Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንብ ኢንሹራንስ ከታክስ በፊት 172.9 ሚሊዮን ብር አተረፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ የ20 ዓመታት ዕድሜ ያለው ንብ ኢንሹራንስ ኩባንያ፣ በ2014 ዓ.ም. የሒሳብ ዓመት ከ709.4 ሚሊዮን ብር በላይ ዓረቦን ገቢ ማግኘቱንና ከታክስ በፊት 172.9 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ፡፡

ንብ ኢንሹራንስ አ.ማ. የ2014 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ በሒሳብ ዓመቱ ማሰባሰብ የቻለው የዓረቦን መጠን ከቀዳሚው ዓመት በ24.8 በመቶ ብልጫ ያለው ነው፡፡

ኢንሹራንስ ኩባንያው ካሰባሰበው ጠቅላላ የዓረቦን መጠን ውስጥ 90.9 በመቶ የሚሆነው ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ የተገኘ ነው፡፡ ቀሪው 9.1 በመቶ የሚሆነው የዓረቦን ገቢ የተገኘው ደግሞ ከሕይወት ነክ የኢንሹራንስ ዘርፍ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

የኢንሹራንስ ሽፋን ለሰጣቸውና ጉዳት ለደረሰባቸው ደንበኞች በሒሳብ ዓመቱ ከ311.3 ሚሊዮን ብር በላይ የካሳ ክፍያ መክፈሉን ገልጿል፡፡ እንደ ቀደሙት ዓመታት ሁሉ በ2014 የሒሳብ ዓመት ከፍተኛ መጠን ያለው የካሳ ክፍያ የፈጸመው ለተሽከርካሪ ወይም ለሞተር ኢንሹራንስ ነው፡፡ ንብ ኢንሹራንስ በሒሳብ ዓመቱ ያስመዘገበው የሥራ አፈጻጸም ከታክስ በፊት 172.9 ሚሊዮን ብር ማትረፉ ተገልጿል፡፡ ይህ የኩባንያው ትርፍ ከ2013 የሒሳብ ዓመት አንፃር ሲታይ የ6.1 ሚሊዮን ብር ወይም የ3.7 በመቶ ብልጫ ያለው ነው፡፡

ከተሽከርካሪ የጉዳት ካሳ ክፍያ ባሻገር ብልጫ ያለው የካሳ ክፍያ የተፈጸመበት ዘርፍ ደግሞ ለሕክምና ዋስትና እንደሆነ የኢንሹራንስ ኩባንው መረጃ ያመለክታል፡፡

ኩባንያው ከታክስ በፊት ካስመዘገበው 172.9 ሚሊዮን ብር ውስጥ 149.9 ሚሊዮን ብር የሚሆነው ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ ነው፡፡ በሒሳብ ዓመቱ የሕይወት ኢንሹራስ ያስገኘው የትርፍ መጠን 20 ሚሊዮን ብር እንደሆነ የኩባንያው መረጃ አመልክቷል፡፡

ከ19ኙ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ የተከፈለ ካፒታላቸውን ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ካደረሱ ሰባት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ንብ ኢንሹራንስ ኩባንያ፣ በ2014 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ የተከፈለ ካፒታሉን 629.9 ሚሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡

የኩባንያው ጠቅላላ የሀብት መጠንም 1.23 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በመላ ኢትዮጵያ ውስጥ 51 ቅርንጫፎች ያሉት ንብ ኢንሹራንስ ኩባንያ 408 ቋሚ ሠራተኞች አሉት፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች