- የስንዴ ምርት ልማቱ ጥሩ ቢሆንም አንዳንዶች ትችት እያቀረቡበት ነው።
- ምን ብለው ተቹ
- የኢትዮጵያ ሕዝብ ጤፍ እንጂ ስንዴ አዘውትሮ አይመገብም እያሉ ነው።
- ድርቅና ረሃብ ሲገጥመን ግን የሚያቀርቡልን ዕርዳታ ስንዴ ነው። አይደለም እንዴ?
- ልክ ነው። ግን እነሱ ምክንያታዊነት አያስጨንቃቸውም።
- እንዴት?
- በቃ መቃወም ከፈለጉ መቃወም ነው። ለዚያውም እስከ ጥግ ድረስ ሔደው የማይገናኝ አገናኝተው ነው የሚቃወሙት።
- ለምሳሌ?
- ሌላ ምሳሌ አያስፈልገንም። በዚሁ የሰንዴ ልማት ላይ ምን እያሉ መሰለዎት?
- እ …
- ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስበው አይደለም።
- እና ለማን ነው?
- ለራሳቸው ነው።
- ለእኛ ምን ያደርግልናል?
- ሥልላጣናቸውን ለማራዘም።
- ኦ..ኦ.. እዚህ ድረስ ዝቅ ብለዋል?
- ለእኔም ግራ ገብቶኛል።
- ምኑ ነው ግራ ያጋባህ?
- ለምን በዚህ ደረጃ ለመቃወም እንደፈለጉ ለመረዳት ተቸግሬያለሁ። አንዳንዶቹ እኮ የሚናገሩት ግራ ያጋባል ክቡር ሚኒስትር?
- ምን ይላሉ?
- በዚህ መጠን የሰንዴ ልማት ውስጥ መግባት ተፅዕኖ እንደሚያመጣ ሳይረዱ ቀርተው አይደለም። አውቀው ነው እያሉ ነው።
- ምን ተፅዕኖ ያመጣል ነው የሚሉት?
- ሌሎች አዝዕርቶች በኢትዮጵያ እንዳይመረቱ ያደርጋል እያሉ ነው።
- ምን?
- አዎ። ሌሎች አዝዕርቶችን ለማጥፋት ነው እስከማለት ደርሰዋል።
- ይደንቃል። ስንዴ ላይ ይህን ያክል ተቃውሞ?
- በዚህ ጭፍን ተቃውሞ ከቀጠሉ በቅርቡ አንድ ነገር ማለታቸው አይቀርም፡፡
- ምን ሊሉ ይችላሉ?
- ጄኖሳይዳል ነው።
- ምኑ?
- የሰንዴ ልማቱ!
[ክቡር ሚኒስትሩ የሰሜኑን ግጭት ለመፍታት የተጀመረውን ድርድር በተመለከተ ከአማካሪያቸው ጋር ሐሳብ እየተለዋወጡ ነው]
- የአንድ ድርድር ውጤታማነት በመጀመሪያዎቹ ቀናት ሁኔታ ወይም ውጤት ይለካል ብሎ ማሰብ ትክክል ይመስልሃል?
- እሱን እረዳለሁ ክቡር ሚንስትር። በእኛ ሁኔታ ግን ከሁለት አንዱ መስመር መያዝ ነበረበት።
- ከሁለት አንዱ ማለት?
- ወይ ድርድሩ ወይም ደግሞ በግንባር ያለው ሁኔታ መስመር መያዝ ነበረበት ማለቴ ነው።
- ስንዴ እየዘራን መሰለህ እንዴ?
- ኧረ ስለ ስንዴ አላወራሁም?
- ታዲያ ምንድን ነው መስመር መስመር …መስመር መያዝ አለበት የምትለው?
- ክቡር ሚኒስትር እኔ ብቻ ሳልሆን ማኅበረሰቡ ጭምር ቅር ብሎታል።
- ለምን?
- አለቃ ሰሞኑን ለውጭ ሚዲያ ስለድርድሩ በሰጡት ቃለ ምልልስ ነው።
- አላየሁትም። ምን አሉ?
- አንደኛው ነጥብ የውጭ ጣልቃ ገብነት በዝቷል የሚል ነው።
- እሺ …
- የውጭ ጫና ከበዛ ሰላም ሩቅ ይሆናል በማለት ጫና መኖሩን ጠቁመዋል።
- እውነት ነው። የውጭ ጣልቃ ገብነትና ጫናው ከፍተኛ ነው።
- ክቡር ሚኒስትር ይህንንማ ራሳችን የፈቀድነው በመሆኑ ጫና እንደሚመጣ ወይም ጫናውን እንደምናመክነው መጀመሪያውኑ ማወቅ ነበረብን።
- እንዴት?
- የአፍሪካ ኅብረትም ይሁን ሌላ እንዲያደራድሩን የተስማማነው በፈቃዳችን አይደለም እንዴ?
- እሱማ ነው!
- ታዲያ አሁን ላይ የውጭ ጣልቃ ገብነትና ጫና ብለን መቃወም ተገቢ ነው?
- ነገሩ አልገባህም። ምን መሰለህ?
- እ …
- አደራዳሪዎቹ አይደለም ጣልቃ እየገቡ ያሉት።
- ማነው?
- ታዛቢዎቹ ናቸው። ድርድሩም የተራዘመው በእነሱ ሴራ ነው፡፡
- እንዴት?
- መንግሥት ቡድኑ ትጥቅ መፍታት አለበት በሚለው አቋሙ ፅኑ ነበር።
- እሺ …?
- ቡድኑ ደግሞ በተቃራኒው ትጥቅ እንደማይፈታ ሽንጡን ገትሮ ሲሟገት የድርድሩ ማብቂያ ደረሰ።
- እሺ …?
- በኋላ ከታዛቢዎቹ ጋር ተመካክሮና ማስተማመኛ አግኝቶ አንድ ጉዳይ ይዞ መጣ።
- ምን ይዞ መጣ?
- ትጥቅ ለመፍታት እስማማለሁ አለ።
- መጨረሻ ላይ?
- አዎ።
- እሺ የእኛ ተደራዳሪዎች ምን አሉ?
- የእኛ ተደራዳሪዎች ምላሽ ከመስጠታቸው በፊት ታዛቢዎቹ በጉዳዩ በጥልቀት ለመነጋገር የድርድሩ ጊዜ መራዘም አለበት አሉ።
- እሺ ከዚያስ?
- ነገሩ የአቋም ለውጥ በመሆኑ የድርድር ጊዜው ተራዝሞ ውይይት ይደረግ ተባለ።
- እሺ?
- ወደ ዝርዝሩ ሲገባ ግን አዲስ ነገር የለም።
- እንዴት?
- ቡድኑ ትጥቅ ለመፍታት እስማማለሁ ነገር ግን ይህንን ተግባር የምፈጽመው በድርድሩ መጨረሻ ላይ ነው አለ።
- ምን …?
- አዎ። ትጥቅ ለመፍታት ዝግጁ ነኝ ግን ትጥቅ መፍታት አንዴ የሚተገበር ነገር አይደለም ስለዚህ ጊዜ ተወስዶ መፈጸም አለበት። እስከዛ ግን በሌሎች ጉዳዮች ድርድሩ ይቀጥል አለ።
ጊዜ መግዣ መሆኑ ነው?
- እንደዚያ ነው። ግን የቡድኑ አይደለም የሚገርመው።
- እ …?
- የታዛቢዎቹ ነው።
- ለምን?
- ቡድኑ ትጥቅ ለመፈታት መስማማቱ አንድ ትልቅ ዕርምጃ በመሆኑ በእናንተ በኩልም አንድ ዕርምጃ መምጣት አለባችሁ አሉ።
- ምን ጠየቁ?
- ተኩስ ማቆም አለባችሁ!
- ወደፊት ትጥቅ እፈታለሁ ስላለ?
- አዎ። ለዚያ ነው አለቃ የውጭ ጣልቃ ገብነትና ጫና በዝቷል ያሉት፡፡
- አሁን ግልጽ ሆኖልኛል ቢሆንም ግን …
- ግን ምን?
- አለቃ የተናገሩት ጫና ስለመብዛቱ ብቻ አይደለም።
- ሌላ ምን ብለዋል?
- ችግራችንን እኛው መፍታት እንችላለን ብለዋል።
- እንደዚያ ያሉት ጣልቃ ለሚገቡት የውጭ ኃይሎች ነው።
- እኔ ግን እንደዚያ ለማለት የፈለጉ አልመሰለኝም።
- ምን ለማለት የፈለጉ ነው የመሰለህ?
- እኛው እንታረቅ ያሉ አስመስለው ሌላ ነገር ለማለት የፈለጉ ነው የመሰለኝ።
- ምን?
- ገላጋይ አይግባ!