Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበፒያሳና መርካቶ አካባቢዎች ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ከመደብሮች ወርቅ ተሰብስቦ ባለቤቶቹ ታሠሩ

በፒያሳና መርካቶ አካባቢዎች ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ከመደብሮች ወርቅ ተሰብስቦ ባለቤቶቹ ታሠሩ

ቀን:

  • ብሔራዊ ባንክ ወርቆቹ በሕገወጥነት ተይዘው የተሰበሰቡ ናቸው ብሏል

በአዲስ አበባ ከተማ ፒያሳና መርካቶ አከባቢዎች የሚገኙ የተመረጡ የወርቅ መሸጫ መደብሮች ውስጥ የሚገኙ የወርቅ ጌጣ ጌጦች በፀጥታ ኃይሎች ተሰብሰቦ ግለሰቦች ታሠሩ፡፡

ሰኞ ጥቅምት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. ከወርቅ መሸጫ መደብሮቹ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች በሳምንቱ አጋማሽ፣ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበው ለተጨማሪ ምርመራ የጊዜ ቀጠሮ እንደተጠየቀባቸው ታውቋል፡፡

ስለወርቅ መደብሮቹ ጥያቄ የቀረበላቸው የፌደራል ፖሊስ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጄይላን አብዲ፣ ጉዳዩ በፍርድ ቤት የተያዘ በመሆኑ ዝርዝር መረጃዎችን መስጠት እንደማይችሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ዋና ኢኮኖሚስት አቶ ፍቃዱ ድጋፌ በበኩላቸው፣ ከፌደራል ፖሊስ ጋር በቅንጅት በተሠራ ሥራ ‹‹በሕገ ወጥነት›› የተያዘ ‹‹ብዛት ያለው›› ወርቅ ተሰብስቦ ወደ ባንኩ መምጣቱን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ወርቁ የተሰበሰበበትን ቦታ ‹‹ይኼ ነው ብለው›› መናገር እንደማይችሉ ገልጸው፣ ‹‹ከድሬዳዋ ሁሉ የመጣ አለ፣ ከመርካቶም ከሌላ ቦታም [ተሰብስቧል] ብለዋል፡፡

ሪፖርተር ፒያሳ ወርቅ መሸጫ መድበሮች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ባደረገው ቅኝት 26 መደብሮች ተዘግተው ተመልክቷል፡፡

በመደብሮቹ ውስጥ የሚገኘው ወርቅ ሰኞ ጥቅምት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. በተሰበሰበበት ጊዜ በታዛቢነት የተገኙ ግለሰቦች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በመደብሮቹ ውስጥ የሚገኘውን ወርቅ የሰበሰቡት የታጠቁ የፀጥታ ኃይሎች፣ የደንብ ልብስ የለበሱና ሲቪል የለበሱ ግለሰቦች ናቸው፡፡

ወርቅ የመሰብሰብና ባለቤቶቹን ወደ ፖሊስ ጣቢያ የመውሰድ ተግባሩ የተፈጸመው በተለዩ የወርቅ መሸጫ ሱቆች ላይ መሆኑ የተሰማ ሲሆን፣ ወርቃቸው ያልተሰበሰበ መደብሮች በመደበኛ ሥራቸው ላይ ተሠማርተው ከደንበኞች ጋር ሲገበያዩ ተስተውሏል፡፡ ወርቃቸው የተሰበሰበ አብዛኛዎቹ መደብሮች ሙሉ ለሙሉ ሲዘጉ አንዳንዶቹ በመጠኑ መዝጊያቸው (ሻተር) ተከፍቶ ታይተዋል፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ በፒያሳ የሚገኝ ወርቅ ቤት ባለቤትና የተሰበሰበው ወርቅ ዓይነትና ብዛት ሲመዘገብ በታዛቢነት የተገኙ ግለሰብ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ወርቁን የመሰብሰብ ሥራው የተሠራው ሲቪል በለበሱት ግለሰቦች ሲሆን፣ በመደብሩ ውስጥ ያለው ወርቅ መሰብሰብ ከመጀመሩ በፊት ከጎረቤት መደብሮች ታዛቢዎች ተጠርተዋል፡፡

‹‹እያንዳንዱ ወርቅ እየተለካ ሲሰበሰብ እስከ ምሽት አራት ሰዓት ድረስ ቆይቻለሁ›› በማለት ወርቅ የመሰብሰብ ሥራው እስከ ምሽት መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው በታዛቢነት የተገኙ ሦስት ግለሰቦች እንደገለጹት፣ ወርቁን ከሰበሰቡት ግለሰቦችም ሆኑ አብረዋቸው የነበሩ የፀጥታ ኃይሎች ለመደብር ባለቤቶች የፍርድ ቤት ማዘዣ ወረቀትም ሆነ መታወቂያ አላሳዩም፡፡

አንዲት ታዛቢ፣ በታዛቢነት በተገኙበት ወርቅ ቤት ውስጥ ስለወርቅ ሰብሳቢዎቹ ማንነት ለቀረበው ጥያቄ የተሰጠው ምላሽ ‹‹ከበላይ አካል ነው›› የሚል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በታዛቢነት የተቆጠሩ ሌላ ግለሰብ በበኩላቸው፣ የፀጥታ አካለቱ የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡ በመደብሩ ወስጥ የነበረው ወርቅ ከተሰበሰበ በኋላ ወርቁ ወደ ብሔራዊ ባንክ፣ የመደብሮቹ ባለቤቶች ደግሞ ወደ ‹‹ማረፊያ ቤት›› እንደሚሄዱ እንደተነገራቸው አስታውሰዋል፡፡

ወርቃቸው ከመደብር ውስጥ የተወሰደ የመደብር ባለቤቶች ስለተጠረጠሩበት ጉዳይ የተደረገላቸው ገለጻ እንደሌለ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሁሉም ግለሰቦች አስረድተዋል፡፡

ሪፖርተር፣ በፒያሳ ወርቅ በተሰበሰበበት አንድ ወርቅ ቤት ውስጥ አግኝቶ ያነጋገራቸው አንድ ግለሰብ፣ የመደብሩ ባለቤት በቁጥጥር ሥር ውለው ሜክሲኮ አካባቢ በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ እንደ ግለሰቡ ገለጻ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች ረቡዕ ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ቀርበው ለተጨማሪ ምርመራ 12 ቀን  የጊዜ ቀጠሮ ተፈቅዶባቸዋል፡፡

ሪፖርተር ከግለሰቦቹ በፍርድ ቤቱ ስለመቅረባቸው ቢያረጋግጥም ምን ያህል ቀን እንደተፈቀደባቸው ትክክለኛ መረጃ አላገኘም፡፡ የፌደራል ፖሊስም ጉዳዩ በፍርድ ቤት በመያዙ መረጃ መስጠት እንደማይችል አስታውቋል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ዋና ኢኮኖሚስት አቶ ፍቃዱ፣ ባንኩ በሕገወጥ መልኩ የሚደረግ የወርቅ ሽያጭና ዝውውር ላይ ጥቆማ እንዲሰጥ ጥያቄ ማቅረቡን አስታውሰው ‹‹[ተሰብስቦ ወደ ብሔራቢ ባንክ የገባው ወርቅ] በዚያ መሠረት እንደመጡ ነው ምናውቀው፤›› ብለዋል፡፡

በአገሪቱ ውስጥ ወርቅ የመሰብሰብ ሥልጣን ያለው ብሔራዊ ባንክ መሆኑንና የሚነግዱ አካላት ወርቁን የሚገዙት ከባንኩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አቶ ፍቃዱ፣ ‹‹ወርቅ ከእኛ ካልገዛ ማንም ሰው መያዝ አይችልም፣ ከእኛ ደግሞ የተገዛ ወርቅ የለም›› ካሉ በኋላ ‹‹የተያዘባቸው ሰዎች ከዚህ ካልገዙ ከየት እንደገዙ መግለጽ አለባቸው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ጉዳዩ በፍርድ ቤት የተያዘ መሆኑን አስታውሰውም ግለሰቦቹ ስለተሰበሰበባቸው ወርቅ ሕጋዊነት ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉ ከሆነ እንደሚመለስላቸው ካልሆነ ግን የተያዘው ወርቅ እንደሚወረስ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...