Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአብን በደቡብ አፍሪካ የሚደረገው የሰላም ንግግር ይሳካል የሚል እምነት እንደሌለው ገለጸ

አብን በደቡብ አፍሪካ የሚደረገው የሰላም ንግግር ይሳካል የሚል እምነት እንደሌለው ገለጸ

ቀን:

የፌዴራል መንግሥትና ሕወሓት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ እያደረጉት ያለው የሰላም ንግግር ይሳካል የሚል እምነት እንደሌለው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አስታወቀ፡፡

‹‹ፓርቲው ሕወሓት የሰለም ንግግሩ ውስጥ የገባው፣ መልሶ ለማገገምና ለመታጠቅ ይረዳው ዘንድ ነው፤›› ያለ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት እየተደረገ ካለው የሰላም ንግግር የሚጠብቀው ውጤት እንደሌለ ገልጿል፡፡

አብን እየተደረገ ባለው የሰላም ንግግርና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ማክሰኞ ጥቅምት 22 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ መንግሥት በሰላም ውይይቱ ሊይዘው የሚገባው አቋም፣ ሕወሓትን ትጥቅ ከማስፈታትና የፖለቲካ ህልውናውን ከማክሰም ያነሰ መሆን እንደሌለበት አቋሙን አሳውቋል፡፡ የፓርቲው ሊቀመንበር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)፣ ‹‹ሕወሓት ልደራደር ሲል እንዲድን ነው፣ መዳን ያለበት ድርጅት ደግሞ አይደለም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በመግለጫው ላይ ማብራሪያ የሰጡት የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ መልካሙ ሹምዬ ደግሞ፣ ‹‹የሰላም ንግግሩ የተጀመረው ሕወሓት ባልተጠበቀ ሁኔታ ሽንፈት ስላጋጠመው ነው፤›› የሚል እምነት እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡ ‹‹[የሕወሓት] ባህሪው ለፖለቲካዊ ንግግር የሚመች አይደለም፤›› ያሉት ምክትል ሊቀመንበሩ፣ ሕወሓት ጊዜ ለማግኘት፣ ለማገገም፣ ለመታጠቅና እንደገና ወረራ ለመፈጸም እንዲያስችለው የሰላም ንግግር ጥሪውን መቀበሉን ተናግረዋል፡፡

ይሁንና አብን ስለሕወሓት ያነሳው ጥርጣሬ ቢኖርም፣ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር እየተደረገ ያለውን የሰላም ንግግር እንደሚደግፍና ንግግሩ እንዲሳካ አስፈላጊውን ጥረት እንደሚያደርግ ምክትል ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡ አቶ መልካሙ፣ ‹‹ወታደራዊ ዘመቻው ሊያሳካው የሚችለው ግብ በሰላማዊ ንግግር ማግኘት ከተቻለ የማንደግፍበት ሁኔታ የለም፤›› በማለት፣ ከላይ ካነሱት ሐሳብ ጋር የሚጋጭ አስተያየት ሰጥተው፣  መንግሥት እየወሰደ ያለው ወታደራዊ ዕርምጃ ግን ከንግግሩ ጎን መቀጠል አለበት የሚልም ሐሳብ አንስተዋል፡፡ ጥምር ኃይሉ ከሚወስደው ዕርምጃ ቀጥሎ ታጣቂዎቹን ትጥቅ የማስፈታት ሥራ መሠራት አለበት የሚለው የፓርቲያቸው አቋም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የፓርቲው ሊቀመንበር በለጠ (ዶ/ር)ም በመግለጫው ላይ ይህንን ሐሳብ ያንፀባረቁ ሲሆን፣ ‹‹ሕወሓት መዳን ያለበት ድርጅት አይደለም፣ በዚህ ላይ ብዥታ የለም፤›› በማለት ሐሳቡን አጠናክረዋል፡፡ ‹‹ሕወሓትን እየተሸነፈ ያለ ድርጅት፤›› ሲሉ የገለጹት ሊቀመንበሩ፣ ከሕወሓት ጋር የሚደረግ ድርድር በመደበኛ ሁኔታ ከሚደረግ ድርድር ጋር ተመሳሳይ ዓይነት ትርጉም ሊሰጠው እንደማይችል ተናግረዋል፡፡

ፓርቲው በመግለጫው ላይ አጽንኦት ሰጥቶ ያነሳው ሌላው ጉዳይ፣ ‹‹የአማራ ሕዝብ ተደራዳሪ ልዑካን›› በሚል የተዋቀረውን ቡድን የሚመለከት ነበር፡፡ አብን፣ ‹‹የሰላም ንግግሩ በብሔሮች መካከል የሚደረግ አይደለም፤›› ሲል፣ ‹‹የአማራ ሕዝብ ተደራዳሪዎች›› በሚል ይፋ የተደረገውን ቡድን ተቃውሟል፡፡

ሊቀመንበሩ በለጠ (ዶ/ር)፣ አብን ቡድኑን የማይቀበለው የሕዝብን ዘላቂ ጥቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን ሲናገሩ፣ ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ መልካሙ ደግሞ፣‹‹አማራ በተለየ ሁኔታ መወከል አለበት የሚለው የሕወሓት ሐሳብ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ባለፈው እሑድ ከሪፖርት ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአብን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የአማራ ተደራዳሪ ቡድን አባል ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)፣ በሰላም ንግግሩ ላይ የአማራ ሕዝብን ለመወከል በተቋቋመው 40 ሰዎችን የያዘ ኮሚቴ ውስጥ፣ ከአሥር በላይ የአብን ማዕከላዊና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት መኖራቸውን ተናግረው ነበር፡፡

በመግለጫው ላይ ስለዚህ ጉዳይ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አቶ መልካሙ፣ የፓርቲያችን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ከሆኑት ውስጥ ደሳለኝ (ዶ/ር)፣ ‹‹እዚያ ውስጥ እንዳለ እናውቃለን፣ ከዚያ በተረፈ እኛ የምናውቀው ነገር የለም፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም፣ አብዛኛው የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የፓርቲውን መስመር ተከትሎ የሚሄድ መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹ከፓርቲ መዋቅር ውጪ አፈንግጠው የተለየ አቋም እያሳዩ ያሉ አካላት አሉ፡፡ እሱ በፓርቲ መዋቅር፣ ገደብና ዲሲፕሊን ራሱን ችሎ የሚገራ ነው የሚሆነው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...