Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ቅስም ሰባሪዎች!

ሰላም! ሰላም! ‘እንደገና ፍቅር እንደገና እንደገና አይገኝምና’ ይሉት ዘፈን እንደ እውነቱ ለፍቅር ቢሠራም ለእኔና ለእናንተ ግን አልሠራም። እንዴት ሰነበታችሁ? ቀኑን እየገፋነው ይሁን ወይ እየገፋን ይኼው በሰንበት አንተጣጣም። በዛም ተባለ በዚህ ዘመኑ የገፊና የተገፊ ነዋ፣ ምን ይደረግ? ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ጋሽ መሐሙድ አህመድ ይህንን የእንደገና ዜማ ርዕሰ ጉዳይ እየለዋወጠ ደጋግሞ ቢጫወተው እንዴት ሸጋ ነበር? አንበርብር ሁሉም ነገር ማለት ይቻላል እንደ ትናንቱ እንዳስቀመጥከው መቼ ታገኘውና?›› ሲለኝ ነበር። ‹‹እንዴት?›› ብዬ ማብራሪያ መጠየቅ በእውነቱ ድካም ሆነብኝ። እያወቅኩት? እያወቅነው? ከአቋም እስከ ጥራጥሬ በነበረበትና በትናንትና ሥፍራው ዋጋው አልገኝ ማለቱን እያየሁ ለምን ብዬ ላድክመው? እናንተዬ ዘመኑና ሰው ትናንት እንደምናውቀው አልገኝ ብሎ አሻፈረኝ እንዳለ ምን አስረጂ ያስፈልገዋል ትላላችሁ? ሰው ብትሉት እንደቃሉ፣ እንዳለባበሱ፣ እንደ ተቀመጠበት ወንበር (ሹመት) ክብደት የመገኘቱ ነገር በተጠያቂነትና ግልጽነት አሠራር ብቻ የሚመለስ እንቆቅልሽ አልሆነም። ታማኝነት፣ ቀናነት፣ ሰው አክባሪነት የሚባለሉ እሴቶች ምን እንደዋጣቸው የታወቀ ነገር የለም። እኔስ አፋልጉን ብለን አደባባይ እንውጣ ይሆን እላለሁ የምለው ሳጣ። ‘የጨነቀው እርጉዝ ያገባል’ ሲሆንብኝ። አሁን አሁን ሆን ብሎ አስረግዞ የሚያገባው በዛ እንጂ። ተመልከቱ ተረትና አባባሉም ለትናንት እንጂ ለዛሬ አልሠራም እያለ መጥቷል። ‹‹ወይ ጊዜ!›› አሉ ባሻዬ፡፡ በስንት ልመናና ምልጃ የቀጠሉት ዕድሜ  ጉድ እያሳየ ቢያስቸግራቸው፡፡ የጉድ ዘመን!

ስለዘመን ካነሳን አይቀር ማለቂያ ባይኖረውም አንዳንድ እንበል እስኪ። እንግዲህ መቼም ወርኃ ጥቅምት መሸት ሲል ቅዝቃዜው የሚብስበት? ታዲያ እንጫወታ። በረባ ባረባው በሚያልቀው ዘመናችን ዘመንን ማማት እንደሆነ ሲወርድ ሲዋረድ የተቀበልነው የአያት የቅድም አያቶቻችን ወግ ነው። በተለይ የአሁኑ ትውልድ ባይኖረውም ይትብሃሉን ለመጠበቅ ደፋ ቀና ሲል እታዘበዋለሁ። ታዲያ ሰሞኑን አንድ ጎልማሳ ወዳጄ ያለሁበት ድረስ መጥቶ፣ ‹‹አንበርብር…›› አለኝ። ‹‹… በዚያን ሰሞን ካስተዋወቅኩህ የከንፈር ወዳጄ ጋር ልንጋባ ቆርጠናል…›› ሲለኝ ‹‹ማለፊያ፣ እንኳን ደስ አለህ ብዬ…›› አቀፍኩና የወዳጅነት ደስታዬን ገለጽኩለት። ‹‹እና ምን ልርዳህ?›› ስለው፣ ‹‹ቤተሰቦቿ ዘንድ ሽማግሌ አድርጌ ልልክህ ነው…›› አለኝ። ‹‹በቃ እንጋባ ብላችሁ ራሳችሁ ቆርጣችሁ ስታበቁ የምን ድራማ ነው?›› ልለው አሰብኩና ከአፌ መለስኩት። በወግና በልማዱ ውስጥ ጣልቃ ገብቼ ባልፈተፍትስ? ‹‹አሁን እኔ ትልቅ ሰው ነኝ። ምን ብዬ ነው ባለቀ ጉዳይ ሄጄ ‘ልጃችሁን ለልጃችን’ የምለው?›› እያልኩ ስጨነቅ ብዙ ቆየሁ። እንዲህ ያለውን ድፍረትና ወኔ ስለማላውቀው በጣም ተጨነቅኩ። በኋላ ውዴ ማንጠግቦሽን፣ ‹‹እንዲያው ምን ይሻለኛል?›› ብላት፣ ‹‹ነገር ማጥበቅ ስትወድ? ደረስ ብለህ ብትመጣ ምን እንዳይቀርብህ ነው? እንዲያው ያንተስ ነገር…›› ብላ አታማርርብኝ መሰላችሁ? እኔ እሷን ሳገባ በሽማግሌ መላክ ምክንያት ያየሁትን አሳር ትናንት ዋጋ ሰጥታ ስታሞጋግሰኝ እንዳልነበር፣ አሁን ለወግ ለልማድ የሚሠራው ሥራና ተውኔት ደጋፊ ሆናልኝ ቁጭ። እንዲህ እውነትን በአደባባይ ‘ዓይንሽን ለአፈር’ ብሎ ሕይወትን ቴአትር ያደረገበት ዘመን ይሁን ግን? ‘የምንኖረው አርቴፊሻል’ አለች ያቺ ድምፀ መረዋ፡፡ ወይ ትወና ስንቱ ውስጥ ዘው ብሎ ገባበት!

እንደምታውቁት እዚህ አገር ሥራ ላይ ብቻ አተኩሮ መኖር ከባድ ነው። ማኅበራዊ ሕይወቱ ራሱ ራሱን የቻለ ሥራ በሉት። መቼስ ምን ይደረግ በዚህ ቀውጢ የኑሮ ማዕበል በራስ ላይ ድራማ ለመሥራት ሥራ አልፈታም፣ ሰላሜንም አላጣ እያልኩ እየተነጫነጭኩ ወደ ሙሽሪት ቤተሰቦች ቤት አመራሁ። አብረውኝ በሩቅ የማውቃቸው ሦስት ጎልማሶችም አሉበት። ‹‹ሲጋቡ ሸምግለን ሲጣሉ ሸምግለን…›› እያለ ከመካከላችን አንዱ አንዲት ቀልድ አወጋን። ‹‹ሚስት ‘እንዲህ በጠጅ የምትጨርሰውን ገንዘብ ብትቆጥበው ዓለምን ትዞርበት ነበር’ ትለዋለች ባልን። ባል ሲመልስ ምን ቢል ጥሩ ነው? ‘አሥር ብርሌ ጠጅ ስጠጣ ራሷ ትዞር የለም ወይ? እኔ ምን አደከመኝ?’ አላት…›› ሲለን ሳቅ በሳቅ ሆንን። ነገ ፍቅር እንደ ጫጉላና የእጮኝነት ጊዜ አልሆን ሲል ሥራ ፈተን ‘ተው!’ ‘ተይ!’ ስንል የምንውለ ራሱ…  ተውት ማሟረት ይሆንብናል። ብቻ በተቀመጠበትና በተተከለበት ሥፍራ የሚገኝ ነገር እየጠፋ ነው። እንደተዋችሁት የምታገኙት ሰው አለ ከተባለ ግን ምናልባት ታክሲ ጥበቃ የተሠለፈ ሰው ብቻ መሆን ይገባዋል። እውነቴን አይደል? ‘ካልተሳፈሩበት ቶሎ ተሽቀዳድሞ፣ ጊዜ ታክሲ አይደለም አይጠብቅም ቆሞ’ እንዳልተባለ ዛሬ ተለውጦ ታክሲ ቆሞ እንዳልጠበቀን ቆመን ጠባቂዎቹ እኛ ሆንን። ‹‹ዘ ይገርም ሻሸመኔ›› ያለው ማን ይሆን!

ስለታክሲ ጥበቃ ሳነሳ ባለፈው ሰሞን አንድ ወዳጄ፣ ‹‹እነሱ ተመችቷቸው በ‘ቪ8’ ይንፈላሰሳሉ እኛ እዚህ እንደ ድንጋይ ተገትረን እንውላለን…›› ሲል ብሰማው፣ ‘ጓደኞችህ ተመችቷቸው በመርስዲስ ይንፈላሰሳሉ አንተ እዚህ ቆመህ ቀረህ! ድንጋይ!’ እያለ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ሥር ቆሞ ይሳደብ ስለነበረው ‘ጀብራሬ’ አንድ መጽሐፍ ውስጥ ያነበብኩት ትዝ ሲለኝ ነበር። የእኛ ኑሮ በትዝታ ሆኗል። ‹‹ማርጀታችን የሚታወቀው በትዝታ መኖር ስንጀምር ነው›› ያለው ሰው እንዴት ያለ ሊቅ ነበር? የሕዝቡ የትራንስፖርት ችግር ፈጽሞ የገባው የማይመስለው ባለስንዴው ልማታዊ መንግሥታችን ምን መፍትሔ እያሰበልን እንደሆነ በእውነቱ እኛም አላወቅንም፣ ቃል አቀባዩ ‘ኢቲቪ’ም አልነገረንም። ድሎትና ቅምጥል ኑሮ አሳዳጅ የሆኑ አንዳንድ ባለሥልጣኖቻችንንና እኛን ላነፃፀረ ግን ወዳጄ ለማለት የፈለገው ነገር በደንብ የሚገለጽለት ይመስለኛል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ለሕዝብና ለእውነት፣ ለማተባቸው ብለው መስዋዕትነት የከፈሉትንና በሕዝብ ሀብት እንቁላል መስለው የሚንፈላሰሱብን ስታስቡ እንዴት ያለ ኅሊና እንዳላቸው ማወቅ አያሰኛችሁም? ሌብነት የኢትዮጵያ የበኩር ልጅ ይመስል የዘራነውን ሁሉ እየወረሰን እስከ መቼ እንደምንኖር ግራ ያጋባል፡፡ እስከ መቼስ በራስ ላይ መቀለድ ተቀናቃኝ የሌለው ሀብታችን ሆኖ ይኖራል? እንጃ ነው መልሱ!

ታክሲ ጥበቃ በተሰለፍንበት ነው ብያችኋለሁ። አንዱ ‘ወይ ሐረር ወይ ሸገር ነይና አጫውችኝ’ በሚለው ዜማ ማፏጨቱን ገታ አድርጎ፣ ‹‹ኤድያ ፍቅር ድሮ ቀረ ታክሲ በሽ በነበረበት ዘመን፡፡ አሁን ነይ ቢሏት እሷስ ልምጣ ብትል በምን ትመጣለች?›› ሲል ፈገግ ያሰኘዋል ሰውን። ሌላው ከአፉ ተቀብሎ፣ ‹‹ኧረ እውነትህን ነው፣ ‘ከትልቁ ሾላ ከሥሩ ደርሼ፣ ያለ ዕድል አይበሉ መጣሁ ተመልሼ’ አይደል የሚለው የአገሬ ሰው። ስም ያተረፈብን ዘመን፡፡ ባዶ ኪስን ማን ይጠጋል?›› ይላል። ‹‹እንዲህ የትራንስፖርት ፖለቲካ ከራሳችን አልወርድ ብሎ እንዴት አድርገን ነው የአሥር ዓመቱን መሪ ዕቅድ የምናሳካው?›› ይለዋል ሌላው። ‹‹መልሱ አልተሰጠም…›› እየሳቀ ይመልሳል ሦስተኛው። ‹‹ውይ ፈጣሪ ሲወዳቸው እኮ…›› ትላለች ደግሞ አንዷ ቀዘባ ሠልፈኛ። ‹‹ማንን?›› ይጠይቃታል አንዱ፣ ‹‹ቪ8 መኪናቸውን መስታወቱን በጥቁር ሸፍነው የሚንቀባረሩ ባለሀብቶቻችንና ባለሥልጣናቶቻችን እንኳን እንዲህ ስንሆን አላዩን…›› አለች ስሜቷን በስላቅ ለመግለጽ እየሞከረች። ‹‹ቢያዩን ዝም የሚሉ ግን ይመስልሻል?›› ከማለቱ ሦስተኛው ሠልፈኛ፣ ‹‹እንዴት ዝም ይላሉ? ‘መንግሥት እኮ ለእያንዳንዱ ዜጋ መኪና ማደል አይችልም አቅም የለንም’ ይላሉ እንጂ እንዴት ዝም ይላሉ?›› ብሎ ፈገግ አለ። ‹‹እንዴት? መቼ ለእያንዳንዳችን መኪና ይሰጠን አልን?›› ሲለው ሌላው ሠልፈኛ ተናዶ የዚያኛው መልስ ተንከትክቶ መሳቅ ነበር። ቅኔው ገባኝ ያለ አብሮት ይስቃል!

በታክሲ እጦት እየተንገላታሁ ሥራ መፈለጌን መቼም አልተውኩትም። ቆይቼ አንድ ሥራ አግኝቻለሁ። ‘የማታ ማታ’ እንዲሉ፣ ሥራው በጣም ዘመናዊና ጥራት ያላቸው የቤት ዕቃዎችን ማሻሻጥ ነው። ከባህር ማዶ መጥቶ እዚህ ጠቅልሎ ለመኖር ያሰበ ‘ዳያስፖራ’ ነው፡፡ የቤቱን ዕቃ በኮንቴይነር ጭኖ ካስመጣ ጉምሩክ መከራረሙን ነገረኝ። አሁን ግን ‘ዕቃህን ውሰድ’ ቢሉት ደውሎልኝ፣ ‹‹የሚገዙ ሰዎች ፈልግ እንጂ እኔ እንደሆንኩ ቤቴን ከሞላሁ ቆይቻለሁ…›› አለኝ። ታዲያ በአካል ሳገኘው፣ ‹‹እንኳን ደስ አለህ…›› አልኩት። ‹‹ኧረ ተወኝ እባክህ? ‘ኑ አገራችሁ’ ይላሉ ይኼው ስንመጣ የሚሠሩትን ሥራ። እኔ የምለው መሰደድ እንዴት አይብስብን? እንዴት ባርነት አያምረን? ሰው በአገሩ እንደ ዜጋ መከበር ካልቻለ መብቱ ያለ አግባብ የማንም መጠቀሚያ የሚሆን ከሆነ አገር ምንድነው?›› ብሎ በምሬት የልቡን አጫወተኝ። ለጊዜው እኔ ምንም ልለው ስላልፈለግኩ ዝም አልኩ። የሕግ የበላይነት ከተረጋገጠ እኮ እንዲህ ብዙ መናገር አይጠበቅብንም ነበር። በለስ ቀንቶኝ ዕቃዎቹን አሻሻጬ ስጨርስ ድርሻዬን ሰጥቶኝ ተለያየን። ሌላ ጊዜ መልሰን እስክንገናኝ!

በሉ እስኪ እንሰነባበት። የእኔ ነገር ለካ የሽምግልናውን ጨዋታ አልጨረስኩትም? አሁን እኔ ሰው ነኝ? ምን ሆነ መሰላችሁ ‘አሁን ማን ነው የሚጀምረው? ምን ብሎ ነው የሚናገረው?’ ስንባባል ሳለን የሙሽሪት እናት በቤተዘመዶቻቸው ታጅበው ጠጁን፣ ጠላውን፣ ሽንጡን፣ ዳቢቱን፣ ሻኛውን ከፊታችን አስቀረቡና ‘በሉ!’ ይሉን ጀመር። አባወራው ደግሞ ‘አሞራው በሰማይ ሲያሽ ዋለን’ ከፍተው ጆሯችንን አደነቆሩት። ‹‹እንዲያው ትንሽ እንኳ ሳንጫወት?›› ሲላቸው ከመሀላችን አንደኛው ሁለቱም የፌዝ ሳቅ ስቀው፣ ‹‹ብሉና ይደርሳል፣ ምን የሚያስቸኩል ነገር ኖረና ለወሬው?›› ብለው በነገር ወጉን። ኃፍረት ቢያሽመደምደንም የመብሉ አጋጣሚ የሚታለፍ አልነበረም። ‹‹ይታይህ እንግዲህ ይኼ ዘመን? ወይ አልሠለጠነ ወይ አንደኛውን ወደኋላ አልቀረ?›› ብዬ ግሮሰሪ ስንገናኝ ምሁሩን የባሻዬ ልጅ ውሎዬን ስነግረው፣ ‹‹እናንተስ ስንት ሽማግሌ የሚያስፈልግበት ሥፍራ እያለ…›› ብሎ በእንጥልጥል ተወው። ‹‹ማለት?›› ስለው፣ ‹‹አገር ናታ በዚህ ጊዜ ሽማግሌ የሚያስፈልጋት እኮ። በአንድ በኩል አውዳሚው ጦርነት ሕዝባችንን እየፈጀና ጥሪቱን እየበላው ነው። በሌላ በኩል ምስኪኑ ሕዝብ ከሚያገኛት ላይ ግብር በአግባቡ እየከፈለ ከኑሮ ጋር ሲታገል፣ አገር እየዘረፉ ሻኛ ያወጡ ሌቦች ግን ጠያቂ ስለሌለባቸው በሕንፃ ላይ ሕንፃ፣ በቪ8 ላይ ቪ8 እየከመሩ መከራ ያሳዩናል…›› ብሎኝ፣ ‹‹ቢራ ድገመኝ!›› አለው ወደ አሳላፊው ዞሮ። ያስጠጣል!

‹‹ቆይ… ቆይ… በቀደም ዕለት ከፕላቲኒየም እስከ ብር ደረጃ ያሉ ግብር ከፋዮች በከፍተኛ ሥነ ሥርዓት ሲሸለሙ አልነበር እንዴ…›› ስለው ከት ብሎ ሳቀብኝ፡፡ ‹‹ልጅ አንበርብር፣ ክብርት ፕሬዚዳንቷም ሆኑ የገቢዎች ሚኒስትሯ ተናገሩ እኮ፡፡ እናንተን በመልካም ሥራችሁ ብንሸልማችሁም እዚህ አገር ውስጥ ሕግ ብቻ ሳይሆን፣ ፈጣሪን ጭምር የናቁ አጭበርባሪዎች አሉ ብለው በቀጥታም በተዘዋዋሪም ተናገሩ እኮ፡፡ ይልቁንስ በቀደም ዕለት አንድ ቦሌ አካባቢ የሚሠራ ወዳጄ የነገረኝን ልንገርህ፡፡ አንዱ ጥግብ ያለ ነጋዴ ነው፡፡ መንግሥት ጦርነት ውስጥ ሆኖ ከሕዝብ በሰበሰበው ገንዘብ የበርካታ ሚሊዮን ብሮች ሥራ ሰጥቶት የበለፀገ ነው፡፡ ነገር ግን ሁልጊዜ ከፋይናንስ ማኔጀሩ ጋር ይጣላል፡፡ ጠቡ ምን ቢሆን ጥሩ መሰለህ፣ ለምን ከገቢዎች ታክስ ኦዲተሮች ጋር ተመሳጥረህ ግብር አትሰውርልኝም ነው፡፡ አንተ በስንፍናህ ምክንያት በመንግሥት ታዘርፈኛለህ እያለ ጭራሽ ራሱን ፃድቅ አድርጎ መንግሥትን ዘራፊ ያደረገ የነጋዴ ሌባ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቢሊኒየር ለመሆን መከራውን ያያል፡፡ እንዲህ ዓይነቱና መሰሎቹ ብዙ ናቸው፡፡ ለአገራቸው ውድ ሕይወታቸውን በክብር የሚሰጡ አሉ፡፡ እነዚህ ደግሞ አገራቸውን አጋድመው ያርዳሉ…›› እያለ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ተንገፍግፎ ሲነግረኝ፣ በተለይ አዲስ አበባ ውስጥ የመሸጉ ዓይን አውጣ ሌቦችን ብዛት ሳስበው የአገሬ ቅስም ሰባሪዎች ነገር አንገሸገሸኝ፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት