Tuesday, February 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ይዞት የመጣው ተግዳሮት

አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ይዞት የመጣው ተግዳሮት

ቀን:

በቅርቡ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዲደረግ የተወሰነው ሥርዓተ ትምህርት አብዛኛውን የማኅበረሰብ ክፍል ሆነ፣ ምሁራንን ሲያነጋገር እንደነበር ይታወሳል፡፡

ሥርዓተ ትምህርቱ ‹‹የግል ትምህርት ቤቶችን ያላማከለና በቂ የሆነ ጥናት ያልተደረገበት›› በማለት የሚከራከሩም አሉ፡፡ ሥርዓተ ትምህርቱ ከመስከረም 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ ቢጀምርም፣ የውጭ አገር ሥርዓተ ትምህርትን የሚከተሉ የግል ትምህርት ቤቶች ግን አሉ፡፡

መንግሥት ሥርዓተ ትምህርቱ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች እንዲተገበር በጥብቅ ያሳሰበና ይህንን በማይተገብሩ ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድ ያስታወቀ ቢሆንም እንቢተኝነቱ ይታያል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን ከአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ፣ ከመንግሥትና ከግል ትምህርት ቤቶች ከተውጣጡ ኃላፊዎች ጋር በአፍ መፍቻ ቋንቋና በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ትግበራ ዙሪያ ችግሮችና መፍትሔዎችን በተመለከተ ጥቅምት 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱም በሥርዓተ ትምህርቱ ላይ እየተፈጸሙ ያሉ አሠራሮችንና ዝርዝር ጉዳዮችን በጽሑፍ መልክ ያቀረቡት የትምህርትና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ፍቅርተ አበራ እንደገለጹት፣ መንግሥት ተግባራዊ እንዲሆን ውሳኔ ያሳለፈበትን የትምህርት ሥርዓት የሚተላለፉ በርካታ ቅድመ መደበኛና አንደኛ ደረጃ የግል ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡

እነዚህም የግል ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ የውጭ አገር የትምህርት ሥርዓትን በመከተል እያስተማሩ መሆኑን፣ ተቋሙም እስካሁን ባደረገው ክትትል ከ70 በላይ የግል ትምህርት ቤቶችን መያዙን ተናግረዋል፡፡

 አብዛኛው ትምህርት ቤቶች ሥርዓተ ትምህርቱ ላይ ያልተካተቱ፣ የከዚህ ቀደም የነበሩና አሁን የታጠፉ የትምህርት ዓይነቶችን እያስተማሩ መሆኑንና መንግሥትም ያስቀመጠውን ፖሊሲ እየጣሱ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

መንግሥት አዲስ ያወጣው ሥርዓተ ትምህርት ፖሊሲ እንደሚያሳየው ከሆነ፣ ከአንድ እስከ ስድስተኛ ክፍል ላይ ያሉ ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋ እንዲማሩ የሚደነግግ ቢሆንም፣ ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ የግል ትምህርት ቤቶች የወጣውን መመርያ እየጣሱ ነው ብለዋል፡፡

በ2015 ዓ.ም. ትምህርት ከተጀመረ ወዲህ ተቋሙ ሁለት ጊዜ ፍተሻ ማካሄዱን፣ በፍተሻው ወቅትም የውጭ አገር የትምህርት ሥርዓትን የትምህርት ጥራት መለኪያ በማድረግ ሲጠቀሙበት የነበሩ የግል ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡

በተለይ ችግሩ እየታየ ያለው ትምህርት ቤቶች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ወላጆች ላይ ጭምር መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ፍቅርተ፣ ‹‹በዚህም የተነሳ ተቋማት ከተቋማት ጋር እርስ በርስ የመወዳደሪያ መንገድ አድርገውታል፤›› ብለዋል፡፡

ይህንን አሠራር የሚከተሉ የግል ትምህርት ቤቶች ለማስተማሪያና ለማጣቀሻ የሚጠቀሟቸው መጻሕፍት፣ በሚመለከተው አካል ያልተገመገሙና የትምህርት ይዘቱን ያላሟሉ መሆኑን ምክትል ሥራ አስኪያጇ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ አራት ዓይነት ተቋማት መፈጠራቸውን፣ እነሱም መንግሥት ያወጣውን ፖሊሲ በመከተል ጥራት ያለው ትምህርት እያስተማሩ የሚገኙ፣ ሥርዓተ ትምህርቱን ጠብቀው በሚያስተምሩ ጊዜ የወላጆች ጫና የሚደርስባቸው፣ የመንግሥትንም የራሳቸውን ትምህርት የሚያስተምሩና የውጭ አገር የትምህርት ሥርዓትን ሙሉ ለሙሉ የሚጠቀሙ እንደሆኑ ወ/ሮ ፍቅርተ አስረድተዋል፡፡  

በከተማዋ ከ1,500 በላይ የትምህርት ተቋማት መኖራቸውን፣ እነዚህም የራሳቸው የሆነ የትምህርት ፖሊሲ ተግባራዊ የሚያደርጉና የውጭ አገር ትምህርት ሥርዓትን የሚጠቀሙ እንዳሉ አብራርተዋል፡፡

በአጠቃላይ ሥርዓተ ትምህርቱን ተከትለው የማያስተምሩ ትምህርት ቤቶች ላይ ዕርምጃ የሚወሰድ እንደሆነ፣ ከአንድ እስከ ስድስተኛ ክፍል ለሚገኙ ተማሪዎች ለማገዝ ከትምህርት ሥርዓቱ ውጪ የትምህርት (ቲቶር) መስጠት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አድማሱ ደቻሳ በበኩላቸው፣ መንግሥት በ2015 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግና ሥርዓተ ትምህርቱ ላይ የመጻሕፍት ክፍተቶች እንዳይኖሩ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በአጠቃላይ ከሦስት ሚሊዮን በላይ መጻሕፍት እንዲታተሙ የታዘዘ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥም 1.2 ሚሊዮን መጻሕፍቱ ለተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተዳርሰዋል ተብሏል፡፡

በመንግሥትም ሆነ በግል ለሚያስተምሩ ተቋማት መጻሕፍት በሶፍት ኮፒ እንዲደርሳቸው መደረጉን፣ አንዳንድ ተቋማት ግን ከዚህ ቀደም የነበሩ ነባር መጻሕፍትን እየተጠቀሙ እንደሆነ አክለው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊትም አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት በምን ዓይነት መልኩ ነው ተግባራዊ የሚደረገው? ምን ዓይነት ችግሮችስ አሉ? የሚለውን ለመፍታት ከመንግሥትም ሆነ ከግል ተቋማት ጋር ውይይት መደረጉን አቶ አድማሱ ተናግረዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች ካነሷቸው ነጥቦች መካከል፣ በመንግሥት በኩል የተቀረፀው ሥርዓተ ትምህርት የግል ትምህርት ቤቶችን ያማከለ አለመሆኑ ይገኝበታል፡፡  

አብዛኛው የግል ትምህርት ቤቶች አዲሱን ሥርዓተ ትምህርት ተከትለው በሚያስተምሩ ጊዜ ወላጆች ቅሬታ እንደሚያቀርቡና ‹‹ትምህርቱ ከመንግሥት ትምህርት ቤት በምን ይለያል?›› የሚል ጥያቄ እንደሚያቀርቡ ከግል ትምህርት ቤት የመጡ ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ለተማሪዎች የሚሆን የመማሪያ መጻሕፍት ባለመኖሩ ወላጆች ቅሬታ እንደሚያቀርቡ፣ አሁን የወጣው የትምህርት ፖሊሲ ትግበራ ላይ በርካታ ችግሮች እንዳሉ በውይይቱ ወቅት ተነስቷል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የካቲት አብዮት – ጥያቄዎችሽ ዛሬም እየወዘወዙን ነው!

በበቀለ ሹሜ አጭር መግቢያ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከ1960ዎች ወጣቶች ርዝራዦች አንዱ...

የሰሞኑ የ“መኖሪያ ቤቶች” የጨረታ ሽያጭ ምን ዓይነት ሕጋዊ መሠረት አለው?   

በዳዊት ዮሐንስ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አየር ላይ ከሚንሸረሸሩ ዜናዎች...

ሁለቱ ወጎች፡ ከሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! እስከ በዓሉ ቤርሙዳ

በተክለ ጻድቅ በላቸው ሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! ከሁለት ሦስት ዓመት...

ለትግራይ ክልል ድርቅ ተፈናቃዮች አፋጣኝና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ...