Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አንበሳ ኢንሹራንስ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት 63.9 ሚሊዮን ብር አተረፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

አንበሳ ኢንሹራንስ በተጠናቀቀው የ2014 የሒሳብ ዓመት 436.5 ሚሊዮን ብር ገቢ ከዓረቦን ክፍያና ከሌሎች የገቢ ምንጮች በመሰብሰብ በዓመቱ መጨረሻ ላይ ከታክስ በፊት 63.9 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ፡፡ 

የኢንሹራንስ ኩባንያው ባለፈው ቅዳሜ ጥቅምት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔው ላይ እንዳስታወቀው፣ በ2014 የሒሳብ ዓመት ማሰባሰብ የቻለው የዓረቦን መጠን ከቀዳሚው ዓመት የ38.2 ሚሊዮን ብር ወይም የዘጠኝ በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡

ኩባንያው የባንክ ወለድን ጨምሮ ከተለያዩ የገቢ ምንጮች 74.2 ሚሊዮን ብር ገቢ በ2014 የሒሳብ ዓመት ያገኘ መሆኑም ተጠቁሟል።

እንደ ሁሉም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አንበሳ ኢንሹራንስ ኩባንያ በሒሳብ ዓመቱ ካሰባሰበው ጠቅላላ የዓረቦን ገቢ ውስጥ አብላጫውን ገቢ ያገኘው ከተሽከርካሪዎች የመድን ሽፋን ነው፡፡ 

ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ 56.7 በመቶ ወይም የሚሆነውን የዓረቦን ገቢ ከተሽከርካሪ የመድን ሽፋን ያሰባሰበ ሲሆን፣ ቀሪው ደግሞ ከሌሎች የመድን ሽፋን ዓይነቶች እንዳገኘ አስታውቋል፡፡  

በሒሳብ ዓመቱ ኩባንያው ለካሳ ክፍያ ያዋለው የገንዘብ መጠን መቀነሱን የገለጹት የኩባንያው የዳይክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ አብርሃም ገብረ አምላክ፣ በሒሳብ ዓመቱ 165.5 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ መክፈሉን ጠቅሰዋል፡፡

የኩባንያው ዓመታዊ የሒሳብ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ ኩባንያው በ2013 የሒሳብ ዓመት ለካሳ ክፍያ ያዋለው የገንዘብ መጠን 188 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ በመሆኑም በ2014 የሒሳብ ዓመት ለካሳ ክፍያ የዋለው የገንዘብ መጠን ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ23 ሚሊዮን ብር ዝቅ ያለ ነው፡፡

ይሁን እንጂ የቦርድ ዳይሬክተሩ ለጠቅላላ ጉባዔ ባቀረቡት ሪፖርት በእንጥልጥል ላይ ያለና ላልተመዘገቡ የካሳ ክፍያ ጥያቄዎች ክፍያ የሚሆን 198.9 ሚሊዮን ብር ወደ 2015 የሒሳብ ዓመት መተላለፉን ገልጸዋል፡፡ 

አንበሳ ኢንሹራንስ ኩባንያ አጠቃላይ የሀብት መጠኑ 1.32 ቢሊዮን ብር የደረሰ መሆኑን የገለጹት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ ይህ የሀብት መጠኑ ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ 35 በመቶ ወይም የ345.1 ሚሊዮን ብር ዕድገት አሳይቷል፡፡

በአንፃሩ ግን የኩባንያው ዕዳ ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ የ296 ሚሊዮን ብር ወይም የ42 በመቶ ብልጫ በማሳየት 989.9 ሚሊዮን ብር መድረሱንም ጠቅሰዋል፡፡ ለኩባንያው ዕዳ ጭማሪ ማሳየት በዋናነት የሚጠቀሰው ለካሳ ክፍያ የሚይዘው መጠባበቂያ ሒሳብ በመጨመሩ መሆኑን፣ የቦርድ ሊቀመንበሩ ያቀረቡት ሪፖርት ያመለክታል፡፡

እስከ ሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ የተከፈለ ካፒታሉ 194.9 ሚሊዮን ብር ማድረግ የቻለው አንበሳ ኢንሹራስ የተፈረመ ካፒታሉ 300 ሚሊዮን ብር እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡ የኩባንያው ባለአክሲዮኖች የሚያገኙትን የትርፍ ድርሻ ጨምሮ ከራሳቸው ተጨማሪ ወጪ በማውጣት የኩባንያውን ካፒታል ለማሳደግ ማዋል እንዳለባቸው የቦርድ ሊቀመንበሩ ጠይቀዋል፡፡

በተለይም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሁሉም የኢንሹራስ ኩባንያዎች ካፒታላቸውን 500 ሚሊዮን ብር እንዲያደርሱ የሚያስገድድ መመርያ ማውጣቱን የገለጹት የቦርድ ሰብሳቢው፣ ባለአክሲዮኖች ይህንን እንዲያውቁትና ለዚህም መዘጋጀት እንደሚገባቸው አሳስበዋል። በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ እየገጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን በሪፖርታቸው ያካተቱት አቶ አብርሃም፣ በተለይ በኢንዱስትሪው በከፍተኛ ደረጃ እየታየ ያለው የዋጋ ሰበራ ጤናማ ፉክክር እንዳይኖር ማድረጉን በዋናነት ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ እየታየ ያለው የፀጥታ መደፍረስ በሽያጭና በካሳ ክፍያ ላይ ተፅዕኖ እንደፈጠረ የጠቀሱት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ ኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ ትልልቅ ተቋራጮች ጭምር ኪሳራ ያጋጠማቸው በመሆኑ፣ ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ያላቸው የተለያዩ የዋስትና ቦንድ ጥያቄዎች የቀረበበት አጋጣሚ መፈጠሩንም በመጥቀስ በኢንዱስትሪው እያጋጠሙ ያሉትን ችግሮች ጠቅሰዋል፡፡  

በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ላይ ጫና ያሳደሩ የተለያዩ ተግዳሮቶች ቢኖሩም፣ ኩባንያቸው በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት 63.9 ሚሊዮን ብር ማትረፉንና በተጣራ ትርፉ ደግሞ 61.8 ሚሊዮን ብር መድረሱ ተገልጿል፡፡ 

ከታክስ በፊት ያገኘው ትርፍ ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ 8.1 በመቶ ወይም የ4.87 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው መሆኑን የኩባንያው ሪፖርት አመልክቷል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ በተገኘው የትርፍ ምጣኔ መሠረት የኩባንያው ባለአክሲዮኖች በአንድ አክሲዮን 8.52 ብር የትርፍ ድርሻ የሚያገኙ ይሆናል፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ በቀደመው ዓመት አንድ አክሲዮን ያስገኘው የትርፍ ድርሻ 9.04 ብር ነበር፡፡ አንበሳ ኢንሹራንስ እስከ ሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ አራት አገናኝና 41 ቅርንጫፍ ቢሮዎች ያሉት ሲሆን፣ የሠራተኞች ቁጥር ደግሞ 355 ደርሷል፡፡   

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች