Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየፌዴራል ዳኞችና ቤተሰቦቻቸው የሕክምና አገልግሎት ሽፋን ጣርያ የሚያሳድግ ደንብ ፀደቀ

የፌዴራል ዳኞችና ቤተሰቦቻቸው የሕክምና አገልግሎት ሽፋን ጣርያ የሚያሳድግ ደንብ ፀደቀ

ቀን:

የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በሦስቱ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ውስጥ ለሚያገለግሉ ዳኞችና ቤተሰቦቻቸው የተመደበውን የሕክምና አገልግሎት ሽፋን ጣርያ በአሥር እጥፍ የሚያሳድግ ደንብ አፀደቀ፡፡

ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ ያለው ደንብ የፌዴራል ዳኞችና ቤተሰቦቻቸው በዓመት ውስጥ እስከ 4,500 ብር ድረስ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የመደበ ሲሆን፣ አዲሱ ደንብ ይህንን ጣርያ በአሥር እጥፍ አሳድጎ 45 ሺሕ ብር አድርሶታል፡፡ የጤና አገልግሎት ሽፋኑ በሦስቱ የፌዴራል ጠቅላይ፣ ከፍተኛና የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ውስጥ ላሉ 386 ዳኞች በሙሉ ተግባራዊ የሚደረግ  መሆኑ ተገልጿል፡፡

በቀድሞው ደንብ መሠረት ለፌዴራል ዳኞች የጤና መድን ሽፋን ለማቅረብ ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት ጋር የተገባው ውል ከአንድ ወር በኋላ ታኅሳስ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. እንደሚጠናቀቅና ከዚህ በፊት በአዲሱ የዋጋ ጣርያ አዲስ ውል እንደሚገባ፣ የጉባዔው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘሪሁን ጌታቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

ጉባዔው አዲስ የሕክምና ሽፋን ጣርያ የያዘውን ደንብ ያፀደቀው ካለፈው ሳምንት አጋማሽ አንስቶ፣ በባህር ዳር ከተማ ለአራት ቀናት ባካሄደው ስብሰባ ላይ ነው፡፡ በዚህ ስብሰባ ጉባዔው ሁለት ደንቦችና ሁለት መመርያዎች ቀርበውለት፣ ከአንዱ መመርያ በስተቀር ሁሉንም አፅድቋል፡፡ ስብሰባው እሑድ ጥቅምት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ከመጠናቀቁ በፊት ጉባዔው ሁለት ደንቦችና ሁለት መመርያዎች ቀርበውለት፣ ከአንድ መመርያ በስተቀር ሦስቱን ማፅደቁን አቶ ዘሪሁን ገልጸዋል፡፡

በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ የሚመራው ጉባዔ በስብሰባው ካፀደቃቸው ሕጎች ውስጥ አንዱ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዳኞችና ቤተሰቦቻቸው የሕክምና አገልግሎት ደንብ ነው፡፡ አዲሱ ደንብ ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ ያለውንና ሳይሻሻል 19 ዓመታት በማስቆጠሩ ለረጅም ጊዜ ዳኞች ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርቡበት የነበረውን ደንብ የሚተካ መሆኑን፣ የጽሕፈት ቤት ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

አሁን በተሻረው ደንብ የፌዴራል ዳኞች ዓመታዊ የሕክምና ወጪ ጣርያ ሦስት ሺሕ ብር ሲሆን፣ ለቤተሰቦቻቸው 1,500 ብር ተመድቦ ነበር፡፡ በአዲሱ ደንብ የፌዴራል ዳኞች የሕክምና ወጪ ጣርያ ወደ 30 ሺሕ ብር ያደገ ሲሆን ለቤተሰቦቻቸው የሚመደበው ገንዘብም 15 ሺሕ ብር ደርሷል፡፡

ከደንቡ ላይ ለውጥ ከተደረገባቸው ክፍያዎች ውስጥ አንዱ ለሕክምና ካርድ የሚወጣው ዋጋ መሆኑን የተናገሩት አቶ ዘሪሁን፣ ከዚህ ቀደም 50 ብር የነበረው የአንድ ካርድ ዋጋ ወደ አንድ ሺሕ ብር አድጓል፡፡ ለሴት ዳኞች የወሊድ አገልግሎት ሽፋንና የዳኞች የመነጽር ሽፋን መሰጠት ኃላፊው “ትልቅ” ለውጦች እንደሆኑ የጠቀሷቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡

በሦስቱ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ውስጥ የሚያገለግሉ ሴት ዳኞች የወሊድ አገልግሎት ሽፋን በማይሰጠው የቀድሞው ደንብ ላይ ቅሬታ ሲያነሱ እንደነበር ገልጸው፣ የመነጽር ጉዳይም እንዲሁ ጥያቄ ሲነሳበት የነበረና ከመዝገብ አተያይ ጋር በተያያዘ የዳኞችን ጤና “ከባድ ጫና ውስጥ የከተተ” ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የ1996 ዓ.ም. ደንብ በድጋሚ ለማውጣት አዲስ ጥናት መካሄዱን የሚናገሩት ኃላፊው፣ ከዚህ ቀደም ተጠንቶ የቀረበው ጥናት ለዳኞች ሕክምና ሽፋን ጣርያ እንዲሆን በምክረ ሐሳብነት ያቀረበው ዋጋ አሁን ከፀደቀው የበለጠ እንደበር ገልጸዋል፡፡ አሁን በተደረገው ጥናት የቀረበው ዋጋ ደግሞ “የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ” በማገናዘብ የተዘጋጀ እንደሆነ በማስረዳት፣ ‹‹ይህንን መጀመርያ እንይና ከዚያ በኋላ ልናሻሽለው እንችላለን ተብሎ ነው የፀደቀው፤›› ሲሉ፣ በደንቡ ላይ ስለተቀመጠው የጣርያ ዋጋ ተናግረዋል፡፡

አቶ ዘሪሁን እንደሚያስረዱት ጉባዔው ለአንድ ዳኛና ቤተሰቦቹ 45 ሺሕ ብር ጣርያ ቢመድብም፣ መንግሥት ለመድን ሰጪ ድርጅቱ የሚከፍለው ዓረቦን ከዚህ ያነሰ ነው፡፡

አዲሱ ደንብ መድን ሰጪ ድርጅት የሚመረጥበትን መንገድ ሲገልጽ፣ ‹‹ከመድን ሰጪ ተቋማት ፕሮፎርማ በመሰብሰብ አነስተኛ ዋጋን ያቀረበ ድርጅት በጽሕፈት ቤቱ የሚመረጥ ይሆናል፤›› በማለት ደንግጓል፡፡ በዚህ መሠረት ሁሉም መድን ሰጪ ድርጅቶች የሚያቀርቡት ዋጋ ለውድድር እንደሚቀርብ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ጉባዔው ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት ጋር ለገባው ውል በየዓመቱ 1.7 ሚሊዮን ብር ይከፍል ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...