Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበምዕራብ ወለጋ የወረዳ አመራሮችና ነዋሪዎች በ‹‹ኦነግ ሸኔ›› ጥቃትና ሥጋት ሳቢያ እየሸሹ መሆኑ...

በምዕራብ ወለጋ የወረዳ አመራሮችና ነዋሪዎች በ‹‹ኦነግ ሸኔ›› ጥቃትና ሥጋት ሳቢያ እየሸሹ መሆኑ ተገለጸ

ቀን:

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው ‹‹ኦነግ ሸኔ›› ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ፣ በምዕራብ ወለጋ ዞን ውስጥ በሚገኙ ወረዳዎች ላይ በከፈተው ጥቃትና ጥቃቱን ተከትሎ በተፈጠረው ሥጋት ሳቢያ፣ ነዋሪዎችና አመራሮች ጥቃት ወደሌለባቸው ወረዳዎች እየሸሹ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ከአራት ወራት በፊት ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ጭፍጨፋ የተፈጸመበት በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ የቶሌ ቀበሌ ነዋሪዎችና አመራሮች፣ ታጣቂዎች በአጎራባች አካባቢዎች ላይ ጥቃት በመክፈታቸው ሳቢያ ወደ ምሥራቅ ወለጋ መሸሻቸውን ነዋሪዎች፣ እንዲሁም የቀበሌና የወረዳ አመራሮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የቀበሌው ነዋሪ፣ የቶሌ ቀበሌ ነዋሪዎች ከአካባቢው መውጣት የጀመሩት ሐሙስ ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ሌሊት መሆኑን ገልጸው፣ በአካባቢ የሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች ከቀበሌው እየወጡ በመሆኑ እነሱም እንዲወጡ እንደተነገራቸው አስረድተዋል፡፡

የቀበሌው ነዋሪዎች ወደ ምሥራቅ ወለጋ ዞን በመሻገር አርጆ ጉደታ ላይ እንደሠፈሩና የፌዴራል ፖሊሶችም ከቀበሌው ነዋሪዎች ጋር አብረው እንደሚገኙም ገልጸው፣ ይሁንና ነዋሪዎቹ መጠለያ ባለማግኘታቸው መንገድ ላይ እንደሚገኙ አክለዋል፡፡

የፀጥታ ኃይሎች ከአካባቢው ሊወጡ መሆኑን ተከትሎ ከነዋሪዎቹ ጋር አብረው ከቀበሌው እንደወጡ ለሪፖርተር የገለጹት የቶሌ ቀበሌ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አህመድ ዘይኑ፣ ‹‹ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ላይ የተወሰኑ ሰዎችን ይዤ ወጥቻለው፣ የተወሰኑት ደግሞ እዚያው ቀርተው በጭንቅ ላይ ነው ያሉት፤›› ብለዋል፡፡  

የቀበሌው አመራሮች የፀጥታ ኃይሎች ከመውጣታቸው በፊት ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ በየቤቱ እየዞሩ ነዋሪዎችን እየቀሰቀሱ እንዲሸሹ እንዳደረጉ ምክትል ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ አህመድ ገለጻ የቀበሌው ነዋሪዎች ከመኖሪያቸው የሸሹት የ‹‹ኦነግ ሸኔ›› ታጣቂዎች ከሳምንቱ አጋማሽ ጀምሮ አጎራባች የሆነውን ቀበሌ ጆግርን ተቆጣጥረው ቤቶችን እያቃጠሉ በመሆኑና ወደ ቶሌ ቀበሌ ይመጣሉ የሚል ሥጋት በመፈጠሩ ነው፡፡

አርሶ አደር የሆኑ የቶሌ ቀበሌ ነዋሪዎች 10 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ የተዘራ የበቆሎ ምርታቸውን ጨምሮ ቤት ንብረታቸውን ጥለው እንደሸሹ ምክትል ሊቀመንበሩ አስረድተዋል፡፡ የቀበሌዋ ነዋሪዎች ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ጭፍጨፋ የተካሄደበትን ጊዜ ጨምሮ ከመኖሪያቸው ሲሸሹ የአሁኑ ለሦስተኛ ጊዜ መሆኑን አክለዋል፡፡

‹‹በእኛ ወረዳ 32 ቀበሌዎች አሉ፡፡ ከቀበሌዎቹ ውስጥ እያለቅንም ቢሆን የቀረው የእኛና አጆር ቀበሌ ነበር፣ ማክሰኞ ዕለት ጆግር ቀበሌ ገብተው እያቃጠሉ ነው ያሉት፣ እኛ ደግሞ ፀጥታ ኃይሉ ሲወጣ አብረን ወጥተናል፤›› ሲሉ በቀበሌውና በአጎራባች አካባቢዎች ያለውን ሁኔታ ገልጸዋል፡፡

በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ቡላ ደመራ፣ በቶሌ ቀበሌ የፀጥታ ኃይሎች ሲወጡ ነዋሪዎችም እንደተከተሉ ተናግረው፣ በቀበሌው ስላለው ሁኔታ ተመሳሳይ ገለጻ ሰጥተዋል፡፡ እንደ ዋና አስተዳዳሪው በቀበሌዋ የሚገኙ የፌዴራል ፖሊሶች ከቀበሌው የወጡት በአካባቢው ይገኙ የነበሩት የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይሎች ቀድመው ወደ ሌላ አካባቢ ከሠፈሩ በኋላ ነው፡፡

በጊምቢ ወረዳ ሥር 32 ቀበሌዎች እንደሚገኙ የገለጹት የወረዳው አስተዳዳሪ፣ ‹‹ሁሉም ቀበሌዎች በእሱ እጅ ውስጥ ናቸው ማለት ይቻላል፤›› በማለት ወረዳው ያለበትን ሁኔታ አስረድተዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ውስጥ የ‹‹ኦነግ ሸኔ›› ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃትና በዚሁ ምክንያት በተፈጠረው ሥጋት ሳቢያ በምሥራቅ ወለጋ ዞን ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች አመራሮች፣ ሚሊሻና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ያሉበትን ወረዳ ለቀው ወደ ሌሎች አካባቢዎች እየሄዱ አቶ ቡላ ገልጸዋል፡፡

በምሥራቅ ወለጋ ዞን ውስጥ ከሚገኙት 21 ወረዳዎች ውስጥ የ11 ወረዳዎችና አንድ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ወረዳቸውን ለቀው መውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደ ዋና አስተዳዳሪ ገለጻ የሀሩና ኦማ ወረዳዎች አመራሮች የዞኑ ዋና ከተማ ጊምቢ ወደምትገኝበት ጊምቢ ወረዳ ገብተዋል፡፡ የቢላና ሀጂ ተቆርሳ ወረዳ አመራሮች ወደ ሁሊሶ ወረዳ ሲሄዱ የቂልጡ ካራ፣ ለታ ሲቡ፣ ዱርሾና ባቦ ወረዳ አመራሮች ወደ ነጆ ወረዳ መግባታቸውን አስረድተዋል፡፡

‹‹በሙሉ ካቢኔያቸው፣ ሠራዊታቸው፣ ፖሊሳቸውና ሚኒሻቸውም ወደ ጊምቢ ነው የመጡት፤›› ሲሉ የሀሩና ኦማ ወረዳዎች አመራሮችን ሁኔታ ገልጸዋል፡፡

የቢኒና ቆንዳላ ወረዳ አመራሮች ደግሞ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ እንደገቡ ጠቅሰዋል፡፡ የመንዲ ወረዳና የመነ ሲቡ ከተማ አስተዳደር አመራሮች በበኩላቸው ተበታትነው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ጃርሶ፣ ባቦ፣ ኦማና ሀሩ ወረዳዎች ‹‹ኦነግ ሸኔ›› ከሰሞኑ በከፈተው ጥቃት በታጣቂዎች ሥር የገቡ ወረዳዎች እንደሆኑ የሚገልጹት አቶ ቡላ፣ ከቀሩት ወረዳዎች ውስጥ የተወሰኑት በታጣቂዎች እጅ ከገቡ ወራት መቆጠሩን ገልጸዋል፡፡ ቆንዳላና በጊ ወረዳዎችን ደግሞ ከፈረሱ ቆይተዋል ብለዋል፡፡

ዋና አስተዳዳሪው ታጣቂቹ፣ ‹‹ነጆ ወረዳ ላይ ከፍተኛ ጥቃት ከፍተው ነበር፤›› ያሉ ሲሆን፣ መንግሥት በወሰደው ዕርምጃ ከደረሰባቸው ኪሳራ በኋላ ወደ ጊምቢ ወረዳ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የደወለላቸው የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰለሞን ታምሩ የስልክ ጥሪውን አልመለሱም፡፡ ምክትል አስተዳዳሪው አቶ ምትኩ ዋጋሪና የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደበላ ወላና ‹‹መልሳችሁ ደውሉ፤›› የሚል ምላሽ ከሰጡ በኋላ በድጋሚ ለተደረጉት የስልክ ጥሪዎች ምላሽ አልሰጡም፡፡

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ በበኩላቸው፣ መረጃ የሚሰጡት የዞኑ አስተዳደር መረጃ ከሰጠ በኋላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...