Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ኢትዮጵያ ግብፅን የምታይበትና ግብፅ ኢትዮጵያን የምታይበት ሁኔታ ይለያያል›› ያዕቆብ አርሳኖ (ፕሮፌሰር)፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ቡድን አባልና ተመራማሪ

በቀጣናዊ ትስስርና በኃይድሮ ፖለቲክስ ላይ ባላቸው ጥልቅ ዕውቀትና ልምድ፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለረዥም ጊዜ የፖለቲካ ሳይንስ በማስተማር ይታወቃሉ፡፡ ከአስተማሪነት ባሻገር በዩኒቨርሲቲው ለረዥም ጊዜያት በኮሚቴዎች አባልነትና በትምህርት ክፍል መሪነት መሰል ኃላፊነቶች አገልግለዋል፡፡ በኃይድሮ ፖለቲክስና በግጭት ላይ ጥናቶችን በማቅረብና የምርምር ሥራዎችን በመምራት ይታወቃሉ፣ ያዕቆብ አርሳኖ (ፕሮፌሰር)፡፡ በኃይድሮ ፖለቲክስና በምርምር ሥራዎች በሚያማክሩበት ወቅትም፣ በዓባይ ወንዝና በተፋሰሱ ዙሪያ ትልቅ ድምፅ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ የውጭ ጉዳይና የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴሮችን ጨምሮ ለበርካታ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም አማካሪ ሆነው ያገለገሉት ያዕቆብ (ፕሮፌሰር)፣ በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋሙና በዓባይ ወንዝ ላይ የሚሠሩ በርካታ ኮሚቴዎችንም በአባልነት ያገለግላሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ በሚደረገው የሦስትዮሽ ድርድር ላይ ኢትዮጵያን ወክለው የሚደራደረው ቡድን አባል ናቸው፡፡ ግድቡን በሚመለከት በኢትዮጵያ ላይ ለሚስተዋሉት የተለያዩ የፖለቲካ ጫናዎችና ድርድሩን በሚመለከት ሳሙኤል ቦጋለ ከያዕቆብ (ፕሮፌሰር) ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተሰናድቷል፡፡

ሪፖርተር፡- በህዳሴ ግድብ ላይ የሦስትዮሽ ድርድሩ ለመጨረሻ ጊዜ ከተካሄደ ዓመት ከግማሽ ሆኖታል፡፡ ያልተቋጩ ጉዳዮች እያሉ እንዴት እስካሁን ዝም ተብሎ ቆየ? ድርድሩ በመዘግየቱስ በኢትዮጵያ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አያመጣም?

ፕሮፌሰር ያዕቆብ፡- እኛ እኮ መጀመርያም አስገዳጅ ሆኖብን ነው እንጂ ለመደራደር ስለፈለግን አልነበረም የገባንበት፡፡ በእርግጥ አሁንም እንደ ንግግር ስለሆነ ይዘቱን ድርድር ብለን አንጠራውም፡፡ አንዳንዶች ድርድር ብለው ይጠሩታል፡፡ ነገር ግን በመሠረቱ ውይይት ነው፡፡ ውኃውን በግዛታችን ለመጠቀም በውኃው አጠቃቀም ላይ ምክንያትዊነትን የሚያነሳ ሌላ አካል ካለ በእሱ ላይ ለመነጋገር ነው፡፡ ግድቡን ገንብቶ ለመጨረስም የድርድሩን ውጤት አንጠብቅም ነበር፡፡ ድርድሩ ጊዜ መፍጀቱ ለእኛ የሚያሠጋ ነገር የለውም፡፡ የሚያሠጋው እኛ ግድቡን ባንጀምረውና እዚህ ደረጃ ባናደርሰው ነበር፡፡ ግብፆች ኢትዮጵያ ላይ አስገዳጅ የሚል የስምምነት ነጥቦች አቅርበው ስለነበር፣ እነዚህ አስገዳጅ ነጥቦች ደግሞ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት ስለሌላቸው፣ እንዲሁም እንደ አሜሪካኖች ኢትዮጵያ አስገዳጅ ነጥቦችን እንድንቀበል የሚያስገድድ አካል ቢመጣም ኢትዮጵያም  የምትቀበለው አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ አስገዳጅ የስምምነት ነጥቦችን ይዛ ትመጣለች፡፡ አሁን [እሑድ ጥቅምት 27 ቀን 2015 ዓ.ም.] ዛሬ ለሚጀመረው የኮፕ27 (COP27) የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረስንም አዘጋጅ በመሆኗ በኢትዮጵያ ላይ አስገዳጅ ነጥቦችን ይዛ በመምጣት ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ታሳምናለች ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይኼ እንቅስቃሴ የውይይቱን አቅጣጫ አያስቀይረውም?

ፕሮፌሰር ያዕቆብ፡- ይህ የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ ቢሆንም ግብፅ አዘጋጅ በመሆኗ፣ ብዙ ተጠቃሚ ለመሆን ግንኙነቶችን በመፍጠር ለሦስተኛ ወገኖች ስለግድቡ የሚያማልሉ አስገዳጅ ሁኔታዎችን ልታቀርብ ትችላለች፡፡ ይህ ግን የግብፅ ፍላጎት ነው፣ አጀንዳ ይዞ ስምምነት ላይ የሚደረስበት ጉዳይ አይደለም፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ አጠቃላይ የዓለም አገሮች ጉዳይ ነው፡፡ በአንድ አገር ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተው የእገሌ አገር ውኃ ቀንሷል፣ የእገሌ አገር ውኃ በዝቷል በማለት አይወያዩም፡፡ ቢሆንም ግን በኢትዮጵያ በኩል የሚቀርቡት ተሳታፊ አባላት፣ የግድቡን የተለያዩ ጥቅሞች በማቅረብ አዎንታዊ ነገሮችን ማሳየት ይኖርባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የዓባይ ወንዝ በቀጣናው ብዙ አገሮችን ያካተተ ስለሆነ፣ ግድቡም የብዙ አገሮች ጉዳይ ሆኖ በኮንፈረንሱ ሊቀርብ አይችልም ማለት ነው?

ፕሮፌሰር ያዕቆብ፡- እንዳይቀርብና ትኩረት እንዳይኖረው ኢትዮጵያ ማቅረብ ያለባት፣ ውኃውን በኅብረትና በአንድ ላይ ሁሉም አገሮች እንዲጠቀሙ ማስረጃዎችን ማቅረብ ነው፡፡ ከዚህ በፊትም በተካሄዱ የተፋሰስ አገሮች ስብሰባና ስምምነት ላይም ግብፅ  አፈንግጣ መውጣቷን፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አገሮች መስማማታቸውን ማስረዳት ይጠበቅብናል፡፡ እኔ ያሠጋል የሚል ምንም እምነት የለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- የሦስትዮሽ ድርድሩ/ውይይቱ አቅጣጫ ወዴት ይሄዳል ብለው ያስባሉ? ወደፊት የውይይት ጉዳዮች ምን ይሆናሉ? የኢትዮጵያ ተወካዮችስ በኮንፈረንሱ ምን ማድረግ አለባቸው?

ፕሮፌሰር ያዕቆብ፡- ወደፊት ሊሆን የሚችለው እንግዲህ ግብፅና ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ለአሥር ዓመታት የተወያዩበትን ሰነድ መፈራረም፣ ተገቢና ፍትሐዊ የውኃ አጠቃቀምን ማረጋገጥ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግብፅ እናንተ ስታለሙ እኔ ማወቅ አለብኝ የምትለው ነገር ተሰሚነት የለውም፡፡ እሷም ስታለማ ማንንም አላሳወቀችም፡፡ ግብፅ ኢትዮጵያን ለመወንጀል የማታደርገው ጥረት የለም፡፡ ስለዚህ የዚህ ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች የመረጃም፣ የማስረጃም፣ የዕውቀትም ሆነ የአቅጣጫ እጥረት ስለሌለባቸው ይህን መከላከል አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ለበርካታ ጊዜያት አጀንዳ ተቀባይ እንደነበረችና ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ በመስጠት እንጂ አጀንዳ ባለማቅረብ ትወቀሳለች፡፡ ይህንን ወቀሳ እርስዎ እንዴት ያዩታል?

ፕሮፌሰር ያዕቆብ፡- በጣም በሚያስገርም ሁኔታ ሕዝቡም፣ ባለሙያውም ሆነ ባለሥልጣኑ ይህን ይናገራል፡፡ በጣም በጥንቃቄ መታየት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ግንባታ በመጀመሯ ራሱ ትልቅ አጀንዳ ነው ያስቀመጠችው፡፡ ሁሉም ስለግድቡ የመጡት ወቀሳዎችና ክርክሮች የግድቡን ግንባታ ተከትለው የመጡ ናቸው፡፡ አሁን ለአጀንዳ መልስ መስጠት እየሆነ ያለው የእነሱ ተራ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ትልቅ አጀንዳ ዘርግታ ነው ያለችው፡፡ ግብፅና ሱዳን ያመጡት ምንም ትልቅ አጀንዳ የለም፡፡ ስብሰባዎችን፣ ኮንፈረንሶችንና መግለጫዎችን መስጠት፣ እንዲሁም ለሦስተኛ ወገን ማቅረብና ስላቅ ስለሚያበዙ እነሱ አጀንዳ አስቀማጭ ነው የሚመስሉት፡፡ ልብ ብለን ካየን እነሱ ናቸው አጀንዳ ተቀባዮች፡፡ በግብፅ በሚካሄደው ኮንፈረንስም የኢትዮጵያ ተወካዮች በምንም ሁኔታ ለሚመጣው አጀንዳ ተቀባይ ሳይሆኑ፣ ኢትዮጵያ ላስቀመጠችው አጀንዳ ተከራካሪ ነው የሚሆኑት፡፡ ከዚህ በፊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት፣ የአሜሪካ መንግሥት፣ በተለይም ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ በርካታ ሦስተኛ ወገኖች ለማደራደር ሞክረው ነበር፡፡ በኢትዮጵያ አጀንዳ ምክንያት፡፡ እነሱም የዚህ አጀንዳ መለሽ ስለነበሩ ነው ወደ ሦስተኛ ወገን ይዘውት የሄዱት፡፡ ነገር ግን ሁሉም አልተሳካም፡፡

ሪፖርተር፡- በእርግጥ በተወሰነ ሁኔታ ግብፆች ጫናው ተሳክቶላቸዋል እኮ፡፡ ኢትዮጵያ ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ አጥታ በራሷ ገንዘብ አይደል እንዴ የምትገነባው?

ፕሮፌሰር ያዕቆብ፡- በእርግጥ የጂኦ ፖለቲካው ሁኔታ ለዚህ ጥልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡  ከግብፅ አንፃር ኢትዮጵያ ለአውሮፓና ለአሜሪካ ጠቃሚና እንደ መሣሪያ የምታገለግል አገር አይደለችም፡፡ ብሔራዊ ጥቅሟን አሳልፋ የማትሰጥና ጠንካራ አቋም ያላት አገር ስለሆነች፣ ኢትዮጵያን እንደ መሣሪያ መጠቀም አይቻልም፡፡ በጂኦግራፊም ግብፅ ለአውሮፓ፣ ለአፍሪካና ለመካከለኛው ምሥራቅ መገናኛ ስለሆነች ለዓለም ኢኮኖሚ በጣም ጠቃሚ ናት፡፡ ነዳጅም ሆነ ሌሎች በርካታ ዕቃዎች በእሷ በኩል ስለሆነ የሚያልፉት ግብፅ ይህን አገልግሎቷን እንድትቀጥል፣ ሰላም እንድትሆንና ጥቅሟን እንድታስከብር ለራሳቸው ጥቅም ተብሎ ወገናዊነት አለ፡፡ ግብፆችም በዚህ ምክንያት እነሱን ለማገልገል ፍላጎታቸውንና ዝግጁነታቸውን ሁሌም ያሳያሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ እስራኤልንና የዓረብ አገሮችን ለማደራደር በርካታ ሥራ እየሠራች ነው ያለችው፡፡ ከማደራደር በተጨማሪ ለምዕራቡ ዓለም የሚጠቅም ሥርዓት በመካከለኛው ምሥራቅ እንዲሰፍን ስለምትሠራ በዚህ ጥቅሟ ምክንያት ለእነሱ ተፈላጊ ናት፡፡ ግብፅ የበለጠ የሰው ኃይል ያላትና የለማች ነች ተብላ በዓረብ አገሮች የምትወደስና የምትፈለግ ስለሆነ፣ የእነሱም ድጋፍ አላት፡፡ ኢትዮጵያ የውጭ ድጋፍ ሳይኖራት ይህን ተፅዕኖ ተቋቁማ መቀጠሏና ቢያንስ የራሷን ጥቅም ማስከበር መቻሏ ሌሎችን ያስፈራል፡፡ የኢትዮጵያ አቀማመጥ በታሪክም ሆነ በሌላም ለአፍሪካ  ነው የበለጠ ጠቃሚነቱ፡፡ ነገር ግን አፍሪካ ጉልበት ስለሌላት በዓለም አቀፍ ደረጃ አይኤምኤፍንም ሆነ የዓለም ባንክን አትቆጣጠርም፡፡ ስለዚህ አፍሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው ድጋፍ ይህ ነው የሚባል አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የህዳሴን ግድብ እንደ ምሳሌ በማየትና ኢትዮጵያ ጫናውን መቋቋሟን በመመልከት፣ ከኢትዮጵያ ትምህርት የሚወስዱና እንደ አርዓያ የሚያዩ የተፋሰሱ አገሮች አሉ፡፡ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?

ፕሮፌሰር ያዕቆብ፡- ኢትዮጵያ ከራሷ ተጠቃሚነት አልፋ ለሌሎች ጠቃሚ የምትሆን አገር እንዳትሆን መቼም ጠላት ተኝቶ አያድርም፡፡ ኢትዮጵያ እንድትዳከም መፈለግና በወዳጅነት አለመፈለግ በግብፅ በኩል በጣም ይታያል፡፡ ደከም የምትልና ፈተና የማትሆን ኢትዮጵያን ግብፅ እንደምትፈልግ እርግጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ምሳሌ ሆና የመታየቷ አዎንታዊ ገጽታ አይፈለግም፡፡ አንዳንድ ጊዜ በኢትዮጵያ የውስጥ ሁኔታዋ ማለትም እንደ ቋንቋ፣ ብሔርና ሃይማኖትን በየአጋጣሚው እየተጠቀመች ሰላምን ለመሸርሸርና የመሳሰሉት ነገሮችን ለማድረግ ግብፅ ሙከራ ታደርጋለች፡፡ ለምሳሌ በግብፅ ሚዲያዎች ላይ ኢትዮጵያ ተከፋፍላ ለማየት ፍላጎቷን በማሳየት፣ ጦርነትንና አማፅያንን በመደገፍ እንደምትሠራ የቅርብ ዘመን ታሪክ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ግብፅን የምታይበትና ግብፅ ኢትዮጵያን የምታይበት ሁኔታ ይለያያል፡፡ ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ የፈለገችውን ለማድረግ ብትሞክርም ብዙ ጊዜ አይሳካላትም፡፡ ኢትዮጵያ ወደቀች ስትባል የምትነሳና የለችም ሲባል የምትኖር አገር ነች፡፡

ሪፖርተር፡- ሱዳን ለህዳሴ ግድብ መጀመርያ የነበራትን የድጋፍ አቋም በመቀየር አሁን ቀንደኛ ተቃዋሚ ሆናለች፡፡ ግድቡ ለአገሪቱና ለመላው የሱዳን ሕዝብ የሚሰጠው ጥቅም እጅግ ከፍተኛ መሆኑን የሱዳን ሕዝብና ፖለቲከኞች እንዴት መረዳት አቃታቸው? ኢትዮጵያስ ይህንን ለሱዳን ማስረዳት ላይ እንዴት ሳይሳካላት ቀረ?

ፕሮፌሰር ያዕቆብ፡- ይህ በጣም ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡ እንዲሁ በቀላሉ ብቻ የሚገኝ መልስም አይደለም፡፡ ቀለል አድርገን ብንመለከተው፣ ግብፅና ሱዳን በታሪክ በጣም የተቀራረቡና ግንኙነታቸው ደግሞ ጠላትነትንና ወዳጅነትን የጨመረ ነው፡፡ ይህም ግንኙነት ቢያንስ ግማሹን የሱዳን ሕዝብ በግብፅ ጥላ ሥር እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ከዚያም በፊት በሃይማኖትና በባህል የተነሳ በርከት ያሉ የሱዳን ማኅበረሰቦች ከታች እስከ ፖለቲከኛው ከግብፅ ጋር ዝምድና አላቸው፡፡ ሌላው ደግሞ የግብፅን ጫናና ጣልቃ ገብነት የሚቃረን በርካታ የኅብረተሰብ ክፍል ሱዳን ውስጥ አለ፡፡ ሱዳን እርግጥ ነው ከተወሰነ ሥጋት በስተቀር ለህዳሴ ግድብ ድጋፍ አሳይታ ነበር፡፡ የጎርፍ ሥጋት የነበረባቸው ጊዜ ኢትዮጵያ አስተማማኝ ጥናት አሳይታ እንደ ኮርቻ ግድብ ዓይነትን በአስፋልት በመሥራት ማስተማመኛ ሰጥታ ነበር፡፡ እስከ መጨረሻው የዋሽንግተን ዲሲው ድርድር ድረስም ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ነበረች፡፡ ከዚያም በኋላ ነው የሱዳን መንግሥት ሲለወጥ የአዲሱ መንግሥት ውስጥ ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅነት የማይፈልጉ፣ እንዲሁም የግብፅን ድጋፍ እያገኙ ኢትዮጵያን ማዳከም የሚፈልጉ ተገኙ፡፡ ወትሮውንም ሱዳን ውስጥ ከግብፅ ጋር የተሻረኩና የተዛመዱ የነበሩ አካላት እንደነበሩ ይህ አንድ ማሳያ ነው፡፡ ሱዳንን አንድ ዓይነት አገርና አንድ ዓይነት ሐሳብ አላት ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ ዋናው የፖለቲከኞች ልዩነት ሲሆን፣ ይህም ሱዳንን በጥቅሟ የተከፋፈለች ያደርጋታል፡፡

ሪፖርተር፡- ለምንድነው ታዲያ ኢትዮጰያ መሀላቸው ገብታ የራሷን ጥቅም ማስከበርና ፖለቲከኞችን መያዝ ያቃታት?

ፕሮፌሰር ያዕቆብ፡- ኢትዮጵያ እኮ ይህን ስታደርግ ቆይታለች፡፡ ኢትዮጵያን የሚፃረር ወገን በሥልጣን ላይ ቢኖርም የሚደግፈውን ወገን ደግሞ ስታቀርብ ነበር፡፡ ኢትዮጵያን የሚደግፈውን ወገንና የህዳሴን ግድብ ጥቅም የሚረዳውን ሱዳን ውስጥ በአዋጅ ባታቀርበውም፣ በፖለቲካ መንገድ ታቀርበዋለች እኔ እስከምረዳው፡፡

ሪፖርተር፡- ዓባይ ተፋሰስ ውስጥ የሌሉ አገሮች የዓረብ ሊግ አገሮችን ጨምሮ በግድቡ ላይ ትክክል ያልሆነ አቋም ያራምዳሉ፡፡ እነሱ የኢትዮጵያን ጥቅም ሲቃወሙ ኢትዮጵያስ በምን መቋቋም ትችላለች?

ፕሮፌሰር ያዕቆብ፡- እነዚህን መቋቋም የሚቻለው በኢትዮጵያ ጠንክሮ መገኘት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነቷን፣ እንዲሁም ብሔራዊ ልማቷንና ጥቅሟን በሚገባ በማስቀጠል መቆየት ይኖርባታል፡፡ አካባቢው በችግር ማዕበል ውስጥ ሆኖም ኢትዮጵያ ራሷን ችላ ለሌሎች ጠበቃ ሆና ቆይታለች፡፡ አሁንም ቢሆን በውኃ ልማቷ ጠንክራ ብትቀጥል 45 ሺሕ ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ትችላለች፡፡ ሁለት ሦስት ተጨማሪ ግድቦችን በመሥራት ማለት ነው፡፡ በተለያዩ ወንዞች ላይም ተመሳሳይ ግድቦችን መገንባት ይቻላል፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅና በሌሎች አገሮች ያለው የኃይል ምንጭ አሁንም ነዳጅ ነው፡፡ ይህም ታዳሽ ኃይል ስላልሆነ ሊያልቅ የሚችል ነው፡፡ በዓለም ላይ ያለው የኃይል አማራጭ ፍላጎት አሁን ተቀይሯል፡፡ አውሮፓውያን ትልቅ የኃይል አቅርቦት ቀውስ ውስጥ ገብተዋል፡፡ የኑኩሌር ኃይል በጣም አደገኛ ሲሆን ዝቃጩን ማስወገድ ደግሞ አስቸጋሪ ነው፡፡ ታዳሽ ኃይል አሁን በጣም አስፈላጊ ነው ይህንን ለማመንጨት ኢትዮጵያ ትልቅ ኃይል አላት፡፡ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል አሁን ወደ ጎረቤት አገሮች እያለፈ ነው፡፡ አልፎም ደግሞ ወደ አውሮፓ መሻገር የሚችልበት አቅም አለው፡፡ ይህንን ትልቅ የመተሳሰርና የሰጪነት ኃይል ኢትዮጵያ እያጎለበተች ነው፡፡ በመሆኑም ወደፊት ለኢትዮጵያ የትብብር ፍላጎት ይዞላት ስለሚመጣ በንቃት መሥራት ይኖርባታል፡፡ ከብሔራዊ ጥቅም አኳያ ሌሎችን የመጥቀም አቅም እይገነባን ስንሄድ ጥሩ ይሆናል፡፡ ጠላቶቻችንም ደግሞ ወደፊት የጠላትነት ፍላጎታቸው እየቀነሰና እየጠፋ ይሄዳል፡፡ አመላካቾችም አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- የተለያየ የፖለቲካ አቋም ያላቸው የፖለቲካ መሪዎች በኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ያላቸው አቋም አንድ ዓይነት ነው፡፡ በየጊዜው የሚፈጠረው ችግር ግን ወደፊት ማነቆ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?

ፕሮፌሰር ያዕቆብ፡- በፖለቲካ አስተሳሰብና በመንግሥት አያያዝ የተቃረኑ፣ አንደኛ ሌላኛውን የሚወቅሱ ሆነው ኢትዮጵያን አስተዳድረው ነበር፡፡ ነገር ግን በዚህ በውኃ ጉዳይ አንድ ሆነው በዓባይ ላይ ወጥ አቋም ይዘዋል፡፡ ይህንን ወንዝ ማልማት ለእነሱም አገዛዝ እንደሚጠቅም፣ እነሱንም እንደሚያስመሠግን ተገንዝበው ጭምር ነው የሠሩት፡፡ ከአገር ጋር የሚሄድ ጉዳይ የማይለወጥና ቀጣይነት ሊኖረው የሚገባ ሆኖ ሳለ፣ በየጊዜው የሚተካኩ አገዛዞች የአገር ጉዳይ ዋናው ንጣፉ መሆኑን ሳይወዱትም ቢሆን ማድረግ የሚገባቸው ነው፡፡ ይህንን አስበው ልማቱን ከፍ ማድረግም የሚያስመሠግናቸው መሆኑን መገንዘብ አለብን፡፡ መሪዎች ተለዋዋጮች ናቸው፣ በመሆኑም እነሱ በዘፈቀደ ሐሳባቸውን መቀያየር አይችሉም፡፡ ግራ የተጋቡ አንዳንድ ወገኖች አገር እነሱ በሚፈልጉት መንገድ ብቻ እንድትመራ በመፈለግ ችግር ውስጥ የሚገቡት ይህንን ካለመገንዘብ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹መንግሥት ለአገር ውስጥ የኅትመት ኢንዱስትሪ ገበያ ከመፍጠር ጀምሮ ሥራ የመስጠት ኃላፊነት አለበት›› አቶ ዘውዱ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ አሳታሚዎችና አታሚዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ

የኅትመት መሣሪያ በጉተምበርግ ከተፈበረከ ከ400 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ በ1863 ዓ.ም. በምፅዋ የተጀመረው የኅትመት ኢንዱስትሪ ከአፍሪካ ቀዳሚ ቢሆንም፣ ዕድገቱ ውስን መሆኑ ይነገራል፡፡ ከኢትዮጵያ በኋላ የኅትመት...

‹‹ከጨረታ በስተጀርባ ያሉ ድርድሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው›› ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር)፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞ ሜቴክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ ከጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ...

‹‹ባለፉት 25 ዓመታት ባለን አቅም ሁሉ የተለያዩ አጀንዳዎችን ለመዳሰስ ሞክረናል›› የራስወርቅ አድማሴ (ዶ/ር)፣ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› በመባል የሚታወቀውን በኢትዮጵያ ታሪክ ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ አካል ገለልተኛ ሆኖ የተቋቋመ ሐሳብ አመንጪ የጥናት ተቋም (ቲንክ ታንክ) ከመሠረቱት አንዱ መሆናቸውን...