Monday, March 4, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በይርጋለም ኢንዱስትሪ ፓርክ ለሚያለሙ ባለሀብቶች መሬት በድርድር ሊቀርብ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በላይነህ ክንዴ ቢዝነስ ግሩፕና ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ፍላጎታቸውን ገልጸዋል

በይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ለማልማት ፍላጎት ላሳዩ ባለሀብቶች መሬት በድርድር እንዲሁም በዝቅተኛ ዋጋ ለማቅረብ መታቀዱን የሲዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡

የይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያለውን የኢንቨስትመንት ዕድልና አማራጮችን ለአገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች ማስተዋወቅ ዓላማው ያደረገ የኢንቨስትመንት ማስተዋወቂያ መድረክ ባለፈው ሳምንት በሐዋሳ ከተማ መካሄዱ የሚታወስ ሲሆን፣ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚና የበላይነህ ክንዴ ቢዝነስ ግሩፕ ባለቤትን ጨምሮ ከ106 በላይ ባለሀብቶች በፓርኩ ገብተው ለማልማት ፍላጎታቸውን ገልጸዋል ተብሏል::

የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መምሩ ሞኬ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ባለፈው ሳምንት በተከናወነው ሁነት 106 ባለሀብቶች በተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ገብተው ለማልማት ፍላጎት ማሳየታቸውን አስታውሰው፣ ባለሀብቶቹ የሚሰማሩበትን ዘርፍ የፍላጎት ማሳወቂያ ቅጽ ከመሙላት ባሻገር የቢዝነስ ዕቅዳቸውን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

‹‹በይርጋለም የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሼድና በለማ መሬት አማራጭ ገብተው ለማልማት ፍላጎት ላሳዩ ባለሀብቶች የመሬት ዋጋ ጉዳይ መሠረታዊ ችግር አይሆንም፡፡ በድርድር ማድረግ የምንችልበት ሁኔታ ስላለ፣ አሁን ባለው ሁኔታ በተወሰነ ሁኔታ መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ዓይተናል፡፡ ባለሀብቶች ከመጡ በራሳችን ደረጃ ተደራድረን በዝቅተኛ ዋጋ ለማድረግ አስበናል፤›› ያሉት አቶ መምሩ፣ ኮርፖሬሽኑ ከዚህ ቀደም ያለውን ዋጋ አሻሽሎ ይፋ እስከሚያደርግ ድረስ በዚህ ወቅት በዝቅተኛ ዋጋ መሬት ለማቅረብ ለባለሀብቶች ቃል መግባቱን ተናግረዋል፡፡

መሬት በአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኩ በሁለት ዓይነት መንገድ ለባለሀብቱ የሚተላለፍ ሲሆን፣ አንደኛ ዘመናዊ ሼዶች ተገንብተው የሚተላለፉበት ሲሆን፣ ሁለተኛው የለማ መሬት በሊዝ የሚተላለፍበት ነው፡፡ በፓርኩ ውስጥ 11 ሼዶች የሚገኙ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ሦስቱ በሙሉ አቅም ሥራ የጀመሩ፣ ሁለቱ በሙከራ ደረጃ የጀመሩ፣ አንደኛው በማሽን ተከላ የሚገኝ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ ማሽን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት፣ ከልማት ባንክ የሚያስፈልጉ ጉዳዮችን በማመቻቸት ላይ እንደሚገኙ አቶ መምሩ ገልጸዋል፡፡

የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ከአርሶ አደሩ በመቀበል የአቮካዶ ዘይት፣ ወተት፣ ማርና ቡናን በማቀነባበር ለአገር ውስጥና ውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ፋብሪካዎችን ወደ ተግባር ማስገባቱን ያስታወቀው ኮርፖሬሽኑ፣ ለአብነትም በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ፓርኩ ውስጥ የሚገኙት ፋብሪካዎች ወደ ውጭ ከላኩት ምርት 2.6 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ከማስገኘታቸው ባሻገር ከ140 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር መፈጸማቸውን ገልጿል፡፡

በይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከሚገኘው አጠቃላይ መሬት 97.5 ሔክታር የሚሆነው የለማ እንደሆነ፣ 8.6 ሔክታር መሬት ደግሞ በሼድ የተሸፈነና የተቀረው ደግሞ በሊዝ የተላለፈ መሆኑን አቶ መምሩ ገልጸዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች