Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናከፊንጫ ደብረ ማርቆስ የሚዘልቀው የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ጥገና በፀጥታ ችግር ተስተጓጎለ

ከፊንጫ ደብረ ማርቆስ የሚዘልቀው የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ጥገና በፀጥታ ችግር ተስተጓጎለ

ቀን:

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከፊንጫ እስከ ደብረ ሰማርቆስ በተዘረጋው የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ የጥገና ሥራ ለማከናወን፣ በወለጋና አካባቢው ያለው የፀጥታ ሁኔታ አስቸጋሪ እንዳደረገበት ገለጸ፡፡

የተቋሙ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለሪፖርተር እንደተናገሩት ምንም እንኳ አሁን ላይ መስመሩ ተበላሽቶ አገልግሎት የተቋረጠ ባይሆንም መስመሩ ከመበላሸቱ በፊት እንደየሁኔታው እየታየ በሁለት ወይም በየሦስት ወራት ውስጥ በቅድሚያ ፍተሻ መደረግ አለበት፡፡

ይሁን እንጂ 350 ኪሎ ሜትር በሚዘልቀውና ከፊንጫ ደብረ ማርቆስ በተዘረጋው 400 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል ተሸካሚ መስመር በፀጥታ ሥጋት ምክንያት ቀድሞ መሠራት ያለበት የመስመር ፍተሻ ሥራ እንዳይሠራ ስለመሆኑና መስመሩ ላይ ምንም ዓይነት ድንገተኛ አደጋ ቢደርስ የኃይል አቅርቦቱ ሙሉ ለሙሉ እንደሚቋረጥ ተናግረዋል፡፡ በኦሮሚያ ምዕራብ ወለጋ ዞኖች ያለው የደን ሽፋን ከፍተኛ በመሆኑ፣ የአሌክትሪክ መስመሩ ላይ ኃይል ሊቋረጥ የሚችልበት ምክንያት ብዙ ስለመሆኑም አክለው ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

በተመሳሳይ የህዳሴ ግድብ-ዴዴሳ-ሆለታ ከፍተኛ መስመር ላይ የፍተሻና የጥገና ሥራ ለማከናወን መስመሩ በሚያልፍባቸው የወለጋ አካባቢዎች በተለይም የምዕራብ ወለጋ፣ የምሥራቅ ወለጋና የምዕራብ ሸዋ ዞኖች ያለው የፀጥታ ሁኔታ እንቅፋት እየሆነ መምጣቱ ተገልጿል፡፡

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ባለው የፀጥታ ችግር የተነሳ በኤሌክትሪክ ጥገና እንዲሁም በተመሳሳይ የሕዝብ አገልግሎቶች ላይ እየደረሱ ስላሉ ጉዳቶችና መስተጓጎሎች በክልሉ በኩል እየተወሰዱ ያሉ ዕርጃዎች ካሉ ለመጠየቅ ሪፖርተር ለኦሮሚያ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ በተደጋጋሚ ስልክ በመደወልና አጭር መልዕክት በመላክ በርካታ ጥረቶችን ቢያደርግም ኃላፊው ስልካቸውን ባለማንሳታቸው ምላሻቸውን ማካተት አልተቻለም።

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት ምክንያት ከወልዲያ እስከ አላማጣ መስመር ባለው የአሌክትሪክ ማስተላለፊያ የደረሰበትን ጉዳት ለመጠገን በቀን እስከ 200 ባለሙያዎችን በመመደብ የጥገና ሥራውን በአጭር ጊዜ አጠናቆ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማስረከቡን አቶ ሞገስ ተናግረዋል፡፡

በአላማጣ የሚገኘው ማስተላለፊያ ጣቢያ በጦርነቱ የደረሰበት ጉዳት ባለመኖሩ ቀደም ሲል ከዚህ ማሠራጫ ጣቢያ አገልግሎት ያገኙ የነበሩ የላሊበላና ሰቆጣ አካባቢዎች ወደ አገልግሎቱ ተመልሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በጦርነት ከሚደርስባቸው ውድመትና በተለያዩ አካባቢዎች ጥገና ለማካሄድ የፀጥታ ችግር ከፈጠረው መስተጓጎል በተጨማሪ ተደጋጋሚ የሆነ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ስርቆት እያጋጠመው መሆኑን ተቋሙ ይናገራል፡፡ ለአብነት የኢትዮ ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ የኃይል ተሸካሚ ማማ ብረቶች በተደጋጋሚ መሰረቃቸውና ለመስመሮች ደኅንነትና ለኮሙዩኒኬሽን የተዘረጋው ኦፕቲካል ግራውንድ ፋይበርና ፋይበር ኦፕቲክስ መገናኛ ሳጥኖች በዘራፊዎች መወሰዳቸውን አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ በቅርቡ ተቋሙ ጥቅምት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. እንዳስታወቀው  ከጣና በለስ ኃይል ማመንጫ ወደ ጃዊ የተዘረጋ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ የኤሌትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች በሌቦች በመፈታታቸው፣ ለበለስ ስኳር ፕሮጀክት፣ ለጃዊና አካባቢው የሚሰጠው የጃዊ ኤሌትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱ ከጥቅምት  20 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ መቋረጡን አስታውቋል

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...