Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ባለፈው ሳምንት ከተማችን ውስጥ አንድ ታዋቂ ሰው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው ነበር፡፡ ፈጣሪ ነፍሳቸውን በአፀደ ገነት ያሳርፈውና እኔም ከቀብር እስከ ሰልስት ቤተሰቦቹን ሳፅናና ነበር የከረምኩት፡፡ በከተማችን ውስጥ አሉ ከሚባሉ ባለፀጎች መካከልም ከቀብሩ በተጨማሪ ወጣ ገባ እያሉ ሐዘኑ ቤት ነበር የሰነበቱት፡፡ እኔም ከሄደ ከመጣው ጋር በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የሚነሱ ወሬዎች በለሆሳስ ሲነገሩ እያዳመጥኩ ወቸ ጉድ ስል ነበር፡፡ ወቸ ጉድ የሚያስብሉ ወሬዎች ደግሞ የሚገኙት በእንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ ስለሆነ፣ ከአንዱ ርዕስ ወደ ሌላው ርዕስ እየተሸጋገሩ የከተማውን ጉዳ ጉድ የሚዘከዝኩ ጉደኞችን ማዳመጤን ቀጥያለሁ፡፡

ቀዳሚው ርዕስ የዶላር ወሬ ነበር፡፡ የዶላር ወሬ ሲነሳ ደግሞ ከእጥረቱ በላይ ያን ሰሞን የባንክ ሒሳባቸው የታገደባቸውና የአባቱ ስም “ዶላር” የሆነው ግለሰብ ጦስ ለብዙዎች መትረፉ መነገር ጀመረ፡፡ ይህንን ወሬ በሹክሽክታ የሚያወራው “ውስጥ አዋቂ” መሳይ የብዙ ታዋቂ ባለሀብቶችን ስም እያነሳ፣ የጥቁር ገበያው ንግድ የሸረሪት ድር ይተነትን ጀመር፡፡ በሪል ስቴት፣ በሆቴል፣ በአስመጪነት፣ በተሽከርካሪና በሌሎችም ንግዶች የተሰማሩ ብዙዎቹ ቱባ ባለሀብቶች ሥራቸው የተመሠረተው በጥቁር ገበያ ንግድ መሆኑን ዘረዘረ፡፡ የአንድ ታዋቂ ባለሀብት ስም ጠርቶ ዋነኛው የዶላር አዘዋዋሪ እንደተያዘ አገር ጥሎ መኮብለሉን አበሰረ፡፡ የጥቁር ገበያው ንግድ ከዱባይ እስከ አዲስ አበባ፣ እንዲሁም ከሐርጌሳ እስከ ቶጎ ጫሌ እንዴት እንደተዘረጋና የብዙዎቹ ባንኮች ኃላፊዎችም ኤልሲ ሲከፍቱ ኮሚሽን ስለሚቀበሉ የጥቁር ገበያው ተሳታፊ መሆናቸውን አስረዳ፡፡ ይህንንም ጉድ የዓለም ባንክና የአይኤምኤፍ ሰዎች ለመንግሥት መንገራቸውን ሲናገር ቦታው ላይ ሆኖ የሰማ ይመስል ነበር፡፡ የጥቁር ገበያው ገመድ ውጭ ካሉ ወያኔዎች ጋር የሚገናኝ በመሆኑ፣ መንግሥትን መገልበጥ የሚያስችል አቅም እንዳለው ሲዘረዝር ያስገርም ነበር፡፡ ጎበዝ ከዋናው ጦርነት ባልተናነሰ ይኸኛው ግንባር አገር ሊያፈርስ ይችላል እኮ፡፡ 

ወደ ሁለተኛው ርዕሰ ጉዳይ ስወስዳችሁ፣ በዚያን ሰሞን የገቢዎች ሚኒስቴር ለ”ግብር ከፋዮች” እንደ አበርክቶዋቸው የሰጠው ሽልማትና ዕውቅና ሌላው አጀንዳ ነበር፡፡ ያ ሰው ይህንን ርዕስ ሲጀምር እየሳቀ ነበር፡፡ አንድ የሚያውቀው የፋይናንስ ማናጀር ድርጅታቸው በወርቅ ደረጃ ሊሸለም እንደነበረ ሲነግረው፣ የድርጅቱ ባለቤት የሽልማቱን ነገር ሲሰማ በጣም መደንገጡን አክሎለት ነበር፡፡ የተሸላሚው ድርጅት ባለቤት በዓመት በትንሹ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ግብር መክፈል ሲጠበቅበት፣ የሚከፍለው ግን አሥር ሚሊዮን ብር ያህል ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ግብር በመሰወር ወይም በማጭበርበር የተካነ ወንበዴ ስለሆነ ነው፡፡ ትሸለማለህ ተብሎ ሲነገረው የደነገጠው በሽልማት ሰበብ እጁ ላይ ካቴና የሚጠልቅለት መስሎት ነው ብሎ ሲስቅ፣ እኔ ግን ውስጤ እያነባ ነበር፡፡ እኛ ምስኪኖቹ በወር ለፍተን ከምናገኘው ደመወዝ ላይ አንድም ቀን ሳናጉረመርም ስንከፍል፣ እንዲህ ዓይነቶቹ ወረበሎች ግን ከራሱ ከገቢዎች ታክስ ኦዲተሮች ጋር እየተሞዳሞዱ አገር ይዘርፋሉ፡፡ ሰውየው ከተሸላሚዎቹ መካከል በስም እየጠራ አጭበርባሪዎች መሆናቸውን በለሆሳስ ሲናገር፣ በሁኔታው ያልተደሰቱ አፍንጫቸውን ነፍተው የሚያዳምጡት መኖራቸው ደግሞ ያስገርም ነበር፡፡

ይኼ ጉደኛ ሰውዬ ሌላ ሦስተኛ ርዕስ አመጣ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የአልጠግብ ባይ ነጋዴዎች አዲሱ ሥልት ከባለሥልጣናት ቤተሰቦች ጋር መወዳጀት ነው አለ፡፡ ለዚህም ሲባል የተለያዩ ስጦታዎችና እጅ መንሻዎች በመያዝ የወለዱ መጠየቅ፣ ክርስትና ላይ መገኘት፣ ሠርግ ላይ ከቤተሰብ በላይ ሆኖ ማዳመቅና የሌብነት ሰንሰለቱ ውስጥ ማስገባት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አሉ የሚባሉ ቁልፍ ባለሥልጣናት ናቸው የሚመረጡት፡፡ ከዚያ በወንድም፣ በእህት፣ በትዳር አጋር ቤተሰቦች ወይም በቅርብ ዘመዶች አማካይነት ዱባይ ወይም ሲሸልስ በመውሰድ ማዝናናትና ዘመናዊ መኪና ገዝቶ መስጠት ይጀመራል፡፡ የንግድ ፈቃድ በማስወጣት የሚፈለገው ዘርፍ ውስጥ በማስገባት የባንክ ብድር፣ የውጭ ምንዛሪ፣ መሬት፣ ከቀረጥ ነፃ ዕድልና የመሳሰሉትን መቀራመት ውስጥ ይገባል፡፡ እንደ ዘይት፣ ሲሚንቶና ሌሎች ምርቶችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ዘረፋ ማጧጧፍ መለመዱን ሲናገር አብሮ ያቀናበረው ይመስል ነበር፡፡ ወይ ኢትዮጵያ አገሬ ያሰኛል፡፡

ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ምስቅልቅላችን በሰፊው በየፈርጁ አንዱ ሲጣል ሌላው ሲነሳ ብዙ ነገሮች ተዳሰሱ፡፡ እኔ እዚህ ያቀረብኩት ቅንጫቢውን ነው፡፡ የሐዘኑ ቤት ወሬያችን አልፎ አልፎ የአገር ጉዳይ ይነሳበትም ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰሜን ዕዝ ሠራዊታችን ላይ በሕወሓት አመራሮች ትዕዛዝ የተፈጸመው አረመኔያዊ ጭፍጨፋ አንዱ ሰበዝ ነበር፡፡ ይህ ሁለት ዓመት የሞላው አረመኔያዊ ጭፍጨፋ ለሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቀስቀስ ምክንያት መሆኑን፣ ለዚህ አስከፊ ጦርነት ተጠያቂውም የወያኔ አመራሮች እንደሆኑና ነገር ግን አሜሪካና ቢጤዎቿ ወያኔን ለማትረፍ የሚፈጽሙት አሳፋሪ ድርጊት በሰፊው ተወራ፡፡ ኢትዮጵያውያን በዚህ ጦርነት ምክንያት የደረሰባቸው መከራ ወያኔ አመጣሽ ሆኖ፣ እነ አሜሪካ ግን ከወያኔ ጎን ተሠልፈው ትርምስ ለመፍጠር መራወጣቸው ይቅር የማይባል ነውር መሆኑ ጭምር ተወሳ፡፡ ለአገር ሲባልም ማንኛውም መስዋዕትነት መከፈል አለበት ተባለ፡፡

በዚህ የሹክሹክታ ውይይታችን ወቅት ዝም ብሎ ሲያዳምጥ የነበረ አንድ ክስትና ግርጥት ያለ ሰው፣ ‹‹ወንድሞቼ የሚባለውን ሁሉ እያዳመጥኩ ነበር፡፡ ለአገር መስዋዕትነት መክፈል አስፈላጊና የግድ መሆኑን ባምንበትም፣ ቅድም ከሰማሁት ጉድ አኳያ አገር የሚዘርፉ ሰዎች በገንዘባቸውም ሆነ በሕይወታቸው፣ ወይም በሕግ ጥላ ሥር ሆነው በእስራት ዕዳቸውን ካልከፈሉ በስተቀር መከራችን ይቀጥላል፡፡ እኔንና መሰል ምስኪኖች ለአገራችን ሕይወታችንንም ሆነ አካላችንን መስዋዕት ማድረጋችን የሚያስቆጭ ባይሆንም፣ በዚህ ዘመን ከምሰማው ነውረኝነትና ምግባረ ብልሹነት በመነሳት ሀብታሞቹ ከእነ ልጆቻቸው እንደ እኛ ሠልጥነውና ታጥቀው ካልዘመቱ በስተቀር ምንም ዋጋ የለንም፡፡ ሌባ ለሚዘርፋት አገር ልጆቼ እንደ እኔ ደማቸውን አፍስሰውና አጥንታቸውን ከስክሰው ለድህነት እንዲዳረጉ አልፈቅድም፡፡ የደሃን አፍ በዳቦ ነው ማዘጋት እየተባለ ቀልድ መቆም አለበት…›› ብሎን ተሰናብቶን ሄደ፡፡ ግንባሩ ላይ የሚታዩት የተገታተሩ ሥሮች ያስደነግጣሉ፡፡ እኔም ብደነግጥ ነው ይህንን የጻፍኩላችሁ፡፡ ልብ ብንል መልካም መሰለኝ፡፡

(ታዲዮስ ጌቱ፣ ከላፍቶ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...