Sunday, June 23, 2024

ትግራይ በጦርነት ማግሥት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ምሽት በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ የሕወሓት ኃይሎች ጥቃት ማድረሳቸው፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ማስጀመሪያ ምክንያት ሆነ፡፡ ለሦስት ተከታታይ ሳምንታት ከተካሄደ ከባድ ውጊያ በኋላ ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. መከላከያ ከቀትር በኋላ እስከ ምሽት አንድ ሰዓት ባካሄደው የተቀናጀ ዘመቻ፣ የትግራይ ክልል መዲና መቀሌ ከተማን መቆጣጠሩ ተነገረ፡፡ የመከላከያ  ኦፕሬሽን ሰላማዊ ዜጎች ሳይጎዱ የተከናወነ መሆኑም በመንግሥት ተነገረ፡፡

በዚህ ድል ማግሥት ስለሕወሓትም ሆነ ስለትግራይ ክልል ጉዳይ ደጋግመው ይሰሙ የነበሩ መረጃዎች፣ ሁኔታዎች የተለየ መልክ መያዛቸውን የሚጠቁሙ ነበሩ፡፡ ‹‹ሕወሓት የተበተነ አመድ (ዱቄት) ሆኗል፡፡ መልሶ ሊሰበሰብ አይችልም…›› የሚለው የመንግሥት ድምዳሜ ደግሞ የቡድኑን ጉዳይ ያበቃለት የሚያስመስል ነበር፡፡ ትግራይ በመከላከያ ሥር መሆኗን ተከትሎ ጊዜያዊ አስተዳደር መመሥረቱ፣ እንደ ሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች ወደ መረጋጋት ትመለሳለች የሚለውን ተስፋ አለምልሞ ነበር፡፡

በስምንተኛው ወር ግን ሁኔታዎች ተቀየሩ፡፡ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ፈረሰ፡፡ መከላከያም ትግራይ ክልልን ለቆ ሲወጣ አበቃለት የተባለው ሕወሓት መልሶ መቀሌን  ተቆጣጠረ፡፡ የዚያን ጊዜውን ሁኔታ የታዘቡ ወገኖች መከላከያ ከባድ ዋጋ ከፍሎ ያስመዘገበውን የጦር ሜዳ ድል፣ መንግሥት በፖለቲካ ሜዳ መድገም ስላቃተው የተፈጠረ ችግር እንደሆነ ትችት አቀረቡ፡፡

ከዚህ አጋጣሚ በኋላ ሁለት ዙር ውጊያዎች ተካሂደዋል፡፡ ውጊያዎቹ ደግሞ ትግራይ ክልልን ተሻግረው አማራና አፋር ክልሎችን ያዳረሱ ሲሆን፣ ኢትዮጵያን እጅግ ከባድ ሰብዓዊና ቁሳዊ መስዕዋት ሲያስከፍሏት ቆይተዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የሰሜኑ ጦርነት ሦስተኛ ዙር ምዕራፍ ውጊያ እንደቀጠለ ሲሆን፣ የመከላከያ ኃይል ገፍቶ መቀሌ ከተማ ዙሪያ ዳግም መድረሱ እየተነገረ ነው፡፡ አሁን የመቀሌና የአንዳንድ ከተሞች በመከላከያ ሥር ዳግም የመውደቃቸው ጉዳይ እጅግ ተጠባቂ ዜና ሆኗል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ የትግራይ ሁኔታ በጦርነቱ ማግሥት ምን ሊሆን ይችላል? የሚለው ጥያቄም በሰፊው በመነሳት ላይ ይገኛል፡፡

መከላከያ ትግራይን በተቆጣጠረበት ወቅት ሰሜናዊ ዞን በሚባለው የሽሬ አካባቢ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ በአመራርነት ተመድበው ለሦስት ወራት ያገለገሉት አቶ ሙሉብርሃን ኃይሌ፣ ያኔ የተሠራው ስህተት አሁን መደገም እንደሌለበት ይናገራሉ፡፡ የሕወሓት ፕሮፓጋንዳ ብዙ ርቀት የሄደ እንደነበር የሚናገሩት የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ሙሉብርሃን፣ ሕዝቡ የሚመጣው ኃይል ይበላሀል ወይም አውሬ መጣብህ እየተባለ ሲነገረው መቆየቱን ይገልጻሉ፡፡

‹‹በትግራይ አራት ዓይነት ማኅበረሰብ አለ፡፡ ገዥ መደብ፣ ከገዥ መደቡ ጋር የተጣበቀ የጥቅም ትስስር ያለው፣ ካድሬውና ከምንም የማይነካካው ሰላማዊ ኅብረተሰብ ነው፡፡ ሕወሓት ከቀበሌ እስከ ዞን ከ750 ሺሕ በላይ ካድሬ እንዳሰማራ መረጃው ነበረን፡፡ ሁሉንም ማኅበረሰብ አንድ ላይ አጭቆ ማወያየቱ የሰላማዊውን ዜጋ ጥያቄ እንዲዋጥ የሚያደርግ ነበር፡፡ ስለዚህ ካድሬውን ለብቻው በሚመጥነው መንገድ ሰብስበን አወያየን፡፡ ነጋዴውን፣ ገበሬውን፣ ወጣቱንና ሌላውን ማኅበረሰብም ለየብቻ ሰብስበን መከርን፤›› በማለት ያን ጊዜ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ሲመደቡ ያከወኗቸውን ይናገራሉ፡፡

‹‹በዚህ ሕዝቡን በማማከር ሒደት ከብዙኃኑ ይገጥመን የነበረው ጥያቄ ተከበናል፣ ልንጠፋ ነው፣ መሬታችን ሊወሰድብን ነው የሚል ብዥታ ነበር፡፡ ረጋ ብለን ተጨባጩን ሁኔታ ለሕዝቡ ለማስረዳት ሞክረናል፡፡ የሕዝቡን ብዥታዎች በማጥራትም ከማኅበረሰቡ ጋር በመግባባት ላይ የተመሠረተ አስተዳደር ለመፍጠር ሞክረን ነበር፤›› ሲሉም ያለፈውን ሁኔታ ያስታውሳሉ፡፡

ይህ አካሄድ በሰፊው ባለመተግበሩ፣ እንዲሁም ሕወሓት አሠላለፉን በመቀያየር የተካነ በመሆኑ ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ መሆናቸውን አቶ ሙሉብርሃን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ጫካ ገብቶ መከላከያን የሚወጋ ሁሉ ደመወዝ ይከፈለው ነበር፤›› በማለትም፣ መንግሥት ጊዜያዊ አስተዳደሩን በማደራጀት ሒደት ስህተት መሥራቱን ይናገራሉ፡፡

አሁን በደቡብ አፍሪካ የተጀመረው የሰላም ንግግር እንደቀጠለ ቢሆንም፣ ከዚሁ ጎን ለጎን ግን የመከላከያ ኃይል በትግራይ አማፂያን ላይ እያስመዘገበ ያለው ድል መቀጠሉም ይነገራል፡፡ ከግንባር እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ፣ የመከላከያ ኃይሎች ከ2013 ዓ.ም. ዘመቻ ልምድ በመውሰድ ፍፁም ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ የአሁኑን ዘመቻ እየከወኑት መሆኑም ይሰማል፡፡

አሁንም ድረስ በሕወሓት ሥር ያሉ አካባቢዎችን ለማፅዳት የመከላከያ ኃይል አቅሙ ቢኖረውም፣ ጀብደኛ ዕርምጃዎችን ከመውሰድ ይልቅ ከዳር ወደ መሀል በጥንቃቄ እያፀዱ መሄድን እየተከተለ መሆኑንም ይነገራል፡፡

ይህ የመከላከያ የዘመቻ አካሄድ ደግሞ በሲቪሎችና በመሠረተ ልማቶች ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት በእጅጉ እንደቀነሰ ነው ለአካባቢው ቅርበት ያላቸው ምንጮች የሚገልጹት፡፡

በመከላከያ ድልና ወደፊት መግፋት የተነሳ ከየአካባቢው የተራረፉ በአማካይ ከ40 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ታጣቂዎች ወደ መቀሌ መሰባሰባቸውን፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ተናግረዋል፡፡ በመቀሌና በዙሪያዋም ለከተማ ውጊያ በሚያመች ሁኔታ እየተዘጋጁ ይገኛል ብለዋል፡፡ እነዚህ ታጣቂዎች በዋናነት መከላከያን ወደፊት ከመግፋት ለማስቆም አቅም ኖሯቸው ሳይሆን፣ የከተማ ውጊያና መተላለቅ በመፍጠር በትግራይ ክልል ያለው ግጭት ወደ ለየለት መጨፋጨፍ ገባ የሚል ግነት የተሞላው ትርክት በመፍጠር ዓለም አቀፍ ጫና ለመቀስቀስ በማለም እንደሆነም ምንጮች ያስረዳሉ፡፡

ከሰሞኑ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች፣ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ተቋማት አመራሮችና በአሜሪካ የሆሎኮስት መታሰቢያ ሙዚየም እያሠራጩት ያለው በትግራይ ክልል የዘር ማጥፋት ሊፈጠር ይችላል የሚል የተጋነነ ግምት ከዚሁ የታጣቂዎች ዝግጅት ጋር የተገናኘ መሆኑን ምንጮቹ ይናገራሉ፡፡ የመከላከያ ሠራዊት እንደ በፊቱ ሮጦ መቀሌ ከመግባት ይልቅ የሚይዛቸውን ቦታዎች ቀስ በቀስ እያፀዳ በጥንቃቄ መግፋቱ፣ ከዚህ አንፃር ውጤታማ የዘመቻ አካሄድ መሆኑን ነው እነዚሁ ምንጮች የሚያስረዱት፡፡

ይሁን እንጂ በመከላከያ ሥር በወደቁት የትግራይ አካባቢዎች ሰላማዊ የተረጋጋ ሁኔታ እንዴት መፍጠር ይቻላል የሚለው ጥያቄ በአሁኑ ጊዜ ጎልቶ እየተነሳ ይገኛል፡፡ መንግሥት መከላከያ በያዛቸው አካባቢዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ የማቅረቡ ሥራ መቀጠሉን በመናገር ላይ ነው፡፡ ያም ቢሆን ግን በአንዳንድ አካባቢዎች የሕወሓት ታጣቂዎች ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ፣ የዕርዳታ መጋዘኖች ተሰብረው መዘረፋቸውን የተለያዩ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡

ለዚህ ይመስላል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር)፣ ‹‹የትግራይ ሕዝብ ሰብዓዊ ዕርዳታም ሆነ ጥበቃ ጉዳይ ለድርድር አይቀርብም፤›› ሲሉ የተናገሩት፡፡ በፌስቡክ ገጻቸው በሰጡት መረጃ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ፣ የሰብዓዊ ዕርዳታና የመሠረታዊ አገልግሎት አቅርቦትን ለማረጋገጥ ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮውን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሐሙስ ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባወጣው መግለጫ፣ በትግራይ ክልል በአማፂያኑ የወደሙ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች በአንድ ወር ጊዜ እንደሚጠገኑ ይፋ አድርጓል፡፡ ከኤሌክትሪክ በተጨማሪ ሌሎች የመሠረተ ልማት አገልግሎቶችን ለማስጀመር መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን ከሰሞኑ ደጋግሞ እየገለጸ ነው፡፡

‹‹በትግራይ ለ48 ዓመታት ከሕወሓት ውጪ አማራጭ የፖለቲካ ኃይል አልነበረም፡፡ ሕዝቡ ለረዥም ዘመናት በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የሕወሓት ፖለቲካ ተጠርንፎ ነው የኖረው፤›› ሲሉ የሚናገሩት አቶ ሙሉብርሃን፣ የትግራይ ሕዝብ ከኖረበት የፖለቲካ ቆፈን ነፃ እንዲወጣ ሊደረግ ይገባል ብለዋል፡፡

ሕወሓት በትግራይ ፓርቲም መንግሥትም ሆኖ መኖሩን ያስታወሱት አቶ ሙሉብርሃን፣ ሕወሓት ሲበተን የክልሉ አስተዳደራዊ መዋቅርም በጠቅላላ አብሮ መበተኑን ያወሳሉ፡፡ ‹‹አሁን የመሠረተ ልማት አገልግሎቶችን፣ ባንክ፣ መብራትና ቴሌ የመሳሰሉትን ከማስጀመር ጎን ለጎን ለትግራይ ሕዝብ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አይዞህ ሊለውና ከጎኑ ሊሆን ይገባል፤›› ሲሉም ምክራቸውን ይለግሳሉ፡፡

በዚህ ረገድ ለትግራይ ሕዝብ እንድረስለት የሚሉ ግለሰቦች በትግል ተነሳሽነት ጥረት መጀመራቸውን የሚያነሱት አቶ ሙሉብርሃን ይህ ደግሞ በታዋቂ ሰዎች፣ በፖለቲከኞች፣ በአርቲስቶችና በሌሎችም ተደማጭነት ባላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ቢደገፍ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር የትግራይ ሕዝብን ለመደገፍ እንደሚንቀሳቀስ እምነታቸውን ተናግረዋል፡፡

አሁን ብዙ ታዛቢዎች እንደሚናገሩት ምዕራባውያኑ ከኢትዮጵያ ሕዝብ በፊት ለትግራይ ጠበቃ ነን ብለው የቆሙ ይመስላል፡፡ የአሜሪካ ፖለቲከኞች በተለይም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሜሪካ ቋሚ መልዕክተኛ ሊንዳ ቶማስ ግራንፊልድ፣ ጥብቅ ትዕዛዝ በሚመስል ድምፀት ግጭቱ በአስቸኳይ ይቁም የሚል መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከንም ይህንኑ ያስተጋቡ ሲሆን፣ ጦርነቱ በአስቸኳይ ካልቆመ አሜሪካ ሌሎች የዲፕሎማሲ ማስገደጃ አማራጮቿን እንደምትጠቀም የአሜሪካ ባለሥልጣናት በመናገር ላይ ናቸው፡፡ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለዚህ ግጭት መቀጠል ምክንያት በሆኑ አካላት ላይ ጠንካራ ዕርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነን ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

ለዚህ የምዕራባውያን ጫና ምላሽ በሚመስል ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ‹‹ኢትዮጵያ በድርድር የምትሸጥ ሳትሆን በልባችንና በደማችን የምናስከብራት ውድ እናት አገራችን ነች፤›› በማለት በትዊተር ገጻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ባጫ ደበሌ (አምባሳደር)፣ ‹‹የሕወሓት መሪዎች ውሳኔ የሚወስኑት በንፁህ አዕምሯቸው አይደለም፡፡ በጎን ወደ ደቡብ አፍሪካ ተደራዳሪዎች ልከናል እያሉ፣ ወዲህ ደግሞ ለጦርነት የክተት አዋጅ ያውጃሉ፤›› በማለት ነው ለጦርነቱ መቀጠል ምክንያት የሆኑት ሕወሓቶች መሆናቸውን የተናገሩት፡፡

በተባበሩት ዓረብ ኤምሬት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ በበኩላቸው፣ ‹‹ለሰላም ድርድሩ መሳካት ግጭቱ ይቁም የሚል ቅድመ ሁኔታ ሕወሓትና ጌቶቹ እያሠራጩ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ድርድሩን ለማክሸፍ ይመስላል፡፡ በለንደኑ የይስሙላ ድርድር ወቅት ተኩስ አቁም ተደርጎ ነበር እንዴ?›› በማለት ነበር በጥያቄ ምዕራባውያኑ እያሳደሩ ያለውን ጫና የተቹት፡፡

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ታዬ ደንደአም ይህን ቀበል በማድረግ፣ ምዕራባውያን ሕወሓትን ከሞት ለማትረፍ ብዙ እየታገሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ምዕራባውያኑ የፈለገ ቢጋጋጡ ከሞት የሚያተርፉት ተላላኪ ኃይል በኢትዮጵያ እንደማይኖር በመግለጽ፣ ከኢትዮጵያ ጋር ቢተባበሩ እንደሚበጅ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሁኔታ አሳስቦናል የሚሉት የምዕራባውያን ፖለቲከኞችና ሚዲያዎች ግን፣ የመከላከያ ሠራዊቱ ወደ ትግራይ መግባቱን ተከትሎ እያወጡት ያለው መረጃ ከሰሞኑ ከግነትም አልፎ መስመሩን እየሳተ የመጣ ይመስላል፡፡

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በጀርመን ናዚዎች አይሁዶች የተፈጸመባቸውን ዘግናኝ የዘር ማጥፋት (ሆሎኮስት) መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በአሜሪካ የተገነባው ሙዚየም በድረ ገጹ ያሠራጨው መረጃ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትን ያበሳጨ ነበር፡፡ ሙዚየሙ በትግራይ ዳግም የሆሎኮስት ዓይነት ጭፍጨፋ ሊከሰት ይችላል ማለቱ በርካታ አፀፋን የቀሰቀሰ ጉዳይ ሆኖ ነው የከረመው፡፡

በዋሽንግተን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለሙዚየሙ በሰጠው ምላሽ፣ ‹‹የሕወሓትን የሐሰት መረጃ ተመሥርቶ በኢትዮጵያ ሆሎኮስት ይፈጠራል ማለቱ የተዛባ መረጃ ማሠራጨት ብቻ ሳይሆን፣ ለአንድ ወገን ያደላ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ነው፤›› ሲል ኮንኖታል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ዓርብ ጥቅምት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫም ጠንካራ አፀፋ ሰጥቷል፡፡ ኃላፊነት የጎደላቸው የምዕራባውያን ሚዲያዎችና አካላት በትግራይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ሊፈጸም ይችላል በሚል፣ በኢትዮጵያ ላይ የሚነዙትን የሐሰት ስም ማጥፋት ዘመቻ መንግሥት ፈጽሞ አይታገስም በማለት ነው ተቋሙ ጠንካራ መግለጫ የሰጠው፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወደ ትግራይ የበለጠ እየገፋ መሆኑ በሚሰማበት በዚህ ወቅት፣ በተያዙ አካባቢዎች የተረጋጋ ሁኔታ እየተመለሰ መሆኑን ምንጮች ይናገራሉ፡፡ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) የሕዝብ ግንኙነትና በ2013 ዓ.ም. ተመሥርቶ በነበረው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ወቅት አመራር የነበሩት አቶ ሙሉብርሃን፣ መከላከያ አሁን ወደ ትግራይ እያካሄደ ያለው አገባብ ፍፁም ኃላፊነት የተሞላበትና በጥንቃቄ የሚደረግ ዘመቻ መሆኑን እንደሚያውቁ ይናገራሉ፡፡ መንግሥት ከያኔው ስህተቱ ተምሯል የሚሉት አቶ ሙሉብርሃን፣ ኦፕሬሽኑ አሁንም በጥንቃቄ መካሄድ እንዳለበት ነው የሚያሳስቡት፡፡

‹‹ሚዲያ የማያገኘውንና ምን እየተካሄደ እንደሆነ ብዙም ያልገባውን፣ በሕወሓት ፕሮፓጋንዳና ግዳጅ ሰለባ የሆነውን የገጠሩን ማኅበረሰብ ማንቃት ያስፈልጋል፡፡ ትግራይን የማቋቋሙ ሥራ ከገጠር ወደ ከተማ እየሰፋ የሚሄድ ቢሆን ይሻላል፤›› ሲሉ የሚመክሩት ፖለቲከኛው፣ በሕወሓት መዋቅር ውስጥ የነበረውን ኃይል በአንድ ማቆያ በመሰብሰብ በሥልጠና ከሕወሓት አስተሳሰብ ነፃ ማውጣት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ በጊዜያዊነት ነፃ በወጡ አካባቢዎች አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ በፌዴራል መንግሥት የሚመራ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጣ የፀጥታ ኃይል ቢሰማራ፣ መረጋጋትና ካለፈው የተሻለ ውጤት ይመጣል ይላሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -