ዘንድሮ በመኸርና በበጋ መስኖ የሚለማው የስንዴ ምርት ለአገር ውስጥ ፍጆታ ከመዋል አልፎ አሥር ሚሊዮን ኩንታል ትርፍ የሚገኝበት መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሚኒስቴሩ እንዳስታወቀው፣ የ2014/15 የመኸር ምርት ዘመን ሰብል በዚህ ወቅት እየተሰበሰበ ሲሆን፣ ይገኛል ተብሎ ከሚጠበቀው 108 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ባሻገር በበጋ መስኖ 52 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚገኝና በድምሩ 160 ሚሊዮን ኩንታል ምርት አገሪቱ ታገኛለች ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል፡፡
የአገሪቱ የሕዝብ ቁጥር ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ፣ በተጨማሪም በየዓመቱ የሚያድገውን የአገር ውስጥ የፍጆታ መጠን በትክክል በማስላት በ2015 ዓ.ም. 97 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለአገር ውስጥ ፍጆታ እንደሚያስፈልግ መረዳቱን ያስታወቀው የግብርና ሚኒስቴር፣ ይህንን ዝርዝር ጥናት በርካታ ኢኮኖሚስቶችና የሰብል ልማት ሰዎች ያጠኑት ስለመሆኑ ገልጿል፡፡
‹‹ሌላው ቢቀር በመኸርና በመስኖ ብንሠራ 107 ሚሊዮን ኩንታል ማምረት እንችላለን፣ በጣም በዝቅተኛ ግምት ነው ይህንን የገመትነው፡፡ ይህን ብቻ በማሰብ አሥር ሚሊዮን ኩንታል ትርፍ ምርት አለን፤›› ያሉት በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆልቲካልቸር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ መኮንን (ዶ/ር)፣ በድምሩ በመኸርና በመስኖ የሚለማው የምርት መጠን ከታቀደው በላይ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡
‹‹አሥር ሚሊዮን አይደለም ከዚያ በላይ ትርፍ ማምረት የምንችልበት ዕድል አለ፡፡ ይህንንም ኤክስፖርት ማድረግ የምንችልበት ዕድል አለ፤›› ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው አክለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በየዓመቱ ስንዴን ከውጭ ለማስገባት ከ700 ሚሊዮን ዶላር እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር ስታወጣ ቆይታለች ያሉት መለስ (ዶ/ር)፣ በዚህ ዓመት አገሪቱ ይህን ወጪ ማቋረጧን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል ብለዋል፡፡
መለሰ (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፣ በ2014/15 ዓ.ም. የመኸር ምርት ዘመን በአገሪቱ 13.4 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በመደበኛና በማሳ ኩታ ገጠም ዘዴ በማረስ 400 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ታቅዶ፣ 13.37 ሚሊዮን ሔክታር የሚሆነው በዘር ተሸፍኗል፡፡ ከዚህም 2.68 ሚሊየን ሔክታር የሚሆነው መሬት በትራክተር መታረሱን ገልጸዋል፡፡
በመኸር ወቅቱ 2.8 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በስንዴ መሸፈኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህም ከ108 ሚሊዮን ኩንታል ያላነሰ ምርት እንደሚጠበቅና ይህም የመኸር ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአማካይ በሔክታር ከ36 እስከ 38 ኩንታል ቢገኝ የሚል ሥሌትን ታሳቢ ያደረገ ነው ተብሏል፡፡ በስንዴ ከተሸፈነው ምርት 1.7 ሚሊዮን ሔክታር የሚሆነው በማሳ ኩታ ገጠም (ክላስተር) የለማ እንደሆነ ታውቋል፡፡
በ2015 በመስኖ ልማት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቼ እየሠራሁ እገኛለሁ ያለው የግብርና ሚኒስቴር፣ በዓመቱ ከ1.3 ሔክታር በላይ የመስኖ ስንዴ ልማት በዘጠኝ ክልሎች እንደሚለማ ገልጿል፡፡ በመስኖ ልማት የሚለማው ምርት በምርታማነት ከመኸር ወቅት የተሻለ ስለሚሆን፣ በሔክታር በአማካይ የሚገኘውን 40 ኩንታል ምርት ከግምት ውስጥ በመክተት ከ52 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴ መሰብሰብ የሚቻልበት ዕድል እንዳለም ተመላክቷል፡፡
ሪፖርተር ከዚህ ቀደም በተለይም በስንዴ ምርት ዙሪያ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን አስመልክቶ ያነጋገራቸው የግብርና ኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደተናገሩት፣ በበጋም ሆነ በክረምት እየተመረቱ ያሉ የምርት እንቅስቃሴዎችን አስታውሰው፣ እነዚህ ሒደቶች ያሳዩት እመርታ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከሚፈለገው አንፃር ምን የተገኘ ነገር አለ? አገሪቱ የሚያስፈልጋትን ያህል ምርት አምርታ ወደ ውጭ መላክ ትችላለች? የሚለው ጥናት የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን ይህ እንቅስቃሴ መጀመሩ እንደተጠበቀ ሆኖ አጠናክሮ ማስቀጠሉ ዋነኛው ጉዳይ መሆኑን ይስማሙበታል፡፡