳዲስ ክስተቶች በሒሳብ ዓመቱ ጎልተው ቢታዩም ዳሸን ባንክ መልካም አፈጻጸም አሳይቷል ብለዋል፡፡ 

በሒሳብ ዓመቱ ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቦበታል ብለው ከጠቀሱዋቸው የባንኩ የሥራ አፈጻጸሞች መካከል በተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰብ ረገድ አመርቂ ውጤት መገኘቱ አንዱ ነው፡፡ 

በዚህም መሠረት ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ 16.7 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ወደ 91.2 ቢሊዮን ብር ማሳደግ ችሏል፡፡ ይህ አፈጻጸም ከቀዳሚው ዓመት የ22.4 በመቶ ብልጫ ያሳየ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ባንኩ በ2013 የሒሳብ ዓመት የነበረው ተቀማጭ ገንዘብ 74.5 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ያሰባሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠንም 5.9 ቢሊዮን መድረሱን የሚያመለክተው የቦርድ ሰብሳቢው ሪፖርት የባንኩ ካፒታል ወደ 14.4 ቢሊዮን ብር ከፍ ያለ መሆኑንና ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ42 በመቶ ብልጫ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡ 

‹‹በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የባንኩን ተደራሽነት ለማስፋት፣ አዳዲስ ደንበኞችን ለማፍራት፣ ከፍ ያለ ተቀማጭ ገንዘብ ለማሰባሰብና የላቀ ትርፍ ማሳመዝገብ ችለናል፤›› ያሉት የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ በበኩላቸው በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ብቻ 128 አዳዲስ ቅርንጫፎች መከፈታቸው አንድ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ 

ይህም አዳዲስ ደንበኞችን ለማፍራት ያስቻለ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የባንክ አጠቃላይ የአስቀማጮች ቁጥር 3.92 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን ይህም ከ720 ሺሕ በላይ የጨመረ ስለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡ 

ባንኩ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግም የተለያዩ ተግባራትን ማከናወኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ነገር ግን በኢንዱስትሪው ውስጥ የተከሰቱት አጠቃላይ ለውጦችን ከግምት ያስገባ የውስጥ ተቋማዊ ቅርፅ ለውጥ ማድረጉንም አመልክተዋል፡፡ 

ከዚህም ሌላ በዚህ የሒሳብ ዓመት ባንኩ ሲመራበት የቆየው የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ በማጠናቀቅ በመሆኑ አዲስ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ የሚነድፍ መሆኑንም አቶ አስፋው ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡ 

አዲሱ ዕቅድም በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ የተከሰቱ ተግዳሮቶችንና ዕድሎችን ከግምት በማስገባት እንደሚዘጋጅ ተገልጿል፡፡ ዳሸን ባንክ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ያደገውን ፋይናንስ ጨምሮ አጠቃላይ የብድር ክምችቱ 79.2 ቢሊዮን ደርሷል፡፡ 

ዘመናዊ የባንክ አልግሎቶችን ከማስፋት አንፃርም ከሌሎች ባንኮች በተለየ እያስፋፋ የመጣው የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶች በርካታ ተገልጋዮችን እንዲዳረስ እንዳደረገም ተብራርቷል፡፡ 

ዳሸን ባንክ በአሁኑ ወቅት የተከፈለ ካፒታሉ 6.86 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን በመላ አገሪቱ የሚገኙ ቅርንጫፎቹን ቁጥር 582 አድርሷል፡፡ የባንኩ ተበዳሪዎች ቁጥር ደግሞ 28,551 እንደደረሰ የሚያመለክተው የባንኩ ሪፖርት የሠራተኞቹ ቁጥር ደግሞ 12,406 ደርሷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች