Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና በሚቆጣጠረው የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ መካከል አለመግባባት ተፈጠረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና የማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና ቁጥጥር በሚያደርግበት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መካከል፣ በአሠራርና በደንብ ምክንያት አለመግባባት ተፈጠረ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን የ2015 በጀት ሩብ ዓመት አፈጻጸምና ከሕዝብ በተነሱ ጥያቄዎች ላይ፣ ሐሙስ ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ  የበላይ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱ ወቅት  የምክር ቤት አባላት በክረምት ወቅት ወደ መረጣቸው ሕዝብ አካባቢ በተጓዙበት ወቅት፣ ከሕዝብ የተነሱ በርካታ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን፣ በተመሳሳይ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አማረች በካሎ (ዶ/ር) ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢንዱስትሪው ዘርፍ በአሥር ዓመት የልማት ዕቅድ መሠረት ማከናወን ስላለበት ጉዳዮችና ጠንካራ አምራች ኢንዱስትሪ ለመፍጠር ምን እየተከናወነ ነው ሲሉ ለሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹ወደ ዋናው ዝርዝር መልስ ከመሄዳችን በፊት በቋሚ ኮሚቴውና በሚኒስቴሩ መካከል ስላለው የሥራ ግንኑነትና ተግባር እስከምን ድረስ ነው በሚለው ላይ እንነጋገር…›› በማለት አባላቱን ጠይቀዋል፡፡ ‹‹እናንተ ለእኛ ያነሳችሁት ጥያቄ አለ፣ እኛም ለእናንተ የምናነሳው ጥያቄ አለ፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ሚኒስቴሩ እንደሚሉት ቋሚ ኮሚቴው እየጠየቀ ያለው የሰው ኃይል ስትራቴጂ፣ ኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ፣ የዘርፉን አዳዲስ ቴክኖሎጂ የሚመለከት ስትራቴጂ፣ ኢንዱስትሪን ውጤታማት የሚያረጋግጡ ስትራቴጂዎች ጨምሮ በርካታ ተደጋጋሚ የሆነ ስትራቴጂ አውጡ ጥያቄ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ነገር ግን የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ቀድሞ የወጣ በመሆኑና ከዚህ ፖሊሲ የሚቀዱ ወደ 65 ስትራቴጂዎች በመኖራቸው፣ ከእነዚህ ወስጥ የቅድሚያ ቅድሚያ እየተመረጡ እንደሚዘጋጁ በተደጋጋሚ መናገራቸውን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ ስትራቴጂ ለምን አልወጣም በሚል በተደጋጋሚ ጥያቄ እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከአሥር ዓመቱ የተቀዳ ዓመታዊ ዕቅድ አዘጋጅቶ ዕቅዱን ከሚመለከታቸው የመንግሥት ዕቅድ ተቆጣጣሪ ተቋማት ጋር ተነጋግሮ በማፅደቅ፣ ሥራውን ለማሳካት ያስችሉኛል ያላቸውን የማስፈጸሚያ ዘዴዎች እንደሚተገብርም አክለው አስረድተዋል፡፡

‹‹ይሁን እንጂ ከቋሚ ኮሚቴ አባላቱ እየመጣብን ያለው ነገር ይህንን ሥሩ፣ ይህንን አትሥሩ የሚል ዓይነት ነገር ነው፡፡ እኛ ይህ ትክክል ነው ብለን አናምንም፣ ትክክል ነው ብለን የምናስበው ያዘጋጀነው የአሥር ዓመቱ ዓመቱ መሪ ዕቅድ አለ፣ ይህ ዕቅድ ተተግብሯል ወይስ አልተተገበረም፣ እንዲሁም በመተግበር ሒደት ላይ ያሉ ልዩነቶች ምንድን ናቸው የሚለውን ልንነጋገር እንችላለን፡፡ ነገር ግን እየተባለ ያለው ይህንን ስትራቴጂ ለምን አላወጣቸሁም? ያንን ስትራቴጂ ለምን አላወጣቸሁም? በመሆኑ ይህም አግባብ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ ሚኒስትሩ አክለውም ከቋሚ ኮሚቴው ምክረ ሐሰብ ሊያቀርብ እንደሚችል በመጥቀስ፣ ነገር ግን አሁንም ምክረ ሐሰቡ ከጠቀመ ሊወስዱት እንደሚችሉ፣ የማይጠቅም ሆኖ ከተሰማቸው ደግሞ የራሳቸውን አማራጭ ሊወስዱ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡

‹‹በመሆኑም ዝርዝር ጥያቄ ወደ መመለስ ከመግባታችን በፊት የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ሥልጣን፣ ተግባርና አሠራር ላይ መነጋገር ያስፈልጋል፤›› ሲሉ ለአባላቱ ሐሳባቸውን አቅርበዋል፡፡ አክለውም ‹‹በነገራቸሁ ላይ እኛም ባለን ቅሬታ የቋሚ ኮሚቴው አካሄድ በዚህ መንገድ ከሆነ ተግባብተን ሥራ ልንሠራ አንችልም ብለን ለምክር ቤቱ አቅርበናል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹እኛ ካዘጋጀነው ዕቅድ ሌላ ዕቅድ እንድናዘጋጅ እየታዘዝን ነው? በዚህ ሁኔታ ስንት ዕቅድ እናዘጋጅ? ለቋሚ ከሚቴ ሌላ ዕቅድ፣ ለምክር ቤቱ ሌላ ዕቅድ፣ ለፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሌላ ዕቅድ ልናዘጋጅ ነው? እንዴት አድርገን ነው የምንሠራው? እናም ትክክል አይደለም ብለን ስለምናስብ በአሠራር ላይ ተነጋግረን ትክክል የሆነውና ያልሆነውን ለይተን ማስተካከል ያለብንን እናስተካክላለን፡፡ ቋሚ ኮሚቴውም ማስተካከል ያለበትን ማየትና ግልጽነት መፈጠር አለበት፤›› ብለዋል፡፡

ይህ ችግር በተደጋጋሚ እንደተነሳባቸው የሚናገሩት አቶ መላኩ፣ ‹‹የእናንተን ክብርና ሞራል ለመጠበቅ የምትሰጧቸውን አስተያየቶች እንወስዳለን ብለን የወሰድናቸው አሉ፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ መቋጫ ስሌለውና አሁንም ሌላ ነገር ይዛቸሁ እየመጣችሁ በመሆኑ በቅድሚያ በአሠራሩ ላይ እንነጋገር፤›› በማለት ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ቋሚ ኮሚቴው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ ቁጥር 6/2008 ዓ.ም. መሠረት፣ የኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በምን ጉዳዮች ላይ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደርግ ማብራሪያ ስጥቷል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ በበኩላቸው ምንም ዓይነት ድንበር የማለፍ ዕሳቤ አለመኖሩን በመግለጽ፣ ይህች አገር እንድትበለጽግ ከተፈለገ ከሁሉም ተቋማት ጋር ቅንጅታዊ አሠራር አስፈላጊ በመሆኑ፣ ፖሊሲና ስትራቴጂ የልማት መሠረት በመሆናቸው ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እነዚህን ወሳኝ ዶክሜንቶች በማዘጋጀት የሚጠበቅበት ሥራ እንዲያከናውን ግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች