Tuesday, February 27, 2024

ከሰላም ንግግሩ እኩል የቀጠለው የምዕራባውያኑ ጫና

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በደቡብ አፍሪካ በኢትዮጵያ መንግሥትና በትግራይ አማፂያን መካከል የሚደረገው የሰላም ንግግር እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ ከዚሁ እኩል ግን የምዕራባውያኑ ጫና መቀጠሉ ይታያል፡፡ የሰላም ንግግር ሐሳብን በዋናነት ሲደግፉና እንዲጀመርም ከፍተኛ ግፊት ሲያደርጉ የቆዩት ምዕራባውያኑ ንግግሩ ከተጀመረ ወዲህም ጫናቸውን መቀጠላቸው አስገራሚ ነበር፡፡ ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ጫናን ለማስቆም ብዙ ጥረቶች ቢደረጉም ጫናው ሲጨምር እንጂ ጋብ ሲል አልታየም፡፡

ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. በተጠራው የተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ላይ በድርጅቱ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ታዬ አጽቀ ሥላሴ  (አምባሳደር) በኢትዮጵያ ላይ ማባሪያ የሌለው ጫና እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹እያየን ያለነውና እየሰማን ያለነው የሰላም ጥሪ ሳይሆን ከግራም ከቀኝም የሚመጣ ጫና ነው፤›› በማለት የተናገሩት ታዬ (አምባሳደር) ኢትዮጵያ በሰላምና በድርድር ጥያቄ ስም ከባድ የውጭ ጫና እየገጠማት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ምዕራባውያኑ በተለያየ መንገድ በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ጫና ያልተገባ መሆኑ ተነግሯቸዋል፡፡ በውጭ የሚኖረው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ተደጋጋሚ የተቃውሞ ሠልፎችንና ጥሪዎችን በተለያዩ የዓለም አደባባዮች አካሂዷል፡፡

በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአውስትራሊያ፣ በዓረብ አገሮችና እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች፣ በተለያዩ አደረጃጀቶች ከኢትዮጵያ ላይ እጃችሁን አንሱ ሲሉ የምዕራባውያን ኃይሎችን ተቃውመዋል፡፡ በኢትዮጵያ ላይ የከረረ አቋም የያዙ የአሜሪካ ፖለቲከኞችን ከማግባባት ጀምሮ የምዕራቡ አገሮች ፖሊሲ አውጪዎችን ለማሳመን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራዎችም በዳያስፖራው በኩል ተሠርቷል፡፡

ይህ ብቻም አይደለም በአገር ቤት ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ከተሞች አደባባዮች በመውጣት የውጭ ኃይሎች ጫና እንዲቆም በተደጋጋሚ ጠይቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ የራሷን ችግር በራሷ መፍታት እንደምትችል በመጠቆም በእኛ ጉዳይ አትግቡብን ሲሉ ኢትዮጵያውያን በተደጋጋሚ ጠይቀዋል፡፡ የምዕራባውያን ጫና የኢትዮጵያን ችግር ከማባባስ ውጭ መፍትሔ እንደማይሆን በመግለጽ በርካታ ፀረ ጣልቃ ገብነት ሠልፎች ተካሂደዋል፡፡ ከሳምንት በፊት የተደረገውን ጨምሮ ምዕራባውያኑ ጣልቃ ገብነታቸውን እንዲያቆሙ ኢትዮጵያውያን ብዙ የአደባባይ ሠልፎች አካሂደዋል፡፡

ከትናንት በስቲያ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ለወቅቱ የአሜሪካን ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ለኔድ ፕራይስ ይሄው ጉዳይ ተነስቶላቸው ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን በአደባባይ ወጥተው የራሳችንን ችግር በራሳችን እንፈታለንና ምዕራባውያኑ ጣልቃ አትግቡብን ብለዋል የሚለውን ጉዳይ ተጠይቀው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ቢሆን ከሰሞኑ የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት በተመለከተ ጠንካራ መግለጫ ማውጣቱ ለኔድ ፕራይስ ተነስቶላቸው ነበር፡፡

አሜሪካ የምትፈልገው መሠረታዊ ጉዳይ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን ነው በማለት የተናገሩት ቃል አቀባዩ ግጭት በአስቸኳይ እንዲቆም አሜሪካ ትፈልጋለች ነበር ያሉት፡፡

ለሰላም ንግግር ወደ ደቡብ አፍሪካ የመጡት የፌዴራል መንግሥትና የትግራይ አማፂያን ተወካዮች ተቀምጦ ለመወያየት እንዲሁም ልዩነታቸውን ለማቀራረብ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ኔድ ፕራይስ ስለ ሒደቱ ተናግረዋል፡፡ ይህ በጎ ጅማሮ መሆኑን የተናገሩት ቃል አቀባዩ፣ ከሰላም ንግግሩ ውጤት እንዲመጣ አሜሪካ እንደምትፈልግ ነው የተናገሩት፡፡ ኔድ ፕራይስ እንደሚሉት ሁለቱ ኃይሎች በሰላም ንግግሩ ውጤት ላይ ቢደርሱ ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ጫና ያቆማሉ ወይ? ለሚለው ጥያቄ ግን ማንም እርግጠኛ የሆነ መልስ ያለው አይመስልም፡፡

ስለዚሁ ጉዳይ የተጠየቁት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና የውጭ ግንኙነት መምህር እንዲሁም በዓባይ ጥናት ተቋም ተመራማሪ የሆኑት አቶ አበበ ይርጋ የምዕራባውያኑ ጫና እንደማይቆም ይናገራሉ፡፡

‹‹ምዕራባውያኑ ከሰላም ንግግሩም ሆነ ከምንም በላይ የሥርዓት (የመንግሥት) ለውጥ ይፈልጋሉ፡፡ የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ወደ ሥልጣን ሲመጣ ለእነሱ የሚላላክ መንግሥት የመጣ መስሏቸው ደግፈውት ነበር፡፡ ነገር ግን አስተዳደሩ ጥቅማቸውን እንደማያስፈጽም በማመን የሕወሓት ኃይሎች ጦርነት እንዲከፍቱና በአገሪቱ የሥርዓት ለውጥ እንዲመጣ ወዲያው ማሴር ጀመሩ፤›› በማለት የሚናገሩት አቶ አበበ ይህ አቋማቸውም እስካሁን መቀጠሉን ያስረዳሉ፡፡

ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ ላይ ጫናቸውን የገፉባቸው ሌሎች ምክንያቶች እንዳሉ የሚናገሩት መምህሩ ‹‹የቻይናን ተፅዕኖ በኢትዮጵያና በምሥራቅ አፍሪካ መግታት ይፈልጋሉ፤›› ሲሉም ያስረዳሉ፡፡ በሌላም በኩል በግብፆች ጉትጎታ ምዕራባውያኑ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ግንባታ ለማስተጓጎል በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዳጠናከሩ አቶ አበበ ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ኢኮኖሚን ክፍት በማድረግ ስምና የኢትዮጵያን ገበያ ለመቀራመት በማሰብ ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንደሚያካሂዱ ነው የተናገሩት፡፡

‹‹የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) መንግሥት መጀመርያ ወደ ሥልጣን ሲመጣ፣ ምዕራባውያንን በተመለከተ የተሳሳተ አረዳድ ስለነበረው ከእነሱ ጋር በተሳሳተ መንገድ ግንኙነት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ግንኙነቶች የኢትዮጵያን ጥቅሞች የሚጎዱ ስለነበር ወዲያው አቋርጧቸዋል፡፡ ተላላኪያችሁ አልሆንም ብሏቸዋል፡፡ ይህ ያበሳጫቸው ምዕራባውያኑ የዓብይ (ዶ/ር) አስተዳደርን ገጽታ አበላሽተዋል፣ የኢኮኖሚ አሻጥሮችንና ዕቀባዎችን ፈጥረዋል እንዲሁም በኢትዮጵያ ግጭት እንዲፈጠር ድጋፍ አድርገዋል፤›› በማለት መምህሩ ይናገራሉ፡፡

ምዕራባውያኑ ሕወሓትን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን መንግሥት የሚያዳክም ኃይልን በሙሉ እንደሚደግፉ አቶ አበበ ይናገራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ዓላማቸውን የሚያስፈጽም ተላላኪ መንግሥት እስኪፈጠር ድረስም ይህን አሻጥራቸውን እንደማያቆሙ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ምዕራባውያኑ ሕወሓትን አፍቅረውና ወደው ሳይሆን ይህን የሚያደርጉት ፍላጎታቸው ከሕወሓት ፍላጎት ጋር በመገጣጠሙ ነው፤›› በማለትም የጫናውን ገጽታና አመጣጥ ያስቀምጡታል፡፡

 በቅርቡ በባህር ዳር ከተማ ተስተናግዶ በነበረው የጣና ፎረም ስብሰባ ላይ ተካፋይ የነበሩት ፓትሪስ ሉሙምባ (ፕሮፌሰር) ‹‹አፍሪካ የራሴን ጉዳይ ለራሴ ተውልኝ ማለት ትፈልጋለች፤›› ሲሉ ነበር የምዕራባውያኑን በአፍሪካ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት አባዜ የተቹት፡፡

በዚሁ መድረክ የመነሻ ጽሑፍ አቅራቢ የነበሩት የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም ይህንኑ ጉዳይ አጉልተው አንስተዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አገሮች በራሳቸው አቅም ያለማንም ጣልቃ ገብነት ችግሮቻቸውን መፍታት ይችላሉ፡፡ ከቅኝ ግዛት ዕሳቤ ተላቀው በራሳቸው ሀብት የራሳቸውን ችግር መቅረፍ ይችላሉ፤›› በማለት ነበር አቶ ኃይለ ማርያም የተናገሩት፡፡

በመድረኩ ከኃይለ ማርያም ጎን የመነሻ ጽሑፍ አቅርበው የነበሩት የምሥራቅ አፍሪካ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ማይክ ሀመር ግን ‹‹አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር ለመፍታት ኃላፊነት መውሰድ መቻል አለባቸው፤›› ነበር ያሉት፡፡ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ አክለውም ‹‹የእናንተ አገር ነው፡፡ ችግራችሁን ለመፍታት ኃላፊነት ውሰዱ፡፡ ያኔ እኛም እንደግፋችኋለን፡፡ በእርግጥ ከእስካሁኑ በተሻለ የአፍሪካውያን መልካም አጋር መሆን እንዳለብን እንገነዘባለን፤›› ሲሉም ነበር የተናገሩት፡፡ ይህ የማይክ ሀመር አገላለጽ ደግሞ አሜሪካ በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ስታደርግ የቆየችው ጣልቃ ገብነት በአሜሪካ ፖለቲከኞች ዘንድ በበጎ ተፅዕኖ እንደሚወሰድ ጠቋሚ ንግግር ነበር፡፡

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲው ምሁር አበበ ይርጋ እንደሚሉት ምዕራባውያን ጣልቃ ገብነታቸው ጎጂ ሚና እንዳለው ወይም አላስፈላጊ እንደሆነ ሳያውቁ ቀርተው እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡

ምዕራባውያኑ ስለጣልቃ ገብነታቸው ሊገባቸው በሚችል መንገድ ሲነገራቸው መቆየቱንም ይጠቅሳሉ፡፡ ከዚህ በመነሳት በኢትዮጵያ ላይ ምዕራባውያኑ የሚያራምዱትን ጣልቃ ገብነት የሚፈትሹት አቶ አበበ፣ ዋና ግባቸውና ዓላማቸው ጥቅማችንን ያስፈጽምልናል የሚሉትን የሕወሓት ኃይል ‹‹ከሞት መታደግ›› መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡

‹‹ጦርነቱ ባሰቡት መንገድ አልሄደም፡፡ ሕወሓት አሸናፊ ሆኖ መውጣት አልቻለም፡፡ የትግራይ ሕዝብም ቢሆን ነፃ እየወጣና የሕወሓትን ሴራ እየተረዳ ነው፡፡ እነሱ ከገመቱት በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በጦርነቱም ሆነ በማዕቀቡና በሌላውም ጫና በጅ የሚሉ አልሆነም፡፡ አሁን ላይ ይህ ያሠጋቸው ምዕራባውያኑ በሰላም ንግግር ሒደት አስታከው የሕወሓትን ዕድሜ ለማራዘም ጊዜ መግዛት የፈለጉ ይመስላል፤›› በማለት አቶ አበበ ይናገራሉ፡፡

የሰላም ንግግሩ እነሱ በሚፈልጉት መንገድ ቢሄድም ባይሄድም እንዲሁም ከሰላም ሒደቱ በጎም ሆነ መጥፎ ውጤት ቢገኝም የምዕራባውያኑ ጫና ግን እንደማይቆም ነው አቶ አበበ የሚገምቱት፡፡

ይህ የሚሆነው ደግሞ ኢትዮጵያ በውስጥ የጓዳዋን የቤት ሥራዎች በአግባቡ ባለመሥራቷ እንዲሁም ለውጭ ጣልቃ ገብነት አጋላጭ ሁኔታዎች ስላሉባት መሆኑንም ያነሳሉ፡፡

ለዚህ መፍቻ መንገድ ያሉትን ሲያስቀምጡም ብቸኛው መንገድ ‹‹ለእነሱ ጥቅም የሚጋለብ ኃይል ወይም ለነሱ ቁማር መጫወቻ ካርድ የሚሆን አካል እንዳይፈጠር ማድረግ ነው፤›› ይላሉ፡፡

‹‹የሰላም ሒደቱም ሆነ የውጭ ጣልቃ ገብነቱ በዋናነት የሚወሰነው መሬት ላይ ባለው ሀቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሕወሓት አማፂያን ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ስለተቀመጠ፣ ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያን ይተዋሉ ማለት ሞኝነት ነው፡፡ ስለዚህ በተጨባጭ ሕወሓትን ማክሰም ነው ጣልቃ ገብነቱን የሚያስቆመው፤›› በማለት ነው አቶ አበበ ይርጋ የተናገሩት፡፡

መሬት ላይ ያለው ሀቅ ሲቀየር የኢትዮጵያ ውጭ ግንኙነት እንደሚቀየር የጠቀሱት አቶ አበበ ‹‹በተቃውሞ ሠልፎች የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት ይቁም ስላልን ሳይሆን ምዕራባውያኑ ሊጠቀሙበት የሚችል ተላላኪ ኃይልን በኢትዮጵያ እንዳይኖር በማድረግ ነው ጣልቃ ገብነቱን ማስቀረት የሚቻለው፤›› ሲሉ ሐሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡

የውስጥ የፖለቲካ ችግርን መፍታት የውጭ ተፅዕኖን ለማስቀረት ወሳኝ ተደርጎ እንደሚታየው ሁሉ የኢኮኖሚ ችግርን በመፍታት ራስን ከድህነት የማላቀቅ ጉዳይም ከውጭ ጣልቃ ገብነት መላቀቂያ ተደርጎ ይታያል፡፡

ከሰሞኑ ለቻይናው ሲጂቲኤን ቴሌቪዥን አስተያየት የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ‹‹የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ለአንድ አገር ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ አንዱ መንገድ ነው፤›› ብለዋል፡፡ የምግብ ዋስትና ጉዳይ ለኢትዮጵያ ብልፅግና መረጋገጥ መሠራት እንደሆነ የተናገሩት ዓብይ (ዶ/ር) ‹‹ከቀኝም ከግራም ከሚመጣ ጣልቃ ገብነት ይልቅ የራሳችንን ወግ፣ ባህልና ሕግ ብናከብር ብዙ ችግሮቻችንን ያለማንም ጣልቃ ገብነት በራሳችን መፍታት እንችላለን፤›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -