በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)
ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮጵያዊው ጀግና በጄኔራል ታደሰ ብሩ የሕይወት ታሪክ ላይ ያጠነጠነ መጽሐፍ በዙፋን ኡርጋ ተጽፎ ለምርቃት በቅቷል፡፡ ታሪካችንን ሙሉዕ ለማድረግና የዛሬውና የነገው ትውልድ በጀግኖች አባቶቹና እናቶቹ የጀግንነት ገድል ብሔራዊ ኩራት እንዲኖረው ለማድረግ፣ እንዲህ ዓይነቶቹ መጻሕፍት መታተም ፋይዳቸው ትልቅ ነውና ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ በዛሬው ጽሑፌም ከጄኔራል ታደሰ ብሩ የሕይወት ታሪክ ጋር በተያያዘ ሁለት ገጠመኞቼን በማስቀደም ጥቂት ነገሮችን ለማንሳት ወደድኩ፡፡
ጀግናው ጄኔራል ታደሰ ብሩ የኦሮሞ ምድር ያፈራቸው ጀግና ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ፣ ጀግንነታቸው ከኢትዮጵያ ምድር አልፎ በአኅጉረ አፍሪካ ጭምር ከፍ ያለ ነው፡፡ ስለ እኚህ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን ጀግንነትና ደቡብ አፍሪካ ድረስ ስለተሻገረው ዝናቸው ያወቅኩባቸው ሁለት አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ የመጀመሪያው በደቡብ አፍሪካ፣ በዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን በምከታተልበት ወቅት በሆነ አንድ አጋጣሚ ነበር፡፡
አጋጣሚው ይህን ይመስላል፡፡ በምማርበት በዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርሲቲ፣ የሮቢን ሙዚየም የማይቡዬ ቤተ-መዛግብት/አርካይቭ ክፍል ኃላፊ፣ የመዛግብት ጥናት መምህራችን የሆነች ደቡብ አፍሪካዊት ፕሮፌሰር ሴት በአንድ ወቅት በዩኒቨርሲቲው አርካይቭ ካለው የፎቶ ስብስቦች ውስጥ ሁለት ፎቶችን አምጥታ አሳየችኝ፡፡ ፎቶዎችን እያቀበለችኝ፣ ‘‘ከነፃነት ታጋያችን፣ ከታታ ማዲባ/ኔልሰን ሮሂላላ ማንዴላ ጋር አብረው የተነሱትን እኚህን ኢትዮጵያዊ፣ ጀግና የጦር መኮንን ታውቃቸው ይሆን?!’’ ስትል ጠየቀችኝ፡፡
እኔም ፎቶውን በኢትዮጵያዊ የጀግንነት ኩራት ትኩር ብዬ እያየሁ… አዎን አውቃቸዋለሁ! ኔልሰን ማንዴላ ያሠለጠኑትና በወቅቱ የኮልፌ ፈጥኖ ደራሽ ማሠልጠኛ አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ታደሰ ብሩ ናቸው፡፡ አልኳት፡፡ ‘‘ኦ! ትክክል ነህ፣ ይገርማል እነዚህን ፎቶዎች ያሳየኋቸው አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውን ተማሪዎች አያውቋቸውም፡፡ እነዚህ ፎቶዎች በቤተ መዛግብታችን/በአርካይቫችን ውስጥ ለብዙ ጊዜ ቆይተዋል፡፡ እዚህ ዩኒቨርሲቲ በስኮላርሺፕ ለሚመጡ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ሁሉ፣ ‘‘እናንተ ኢትዮጵያውያን ለእኛ ለደቡብ አፍሪካውያን ከዘረኛው አፓርታይድ አገዛዝ ነፃ እንድንወጣ ላደረጋችሁት አስተዋጽኦ ባለውለታዎቻችን ናችሁና ሁሌም አመሥጋኞቻችሁ ነን በማለት፣ ይህን ታሪካዊ ፎቶዎች እያሳየኋቸው በኩራት እነግራቸዋለሁ፤’’ አለችኝ፡፡
በእርግጥም፣ የነፃነት አርበኛ፣ የሰላም አባት፣ የይቅር ባይነት ተምሳሌት፣ የአይበገሬነት የፅኑ መንፈስ ባለቤት፣ የመለያየትንና የዘረኝነትን ፅኑ ግንብ በወንድማማችነት መንፈስ ያፈረሱ፣ የጠላትነትን ክፉ የጥላቻ ዘር በፍቅር ያመከኑ፣ በሰላምና እርቅ ጥሪያቸው ለበቀል የተመዘዙ የጥፋት ሰይፎችን ወደ ሰገባቸው እንዲመለሱ ያደረጉ፣ የሰው ልጆች ሁሉ አንድነት፣ የሰብዓዊነት ክብር ምልክት በመባል የሚታወቁት- ታታ ማዲባ/ኔልሰን ማንዴላ – የነፃነት ትግል ሕይወት ውስጥ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ያለን ሥፍራ በእጅጉ የተለየና ታላቅ ነው፡፡ የዚህ ታሪክ ተጋሪና የፀረ አፓርታይድ ትግሉ አጋር ከሆኑ ኢትዮጵያኖች መካከል ደግሞ ኢትዮጵያዊው ጄኔራል ታደሰ ብሩ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ይህን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በልባቸው ውስጥ ያላቸውን ታላቅ ሥፍራና ክብር በተመለከተ፣ ራሳቸው ማንዴላ በጻፉት ‘‘Long Walk to Freedom’’ በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ እንዲህ በማለት ነበር የገለጹት፡፡
‘‘Ethiopia has always held a special place in my own imagination and the prospect of visiting Ethiopia attracted me more strongly than a trip to France, England and America combined. I felt I would be visiting my own genesis, unearthing the roots of what made me African.’’
ሌላኛው ጄኔራል ታደሰ ብሩን በይበልጥ ታሪካቸውን እንዳውቅ ያደረገኝ አጋጣሚ ደግሞ ይህን ይመስላል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት የደቡብ አፍሪካው የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ/ኤኤንሲ መቶኛ ዓመቱን ለማክበር ሲዘጋጅ፣ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በኤኤንሲ ፓርቲና በኔልሰን ማንዴላና የትግል ጓዶቹ የፀረ-አፓርታድ ትግል ዙሪያ የሚያጠነጥን ዶክመንተሪ ፊልም ለመሥራት የደቡብ አፍሪካ DV8 እና የእንግሊዝ ቢር ኸርት ሊሚትድ የተባሉ የፊልም ካምፓኒዎች የተጣመሩበት ቡድን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ነበር፡፡
ይህ ዶክመንተሪ ፊልም ዋናው ዓፅመ ታሪኩ የሚያጠንጥነው ኔልሰን ማንዴላ ለወታደራዊና ለፖለቲካዊ ሥልጠና ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ወደ አገራቸው በሚመለሱበት ወቅት በአሠልጣኛቸው በጄኔራል ታደሰ ብሩ በተበረከተላቸው ቡልጋሪያ ሠራሽ ማካሮቭ ሽጉጥ ላይ ነው፡፡ ታዲያ ማንዴላ ሥልጠናቸውን አጠናቀው ወደ አገራቸው ደቡብ አፍሪካ ሲመለሱ ይህን ማካሮቭ ሽጉጥ በጆሐንስበርግ ከተማ በሚገኘው የኤኤንሲ ፓርቲ ህቡዕ መሰብሰቢያ ግቢ ውስጥ ባለ አንድ ዛፍ ሥር በሚስጥር ቀብረውት ነበር፡፡
ማንዴላ በኢትዮጵያ በተመለሱ ማግሥትም በዘረኛው የአፓርታይድ መንግሥት ‘‘በአገር ክዳት’’ ወንጀል ተከሰው ወደ ወኅኒ እንዲወረወሩ ተደረጉ፡፡ ማንዴላ ከ27 ዓመታት እስር በኋላ ከእስር ቤት ሲወጡ ያቺን የኤኤንሲ ፓርቲ የትጥቅ ትግል ማብሰሪ የሆነች ማካሮቭ ሽጉጥ ከቀበሩበት ለማውጣት፣ ወደ ጆሐንስበርግ የቀድሞው የፓርቲያቸው ህቡዕ መስበሰቢያ አዳራሸ ግቢ ከትግል ጓዶቻቸው ጋር አምርተው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ቦታው በመቀያየሩና ጊዜው በመርዘሙ የተነሳ ማንዴላ በትክክል ቦታውን ለመጠቆም አልቻሉም ነበር፡፡ እናም ከኢትዮጵያዊው አሠልጣኛቸው ከጄኔራል ታደሰ ብሩ በስጦታ የተበረከተላቸውን ያችን ማካሮቭ ሽጉጥ ከተቀበረችበት ቆፍሮ በማውጣት ከኤኤንሲ 100ኛ ዓመት ምሥረታ በዓል ጋር በማስተሳሰር፣ የፀረ አፓርታይድ ትግል ረዥሙ ጉዞ ታሪካዊ ቅርስና አሻራ እንድትሆን በማሰብ የተደረገው ሙከራም ሳይሳካ ይቀራል፡፡
ሽጉጧን ቆፍሮ ለማውጣት የተደረገው ሙከራ ባይሳካም፣ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በኔልሰን ማንዴላና በኤኤንሲ የፀረ-አፓርታይድ ትግል ታሪክ ውስጥ ደማቅ አሻራ ያላትን ከኢትዮጵያዊው ጄኔራል ታደሰ ብሩ ለማንዴላ የተበረከተችውን ሽጉጥ፣ የደቡብ አፍሪካውያን የነፃነት ትግል ቋሚ ማስታወሻ ቅርስ ናት፡፡ እናም ታሪኳ በሚገባ ሊዘከር ይገባል ሲል ‘‘The Mandela’s Gun’’ በሚል አርዕስት ዶክመንተሪ ፊልም ለመሥራት ነበር፣ የደቡብ አፍሪካና የብሪቲሽ የፈልም ካምፓኒዎች የተጣመሩበት ቡድን ወደ አገራችን የመጡት፡፡
በዚህ ዶክመንተሪ ፊልም ፕሮጀክት ውስጥ የማንዴላን የኢትዮጵያ ቆይታ፣ ወታደራዊና ፓለቲካዊ ሥልጠና በተመለከተ የጥናት ምርምር ሥራ ለመሥራት ቀዳሚ ተመራማሪ (Senior Researcher) ሆኜ ለመሥራት ዕድሉ ገጥሞኝ ነበር፡፡ በወቅቱ በዚህ ፕሮጀክት ውስጥ መሳተፌ ስለ ጄኔራል ታደሰ ብሩ በይበልጥ ለማወቅ ትልቅ ዕድል ነበር የሰጠኝ፡፡ ታዲያ በወቅቱ ስለጄኔራል ታደሰ ቃለ መጠይቅ ካደረኳቸው መካከል ታናሽ እህታቸው ወ/ሮ ፀሐይ ታደሰና የማንዴላ የቅርብ ሰውና ሌላኛው አሠልጣኛቸው የነበሩት ኮሎኔል ፈቃዱ ዋኬኔ ይገኙበታል፡፡
ከወ/ሮ ፀሐይ ጋር በነበረን ቆይታም ታላቅ ወንድማቸው ጄኔራል ታደሰ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ አስፈላጊ ያሏቸውን መረጃዎችና ታሪካዊ ሰነዶች እንዳስረከቧቸው፣ እነዚህን መረጃዎችም በብረት ሳጥን ውስጥ ቆልፈው እንዳስቀመጧቸው አጫውተውኝ ነበር፡፡ ጄኔራሉ በተለይ ለነፃነት፣ ለፍትሕና እኩልነት ካደረጉት ትግላቸው ባሻገርም ከእነ ፕ/ር ኤፍሬም ይስሐቅ ጋር በመሆን በአብዛኛው በማይምነት ጨለማ ውስጥ የነበረውን የገጠሩን ኢትዮጵያዊ ከማይምነት እንዲላቀቅ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ነግረውኛል፡፡ በወቅቱ ለማስተማር ይጠቀሙበት የነበረው የፊደል ሠራዊት ያየዘው የፊደል ገበታም ለታላቅ ወንድማቸው፣ ለጄኔራል ታደሰ ብሩ መታሰቢያነት በሚል በመኖሪያ ቤታቸው መግቢያ ግድግዳ ላይ በክብር ተሰቅሎ አስተውያለሁ፡፡
ወ/ሮ ፀሐይ እንደነገሩኝ፣ ወንድማቸው ለነፃነትና ለፍትሕ ሲታገሉ የነበሩ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ነበሩ፡፡ ከደቡብ አፍሪካውያን የፀረ አፓርታይድ ተጋድሎ ታሪክ ጋር በተያየዘም ጄኔራሉ ለወታደራዊና ለፖለቲካዊ ሥልጠና ወደ ኢትዮጵያ የመጡትን ኔልሰን ማንዴላን ለእውነትና ለፍትሕ፣ ለሰው ልጆች ነፃነት በጽናት እንዲቆሙ አስተምሯቸዋል፡፡ ዘረኛውን የአፓርታይድ ሥርዓት ለማስወገድ ማንዴላና የትግል አጋሮቻቸው ለጀመሩት የትጥቅ ትግል መታሰቢያ ይሆን ዘንድም፣ ጄኔራል ታደሰ ብሩ ለማንዴላ ሽጉጥ አበርክተውላቸው ነበር፡፡
ይህች ሽጉጥም ከነፃነት ምድር፣ ከጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ታሪክ፣ የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ፣ ቅርስና የሥልጣኔ እምብርት ከሆነችው ከኢትዮጵያዊው መኮንን ከጄኔራል ታደሰ ብሩ ዘንድ በስጦታ የተገኘች ናትና በማንዴላና በትግል ጓዶቻቸው/በኤኤንሲ ፓርቲ ልብ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ያላት ናት፡፡
ይህች ሽጉጥ ተራ ሽጉጥ አይደለችም፡፡ ይህች ሽጉጥ የከበረውን የሰውን ልጅ ደም በከንቱ ለማፍሰስ የተሰጠችም ሽጉጥ አይደለችም፡፡ ይህች ሽጉጥ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ለነፃነታቸው ክብር የከፈሉትን ክቡር መስዋዕትነት የምታሳስብ፣ ለጥቁር ሕዝቦች ነፃነት ተምሳሌት ትሆን ዘንድ ከጥቁሮች አናብስት ምድር ለማንዴላ የተበረከተች ማስታወሻ ናት፡፡
ይህች የጄኔራል ታደሰ ብሩ ስጦታ የሆነች ሽጉጥ፣ ማንዴላና ደቡብ አፍሪካውያን ፈጣሪ በሰጠን ውብ ምድር ላይ ነፃነት፣ እውነትና ፍትሕ … ድል ነስተው እስኪወጡ ድረስ የአንቺ ሥፍራ የከበረ የአገራችን ጥቁር አፈር ነው ሲሉ፣ ያችን ነፃነት ዓርማ የሆነች ሽጉጥ በዘረኞቹ የአፓርታይድ አራማጆች ስብከትና የጥይት አረር በጥቁሮች ሕዝብ ደም ለጨቀየችው፣ በሕዝቦቿ ግፍና ሰቆቃ ለተጨነቀችው ምድራቸው በአደራ አስረከቧት፡፡
በኢትዮጵያዊው ጀግና በጄኔራል ታደሰ ብሩ ልብ ውስጥ የናኘው የኢትዮጵያዊነት የነፃነት ህያው መንፈስ፣ አይበገሬነት፣ ቆራጥነትና የጀግንነት ወኔ- ከኢትዮጵያ ምድር ተሻግሮ በማንዴላና በደቡብ አፍሪካውያን የነፃነት አርበኞች ልብ ውስጥ ትልቅ የነፃነት ሐውልት ተክሏል፡፡ እናም ኢትዮጵያዊው ጀግና ጄኔራል ታደሰ ብሩ የፀረ አፓርታይድ ትግል አጋር አፍሪካዊው ጄኔራል መባላቸውን ትክክል የሚያደርገው፣ ይህ የከበረ ታሪካቸውና እኛም እንደ ኢትዮጵያዊ የምንጋራው አኩሪ የታሪካችን አካል መሆኑ ነው፡፡ ሰላም!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡