Monday, January 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየዴር ሡልጣን ገዳም ‹‹የግብፅ ንብረት ነው›› መባሉን ቅዱስ ሲኖዶስ ተቃወመ

የዴር ሡልጣን ገዳም ‹‹የግብፅ ንብረት ነው›› መባሉን ቅዱስ ሲኖዶስ ተቃወመ

ቀን:

  • መንግሥት ጥብቅ ክትትል እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል

በቅርቡ በግብፅ በተካሄደው ሦስት የመካከለኛው ምሥራቅ ኦርቶዶክስ ፓትርያርኮች ጉባዔ ላይ ‹‹በኢየሩሳሌም የሚገኘው የዴር ሡልጣን ገዳም የኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ንብረት ነው፤›› በማለት መሪዎቹ መግለጫ መስጠታቸውን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አጥብቆ ተቃወመ፡፡

በጥቅምት ወር ሁለተኛ ሳምንት በተካሄደውና ግብፅን ባካተተው የመካከለኛው ምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት 13ኛው ስብሰባ ላይ የተሳተፉትና የዴር ሡልጣን ገዳም ይዞታ ‹‹የግብፅ ነው›› ከማለት ባለፈም፣ በገዳሙ ባለቤትነት ላይ ‹‹ከግብፆች ጎን በመቆም እንደግፋለን›› ያሉት የሶሪያ አንጾኪያ ቤተ ክርስቲያንና በሊባኖስ የሚገኘው የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ናቸው፡፡

ይህን የጋራ መግለጫቸውን ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ተቃውሞውን ያሰማው፣ የጥቅምት ጉባዔውን ማጠናቀቁን አስመልክቶ ዓርብ ጥቅምት 25 ቀን 2015 ዓ.ም.  ባወጣው መግለጫው ነው፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹አብያተ ክርስቲያናቱ በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ገዳም ይዞታችን ላይ የሰጡት የተሳሳተ መግለጫ የቤተ ክርስቲያናችንና የአገራችንን ኢትዮጵያ ክብር የሚነካ ስለሆነ ጉባዔው በእጅጉ ተቃውሞታል፤›› ብለዋል፡፡

አያይዘውም ሦስቱ አብያተ ክርስቲያናት (ግብፅ፣ ሶሪያና አርመን) የሰጡትን መግለጫ መልሰው እንዲያጤኑትና የማረሚያ መግለጫ እንዲሰጡ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም በጉዳዩ ጥብቅ ክትትል እንዲያደርግበት ጉባዔው ጥሪውን ማቅረቡንም ተናግረዋል፡፡

 በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙት ሦስቱ አብያተ ክርስቲያናት ስብሰባቸውን በግብፅ ያካሄዱት ከጥቅምት 8 እስከ 10 ቀን 2015 ዓ.ም. ነበር፡፡

ግብፅ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ዴር ሡልጣን ገዳም ይዞታ ላይ እየፈጠረች ያለውን አሳሳቢ ችግር መንግሥት አስፈላጊውን መፍትሔ እንዲያስገኝ ቅዱስ ሲኖዶስ ከአራት ዓመታት በፊት  ሲጠይቅ፣ ‹‹ዴር ሡልጣን ትናንትም ዛሬም ነገም የኢትዮጵያ ገዳም ነው››  ማለቱንም መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በወቅቱ ሲኖዶሱ በሰጠው መግለጫ እንዳሳሰበው፣ የግብፅ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ በይዞታችን ላይ አግባብነት የሌለው ሥራን የማደናቀፍና በታሪክም ሆነ በማንኛውም የሰነድ መረጃ የሌለው የባለቤትነት ጥያቄ በማንሳት፣ እየተፈጠረ ያለውን አላስፈላጊ ሁከትና ብጥብጥ ማቆም አለባቸው ብሎ ነበር፡፡

የኢትዮጵያውያን  የኢየሩሳሌም  ይዞታ  ከቅዱሳት  መጻሕፍት  ማስረጃነት   በተጨማሪ  ኢየሩሳሌምን  ይገዙ  በነበሩ  መሪዎች  የግብርና  የመንግሥት  አዋጅ   መዛግብት፣  ኢየሩሳሌም  ድረስ  ተጉዘው  ታሪክ  በጻፉ   ምሁራን፣   በኢየሩሳሌም ተሳላሚዎች የግል ማስታወሻና  በዓለም  አቀፍ  መዛግብት  ሳይቀር  ተመዝግቧል፡፡ ከእነዚህም መካከል  እንደእነ አባ  ጀሮም  ያሉ  የላቲን  ታሪክ ጸሐፊዎች፣  እንደእነ ከሊፋ ዑመርና  ሳላሃዲን  ባሉ  ገዥዎች፣  በኢየሩሳሌም  ተመሳሳይ  ይዞታ  ባላቸው  በአርመንና  በሶሪያ  ኦሬንታል  ኦርቶዶክስ  አብያተ  ክርስቲያናት፣  በግሪክና  በሩሲያ  ኦርቶዶክስ  አብያተ  ክርስቲያናት፣ እንዲሁም በካቶሊክ  ቤተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ ገዳማት መዛግብት  የተመሰከረ  ነው፡፡

ንግሥት እሌኒ በአራተኛው ምዕት ዓመት (326 ዓ.ም.) የክርስቶስ መስቀል ተቆፍሮ የተገኘበትን ዋሻ ቀደም ብለው ለተገኙትና በዚያም ይኖሩ ለነበሩት ኢትዮጵያውያን መስጠቷ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ በጌቴሰማኒና በቤተልሔም ሌሎች ቦታዎችን መስጠቷ ‹‹ኢትዮጵያና ኢየሩሳሌም›› የሚባለው መጽሐፍ ይገልጻል፡፡ ይኸው መጽሐፍ ዴር ሡልጣን ገዳም የሚገኝበት ቦታ ንግሥት ማክዳ ለመጀመርያ ጊዜ በኢየሩሳሌም ለኢትዮጵያ የታሪክ የባለመብት ርስት የመሠረተችው ከ4485 ዓመተ ዓለም ጀምሮ [ዘንድሮ 7515 ዓመተ ዓለም] መሆኑንም የታሪክ ማኅደር እንደሚያስረዳ ጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያን ባለቤትነት የሚያረጋግጡት መረጃዎች የሚገኙባቸው የተሳላሚዎችና አገር ጎብኚዎች፣ የታሪክ ተመራማሪዎች መጻሕፍት፣ ጥናቶችና ጽሑፎች፣ የቱርክ ሡልጣኖችና የኢየሩሳሌም አገረ ገዥዎች ድንጋጌዎች፣ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ በመንግሥታትና በአብያተ ክርስቲያናት መሪዎችና ተጠሪዎች መካከል የሐሳብ ልውውጥ ደብዳቤዎች፣ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎችና ወኪሎች ምስክርነት፣ የነዋሪዎች ሕዝበ ክርስቲያንና ሽማግሌዎች ምስክርነት፣ የሕግ አስተያየቶች በሚል መልክ ተለይተው ሊታዩ እንደሚችሉ ተመልክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...