Monday, January 20, 2025
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትይቅር ይባል ይሆናል እንጂ ‹‹መቼም አልረሳውም››

ይቅር ይባል ይሆናል እንጂ ‹‹መቼም አልረሳውም››

ቀን:

spot_img

በገነት ዓለሙ

የዚህ ዓመት ጥቅምት የመጨረሻ ሳምንት ከደቡብ አፍሪካዋ አስተዳደራዊ ርዕሰ ከተማ ከፕሪቶሪያ ወሬና ዜና ለመስማት ጆሯችንን ቀስረን፣ ዓይናችንን ተክለን የምንከታተልበት ጊዜ ከመሆኑ ጋር ዓምናስ፣ ካች ዓምናስ ምን ላይ ነበርን ብለን፣ እንደሚባለውም ታሪክን የኋሊት የምንቃኝበት ጊዜ ጭምር ነው፡፡ እንዲያውም የ2015 ዓ.ም. የጥቅምት ወር አራተኛ ሳምንት ዋዜማ ይሁን ወይም መግቢያ ላይ ጀምሮ፣ (ከጥቅምት 21) የ‹‹መቼም አልረሳውም›› ንቅናቄ ሲቀነቀን እየሰማን ነው፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎትን መግለጫና በዚህም ላይ የተመሠረተውን መርሐ ግብር መነሻ ምክንያትና አጋጣሚ በማድረግ ሚዲያዎችም፣ በተለይም የመንግሥት ሚዲያዎች አጀንዳውን ሲሉት እየተከታተልኩ ነው፡፡ ያሰመርኩበን ቃል (ሲሉትን) የመረጥኩት አያያዛችን/አያያዛቸው ስላላማረኝ ነው፡፡ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም፣ የመሰለ ቀን ታሪክ በሚገባ ተነግሯል ብዬ ስለማላምን ነው፡፡ ‹‹መቼም አልረሳውም››፣ ‹‹እንዴትስ ይረሳል?›› ማለትን የመሰለ ነገር በደንብና ለሁላችንም የሚመጣውን መጀመርያ ነገርየውን በደንብ ስንተርከው ነው፡፡

አዎ፣ ቢያንስ ቢያንስ፣ ሌላው ቢቀር በደረሰብን፣ አገር መከላከያ አቅም ላይ በውጤትነት በተከተለው ጉዳት ልክ እንኳን ጥቃቱ የሚረሳ አይደለም፡፡ ልርሳህ ቢሉትም አይረሳም፡፡ በውሳኔም፣ በመንግሥት ትዕዛዝም፣ በውሳኔ ሕዝብም ‹‹ይቅር ይባል›› ይሆናል እንጂ ይረሳ አይባልም፡፡ ጥቅምት 24 የሆነውና ከዚያ ጊዜ አንስቶ ባየነውና እየተገላለጠ በመጣው ልምድ መሠረት ‹‹ወረራ›› ወይም የወረራ ትርጉም ውስጣዊ ወረራ ወይም ውጫዊ ወረራ እየተባለ መስተካከል የሚያስፈልገው አይደለም እንጂ ያ ቀን የወረራ ቀን ነበር፡፡ ለዚህ ነው ጥቅምት ወር (2015 ዓ.ም.) አራተኛ ሳምንት ላይ ‹‹መቼም አልረሳውም››ን ሚዲያው/ኢቲቪው ሲያስተዋውቅና ነገሩንም ‹‹በመከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈጸመበትን ጥቃት›› ሲለው ሕመም የሚሰማኝ፡፡ ተራ ጥቃት ብቻ አይደለም፡፡ ጥቃትም በጭራሽ አይገልጸውም፡፡

ይህን የመሰለ፣ ጥቅምት 24 የደረሰብንን ዓይነት እንግዳ ነገር ከዚህ በፊትም ሆነ ሌላ ቦታ ማስታወስ ወይም ፈልጎ ማግኘት ይከብዳል፡፡ የዚያ ዓይነት እንግዳ ልምድ ፊትም የታየ ወደፊትም የሚደገም ስለመሆኑ መጠርጠር ያስቸግራል፡፡ አናሳ ነጭ ዘረኛ ገዥዎች ደቡብ አፍሪካንና ሮዴዥያን ተቆጣጥረው በነበረበት ዘመን ጥቁሮች ወታደርና ሰላይ እየሆኑ (የእንጀራ ገመድ ይዟቸው) አገልግለዋል፡፡ ለረዥም ጊዜ ቅኝ በተያዙም ሆነ ለአጭር ጊዜ በቅኝ ገዥዎች ኃይል ነፃነታቸውን ተገፈው፣ በዱር በገደል የአርበኝነት ትግል ውስጥ በነበሩ አገሮችም ዘንድ ለቅኝ ገዥዎች ባንዳነት መግባት እንግዳ ነገር አልነበረም፡፡ ፋሺስት ጣሊያን ለአምስት ዓመት በኢትዮጵያ በቆየበት ጊዜ ባንዳ ሹሞችና ወታደሮች ነበሩ፡፡ በባንዳነት ሽፋን የሚስጥር አርበኝነት ሥራ መሥራት፣ አዘናግቶና ስንቅ ዘርፎ ከባንዳነት ወደ አርበኝነት መግባት፣ በጦርነት እሳት ውስጥ አፈሙዝን ወደ ጠላት ማዞር ሁሉ በእኛም አገር ሆነ በሌሎች አገሮች ውስጥ ታይቷል፡፡

በአንድ ሉዓላዊ አገር ውስጥ ዋና ገዥ ሆኖ ለረዥም ጊዜ የቆየ፣ በስተኋላም ዋና ገዥነቱ ጥቂት ከመቀነሱ በስተቀር በብዙ ሥፍራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መረብ የነበረው፣ በክልል ላይም የተደላደለ ገዥነት ያለው ቡድን፣ በገዛ አገሩ የፀጥታና የመከላከያ አካላት ውስጥ ሚስጥራዊ ከዳተኞችን ከፌዴራል ማዕከል እስከ ክልል ማዕከል ድረስ አዘጋጅቶና አካባቢያዊ ፖሊስንና ልዩ ኃይልን የቡድናዊ ፍላጎቱ ሎሌዎች አድርጎ፣ ክፉ ጥርጣሬ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ በገዛ አገሩ ወረራ ሲያካሂድ ማየት ግን ለኢትዮጵያም ለዓለምም እንግዳ ነገር ነው፣ ወይም ይመስኛል፡፡ የተወሰነ የዕዝ ማዕከልን በፈጣንና በሚስጥራዊ እንቅስቃሴ ቆርጦና አደንዝዞ ማዕከላዊ ሥልጣንን መቆጣጠር፣ የመንግሥት ግልበጣ የተለመደ ባህርይ ነውና አያስገርምም፡፡ ሕወሓትና ጽንፈኞቹ የፈጸሙት ግን ከዚህ እጅግ የከፋ ነው፡፡ በሚገዙት ሕዝብ ዘንድ በበጎ ሕዝባዊ ሥራው የተከበረና የተወደደ የመከላከያ ዕዝ ላይ ጨካኝ የበቀል ጭፍጨፋ ፈጽሞ በተዘረፈ መሣሪያ የአገሪቱን ቀሪ የታጠቀ ኃይል ድባቅ መትቶ አገሪቱን ራሷን ‹‹መገልበጥ›› ግን እንግዳ ነገር ነው፡፡ እንግዳ የሆነውም ይኼው ተግባር ነው፡፡

የውስጥ ወረራው በመከረኛ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሸፈ፡፡ ይህንን የውስጥ ወረራ ማክሸፋችንን ሳይሆን፣ ወይም በቀጥታ ወረራውን ማክሸፋችንን ሳይሆን፣ ወረራውን ለማክሸፍ የተገለገልንበትን ከጦርነት ሕግና ከሰብዓዊነት፣ ከዓለም አቀፋዊነትም ሕግ ያልወጣ ቅንጅትና ትብብር ግን ዛሬም ሰበብና መቃወሚያ አድርገው የአሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት የሚመራው ‹‹የዓለም ሥርዓት›› ይወጋናል፣ ውጋት ሆኖብናል፡፡ ሌላው ቀርቶ የሰላም ውይይቱ አንዱ ‹‹ቁምነገር›› አድርጎ ይጮኸዋል፡፡

የጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የውስጥ ወረራ ከከሸፈ በኋላ ወራሪዎቹ ተደምስሰውና መቀሌን ለቀው ተሳዳጅ በሆኑበት ጊዜ፣ የበቀሉበትን ሕዝብ (ከዚያም በላይ የእኛ ነው ብቻ ሳይሆን እኛ ነን የሚሉትን ሕዝብ) የባንክ ገንዘብ፣ መድኃኒትና ሌሎች ስንቆች ከመዝረፍ በላይ በአሥር ሺሕ የሚቆጠር እስረኛ ከተማው ላይ በትነው ሕዝብ በወሮበላ ቁም ስቅሉን እንዲያይ አደረጉ፡፡ በዚህ አማካይነትም የወሮበላ፣ የዱርዬና የወመኔ ፖለቲካቸውን አጋለጡ፡፡ እነሱ የሕዝብ ሀብትና ጥሪትን የጦርነት መደገሻ አድርገው ዕጦትና ችግር በተባባሰበት ሕዝብ ላይ እንደገና ወሮበላ ረጭተው፣ ለፈጠሩት ሥርዓት አልባነት በጊዜያዊነት የተቋቋመን አስተዳደር ተወቃሽ አደረጉ፣ ሌላው የዱርዬ ዱርዬነት፡፡

ሌላ ዱርዬነት፣ ሌላ ባንዳነትም ነበር፡፡ የጎረቤት አገሮችን በገዛ አገር ላይ ወረራ እንዲያካሂዱና ለእርስ በርስ ፍጅት አብሲት የሚሆኑ ጭፍጨፋዎችን እንዲያጎበጉቡ አማካሪና ድልድይ ሆነው አገለገሉ፡፡ እናትን ገበያ አውጥቶ ከማስማማት የከፋ የክህደት ተግባር፣ ሌላ እንግዳ የሆነ ባንዳነት ነው፡፡ ‹‹ይህ ድርጊታችሁ ቢሳካ ምን ጥቅም ታገኛላችሁ?›› ተብለው ቢጠየቁ ምን መልስ ይሰጣሉ? ከእርስ በርስ ፍጅትና መበታተን ውስጥ ትግራይን እንደ ነበረች እናገኛትና ሥልጣን ላይ እንወጣለን ብለው ሳይሆን ልባቸውንም፣ ምላሳቸውንም የሚመራው የበቀል እሳት ነው፡፡ ኢትዮጵያን እኛ ብቻ ካልገዛናት፣ ግጠን ካልበላናት፣ ምርኮ ካልያዝናት እንበታትናታለን፣ እናፈራርሳታለን፣ ለማፈራረስም ገሃነም ድረስ ለመሄድ እንፈጠማለን ያሉ አፍራሾችና ጥፋቶች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያም ትግራይም እንዳይሆኑ ሆነው ሲቃጠሉና ሲጋዩ በማየት እሰይ አንጀቴ ቅቤ ጠጣ የሚሉ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ፣ ይበልጥ ጉዳት የደረሰበት የትግራይን ሕዝብ ጨምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬ ግብግብ የገጠመው ከዚህ ዓይነት ጉግማንጉግ በቀል ጋር ነው፡፡

እነዚህ ጉግማንጉጎችን ቡድን ከጥቃት በላይ የጎረቤት አገር ወረራና የሰላም በጥባጭነት፣ አማካሪና አቀናባሪ እስከ መሆን ድረስ በበቀል የሰከረ ክህደት እየፈጸሙ ነው፡፡ የወረራው መክሸፍና በየዓመቱ፣ ልክ በዓመቱ ያስተናገድነው አዲስ አበባ ገባሁ ብሎ ያስፈራራ ‹‹ወረራ›› ቢከሽፍም፣ ኢትዮጵያን ወጥሯት የቆየው የጥቃት አማሽነት በቀልም፣ ባለፈው ዓመት በነሐሴ ላይ እንደገና ለሦስተኛ ጊዜ የተለኮሰው ጦርነት በስኬት ቢመከትም፣ ጥቃት አድራሽነቱን ግን ፕሪቶሪያ ድረስ ይዘው መሄድ የሚያስችል አቅም፣ ደጋፊን አይዞህ ባይ አላጡም፡፡

ይህ ቡድን ኢትዮጵያን ካደ፣ ወረረ ማለት ሁሉንም እውነት ብቻውን አይናገርም፡፡ ‹‹ውስጥ አዋቂ›› ሆነው ከሌሎች ጎረቤቶችን ጋር በሰላም አብሮ መኖራችን ላይ የድለላና የአማካሪነት ሥራ ሠርተውብናል፡፡ ሱዳን ከኢትዮጵያ ወዳጅነት ያፈነገጠችው፣ ድንበር አልፋ ብዙ ንብረት አውድማ ጦርነት የሚጋብዝ መሬት መያዝ ድረስ የተዳፈረችው፣ በዚህ ቡድን ጠላትነትና ጠንቀኝነት ምክንያት ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ብቻውን በህዳሴው ግድብ አማካይነት ጭምር ጠላት ይጠራብናል፣ ክፋት ይደግስብናል፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገር ሲቀፈቀፍና ሲደገስ ከሱዳን ጋር ሠልፍ የምትገባው ግብፅ ብቻ አይደለችም፡፡ የግብፅ ነገር የአገራችን ሰው እንደሚለው፣ ‹‹ጠላትማ ምንጊዜም ጠላት ነው›› ብቻ አይደለም፡፡ ግብፅ የኢትዮጵያ ልማት ለህልውናዬ አደጋ ነው ብላ ፖሊሲ የቀረፀችና የተፈጸመች አገር ናት፡፡ የኢትዮጵያን መጠንከር ብሔራዊ ሥጋት አድርጋ የምትቆጥር፣ ከዚህ ቀደምም ለምሳሌ የኤርትራን ትግል የኢትዮጵያ ማዳከሚያ አድርጋ የተጠቀመች ነች፡፡ ይህን ጥልፍልፎሽ ወያኔና ግብፅ ‹‹ጆይንት ቬንቸር›› አድርገው ይሠሩበታል፡፡ ከግብፅም በተጨማሪ ክፋቱና ሴራው፣ እንዲሁም ‹‹የጋራ ትብብሩ›› ከወዲህም ከወዲያ፣ ከቅርብም ከሩቅ ብዙ እጅ የሚገባበት ውስብስብ የጎራዎች ጦርነት ወደ መሆን ያደገ ነው፡፡ እዚያው ‹‹ግብፅ›› ውስጥ እንኳን ብንወስን የያዝነው ወር ኖቬምበር መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡ የዚህ የኖቬምበር ወር ሁለተኛና ሦስተኛ ሳምንት (ከ6 እስከ 18 ያለው ጊዜ) ሻርም አልሼክ (ግብፅ) የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ የሚካሄድ መሆኑን ከወዲሁ ማወቅና እንደ ቆቅ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡

ሕወሓቶች የሚለፉትና የሚረባረቡት የጎረቤት ጠላት በኢትዮጵያ ላይ በማማከር፣ በማሰማራትና በማሰባሰብ ላይ ብቻ አይደለም፡፡ ይበልጥ እንደሚታወቀው የምዕራቡን ዓለም ከኢትዮጵያ ለማቆራረጥ ብዙ ሠርተዋል፣ ብዙ ርቀትም ተጉዘዋል፡፡ ሐሳዊ የመረጃ ሞገድ የማሠራጨቱና የማካሄዱ ተግባር የሚዲያው ብቻ አይደለም፡፡ የዩኒቨርሲቲዎችን፣ የየቲንክ ታንኮችን ‹‹ቅጥር›› ምሁራን ‹‹ጠበቃ›› አቁመዋል፡፡ ከእነዚህም በላይና በተጨማሪ፣ ከእሱም ጋር አብረው ያበሩና በኢትዮጵያ ላይ ያሴሩ፣ ነገር ግን ከመንግሥታቱ ድርጅት መርህ፣ ሥርዓትና ሕግ ውጪ የሆኑ ቡድድኖችም ኢትዮጵያ ላይ ተባብረዋል፡፡ በዚህ ሴራ፣ በዚህ ‹‹የማርያም ጠላት›› ዓይነት ርብርብ ውስጥ እነ ፔካሃቪስቶን (Pekka Haavisto)፣ እነ ቦሬልን የመሰሉ ለጉድ የተፈጠሩ የሚባሉ ‹‹ግለሰብ›› ጉግማንጉጎችም ዓይተናል፡፡ ለምሳሌ መጀመርያ የተጠቀሰው የፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ ሆኖ የሥራ ሰው ነው፡፡ በድብቅ፣ በሚስጥር፣ ማንም ሰው ሳይሰማ ማለትም ‹‹In Closed Door Talks›› ‹‹የአንድ ብሔረሰብ ሕዝብ ለመቶ ዓመት ጠራርጎ ማጥፋት›› ዕቅዳቸው እንደሆነ ነግረውኛል ብሎ፣ በአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ መግለጫው የ‹‹መሰከረ›› ሰው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ‹‹ምስክርነት›› የሚሰጥን ሰው ሌላው ቢቀር መቼ ነው እንዲህ ያሉህ? አንተ ይህን ለመጀመርያ ጊዜ የተናገርከው መቼ ነው? በወቅቱ ይህን ያሉህን ነገር የያዝክበት ‹‹Contemporaneous Notes›› አለህ ወይ? ብሎ እንኳን የጠየቀው የለም፡፡ ይህ የሰኔ 8 ቀን 2013 ዓ.ም. የሰውየው ወራዳ መግለጫ (የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ሰኔ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. መልስ ሰጥቶበታል) አዝማችም፣ አይዞህ ባይም፣ ‹‹እንዲህም ይባላል እኮ›› ብሎ መካሪም ሆኖ ተጠናክሮ የቀጠለው የዘር ማጥፋት ወንጀል/የጄኖሳይድ ‹‹ክስ››፣ ዛሬም በሰላም ስምምነት ንግግሩ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ የውስጥ ወረራ ወንጀል የፈጸመው የወንበዴው፣ የሽፍታውና በይፋና በሕግም አሸባሪ ተብሎ የተሰየመው ቡድን (በተለይም በጦር ሜዳው መስክና ዘርፍ ሸንፈት ሲያጋጥምና አልቀና ሲል) ዋነኛም ተለዋጭም መሣሪያ ነው፡፡

ጄኖሳይድ በጣም ከፍተኛ ወንጀል ነው፡፡ ያንኑ ያህልም፣ ምናልባትም ከራሱ ከጄኖሳይድ ከፍተኛነት ክብደትና ብርቱነት በላይ ጄኖሳይድን ለማስረዳት እጅግ በጣም ከባድ ነው፡፡ ዕልቂትን፣ ጭፍጨፋን ከማሳየትና ከማስረዳት፣ እንዲሁም ከማረጋገጥ በላይ ‹‹ሆን ብሎ የማጥፋትን›› ሐሳብና ፍላጎት ማሳየት፣ ማስረዳትና ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ያለ ነገር በፍርድ ቤት ለማስረዳት ደግሞ እንደ ፊንላንዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያለ ሰው ‹‹ወሬ››፣ ‹‹አሉባልታ›› አይጠቅምም፡፡ ይህ ወሬ እንኳንስ ረቺ ማስረጃ ተራ ወሬም መሆን ባልበቃ ነበር፡፡ ታዲያ ይህን የመሰለ ‹‹ክስ››፣ ስሞታና አቤቱታ ለምን የሕወሓት የየዓለም አደባባዩ መደበኛ ሥራ ሆነ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ድርጊት ከፍ ብሎም እንደገለጽኩት ጥቃት ተብሎ የሚታለፍ አይደለም፣ ወረራ ነው፡፡ ብዙ ያልተነገረለት እውነቱ ሁሉ ያልተነገረለት ወረራ ነው፡፡ ከዚህ ወረራ እንደተካሄደ፣ ከክህደቱ ከፍጅቱ እየተተኮሰ ያመለጠው የሰሜን ዕዝ ተራፊዎች ከቀረው የኢትዮጵያ ክፍል በደረሱለት የኢትዮጵያ ኃይሎችና በኤርትራ ታግዘው ለደረሰባቸው ጅምላ ጥቃት ጅምላ በቀል በመውሰድ በቀል ሳይሰክሩና ሳያብዱ፣ በ15 ቀናት ውስጥ በድል መቀሌን ያዙ ተቆጣጠሩ፡፡ ሕወሓቶች ግን አሁንስ ይብቃ የትግራይ ሕዝብም ከመከራ ይተንፍስ አላሉም፡፡ ብዙ ሺሕ ደረቅ ወንጀለኞችን ከወህኒ ለቀቁ፡፡ ከሞላ ጎደል የራሳቸው ካድሬዎች የተቆጣጠሩትን የጊዜያዊ አስተዳደር መዋቅር ማሻጠሪያ በማድረግ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ ወታደራዊ የደንብ ልብስ የለበሱ ሸሮችን በመሥራት ጭምር በሰላም ሠርቶ መግባት አቃተ፡፡ የትግራይን ሕዝብ ብሶት ጉስቁልና እያበረከቱ የሕዝብ ቁጣ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ላይ እንዲፈላ እያደረጉ፣ የትግራይን ሕዝብ መከራ እየቸረቸሩ ቀጣፊ የፖለቲካ ትርፍ ነገዱ፡፡ በፈለጉትም መሠረት የበቀል ቁጣን በሸር አፍልተው የመከላከያ ሠራዊቱን ሆነ ብለው ከሕዝብ ጋር ፊት ለፊት እንዲገጥም፣ እንዲጋጭ ፈለጉ፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱም ከተጠመደለት ሴራና ሕዝብን ከመፍጀት እየሸሸ ከትግራይ ወጣ፡፡

በዚህ አላበቃም፣ በጦርነቱ ቀጥለው ከትግራይ ውጪ ጦርነቱን አስፋፉት፣ ወዘተ… የአፋርና የአማራ ሕዝብ ከኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ጋር ሆኖ ቁጭት በቁጭት ነዶ ወደ ትግራይ በመግባት የትየለሌ የግፍ ብቀላ እንዲፈጽም፣ ሕዝብ ከሕዝብ እስከ መጨረሻው እንዲቆራረጥላቸው አባበሉ፡፡ ማባበያቸውን ለጦርነታቸው ማገዶ ያደረጉትን የትግራይ ሰውና ታዳጊ በንፁኃን የአፋርና የአማራ ሲቪሎችና ሲቪል ተቋማት ላይ በነውረኛ ስድብና ማዋረድ የቀለመ ኢሰብዓዊና ጨካኝ አረመኔያዊ ጥቃት እንዲፈጸምና ቤተ እምነቶችን እንዲደፍር በማድረጋቸው ጭምር ነው፡፡ ሕወሓቶች ወረራው ከተመከተ በኋላ የተረፈው ተርፎ ወደ ትግራይ ተመልሶ የገባውን ትራፊ ኃይል እንኳን ዕረፍት አልሰጠው ብለው እንደገና እየተወረወሩ አፋርና አማራ ላይ አስከፊና አረመኔያዊ ጥፋት በመፈጸም፣ በቀል የገፋፋው ጅምላ ጥቃትና ጭፍጨፋ በትግራይ ሕዝብ ላይ እንዲመጣ መለማመኛ ያደረጉ ጉግማንጉጎች ናቸው፡፡

ለምን? ከጅምሩ እስካሁን ድረስ ‹‹በትግራይ ሕዝብ ላይ ዘር የማጥፋት ግፍ ተፈጸመ›› የሚል ውንጀላና ዋይታ ሙጭጭ ብለው ያዙ? ለምንስ በትግራይ ሕዝብ ላይ እንደፈለጉት ዓይነት የለመኑት፣ የገፋፉትና ያባበሉት ዓይነት ግፍ እንዲፈጸም ይፈልጋሉ ለምን? ለምን?

በተመድና ተመድ ተቋቁሞ በሚመራው ዓለም አቀፋዊ ሥርዓተ ማዕቀፍ ውስጥ፣ በተለይም እንደ ፖለቲካው ቁማር መጫወቻ በሆነው የዘመኑ አሠራር ውስጥ፣ ቅኝ ተገዛሁ ያለና አዎ ተገዝቷል ያሉት ሕዝብ ከቅኝ ገዥው የመለየት መብት የታወቀ ሆኗል፡፡ እነሱ እንደፈለጉትና የፈለጉትን ያህል፡፡ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ የተካሄደበት ሕዝብም ከጭፍጨፋ አደጋ መገላገልን ከመነጠል ጋር አያይዞ ሲንቀሳቀስ ጥያቄውን ተገቢ አድርገው የመደገፍና ‹‹በሕግ አግባብ›› የማስተናገድ፣ አለዚያም በአንድ አገር የውስጥ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ የመግባት ዝንባሌ አለ፡፡ ሕወሓቶች ይህንን ያውቃሉ፡፡ ባያውቁም ይህንን የሚያውቁና የማያስፈጽሙ በዘረፋው ጊዜ፣ አገርን ምርኮ ይዞ ግጠው ይበሉ በነበረበት ጊዜ የከፈሏቸው ‹‹ባለሙያዎች›› አሉ፡፡ ‹‹ዘ ሪስፖንሲቢሊቲ ቱ ፕሮቴክት›› የሚባል ዘፈን ሰምታችሁ ከሆነ ይህ በኢትዮጵያ ላይ እየተመረጠ የሚዘፈነው በዚህ ምክንያት ነው፡፡

በዚህ ምክንያት ነው ከዚህ በፊትም ሕወሓቶች በዚህም በዚያ ብለው የትግራይን ሕዝብ በማኅበረሰብ ጥላቻና በበቀል አውረው የእርስ በርስ ፍጅት ውስጥ እንዲገባ፣ ደመኛ ሒሳብ ይወራረድበታል የተባለ ሕዝብን በግፍ አንጨርጭረው ግዙፍ የጅምላ ጭፍጨፋ በትግራይ ሕዝብ ላይ እንዲወርድ ግብዣ ሲያደርጉ የኖሩት፡፡ የኢትዮጵያ ቀሪ ሕዝቦች የትግራይ ሕዝብ እንደገና አብሮ እንዳይኗኗር ለማድረግ በጨካኝ ሸሮች ሸለቆ የመፍጠር ሥራ የሠሩት፡፡ በዚህም አማካይነት በየትኛውም ዘግናኝ መጨራረስ የኢትዮጵያን ሕዝቦች መጨራረስና መፋጀት ሲደግሱ የኖሩት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በትግራይ ሕዝብ ላይ እንዲፈጸም የፈለጉት ጅምላ ጭፍጨፋ አልሳካ ሲላቸውም፣ ‹‹ዘር የማጥፋት ግፍ በትግራይነት ላይ ተፈጸመ›› የሚል በሐሳዊ ወሬ ላይ የተቀናበረ ልብ ወለድ የሙጥኝ ይዘው የሚጮሁት፣ እንደ ፊንላንዳዊ ያለ የኢትዮጵያን የዘር ማጥፋት ‹‹ብሉ ፕሪንት›› ይዞ የሚዞርና ይዞ የሚኖር ሰው ‹‹ምስክርነት›› የሚጠሩት ለዚሁ የበቀል ዓላማ ነው፡፡ ኢትዮጵያ፣ ትግራይን የሚጨምረው ኢትዮጵያና ሕዝቡ የዚህን ጉዳይ ውሸትነትና፣ ሕጋዊነቱንም በመንግሥታቱ ድርጅት ቻርተር ማዕቀፍ ውስጥ መታገልና መዋጋት አለባቸው፡፡

በወራዳነቱ ወደር የሌለውንና በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አዕምሮ ውስጥ ተመዝግቦ የሚኖረውን ይህንን ጥቅምት 24ን ሰንዘክር፣ ‹‹መቼም አልረሳውም›› ስንል አብሮ የሚያንገበግቡኝና የሚከነክኑኝ ሌሎች ነገሮችም አሉ፡፡ አንደኛው የፌዴራል መንግሥት ዛሬ አይደለም፣ ያኔም ቢሆን በወሳኝ ደረጃ ወረራውን ከተከላከለ በኋላ ትንፋሹ ከተመለሰ ወዲህ ጀምሮ የሕወሓትን ግፈኛ የጦርነት አጀማመር መረጃዎችን በምሥልና በቃለ መጠይቅ እያደራጀ ለኢትዮጵያውያን ማርዳትን፣ ለዓለም ማጋለጥን በአግባቡ ሊሠራበት ለምን እንዳልቻለ ዛሬም ያመኛል፣ ይከነክነኛል፡፡ ሌላው የኤርትራ ድጋፍና ዕርዳታ ጉዳይ ነው፡፡ የሕወሓትን የውስጥ ወረራ በማጋለጥ፣ ዘርግፎ በመንገር ሒደት ውስጥ የኤርትራን ሠራዊት መግባትና አገባብም በኩራትና ከወረታና ከምሥጋና ጋር ጭምር መግለጽ ሲችል፣ መደበቁ ሕወሓቶች ለጊዜውም ቢሆን የግፍ ገመናቸውን በተጠቂነት ዋይታ እንዲጋርዱና እንዲዋሹ፣ ዛሬም ቢሆን ጠንቁ ያልተነቀለ ሰበብ እየፈጠሩ መከራከሪያ እንዲያገኙ፣ ‹‹ኤርትራ ሠራዊት ከኢትዮጵያ ይውጣ›› እንዲሉ አግዘዋቸዋል፡፡    

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

መንግሥት ገቢ ከመሰብሰብ ባሻገር ለሕዝብ ኑሮ ትኩረት ይስጥ!

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማደግ ያለበት በተገኘው ቀዳዳ ሁሉ ከሚሰበሰብ ታክስ...

የኢትዮጵያን ትንሳዔ ለማብሰርና ለመከወን ምን እናድርግ?

በጌታነህ አማረ ኢትዮጵያ ማለት ታላቅ አገር ቀደምት የሰው ዘር መገኛና...

የምድራችን (የሰው ልጆች) ተማፅኖ — አረንጓዴ ፖለቲካ!

(ወጥመዶችና ማምለጫችን) በታደሰ ሻንቆ የወጥመዶች ዓለም በአፍሪካ ቀንድ አገሮች ዘንድ ያሉ...