Friday, May 24, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ዘጠና በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያ ሸቀጣ ሸቀጥ ስለሚያጓጉዘው ንግድ መርከብ ምን እናውቃለን? (ክፍል ሦስት)

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

በቀዳሚዎቹ ሁለት ክፍሎች የመርከብ አመጣጥ ታሪክ፣ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብና ስለዘመናዊ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ታሪክ ተመልክተናል፡፡ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ንግድ ምሥረታ የንጉሠ ነገሥቱና የባለሥልጣኖቻቸው ሚና ምን እንደነበር ጭምር ቀጣዩ ክፍል እነሆ፡፡

የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የገንዘብ ሚኒስትር ለክቡር አቶ ከተማ አበበ የባህር ክፍል ምክትል ሚኒስትር በ1956 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት 40 በመቶ ባለ ዕጣ ሆኖ፣ ቶርስ ኢንቨስትመንት ኮርፖሬሽን ከሚባለው የአሜሪካ ባንክ ጋር በመተባበር አንድ የኢትዮጵያ የንግድ መርክብ ሥራ ማኅበር ለማቋቋም በፕላኒንግ ቦርድ ዋና ኮሚቴ ተወስኖ መሠረታዊ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ፣ ለክቡራን ሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ክቡርነትዎ ባለበት በተፈቀደው መሠረት መነሻ ካፒታሉ 50,000 ብር የሆነ ማኅበር ለመመሥረት፣ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል እርስዎና አቶ ሙላቱ ደበበ የማኅበሩን መመሥረቻ ውልና ደንብ ፈርማችሁ ማኅበሩ እንዲቋቋም እንዲያደርጉ በማክበር አስታውቃለሁ ብሏል፡፡

የንግድናመርከብ ማኅበር ማቋቋም ስምምነት

የንግድ መርከብ ማኅበር ለማቋቋም ሙሉ ጥናት ተዘጋጅቶ ለፕላን አስፈጻሚ ኮሚቴ ቀርቦ ከተመከረበት በኋላ፣ የቴክኒክ ኤጀንሲ ሐሳብ ይስጥበት ተብሎ ተወሰነ፡፡ ኮሚቴውም በዚህም ሐሳብ ተስማምቶ ለጊዜው ኩባንያው በአነስተኛ ካፒታል በ50,000 ብር እንዲቋቋምና ወደፊት የማኅበሩ ቦርድ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው፣ ካፒታሉ ወደ 3,750,000 እንዲደርስ ወስኖ፣ ሥነ ሥርዓቱን የሚያከናውኑ ሰዎችን መርጦ፣ እነሱም ወዲያውኑ ስምምነቱን ከውጭ አገር ሰዎች ጋር ፈረሙ፡፡

ስምምነት

የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥትና ‹‹ቶሮስ ኢንቨስትመንት ኢን ኮርፖሬትድ›› እየተባለ የሚጠራው ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የአሜሪካን ባንክ እንደሚከተለው ተዋውለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ባለአክሲዮን ማኅበር እየተባለ የሚጠራ ለጊዜው መነሻው ካፒታል 50,000 የሆነ አንድ ኩባንያ ይቋቋማል፡፡ የዚህም ኩባንያ ካፒታል ወደፊት 3,750,000 ይሆናል፡፡ ቶርስ ኢንቨስትመንት ኢንኮርፖሬትድ የዚህን ማኅበር ካፒታል 40 በመቶ ያወጣል፡፡ ይህንኑ ገንዘብ በ60 ቀናት ውስጥ ይከፍላል፡፡ ማኅበሩ ቦርድ በሁለቱም ክፍል የሚኖሩት አባሎች ቁጥር በካፒታሉ መዋጮ መሠረት ይወሰናሉ፡፡ ቶሮስ ኢንቨስትመንት ኢንኮርፖሬትድ ሁለት አባሎች ይወክላል፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኘው የቶሮስ ኢንቨስትመንት ባንክ ቅርንጫፍ የካፒታሉን ሁለት በመቶ ያወጣል፡፡ ይህም ማኅበር አንድ የቦርድ አባል ይኖረዋል፡፡

ቀሪውን 49 በመቶ ካፒታል የኢትዮጵያ መንግሥት ይከፍላል፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት በቦርዱ ውስጥ ሁለት አባሎች ይኖሩታል፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ድርሻውን ገንዘብ በ60 ቀናት ውስጥ ለመክፈል ተስማምቷል፡፡

እያንዳንዱ አክሲዮን 100 ብር ዋጋ አለው፡፡ እ.ኤ.አ. ከጥር 1 ቀን 1964 በፊት ዕጣውን ለማንም እንዳይሸጥ ቶሮስ ኢንቨስትመንት ኢንኮርፖሬትድ ቃል ገብቷል፡፡ አክሲዮኑን በሚሸጥበት ጊዜ ሌሎች የማኅበሩ አባሎች እንዲገዙ የመጀመሪያው ዕድል ይሰጣቸዋል፡፡ ወደፊት በተጨማሪ አክሲዮን በሚሸጥበት ጊዜ የማኅበሩ ተባባሪ አባሎች አሁን ባላቸው አክሲዮን መሠረት ተጨማሪ አክሲዮን ይኖራቸዋል፡፡

የማኅበሩ የቦርድ አባሎች ችሎታ ያለው ዋና ሥራ አስኪያጅ ይመርጣሉ፡፡ እሱም ኃላፊነቱ ለቦርዱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የንግድ መርከብ ኩባንያ ቦርድ አባሎች ‹ቬርሎሜ› ከሚባለው የሆላንድ መርከብ ሥራ ኩባንያ ጋር መርከቦቹን ለማሠራት፣ ለማዋዋል፣ የቴክኒክ ዕርዳታ ለማግኘት፣ ሠራተኞች ለማሠልጠንና የማኅበሩን ሥራ ስለመምራት ጉዳይ ንግግር ያደርጋሉ፡፡ የሚገዙት መርከቦች ብዛትና ዓይነታቸው በቦርዱ አባሎች ይወሰናል፡፡ የቦርዱ አባሎች ቬርሎሜ ያቀረበውን ሐሳብ እስከ 30 ቀናት ድረስ ላለመቀበል መብት አላቸው፡፡ በማይከላከለው ችግር ምክንያት ቬርሎሜ ያቀረበውን ሐሳብ እስከ ሚያዝያ 30 ቀን 1964 ድረስ ሊሰረዝ ይችላል፡፡ መርከቦቹን ለማሠሪያ አስፈላጊውን የክሬዲት ገንዘብ ቬርሎሜ ለማስገኘት ተስማምቷል፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት በሚከተሉት ጉዳዮች ላይ ለኩባንያው ዕርዳታ ለማድረግ ተስማምቷል፡፡

 1. ከአሰብ የዘይት ማጣሪያ ኩባንያ ጋር ለረዥም ጊዜ ስምምነት በማድረግ የዘይቱን ድፍድፍ ለመጫን፣
 2. የጭነት ዕቃ መርከቦቹ በቂ ሥራ እንዲኖራቸው፣
 3. ለመርከቦቹ ዋጋ በቅድሚያ የሚከፈለውን 15 እና የሥራ ማስኬጃውን ወጪ ለመሸፈን 5,000,000 ብር ከንግድ ባንክ ለመበደር የማኅበሩ ቦርድ የሚያስፈልገውን ዕርምጃ ይወስዳል፡፡
 4. የማኅበሩን የፋይናንስ ጉዳይ የሚያከናውን ባንክ ቦርዱ ይመርጣል፡፡
 5. ማኅበርተኛው በየበኩላቸው ለሚደርስባቸው ብድር ዋስትና ይሰጣሉ፡፡
 6. የኢትዮጵያ የንግድ መርከብ ማኅበር አጥቢያ ኮከብ የተባለችውን የመንግሥት መርከብ ይገዛል፡፡
 7. የኢትዮጵያ የንግድ መርከብ ማኅበር ሥራውን የሚያቃናለትንና ትርፍ የሚያስገኝለትን ነገር ሁሉ ማከናወን ይችላል፡፡

የማኅበሩ አባሎች ወኪሎች ይህን ስምምነት በሦስት ኮፒ በዛሬው ቀን መጋቢት 1 ቀን 1956 ዓ.ም. ፈርመዋል፡፡

ስለ፡-  የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት

ስለ፡- ቶሮስ ኢንቨስትመንት ኢንኮፖርሬትድ (ዋሺንግተን ዲሲ)

ስለ፡- ቶሮስ ኢንቨስትመንት ኢንኮፖርሬትድ ኢትዮ ሊሚትድ

ስለ፡- ቨርሎሜ ዩናይትድ ሺኘ ያርድስ ኤንድ ኢንጂነሪንግ ካምፓኒ

በዚህም ስምምነት መሠረት 49 በመቶው የኢትዮጵያ መንግሥት (የገንዘብ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ) ድርሻ፣ 51 በመቶው ደግሞ አሜሪካዊ የንግድ ድርጅት ድርሻ ሆኖ የመጫን ችሎታቸው እያንዳንዳቸው 6,544 ቶን የሆኑ የይሁዳ አንበሳና ንግሥተ ሳባ የተባሉ የደረቅ ዕቃ መጫኛ መርከቦች እንዲሁም 34,075 ቶን የሆነ የመጫን ችሎታ ያላት ላሊበላ የተባለች መርከብ ተገዝተው ሥራቸውን ቀጠሉ፡፡

እ.ኤ.አ. በ1968 ወደ ወደቦች ሄዶ የነበረው ‹‹ሚረር›› የተባለው መጽሔት ቅጽ 6፣ ቁጥር 4 አዘጋጅ ‹‹ንግሥተ ሳባ›› ስለተባለችው መርከብ ካፒቴን ቫንደር በረግ፣ ዓምደ መስቀል ጊደይ (ኢንጂነር)፣ ቺፍ ኢንጂነር ኤልፒሆኬ፣ ቺፍ ኢንጂነር ሁጌንዶክ ብክል፣ ዎርዶፋ ተስፋዬ፣ ኪዳኔ ገልፆ የተባሉትን አነጋግሮ ነበር፡፡ በተለይም ካፒቴን ቫንደር በረግ፣ ‹‹ንግሥተ ሳባ››ን ሲገልጽ፡-

‹‹ንግሥተ ሳባ በጣም ውብ የባህር መርከብ ናት፡፡ ዘመናዊ የሆኑ መሣሪያዎችና የሬድዮ ቴሌ አላት፡፡ ሁሉም ነገሯ የተሟላ ነው፡፡ ይህች 6,500 ቶን የመጫን አቅምና 300,000 ኪዮቢክ ይዘት፣ 54,000 የፈረስ ጉልበት ያለው ኢንጂን ያላት መርከብ፣ 40 ቶን ክብደት የሚያነሳ ሸበል አላት፡፡ የአየር ሙቀቷንም እስከ 20 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ዝቅ ማድረግ ይቻላል›› ብሏል፡፡

ኢትዮጵያን ሄራልድ በቁጥር 34 ጥር 1952 (እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 1960) ደግሞ ‹‹ለብዙ ጊዜያት የወደብ መርከቦች መሀል አገርን በስልክ የማገናኘት ፍላጎት ከፍተኛ ነበር፡፡ ይህንንም ችግር ለማስወገድ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ቴሌኮሙዩኒኬሽንና የባህር መምርያ በጋራ ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ይኼውም ጥረት እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 1 ቀን 1959 ጀምሮ በመጠናቀቁ በስልክም ሆነ በቴሌግራም ለመገናኘት ተችሏል›› ሲል አሥፍሯል፡፡

ቺፍ ኢንጂነር አርሲኤል ሆገን ደግሞ ማሽኗ እጅግ ዘመናዊ ሲሆን፣ በቀላሉ መጠገን ይቻላል ብሏል፡፡ በተጠቀሰው መጽሔት እንደሠፈረው ሁሉ፣ ምንም እንኳን መርከቧ የምትንቀሳቀሰው በፈረንጆች እንደነበር ባይካድም፣ ፈረንጆቹን በኢትዮጵያውያን ለመተካት የሚደረገው ጥረት ፈጣን ነበር፡፡ ስለሆነም መርከቦቹ በተገዙ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሆላንድ ውስጥ የሠለጠኑ ካዴቶች የሥራ ሥልጠና አግኝተው መኮንኖች ሆነዋል፡፡ ሌሎች ባህረኞችና በምግብ ዝግጅት ኃላፊነቱን በብቃት ለመውሰድ የሚችሉ ኢትዮጵያውያን እየተተኩ ነው፡፡ ምንም እንኳን አንድን የባህረኛ ቡድን በተሟላ ሁኔታ ለማዘጋጀት ብዙ ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያውያን ግን ሥራቸውን ስለሚወዱና ራሳቸውን ለማሻሻል ብርቱ ፍላጎት ስላላቸው በቀላሉ ይማራሉ ሲል ቺፍ ኢንጂነሩ ያረጋግጣል፡፡

‹‹መነን›› የተሰኘው መጽሔት በቁጥር 6 መጋቢት 1956 ዓ.ም. በወጣው ዕትሙም፣ ‹‹የባህር ክፍል መምርያ ቤትና ተግባሮቹ›› በሚል ርዕስ ባወጣው ጽሑፍ አቶ ከተማ አበበን የተባሉ የባህር ክፍል መምርያ ኃላፊን፣ የመቶ አለቃ መስፍን ብርሃኔ የተባሉ የንግድ መርከብ የንግድ ኃላፊን፣ አቶ መስፍን ፈንታ የተባሉ የበጀትና የኢኮኖሚ መምርያ ኃላፊን፣ አቶ ወልደ ሰንበት ይረጌ የማስታወቂያ መምርያ ኃላፊንና አቶ ደመቀ መታፈሪያ የቴክኒክ ክፍል ኃላፊን በማነጋገር በወቅቱ የነበረውን እንቅስቃሴ በሰፊው አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ በ1959 ዓ.ም. አዶሊስ የተባለችውን 4,700 ቶን የምትጭን ገዛ፡፡ በኢትዮጵያ ንግድ መርከብ አማካይነት ከአውሮፓ ወደ ኢትዮጵያ፣ ከኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ ያለ ችግር የማጓጓዙ ሒደት በመቀጠሉም አድናቆትን እያገኘ መጣ፡፡ ይልቁንም የባህሩ ሥራ የበለጠ ጠንካራ የሚሆነው አዲስ አበባና ሮተርዳም በነበሩት ጽሕፈት ቤቶች ስለነበር፣ የእነዚህ ጽሕፈት ቤቶች መጠናከር ብቃት የሚመሠገን ሆነ፡፡

ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ሥራውን በጀመረበት ወቅት የሚመራው በዳይሬክተሮች ቦርድ ሆኖ፣ በዋና ሥራ አስኪያጅ አመራር ሥር የቴክኒክ፣ የፍሬት፣ የሒሳብ፣ የፐርሶኔልና የኢንሹራንስ የሥራ ክፍሎች ነበሩት፡፡

የንግድ መርከብ አገልግሎት ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለው እንደመሆኑ፣ መርከቦች የሚያጓጉዙትን ጭነት አፈላልጎ የማግኘት፣ መርከቦች በደረሱባቸው ወደቦች ሁሉ ጊዜ ሳያባክኑ የመጫንና የማራገፍ ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ የማድረግ፣ የማስጫኛና የማራገፊያ እንዲሁም ሌሎች ወጪዎችን የመቆጣጠርና ባህረኞች ከመርከብ በሚወርዱበትና በሚወጡበት ጊዜ የመርዳትና በአጠቃላይ የኩባንያውን ጥቅም የሚያስከብሩና በዋናው መሥሪያ ቤት በመርከቦቹ እንዲሁም በደንበኞችና አገልግሎት ከሚሰጡ የውጭ ድርጅቶች ጋር ያለውን ሥራ የማስተባበር የመሳሰሉት ተግባሮችን የሚያከናውን አካል ወይም ወኪል መርከብ በሚያገለግልበት ወደቦች ሁሉ እንዲኖረው ያስፈልጋል በሚል እምነት ሲንቀሳቀስ ቆየ፡፡ ይሁንና በ1959 ዓ.ም. ማለትም የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ሥራውን በጀመረ ከሦስት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የእስራኤልና የዓረቦች ጦርነት ተጀመረና ስዊዝ ካናል ተዘጋ፡፡

የስዊዝ ካናል መዘጋትም በቀይ ባህርና በአካባቢው የመርከቦች እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ለውጥን አስከተለ፡፡ በዚህም መሠረት ቀደም ሲል በቀይ ባህርና በአካባቢው የባህር ትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጡና ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ፣ ይጭኑና ያራግፉ የነበሩ መርከቦች በደቡብ አፍሪካ ዞሮ መምጣት በትርፍ በኩል የማያዋጣቸው በመሆኑ ወደ ሌላ አቅጣጫ ተሰማሩ፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ኩባንያም በነበሩት መርከቦች ብቻ የአገራችንን ፍላጎት የሚያሟላ አልነበረም፡፡ ስለዚህም የውጭ ንግዱ ሳይቋርጥ እንዲካሄድ ያገለገሉ ተጨማሪ መርከቦች መግዛት ተገደደ፡፡ በዚህም መሠረት፣

8,900 ቶንስ የምትጭን ጣና ሐይቅን በ1960 ዓ.ም፣ 564 ቶንስ የምትጭን አሸንጌ ሐይቅን በ1961 ዓ.ም.፣ 2,980 ቶንስ የምትጭን ዝዋይ ሐይቅን በ1961 ዓ.ም. መርከቦች ገዛ፡፡ በመግዛቱም በአገልግሎት ላይ በማዋሉም የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ የባሰ እንቅፋት ሳያጋጥመው ሊቀጥል ቻለ፡፡ በፈተናና በችግር ወቅት ለአንድ አገር የራሱ የንግድ መርከብ አገልግሎት መኖር ምን ያህል አስፈላጊና አስተማማኝ መሆኑንም አረጋገጠ፡፡ ይህም ማለት ግን ድርጅቱ አትራፊ ነበር ማለት አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ 1966 – 1983 ዓ.ም.

እርግጥ ነው እስከ 1966 ዓ.ም. በነበረው ጊዜ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ የሚሰጠውን ጠቃሚ አገልግሎት እንጂ የደረሰበትን ኪሳራ የሚያሳይ መረጃ በቅርቡ አይገኝም፡፡ በ1966 ዓ.ም. በቀረበው ጥናት ግን ኪሳራው እየተጠናከረ መጥቶ ከተመሠረተ ከሰባት ዓመታት በኋላ፣ ማለትም በ1965 ዓ.ም. ላይ 23 ሚሊዮን ብር ደርሶበት እንደነበር የጥሬ ገንዘብ እጥረት አጋጥሞት ሥራውን ለማቆም ተቃርቦ እንደነበር እንረዳለን፡፡ ለኪሳራ ተዳረገ ተብሎ ከቀረበው ምክንያት ጥቂቱም፡-

 1. ለኪሳራው ወይም ለውድመቱ ዋና መንስዔ የአደረጃጀት ጉድለት ያለበት መሆኑ፣ የመርከቦችና የውክልና ሥራው በውጭ አገር ሰዎች በመያዙ ካለው የመርከብ ገበያ ጋር ተወዳዳሪ ሊሆን አለመቻሉ፣
 2. በዱቤ የተገዙ መርከቦች ዋጋ ውድነትና የወለዱ ከፍተኛነት፣
 3. በስዊዝ ካናል መዘጋት ምክንያትና የተገዙት አዱሊስ፣ ጣና ሐይቅ፣ ዝዋይ ሐይቅና አሸንጌ ሐይቅ የተባሉት መርከቦች ያረጁ በመሆናቸው፣
 4. የስዊዝ ካናል ሲዘጋ ከአውሮፓ የሚመጣው በደቡብ አፍሪካ ዞሮ እንዲሄድና በዚህም ምክንያት ለከፍተኛ ወጪ በመዳረጉ ነበር፡፡

በዚህም መሠረት ለኪሳራ የዳረጉት አሮጌ መርከቦች እንዲሸጡ ተደረገ፡፡ በ1970 ዓ.ም. ላይም የመንግሥት ልዩ ልዩ ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ጋር እንዲተባበሩ የሚያስችል ፖሊሲ ወጣ፡፡ ከቀይ ባህር እስከ ሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ተወስኖ የነበረው የንግድ መስመር ወደ ምሥራቅ አውሮፓም ተስፋፋ፡፡ የስዊዝ ካናልም በመከፈቱ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ኩባንያ ማትረፍ ጀመረ፡፡

ከ1966 ዓ.ም. በፊት በነበሩት ሦስት ደረቅ ዕቃ ጫኝ መርከቦች ዕድገት ያሳየው ድርጅት በ1972 ዓ.ም. ባሉት ሰባት ዓመታት አሥር መርከቦችን ለመጨመር ቻለ፡፡

9,215 ቶንስ የመጫን ችሎታ ያለው ራስ ዳሽን በ1966 ዓ.ም.፣ 2,200.00 ቶንስ የሚጭነው ነበልባል 1969 ዓ.ም.፣ 2,428.00 ቶንስ የሚጭነው ካራ ማራ በ1972  ዓ.ም.፣ 4,107.00 ቶንስ የሚጭነው ቀይ ኮከብ 1974 ዓ.ም.፣ 4,107.00 ቶንስ የሚጭነው ወልወል በ1974 ዓ.ም.፣ 3,500.00 ቶንስ የሚጭነው፣ ኦሞ ወንዝ በ1978 ዓ.ም. 3,276.00 ቶንስ የሚጭነው ዓባይ ወንዝ በ1977 ዓ.ም. 1,5107.00 ቶንስ የሚጭነው አብዮት በ1977 ዓ.ም፣ 15,107.00 ቶንስ የሚጭነው አንድነት በ1977 ዓ.ም. በአገልግሎት ላይ ዋሉ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ 1983 – 2000 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ኮርፖሬሽን እየተባለ ይጠራ የነበረው መሥሪያ ቤት በመንግሥት ልማት ድርጅቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/1984 መሠረት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 196/1986 የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ድርጅት ተብሎ በ122 ሚሊዮን ብር ካፒታል ከሐምሌ 1 ቀን 1986 ዓ.ም. አንስቶ በንግሥት ልማት ድርጅትነት እንደገና ተቋቁሞ መሥራት ጀመረ፡፡ በድርጅቱ ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 196/1986 መሠረትም የድርጅቱ የበላይ አካል የሥራ አመራር ቦርድ ሲሆን፣ ድርጅቱ በዋና ሥራ አስኪያጅ በሚመሩ አምስት መምርያዎች፣ አንድ አገልግሎትና ሁለት ቢሮዎች ተደራጅቶ መሥራት ቀጠለ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ድርጅት ራሱን ችሎ በገቢው እየተዳደረ እንዲያስገኝ ከሚጠበቅበት የፋይናንስ ጥቅም ሌላ የሚከተሉት ዓላማዎችና ተግባሮች እንዲኖሩት ተደረገ፡፡  እነሱም፡-

 1. በጠረፍ አካባቢም ሆነ በዓለም አቀፍ ባህሮች ላይ የባህር ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት፣
 2. አገሪቱ በትራንስፖርት ረገድ መሠረታዊ የሆነ ፍላጎቷን የምታሟላበት በዓለም አካባቢ በሚከሰቱ ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችና የአካባቢ ግጭቶች ሳቢያ ሊፈጠር የሚችል የአገልግሎት መጓደልና የዋጋ ንረት በብሔራዊ ኢኮኖሚዋ ላይ ተፅዕኖ እንዳያደርስ አስተማማኝ የሆነ የባህር ማጓጓዣ አገልግሎትና የትራንስፖርት ዋጋ መረጋጋት እንዲኖር ማድርግ፣
 3. ለአገሪቱ የገቢና ወጪ ንግድ አገልግሎት በመስጠት ለባህር ትራንስፖርት የሚከፈለውን የውጭ ምንዛሪ ማዳንና ማፍራት፣
 4. የንግድ መርከብ ሥራና ቴክኖሎጂን በአገር ውስጥ ማስተዋወቅና ማስፋፋት፣
 5. ኢትዮጵያውያን በመርከበኝነት በንግድ መርከብ ሙያ በማሠልጠን የሥራ ዕድል መክፈት፣

ድርጅቱ ቀደም ሲል በተጠቀሰው አዋጅ ከተቋቋመ ወዲህ እንደ ሥራው ስፋትና ክብደት እየተመጠነ አደረጃጀቱ በየጊዜው ሲሻሻል የቆየ ሲሆን፣ አዲስ አበባ በሚገኘው በዋና መሥሪያ ቤትና በውጭ አገር በተጠሪና አስተባባሪ ጽሕፈት ቤቶች ተደራጅቷል፡፡  በሆላንድ/በሮተርዳም ከተማ የድርጅቱን የአውሮፓ ኦፕሬሽን የሚያስተባብርና የመርከቦችን የቴክኒክ ጥገና፣ የመለዋወጫ ዕቃ ፍላጎትንና ሌሎች አቅርቦቶችን የሚከታተልና ከዋናው መሥሪያ ቤት በሚሰጠው መመርያ መሠረት የሚያስፈጽም የራሱ የሆነ «የውጭ አገር ተጠሪ ጽሕፈት ቤት» ሲኖረው በጣሊያንና በተባበሩት የዓረብ ኢምሬት በየወደቡ ወኪል ቢሮ ውስጥ ሆነው ኦፕሬሽን የሚያስተባብሩ የድርጅቱ ተጠሪ ተመደቡ፡፡

በጂቡቲ ወደብም ቀደም ሲል የመርከቦቹን የመጫንና የማራገፍ ሥራ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶችና አቅርቦቶችን ለማቀላጠፍ ከወኪሉ ከባህር ትራንዚት አገልግሎት ድርጅት ጋር በመተባበር የሚሠራ «የጂቡቲ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት» ከፈተ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ድርጅቱ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ወደቦች እንደ አስፈላጊነቱ በቋሚነትም ሆነ በጊዜያዊነት የሚሠሩ የመርከብ ወኪሎች ተጨመሩ፡፡  እነዚህም የመርከብ ወኪሎች ኮሚሽን እየተከፈላቸው የሚጓጓዘውን ጭነት የሚያሰባስቡ፣ መርከቦቹን የሚያስተናግዱ፣ በተወከሉበት ወደብ የኦፕሬሽን እንቅስቃሴ የሚከታተሉ፣ የሚቆጣጠሩና በአጠቃላይ የድርጅቱን ጥቅም የሚያስከብሩ ነበሩ፡፡

ድርጅቱ በሰው ኃይል ረገድ ያለበትን ችግሮች ለመወጣት በሥራው መስክ ኢትዮጵያውያንን ወደ ውጭ አገር በመላክ እንዲሠለጥኑ በኔዘርላንድ፣ በጣሊያን፣ በጋና፣ በፓኪስታን፣ በግሪክ፣ በፖላንድ፣ በቡልጋሪያና በእንግሊዝ የኖቲካልና የማሪን ኢንጂነሪንግ የትምህርት ተቋሞች ውስጥ እንዲሠለጥኑና ኢትዮጵያውያን ለመሪና ለመሐንዲስ መኮንንነት የሚያበቃቸውን በየደረጃው የሚፈለገውን የምስክር ወረቀት እንዲያገኙ አድርጓል፡፡

በየብስ ላይ የተመደቡትንም ሠራተኞች ለንግድ መርከብ ለየት ያለ የሥራ ባህርይ እንዲመጥኑና በፈጣን ዕድገት ላይ የሚገኘውን የንግድ መርከብ አሠራር ሥልት እንዲቀስሙ በእንግሊዝ፣ በኖርዌይና በስዊድን፣ ወዘተ. ከዲፕሎማ እስከ ድኅረ ምረቃ በቴክኒክ፣ በማኔጅመንት፣ በኢንሹራንስ የሥራ ዘርፍ ከ35 በላይ ሠራተኞች የሠለጠኑ ሲሆን፣ ከዚህ ሌላ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ወኪሎች ቢሮዎች ውስጥ የሥራ ላይ ልምምድ በማድረግ ሠራተኞች ሙያቸውን እንዲያዳብሩ ተደርጓል፡፡

ከድርጅቱ ምሥረታ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከ345 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ለመርከብ ላይ ሥራ በተዘረጋው የሥልጠና ፕሮግራም ላይ የተሳተፉ ቢሆንም፣ አብዛኛዎቹ በተለያዩ ምክንያቶች ከድርጅቱ ስለለቀቁ በአሁኑ ሰዓት 93 የሠለጠኑ ኢትዮጵያውያን በመሪና በመሐንዲስ መኮንንነት፣ በተለያዩ የሥራ ደረጃዎች በድርጅቱ መርከቦች ላይ ተመድበው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም 13 ካዴቶች ለመሪ መኮንንነት፣ ስድስት ካዴቶች ለመሐንዲስነት የሚያበቃቸውን የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ለማግኘት በመርከቦች ላይ ተመድበው የሚፈለገውን የባህር ላይ ልምምድ ጊዜ በማሟላት ላይ ናቸው፡፡ የመሪና፣ የመሐንዲስ ክፍል ካዴቶችም ለመጀመሪያ ደረጃ መኮንንነት የሚያበቃቸውን ትምህርት በህንድ አገር በመከታተል ላይ ይገኛሉ፡፡

አሁን ያሉትም ሆነ ወደፊት የሚኖሩትን የድርጅቱ መርከቦች ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን መሪና መሐንዲስ መኮንኖች ለመምራትና ለማንቀሳቀስ ለመርከብ ላይ ሥራ የሚያስፈልገው የመጀመሪያ ደረጃ የሙያ ሰርተፊኬት ሥልጠናም ሆነ ለተከታታይ ደረጃ ብቃት የሥልጠና ፕሮግራም የሚቀጥል ይሆናል፡፡

ድርጅቱ ሲቋቋም አገልግሎት የጀመረው በወቅቱ የአገሪቱ የውጭ ንግድ በሚያመዝንበት የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ መስመር ላይ ብቻ በማተኮር ነበር፡፡  በኋላ ግን የአገሪቱን የንግድ አቅጣጫ በመከተልና የድርጅቱንም መርከቦች ብዛትና ጥንካሬ መጎልበት በማጤን፣ ሌሎች ተጨማሪ የአገልግሎት መስመሮች እንዲከፈቱ ተደርጓል፡፡  በአሁኑ ጊዜም መደበኛ አገልግሎት የሚሰጥባቸው መስመሮችና የተጀመሩበት ዘመን እንደሚከተለው በግልጽ ቀርቧል፡፡

በ1958 ዓ.ም. ከቀይ ባህር ሰሜን ምዕራብ አውሮፓና እንግሊዝ አካባቢዎች፣ በ1966 ዓ.ም.    ከቀይ ባህር ሰሜን ምሥራቅ አውሮፓ አካባቢ፣ 1972 ዓ.ም. ከቀይ ባህር ሜዲትራንያንና አድሪያቲክ አካባቢ፣ በ1974 ዓ.ም.      ከቀይ ባህር መካከለኛ ምሥራቅ አካባቢ፣ በ1979 ዓ.ም. ከቀይ ባህር ሩቅ ምሥራቅ ደቡብ ምሥራቅ እስያ አካባቢ፣ በ1981 ዓ.ም.      ከቀይ ባህር የመን አካባቢ (በራስ መርከብ የነዳጅ ማጓጓዝ አገልግልሎት) በ1986 ዓ.ም.  ከቀይ ባህር ባህረ ሰላጤ አካባቢ፣ በ1989 ዓ.ም. ከቀይ ባህር ህንድ ክፍለ አኅጉር አካባቢ፣ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ድርጅቱ አገልግሎቱን የጀመረው «ንግሥተ ሳባ» እና «የይሁዳ አንበሳ» ተብለው በሚጠሩ ሁለት ባለ 6,655 ቶን ደረቅ ዕቃ ጫኝ አዳዲስ መርከቦችና «ላሊበላ» ተብላ ትጠራ በነበረች አንድ ባለ 34,075 ቶን ድፍድፍ ነዳጅ ጫኝ የሆነች አዲስ መርከብ ነበር፡፡ ነገር ግን ድርጅቱ ሥራውን በጀመረ በዓመቱ የስዊዝ ቦይ በመዘጋቱ፣ የነበሩት በተለይ ደረቅ ዕቃ ጫኝ ሁለት መርከቦች በደቡብ አፍሪካ በአትላንቲክ ውቅያኖስ እየተዞረ ወደ ሰሜን አውሮፓ ለሚሰጠው አገልግሎት በቂ ባለመሆናቸው ከሌሎች የውጭ አገር የንግድ መርከብ ድርጅቶች ጋር ለመወዳደር ካለመቻሉም በላይ ድርጅቱም ለኪሳራ ተዳርጎ ነበር፡፡ ይህንን ችግር ተቋቁሞ የአገሪቱን ጥቅም ለማስጠበቅ፣ አገልግሎቱን ለማጠናከርና ለማስፋፋት የተለያዩ ያገለገሉ መርከቦችን በመግዛት በሥራ ላይ አሰማርቶ ነበረ፡፡ በሌላ በኩል ግን መርከቦቹ ያላቸውን አገልግሎት ከሚያስከትሉት ወጪ ጋር በየጊዜው በመገምገም ጠቀሜታ የሌላቸው እንዲሸጡ ተደርጓል፡፡

በአጭሩ መንግሥት የድርጅቱን ዕዳ ሙሉ በሙሉ ከመዝጋቱም በላይ ለድርጅቱ በመርከብ ግዥም ሆነ በሌላ በኩል አስፈላጊውን ድጋፍ በመስጠቱ፣ በተለይም ከ1972 ዓ.ም. ወዲህ ባሉት አሥር ዓመታት ውስጥ ብቻ አራት ያገለገሉና አምስት በትዕዛዝ የተሠሩ አዳዲስ መርከቦች ተገዝተዋል፡፡ በመሆኑም ድርጅቱ ከምሥረታው ጀምሮ እስከ አሁን «ዝዋይ» እና «ጫሞ» ተብለው ይጠሩ የነበሩትን ሳይጨምር፣ ዘጠኝ አዳዲስ እንዲሁም «ተከዜ» የተባለችውን መርከብ ጨምሮ 12 ያገለገሉ በጠቅላላ 21 መርከቦችን ገዝቶ የነበረ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ የተወሰኑ መርከቦችን በእርጅናና በሌሎች ምክንያቶች እንዲሸጡ በማድረግ አዳዲስ መርከቦችን በማሠራት አሰማርቷል፡፡ እነዚህም አድማስ በ… ተሠራች፣ 13,593 ቶንስ የመጫን ችሎታ፣ ተከዜ በ1990 ተሠራች 18,145 ቶንስ የመጫን ችሎታ፣ ጊቤ ወንዝ 1998 ተሠራች 25,000 ቶንስ የመጫን ችሎታ፣ ሸበሌ ወንዝ በ1999 ተሠራች 25,000 ቶንስ የመጫን ችሎታ ያላቸው ናቸው፡፡

በአገሮች መካከል የሚካሄደው ንግድ በመጠኑም ሆነ በዓይነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ ለተለያዩ የሸቀጣ ሸቀጥ ዓይነቶች የተለያየ የመርከብ ዓይነት የሚጠይቅ ሆኗል፡፡ በዚሁ መሠረት በመርከቦች አሠራር ረገድ ፈጣን የቴክኖሎጂ ዕድገት ታይቷል፡፡ በዘመኑ የምናያቸው ሮልኦን እና ሮል ኦፍ (Roll on Roll-off) ኮንቴይነር ጫኝ የመሳሰሉት መርከቦች በየደረሱባቸው ወደቦች ዕቃ ለማራገፍና ለመጫን የሚያስችሉ ዘመናዊና ቀልጣፋ መሣሪያዎች ስላሏቸው በወደቦች መካከል ፈጣን ምልልስ በማድረግ የተሻለ ወጤትም ለማስገኘት አስችሏል፡፡ ስለዚህ አገሪቱ የምትፈልገውን የባህር ትራንስፖርት አገልግሎት በአስተማማኝና በተቀላጠፈ ሁኔታ ለመቀጠል የገፉ መርከቦችን የሚተኩ በዓይነትና በመጫን ችሎታቸው ተስማሚ የሆኑ መርከቦች ያስፈልጋሉ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ከ2000 ዓ.ም. ወዲህ

የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ እየተባለ ይጠራ የነበረው ድርጅት፣ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፓርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት (ኢባትሎአድ) እየተባለ ይጠራል፡፡ በአሁኑ ጊዜ አሶሳ፣ ጋምቤላ፣ ሐረር፣ መቐለ፣ ሰመራ፣ ፊንፊኔ፣ ሐዋሳና ባህር ዳር የተባሉ መርከቦችን የጨመረ ሲሆን፣ ሸበሌና ጊቤም አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡ ዕድሜ ከሰጠኝና የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት መረጃ በመስጠት ከተባበረኝ እቀጥላለሁ፡፡ ለጊዜው እዚህ ልግታው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles