Monday, March 4, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባንኮች ከሚያበድሩት 20 በመቶውን የግምጃ ቤት ሰነድ እንዲገዙበት የሚያስገድድ መመርያ ፀደቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሁሉም የንግድ ባንኮች ከሚለቁት ብድር ውስጥ 20 በመቶውን በየወሩ ወደ መንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ ግዥ ፈሰስ እንዲያደርጉ የሚያስገድድ መመርያ ፀደቀ፡፡ በብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ተፈርሞ ከትናንት ጥቅምት 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው መመርያ፣ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ውጪ በሁሉም ባንክ ላይ ተግባራዊ ይሆናል፡፡

ባንኮቹ ያበደሩትን 20 ከመቶን በየወሩ እያሠሉ የግምጃ ቤት ሰነድ የሚገዙበት ገንዘብ ተጠራቅሞ አምስተኛው ዓመት ላይ የሚመለስላቸው ሲሆን፣ የወለድ መጠኑም ከተቀማጭ ወለድ ላይ ሁለት ከመቶ በመጨመር ይሆናል፡፡ ይህም ማለት ለምሳሌ አሁን ያለው ሰባት በመቶ የተቀማጭ ወለድ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ፣ ወለዳቸው ዘጠኝ በመቶ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ካለፈው ዓመት መስከረም ወር ጀምሮ ባንኮች የጠቅላላ ዓመታዊ ብድራቸውን አንድ በመቶ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክን ቦንድ እንዲገዙበት የሚያዘው መመርያ እየተተገበረ ሲሆን፣ ይህ መመርያ ለአሥር ዓመታት የሚቀጥል ነው፡፡ አዲስ ከወጣው መመርያ ጋር ባንኮች በአጠቃላይ ከሚያበድሩት 21 በመቶውን ወደ መንግሥት ፋይናንስ ፈሰስ ያደርጋሉ ማለት ነው፡፡ ከዚሁ በተጓዳኝ ባንኮች ሰባት ከመቶ መጠባበቂያ ገንዘብ ማስቀመጥ እንዳለባቸው ይታወቃል፡፡ ስለዚህ በአጠቃላይ ባንኮች ከሚሰበስቡት ጠቅላላ ተቀማጭ ውስጥ 28 በመቶውን በተለያየ ምክንያት መልሰው ለማበደር ሊጠቀሙት አይችሉም ማለት ነው፡፡

አዲሱ መመርያ ከዚህ ቀደም ባንኮች ይሰጡ ከነበረው የ27 በመቶ ግዴታ ጋር ተመሳሳይ ሲሆን፣ ልዩነቱ ይኼኛው በየወሩ መሆኑ፣ ወለዱ ከፍ ማለቱና ከባንኮች የተሰበሰበው የግምጃ ቤት ሰነድ መግዣ ገንዘብ በንግድ ባንክ በኩል ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች መሰጠቱ ነው፡፡ መንግሥት ወለዱን በየዓመቱ የሚከፍል ሲሆን፣ ዋናውን (የተጠራቀመውን 20 በመቶ) በአምስተኛው ዓመት ይከፍላል፡፡

አዲሱ መመርያ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት የመንግሥትን የበጀት ጉድለት ለመሸፈን መሆኑ ታውቋል፡፡ ለተያዘው 2015 በጀት ዓመት ከፀደቀው 787 ቢሊዮን ብር ውስጥ የበጀት ጉድለቱ 308 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ከጠቅላላ አገራዊ ምርቱ (GDP) 4.1 ከመቶ ይይዛል፡፡ ከ308 ቢሊዮን ብር በጀት ጉድለቱ ውስጥ 266 ቢሊዮን ብሩ ከአገር ውስጥ ብድር ይሸፈናል ተብሎ መወሰኑም ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ ከአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ምንጮች ይገኛሉ ተብሎ የተጠበቀው ባለመሳካቱ፣ መንግሥት አዲሱን መመርያ ለማውጣት መገደዱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በተለይ በትልቁ ሲጠበቅ የነበረው የውጭ ዕዳ ሽግሽግና አዲስ የ‹‹አይኤምኤፍ ፕሮግራም›› በውጭ ፖለቲካ ጫና ምክንያት መዘግየቱ፣ መንግሥት የበጀት ጉድለቱን ለመሙላት ወደ አገር ውስጥ ምንጮች እንዲያማትር ማስገደዱ ተገልጿል፡፡

የአገር ውስጥ ምንጮች የተባሉት አንደኛው በብሔራዊ ባንክ በኩል የሚሸጥ የግምጃ ቤት ሰነድ ሲሆን፣ ሌላው መንግሥት ቀጥታ ከብሔራዊ ባንክ የሚበደርበት ሁኔታ ወይም የቀጥታ ብር ኅትመትና ሥርጭት ነው፡፡ ሁለተኛው አማራጭ የዋጋ ግሽበቱን የበለጠ እንዳያባብሰው ስለተፈራ ብዙም እንዳልተሄደበት ምንጮች ጠቅሰዋል፡፡

ምንም እንኳን በመደበኛው ግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ ላይ የባንኮች ተሳትፎ እያደገ ቢመጣም፣ ከፍተኛ የሆነውን የመንግሥት የበጀት ጉድለት ለመሸፈን አልቻለም፡፡ ከዚህ ቀደም በአብዛኛው የግምጃ ቤት ሰነድ የሚገዙት ሁለቱ የጡረታ ኤጀንሲዎች የነበሩ ሲሆን፣ በ2014 ዓ.ም. ግን ባንኮች በግምጃ ቤት ሰነድ ላይ የሚያደርጉት መዋዕለ ንዋይ ብልጫ አሳይቷል፡፡

በ2013 ዓ.ም. የነበሩት 19 ባንኮች 329 ቢሊዮን ብር ብድር የለቀቁ ሲሆን፣ አሁን ግን የባንኮች ቁጥር 30 በመድረሱ፣ በዚህ ዓመት እስከ 500 ቢሊዮን ብር ብድር ይለቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዚህም ላይ 20 በመቶው ሲሠላ መንግሥት እስከ 100 ቢሊዮን ብር ከአዲሱ የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ በዚህ ዓመት ሊሰበስብ ይችላል፡፡

ይሁን እንጂ የባንክ ፕሬዚዳንቶችና ባለሙያዎች አዲሱ መመርያ በባንኮች ላይ ጫና ማምጣቱ የማይቀር መሆኑንና ባንኮች ከፍተቱን ለመሙላት ከአሁኑ አዳዲስ አማራጮችን መቀየስ እንዳለባቸው ለሪፖርተር ይገልጻሉ፡፡

‹‹ባንኮች ከሚሰበስቡት ተቀማጭ ላይ አሁን አበድረው ወለድ ሊያገኙበት የሚችሉት 72 ከመቶውን ብቻ ነው፡፡ ባንኮች ከፍተኛ የጥሬ ገንዘብ እጥረት (Liquidity Crunch) ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ ተጨማሪ ብዙ ተቀማጭ ሰብስበው ለማበደር መዘጋጀት አለባቸው፡፡ ከማበደር የሚያገኙትም ወለድ ገቢ ስለሚቀንስ ትርፋቸው እንዳይጎዳ የወለድ ምጣኔያቸውን ከፍ ሊያደርጉ ይችላሉ፤›› ይላሉ በባንክ ዘርፉ ከ20 ዓመታት በላይ ያገለገሉና ለሪፖርተር ሐሳባቸውን ያካፈሉና ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የባንክ ፕሬዚዳንት፡፡

የባንክ ፕሬዚዳንቱ እንደሚሉት፣ ረቂቅ መመርያው ከመፅደቁ በፊት ለባንኮች ተልኮ የነበረ ሲሆን፣ ሁሉም ባንኮች የተቃውሞ ሐሳብ አቅርበው የነበረ ቢሆንም፣ ብሔራዊ ባንክ ግን ሐሳባቸውን እንዳልተቀበለው ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

የባንክ ኃላፊው፣ ‹‹ይህ መመርያ በተለይም አዳዲስ በተቋቋሙ ባንኮችና ትንንሽ ባንኮች ላይ ከፍተኛ ጫና ያመጣል፤›› ይላሉ፡፡

የአዲሱ መመርያ ተፅዕኖ ለመቋቋም ባንኮች ብዙ ዕርምጃዎችን መውሰዳቸው የማይቀር መሆኑንና ይህም በተበዳሪዎች ላይ ጫና እንደሚያመጣ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ለምሳሌ ወለድና የአገልግሎት ክፍያ (Service Charge) ከፍ ማድረግ አንዱ ነው፡፡

‹‹መመርያው ለመንግሥት የመጨረሻው አማራጭ ነው፡፡ በተለይ በጦርነቱ ምክንያት የመንግሥት ወጪ በመብዛቱና የውጭ ገንዘብ ምንጮች በመዘጋታቸው ሌላ የገቢ አማራጭ የለም፡፡ ነገር ግን ይህ ውሳኔ በባንኮችና በፋይናንስ ገበያው ላይ ተደራራቢ ጫና ማምጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ በመደበኛው የባንክ ብድር አሰጣጥና የግምጃ ቤት ሰነድ፣ በአብዛኛው ትኩረቱ የአጫጭር ጊዜ በመሆኑ ለመንግሥት ሊጠቅም አልቻለም፡፡ መንግሥት ከረዥም ጊዜ በኋላ የሚከፍለው ብድር ነው የፈለገው፡፡ ግን ይህ ውሳኔ በባንኮች ላይ ከፍተኛ የጥሬ ገንዘብ እጥረት የሚፈጥር ሲሆን፣ በኢኮኖሚው ውስጥ ደግሞ የዋጋ ግሽበቱን ያባብሰዋል፤›› ይላሉ ባለሙያው፡፡

ይሁን እንጂ መንግሥት ከተጋረጠበት የሥራ ማስኬጃና የፕሮጀክት በጀት እጥረት አንፃር መመርያው ‹‹እንደ አደጋ ጊዜ ዕርምጃ›› የሚወሰድ በመሆኑ ባንኮች ቢቃወሙም ያለ ውዴታ መቀበላቸውን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች