Thursday, November 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ካፒታሉን ከ1.2 ቢሊዮን ብር ወደ አራት ቢሊዮን ለማሳደግ ውሳኔ አሳለፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በተጠናቀቀውየሒሳብ ዓመት 9 ሚሊዮን ብር አትርፏል

 በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከፍተኛ ትርፍ በማግኘት ከግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ግንባር ቀደም የሆነው አዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ በአሁኑ ወቅት ያለውን 1.2 ቢሊዮን ብር ካፒታል ወደ አራት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰነ። 

ኩባንያው ባለፈው ቅዳሜ በአንድ ጊዜ እንዲጨመር የወሰነው የካፒታል መጠን 2.8 ቢሊዮን ብር ሲሆን ይህንን ካፒታል ለማሟላት አዳዲስ አክሲዮኖችን በዋናነት ለነባር ባለአክሲዮኖች እንደሚሸጥ አስታውቋል። የወሰነውን ካፒታል ለማሟላት ለገበያ ከሚያቀርባቸው አዳዲስ አክሲዮኖች ውስጥ 220 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ አክሲዮኖችን የሚቀርቡት አዲስ ለሠራተኞቹ ቅድሚያ በመስጠት የተቀረውን ለማኅበረሰቡ እንደሚሸጥም አስታውቋል።

ኩባንያው ካፒታሉን ወደ አራት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ የቀረበውን ሐሳብ ባለአክሲዮኖቹ ተቀብለው በሙሉ ድምፅ አጽድቀዋል፡፡ 

እስካሁን ድረስ ከግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከፍተኛ የሚባለውን የ1.2 ቢሊዮን ብር ካፒታል ይዞ የቆየው አዋሽ ኢንሹራንስ ተወዳዳሪነቱን የበለጠ ለማሳደግ የካፒታል መጠኑን ወደ አራት ቢሊዮን ለማሳደግ መወሰኑ አሁንም ከግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በቀዳሚነት እንዲቀመጥ የሚያደርገው ይሆናል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት እስካሁን ድረስ የካፒታል መጠናቸውን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ያደረሱ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሉም።

የካፒታል ማሳደጉን አፈጻጸም በተመለከተ ከተላለፈው ውሳኔ መረዳት እንደተቻለው ባለአክሲዮኖች አሁን ባላቸው የአክሲዮን መጠን ላይ ተመሥርተው የኩባንያውን ካፒታል ለማሳደግ ለሽያጭ የሚቀርቡ 2.58 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አዳዲስ አክሲዮኖችን እንዲገዙ የሚደረግ ሲሆን ፣ ነባር ባለአክሲዮኖች በተፈቀደላቸው መሠረት ለአዲስ አክሲዮን ግዥ ውል በመፈረም ክፍያውን በአራት ዓመት ውስጥ እንዲጠናቀቁ ይደረጋል፡፡ ይህንንም ሐሳብ ጠቅላላ ጉባዔው ተቀብሎ አጽድቆታል፡፡

ኩባንያው ካፒታሉን ለማሳደግ ለሽያጭ ከሚያቀርባቸው አዲስ አክሲዮኖች ውሽጥ 20 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች በቅድሚያ ሠራተኞቹ እንዲገዙ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ቦርዱ ይህንን ሐሳብ ያቀረበው የኩባንያው ቋሚ ሠራተኞች ከኩባንያው ጋር ያላቸውን ግንኙነትና የባለቤትነት ለማጠናከር እንዲረዳ ታሳቢ ተደርጎ መሆኑን የገለጹት የኩባንያው የቦርድ ሊቀመንበር ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ጠቅላላ ጉባዔው አዎንታዊ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ 

ኩባንያው ለባለአክሲዮኖችና ለሠራተኞች እንዲሸጥ ውሳኔ ካሳለፈበት አክሲዮን ሌላ ቀሪውን የ200 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን አክሲዮኖች ለአዲስ አክሲዮን ገዥዎች እንደሚሸጥ አስታውቋል፡፡ 

ለአዳዲሶቹ ባለአክሲዮኖች የሚሸጠው 200 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች ግን ቢያንስ በ50 በመቶ የዋጋ ጭማሪ (ፕሪሚየም) የሚሸጥ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በዚህ ውሳኔ መሠረት አክሲዮኑ ባይሸጥ ባለአክሲዮኖች እንዲገዙት ይደረጋል ተብሏል፡፡ 

ኩባንያው በኢንዱስትሪው ባልተለመደ ሁኔታ ከሦስት እጅ በላይ ካፒታልን ለማሳደግ ውሳኔ ላይ የደረሰበትን ምክንያት በተመለከተ በዝርዝር ከቀረቡ ምክንያቶች ውስጥ የኩባንያውን ኃላፊነት የመሸከም አቅም ለማሳደግ የሚለው በዋናነት ተቀምጧል፡፡ ከዚህም ሌላ ካፒታል ማሳደግ በጠለፋ ዋስትና ሰጪዎችና በደንበኞቹ ዕይታ ኩባንያውን በተሻለ ቁመናና የፋይናንስ አቋም እንዲኖረው የሚያደረግ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የኩባንያው የዓረቦን ዕድገት አንፃርም የኩባንያውን ካፒታል ማሳደግ ሌላው አመክንዮ እንደሆነ የኩባንያው  የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ከበደ ቦረና ገልጸዋል፡፡ 

እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎች የተላለፉት የአዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ጠቅላላ ጉባዔ የ2014 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙ በቦርድ ሊቀመንበሩ የቀረበበት ነበር፡፡ በዚህም ሪፖርታቸው የ2014 የሒሳብ ዓመት ከግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከፍተኛ ነው የተባለውን የ1.76 ቢሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ በማሰባሰብ መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡ ይህ የዓረቦን መጠን ከቀዳሚው ዓመት ከ470 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው መሆኑን በቅዳሜው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተገልጿል፡፡ 

እንደ ቦርድ ዳይሬክተሩ ገለጻ በሒሳብ ዓመቱ የተመዘገበው የዓረቦን መጠን አሁንም ከግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ቀዳሚ ሆነው እንዲቀጥሉ ያስቻላቸው እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ከበደ፣ ኩባንያው ከቦንድ ሥራ ውል በስተቀር በሌሎቹ የመድን ሽፋን ዓይነቶች ከ20 እስከ 87 በመቶ ዕድገት የተመዘገበበት ውጤት ማገኘቱ የኩባንያውን የሥራ አፈጻጸም አመርቂ አድርጎታል ተብሏል፡፡ 

ኩባንያው በትርፍ ረገድም በኢንዱስትሪው ከፍተኛ የሚባለውን የትርፍ መጠን ማግኘቱ የተገለጹ ሲሆን፣ በ2014 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 350.3 ሚሊዮን ብር አትርፏል፡፡ የተጣራ ትርፍ ደግሞ 333.9 ሚሊዮን ብር መሆኑንና ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ23.6 በመቶ ብልጫ እንዳለው ኩባንያው አመልክቷል፡፡ 

ኩባንያው በአዲስ ኩነት መቅረቡን የገለጹት የአዋሽ ኢንሹራንስ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጉዲሳ ለገሠ፣ አዋሽ ኢንሹራንስ ባለፉት 27 ዓመታት ያስመዘገበውን ውጤት ጠብቆ በአዲስ አቀራረብና ዝግጅት በኢንዱስትሪው የያዘውን ደረጃ ይዞ ለማስቀጠል እየሠራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በተለይ ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ ከተወሰዱ ዕርምጃዎች መካከል ኩባንያውን ‹‹ሪብራንድ›› ማድረግ ሲሆን ይህም ሥራ ተጠናቆ በዕለቱ ይፋ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ 

በዕለቱም የኩባንያው አዲሱ ዓርማ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ቺፍ ኢኮኖሚስት በተገኙበት በይፋ ተመርቋል፡፡ 

አዋሽ ኢንሹራንስ ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት ሲመሠረት የነበረው ካፒታል በ4.9 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ በየጊዜው ካፒታሉን እያሳደገ በመምጣት አሁን ካፒታሉን ወደ አራት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወስኗል። በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ይሰበሰብ የነበረው 15 ሚሊዮን ብር ዓመታዊ ዓረቦን አሁን ላይ 1.76 ቢሊዮን ብር መድረሱን የኩባንያው ኃላፊዎች ጠቅሰዋል። ታኅሳስ 1987 ዓ.ም. በ456 ባለአክሲዮኖች የተመሠረተው አዋሽ ኢንሹራንስ አሁን ላይ 1713 ባለአክሲዮኖች እንዳሉትም ገልጸዋል፡፡ 

ባለፉት 27 ዓመታት የኩባንያውን ዕድገት በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያም የኩባንያው ጠቅላላ የሀብት መጠንም ከ4.1 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱንና አጠቃላይ የኢንቨስትመንት መጠኑንም ወደ 2.2 ቢሊዮን ብር ከፍ ማድረጉን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡ 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች