Tuesday, May 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ መወሰኑን ተከትሎ የተነሳው ሙግት

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የውጭ ባንኮችን እንዲገቡ በፖሊሲ ደረጃ ውሳኔ ተላልፎ ይህንን ለማስፈጸም የሚችል ረቂቆች በተዘጋጁበትና ተጨማሪ ሥራዎች እየተሠሩ ባሉበት ወቅት ባንኮቹ እንዴት ይግቡ የሚለው ጉዳይ አከራካሪ እየሆነ መጥቷል፡፡ ባንኮቹን ለማስገባት የወጡ ረቂቅ ሕጎች ላይም እየተነሳ ያለው ጥያቄ እየጨመረ ነው፡፡ በቀጣይ በሚወጡ መመርያዎች ውስጥ ሊካተቱ ይገባል ያሏቸውን ምክረ ሐሳቦች እያቀረቡ ያሉ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ባለሙያዎች የውጭ ባንኮችን ለማስገባት እንደ መንደርደሪያ የተቀመጡ የመንግሥት ግቦች ሳይቀሩ መስተካከል አለባቸው እያሉ ነው፡፡   

የውጭ ባንኮች እንዴት እንደሚገቡ የሚያሳየው ረቂቅ መመርያ ይፋ ከሆነ በኋላ በጉዳዩ ላይ ለመምከር በተዘጋጁ የተለያዩ የውይይት መድረኮች ላይ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት መስተካከል አለባቸው ያሏቸውን ሐሳቦች ቢያንፀባርቁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ግን የውጭ ባንኮች መግባታቸው የማይቀር መሆኑን አስታውቋል፡፡ 

በመንግሥት በተወነው መሠረት የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ተብሎ የተቀመጡ አማራጮች ከዚህ በኋላ በሚወጡ መመርያዎች መስተካከል ካልቻሉ ችግር ሊፈጥሩ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል የሚለው ነጥብ ጎልቶ ወጥቷል፡፡ በተለይም መንግሥት የውጭ ባንኮችን ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት የመረጠበት ወቅትና የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ የሚጣጣም አይደለም ብለው የሚያምኑ የፋይናንስ ተቋማት መሪዎችና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ይህንኑ አቋማቸውን በግልጽ አንፀባርቀዋል።

የመንግሥት ፖሊሲ ከወቅታዊነቱና ከአገር ኢኮኖሚ አንፃር የሚኖረው ተፅዕኖና መልካም ዕድል ላይ ሐሳባቸውን የሰነዘሩ የኢኮኖሚና የሕግ ባለሙያዎች የውጭ ባንኮቹ እንዲገቡ የሚያስችል የፖሊሲ ውሳኔ መፅደቁ ላይ ቅሬታ የላቸውም። በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ከሞላ ጎደል ሁሉም ባለድርሻ አካላትና ባለሙያዎች ዘርፉ ለውጭ ኩባንያዎች መፈቀዱ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ያምናሉ፡፡ 

ይሁን እንጂ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ የመሻታቸውን ያህል ረቂቅ ሕጉ ይፋ ከሆነ በኋላ ግን ክፍተቶች እንዳሉ በመገንዘባቸው ረቂቁ ደግሞ መፈተሽ እንዳለበት በመወትወት ላይ ናቸው፡፡ በዚህ ረቂቅ ላይ ሐሳባቸውን እየሰጡ ካሉት የባንክ ባለሙያዎች መካከል የአሃዱ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ እሸቱ ፋንታዬ አንዱ ናቸው፡፡ 

ሐሳባቸውን ለሪፖርተር ያጋሩት አቶ እሸቱ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ መፈቀዱ አግባብ መሆኑን ያምናሉ፡፡ ነገር ግን የውጭ ባንኮች እንዲገቡ የተፈለገበትና የእነሱ መግባት የሚያስገኘው ጥቅም ተብሎ በመንግሥት በኩል የተዘረዘሩ አንኳር ነጥቦች ትክክል ናቸው ብለው አያመኑም፡፡ ስለዚህ መንግሥት አሁን ባወጣው ረቂቅ መመርያ መሠረት በተለይ የውጭ ባንኮች ሙሉ በሙሉ እንዲገቡ ቢፈቀድ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል የሚል እምነት አላቸው፡፡ ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎችም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ የመሻታቸውን ያህል እንዲገቡ የሚፈቀድበት መንገድ ግን ለባንኮች ብቻ ሳይሆን አገርንም ይጎዳል የሚል ሥጋታቸውን በተለያዩ መንገዶች ገልጸዋል፡፡

እነዚህ የውጭ ባንኮች በየትኛውም መንገድ ይግቡ ሊሠሯቸው የሚችሉና መሥራት የሌለባቸው ሥራዎች መገደብ አለበት የሚሉት አቶ እሸቱ እንደ ምሳሌ የሚያነሱትም በወጪ ንግድ ሥራ ላይ እንዲሰማሩ ከተፈቀደ አገር በቀል ባንኮች ላይ አደጋው የከፋ ነው ይላሉ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያሉና ሌሎች በኢንዱስትሪው የቆዩ የግል ባንኮች አንድ ሦስተኛ ገበያቸው ከወጪ ንግድ ጋር የተያያዘ በመሆኑ የውጭዎቹ ባንኮች በዚህ ሥራ ይሰማሩ ከተባለ እነዚህ የአገር ውስጥ ባንኮች በከፍተኛ ደረጃ ተጎጂዎች ስለሚሆኑ ከዚህ በኋላ የሚወጣው መመርያ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን በጥንቃቄ አጢኖ ማስተካከያ የማያመጣ ከሆነ የውጭ ባንኮች መግባት ከሚያስገኘው ፋይዳ ይልቅ ጉዳቱ ሊያይል ይችላል ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ 

የውጭ ባንኮች መግባት አለባቸው በሚል ለዓመታት ሲሞግቱ የነበሩት ጉምቱው የፋይናንስ ባለሙያ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ለሪፖርተር እንደገለጹት ደግሞ፣ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ መንግሥት መወሰኑ የሚደገፍ ብቻ ሳይሆን በእሳቸው እምነት የዘገየ ውሳኔ ነው።

ነገር ግን የውጭ ባንኮች ከመግባታቸው በፊት ሊደረግ የሚገባውን ዝግጅትና ጥንቃቄ የተመለከተ ምክረ ሐሳብ ለመንግሥት ሲያቀርቡ ቢቆዩም መንግሥት ለእነዚህ ምክረ ሐሳቦች ተገቢውን መልስ ባለመስጠቱ የአገር ውስጥ ባንኮችና ሌሎች ባለድርሻዎች ሥጋት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።

በመሆኑም የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡበት መንገድ ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን ይገባል የሚለውን ሐሳብ እሳቸውም እንደሚጋሩት ጠቁመዋል። አቶ ኢየሱስ ወርቅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሰሞኑን ያወጣው አንድ መመርያ በማስታወሰውም የውጭ ባንኮች ይግቡ እየተባለ በሌላ መንገድ ይህንን የሚፃረሩ መመርያዎችን ማውጣት አተገባበሩ ላይ ችግር ሊያመጣ እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡ 

‹‹አንዳንድ ሁኔታዎችን ስናይ አሁንም ከቀደመው አሠራር ያልወጣን መሆኑን ያሳያል›› የሚሉት አቶ ኢየሱስወርቅ፣ የውጭ ባንኮች ይግቡ እየተባለ ባለበት ወቅት ብሔራዊ ባንክ ተመልሶ ባንኮች ከሚያበድሩት ገንዘብ ላይ ሃያ በመቶ የትሪዥሪ ቦንድ (የግምጃ ቤት ሰነድ) ግዙ ብሎ ማስገደድ ነገሮችን ያደበላልቃል ብለዋል፡፡ እንዲህ ያሉ መመርያዎችን ማውጣት ቅራኔ ያለው ነገር በመሆኑ ጉዳዩን በጥንቃቄ ማየት ተገቢ እንደሚሆን ይመክራሉ፡፡ 

እንዲህ ያሉ መመርያዎች እየወጡ የትኛው የውጭ ባንክ ወደ ኢትዮጵያ ሊገባ ይችላል? የሚል ጥያቄ የሚያነሱት አቶ የኢየሱስወርቅ እንዲህ ያሉ የተዘበራረቁ መመርያዎች እንዴት እንደሚወጡ ለመገንዘብ እንደሚቸግራቸውና እንደሚያስገርማቸው ይገልጻሉ። በዚሁ ጉዳይ ላይ ሲቀጥሉም፣ ብሔራዊ ባንክ ሰሞኑን ያወጣው መመርያ በግልጽ እያለ ያለው በዘጠኝ በመቶ ወለድ ያበደሩ ባንኮች ከሰጡት ጠቅላላ የብድር መጠን ሃያ በመቶ የሚሆነውን የግምጃ ቤት ቦንድ በዝቅተኛ ወለድ እንዲገዙ የሚያስገድድ እንደሆነ ያስረዳሉ። ብሔራዊ ባንክ ባንኮችን እንዲህ ዓይነት ዝቅተኛ ወለድ የሚከፈልበት ቦንድ እንዲገዙ እያስገደደ እሱ ግን የገንዘብ እጥረት ለገጠማቸው ባንኮች ለሚሰጠው ብድር በ16 በመቶ ወለድ የሚያስከፍልበት የተዛባ አሠራር መፈጠሩን ተችተዋል። ይህ የትኛውም ዓለም የሌለ አሠራር እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ኢየሱስወርቅ፣ እንዲህ ያሉ የተዘበራረቁ አሠራሮችን እየተገበሩ የውጭ ባንኮችን ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ መጋበዝ ብዙ ርቀት አያስጉዝም ሲሉ ይከራከራሉ። በመሆኑም አጠቃላይ የብሔራዊ ባንክ አካሄድ ቀድሞ ሲጓዝበት ከነበረው መንገድ የማይለወጥ ከሆነ የውጭ ባንኮችን ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ማድረግ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

የውጭ ባንኮች መግባት ጠቀሜታና ተግዳሮቶችን በተመለከተ በተሰናዱ የውይይት መድረኮች ላይ የብዙዎች አስተያየት ሆኖ ከቀረቡት ነጥቦች መካከል የውጭ ባንኮች እንዲገቡ የተፈቀደበት ወቅት ተገቢ አይደለም የሚለው ይገኝበታል፡፡ ይህንን ሐሳብ ብዙ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይገዙታል፡፡ እዚህ ሐሳብ ላይ ጠንከር ያለ ሐሳባቸውን ካቀረቡ የባንክ የሥራ ኃላፊዎች መካከልም የኅብረት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ መላኩ ከበደ ይገኙበታል፡፡ የውጭ ባንኮች በዚህ ወቅት መግባታቸው አደጋ ሊኖረው ከሚችልባቸው ምክንያቶች አንዱ ባልተረጋጋ ኢኮኖሚ ውስጥ እነዚህን ባንኮች ማስገባት ኢኮኖሚው ላይ ጭምር ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ያመለክታሉ።

አገሪቱ ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚው ችግር ውስጥ ባለችበት ወቅት ይህንን ዕርምጃ መውሰዱ ኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩ አይቀርም በማለት የተለያዩ አስረጂዎችን በመጥቀስ ተከራክረዋል። የውጭ ባንኮች ይገባሉ በሚል ባንካቸው እየተዘጋጀ ቢሆንም ፖሊሲው ለመተግበር የተመረጠው ወቅትና አገራዊ ሁኔታ ላይ ሥጋት እንዳላቸው አቶ መላኩ አመልክተዋል፡፡ ይህንን የአቶ መላኩን ሐሳብ የሚያጠናክር ምልከታቸውን የሰጡት ሌላው የፋይናንስ ባለሙያ ደግሞ ኬንያ ከዚህ ቀደም ባልተረጋጋ ኢኮኖሚ ውስጥ ሆና የውጭ ባንኮችን አስገብታ ከ30 ያላነሱ ባንኮች ከገበያ ውጭ እንደሆኑባት ጠቅሰዋል፡፡ ስለዚህ ባልተረጋጋ ኢኮኖሚ ውስጥ በችኮላ የሚካሄድ አሠራር ሊኖረው የሚችለውን ተፅዕኖ መፈተሽ ከብዙ አደጋ ያድናል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ታዋቂው የኢኮኖሚ ባለሙያ ዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር) የሰጡት አስተያየትም ከፋይናንስ ተቋማቱ መሪዎች የሚመሳሰል ሲሆን፣ እሳቸውም የውጭ ባንኮችን በዚህ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን አይደግፉትም፡፡

የተደረጉ ጥናቶችን ዋቢ በማድረግ የማክሮ ኢኮኖሚ ችግር ባለበት ወቅት የዋጋ ንረት ገዝፎ በሚታይበትና ጦርነት ውስጥ ባለ አገር ለውጭ ባንኮች በር መክፈት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል በማለት የብዙዎቹን ሐሳብ የበለጠ ያጠናከረ ሙያዊ ትንታኔያቸውን ሰጥተዋል፡፡ 

‹‹መንግሥት ደካማ በሆነበት ጊዜ ነው ይህንን ውሳኔ የወሰደው፤›› የሚሉት አቶ ኢየሱስወርቅም፣ የውጭ ባንኮችን ማስገባት የሚመከረው አገሪቱ እንዲህ ዓይነት የኢኮኖሚ አጣብቂኝ ውስጥ ሳትገባና የውጭ ምንዛሪ ችግሩም ዓይኑን አፍጥጦ ሳይመጣ ነበር ብለዋል።

በተለይ መንግሥት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር መክሮ እንዳልሆነ አንዳንድ ውሳኔዎቹ የሚያመለክቱ መሆኑን የገለጹት አቶ መላኩ፣ ዋናው ጉዳይ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት በሌለበት የውጭ ባንኮች መግባት እንደማይኖርባቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ጭምር የሚስማሙበት በመሆኑ ይህንን ገዥ ሐሳብ መንግሥት በግብዓትነት ሊጠቀምበት ይገባል ይላሉ፡፡ ወቅታዊውን የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ ለማረጋጋት ዓመታት ይወስዳል በሚል ዕሳቤ የውጭ ባንኮች አሁን እንዲገቡ ተፈልጎ ከሆነም ትክክል እንዳልሆነ አስተያየት ሰጪዎቹ ሞግተዋል።

ማክሮ ኢኮኖሚው ባልተረጋጋበት ሁኔታም ቢሆን ይግቡ ከተባለ ደግሞ ትግበራው ብልጠትን የተላበሰ መሆን እንዳለበት መክረዋል። መንግሥት የውጭ ባንኮች እንዲገቡ ሲፈቅድ አምስት ግቦችን ያስቀመጠ መሆኑን የገለጹት አቶ መላኩ የተቀመጡት ግቦች ምን ያህል አዎንታዊ ናቸው የሚለው ጉዳይ ላይ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ መንግሥት የውጭ ባንኮች እንዲገቡ ሲወስን ያስቀመጣቸው ግቦች ተደራሽነትን ለማስፋት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለማቃለል፣ ቴክኖሎጂን ወደ አገር ለማስገባት፣ የሠራተኞች ቁጥር ዕድል ለመፍጠርና የብሔራዊ ባንክን አቅም ለማሳደግ የሚሉ ናቸው፡፡

የውጭ ባንኮች በፋይናንስ ተደራሽነትን ለማስፋት አስበው ይመጣሉ የሚል እምነት እንደሌላቸው የተናገሩት አቶ መላኩ ሌሎች እንደ ግብ የተቀመጡትን ለማሳካትም ቢሆን መንግሥትም ሆነ ብሔራዊ ባንክ የሚያወጧቸው መመርያዎች ወሳኝ እንደሆኑ ያመለክታሉ፡፡ 

ብዙዎች የባንክ የሥራ መመርያዎችና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የተቹትና አስተያየት የሰጡበት ጉዳይ መንግሥት እንደ ግብ ካስቀመጣቸው አምስት ጉዳዮች መካከል ‹‹የውጭ ባንኮች መግባት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን አቅም ያሳድጋል›› የሚለው ነው፡፡ 

ብሔራዊ ባንክ ራሱ ተዘጋጅቶ አቅሙን አሳድጎ መጠበቅ አለበት እንጂ አቅሙን የሚያሳድገው የውጭ ባንኮች ሲገቡ ነው የሚለው ጉዳይ ተገቢ እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡ 

በዚህ ሐሳብ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡት አቶ አስፋው የውጭ ባንኮች ይግቡ ተብሎ ከገቡ በኋላ ተቆጣጣሪው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አቅሜን አሳድጋለሁ ወይም የባንኮቹ መግባት ለአቅም ግንባታ ያግዛል መባሉን አይስማሙበትም፡፡ ቀድሞ መዘጋጀት ሲገባው ከገቡ በኋላ አቅም እፈጥራለሁ ማለት ብዙ ነገሮችን ሊያበላሽ ይችላል የሚል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

ይህ ፖሊሲ በዚህ ወቅት ከመተግበር አንፃር ብዙ ሥጋቶች እንዳለባቸው የሚያመለክቱት አቶ እሸቱ በተለይ ባንኮች አሁን ባሉበት ቀና ለዓለም አቀፍ ውድድር እንዲዘጋጁ በመንግሥት ፖሊሲ ልምድ እንዲኖራቸው አለመደረጉ በመሆኑ አሁንም በጥድፊያ ይግቡ ማለት ስህተት ውስጥ ሊከት የሚችል በመሆኑ ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ባንኮች በዛሉበት ጊዜ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ መፈቀዱ ላይ ጥያቄ የሚያነሱት በፖሊሲ ሀብት ሰብሳቢ ብቻ ሆነው እንዲኖሩ ተፈርዶባቸው ቆይተው በዚህ በዛለው ጡንቻቸው ከትልልቅ ባንኮች ጋር እንዲሮጡ መደረጉ አግባብ ነው ብለውም አያምኑም፡፡ ስለዚህ ይህ ፖሊሲ እንዲተገበር የተፈለገበት ጊዜ አደገኛ እንደሆነም በመግለጽ በመንግሥት እንደ ግብ የተቀመጠው አምስት ጉዳዮችን መተግበር አይደለም ጉዳታቸው ሊያመዝን እንደሚችል የተያዩ ምሳሌዎችን ጠቅሰው አስረድተዋል፡፡ 

ብዙዎች መንግሥት የውጭ ባንኮችን ለማስገባት የተጣደፈበትን ምክንያት አሁን ካለው የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር ያያይዙታል፡፡ በፖሊሲውም ላይ ይህ ሐሳብ የተንፀባረቀ ስለሆነ አሁን ያለውን ችግር ለመውጣት በጥድፊያ የሚፈጸም ነገር ተገቢ ያለመሆኑን የሌሎች አገሮችን ልምድ በማየት አገባባቸው ደረጃ በደረጃ እንዲሆን ይመክራሉ፡፡ በተለይ ሙሉ በሙሉ እንዲገቡ ከመፍቀድ በጆይንት ቬንቸር እንዲገቡ ማድረግ ይመረጣል ተብሏል፡፡ በኢትዮጵያ ባንክ ውስጥ እስከ 40 በመቶ ድርሻ እንዲኖቸው በረቂቁ የተገለጸው ድንጋጌም መፈተሽ እንዳለበት የጠቆሙ የፋይናንስ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች አሉ፡፡  

የሕግ ባለሙያው አቶ ፈቃዱ ጴጥሮስ የውጭ ባንኮች ከመግባታቸው በፊት መስተካከል ካለባቸው ድንጋጌዎች ውስጥ አንዱ አንደ የባንክ አክሲዮን በአንድ ባንክ ውስጥ የሚኖረው የባለቤትነት ድርሻን የሚመለከተው ድንጋጌ ነው፡፡ 

የውጭ ባንኮችን በሚፈቅደው ሕግ አንድ የውጭ ኩባንያ 30 በመቶ ድርሻ እንዲኖረው የሚፈቅድ ከሆነ ይህ ለኢትዮጵያውያንም መፈቀድ አለበት ብለዋል፡፡ 

ብሔራዊ ባንክን አቅም በተመለከተ መደረግ አለባቸው ብለው ከገለጹት ውስጥ እንደ ኢንሹራንስ ኩባንያ የፋይናንስ ሊዝና ሌሎች ዘርፎችን ከእርሱ ቁጥጥር ውጪ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የሚቆጣጠራቸው ነገሮች የበዙ ስለሆነ ይህንን በመቀነስ አቅሙን ማሳደግ ይቻላል ይላሉ፡፡ 

አቶ ኢየሱስወርቅም ሆኑ አቶ እሸቱ አሁን ኢትዮጵያ በገባችበት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ቁልፍ ምክንያት የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀማችን ጉድለትና ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ለማመንጨት ያሉ በርካታ ዕድሎችን ለመጠቀም አለመቻል ነው፡፡ 

የውጭ ባንኮች ውሳኔ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅፍ ብቻ መሆን እንደሌለበት የሚያምኑት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ለውጭ ምንዛሪ ችግሩ መባባስ ምክንያቱ ምንድነው ብሎ በመጠየቅ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ይገባል ይላሉ፡፡ በሃምሳና በመቶ ዶላር ኤልሲ ተፍተው ተሽከርካሪዎች እየገቡ እንዴት መጡ የሚል ጥያቄ ማቅረብ ባለመቻሉ መንግሥትም እንዲህ ያለው ሕገወጥ ተግባር እያወቀ ዝም ብሎ የውጭ ምንዛሪ ዙሪያ ሕገወጥ ተግባር እንደሚፈጸም ማስታወሱ ተገቢ ነው፡፡ 

ወደውጭ የሚላክ ቡናና ሌሎች የውጭ ንግድ ምርቶች ከዋጋቸው በታች በኪሳራ ሲላኩ እየታወቀ ይህ ያለመታረሙ የአገሪቷን የውጭ ምንዛሪ አመንምኖታል፡፡ ስለዚህ እጥረቱ ብዙ ምክንያት ቢኖረውም ተደራርቦ የመጣው ችግር ዛሬ ደርሷል ብለው ያምናሉ፡፡ 

ወቅታዊውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ ባንኮችን በቶሎ መሸጥ ታስቦ ከሆነ ትልቅ ስህተት ነው የሚሉት ሌላው አስተያየት ሰጪ ደግሞ ይህ የአገሪቱን ባንኮች ዋጋ ማሳነስ እንዲሁም በውጭ ባንኮች እንዲዋጡ ማድረግ ነው ይላሉ፡፡ 

ከውጭ ባንኮች መግባትና አገባባቸውን በተመለከተ እየተሰነዘሩ ያሉ አስተያየቶች በዚህ ብቻ የሚወሰኑ ያለመሆኑን ሪፖርተር እየሰበሰባቸው ካሉ መረጃዎች ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ ባንኮች ሼራቸውን ለውጭ ባንኮች መሸጥ የሚችሉ ከሆነ ሽያጩ የሚፈጸመው በውጭ ገንዘብ (በዶላር) እንደሆነ ይታመናል፡፡ ከሽያጩ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ እንዴት ጥቅም ላይ ይውላል የሚለው ነገር ሌላ አነጋጋሪ ሆኖ የሚቀርብ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ኢየሱስወርቅ ከዚህ ቀደም ሼራችንን ለትውልደ ኢትዮጵያውያን ለመሸጥ ስንዘጋጅ በውጭ ምንዛሪ ከተገኘው ሽያጭ 70 በመቶውን ለብሔራዊ ባንክ አስገቡ መባሉ የተፈጠረውን ዓይነት ችግር እንዳይኖር ይሻሉ፡፡ 

ባንኮች ሼራቸውን ሲሸጡ አሁን ባለው ሕግ 70 በመቶውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እወስዳለሁ ካለ አግባብ እንደማይሆንም አቶ ኢየሱስወርቅ ይሞግታሉ፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ እነዚህ ባንኮች የሚሸጡት ካፒታላቸውን ነው፡፡ ካፒታላቸውን በዶላር ሸጠው ገበያችሁን የሚትቀበሉት በብር ነው ማለት ፈጽሞ አግባብ አይሆንም፡፡ 

መንግሥት 70 በመቶውን እወስዳለሁ ካለ ባንኮችን ማጽደቅ ነው፡፡ ‹‹የባለቤት ድርሻችንን ሸጠን የሚገኘውንም የውጭ ምንዛሪ ባንኮች ራሳቸው እንዲጠቀሙበት ማድረግ አለበት፤›› በማለት ከድርሻ ሽያጩ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ለብሔራዊ ባንክ መግባት የለበትም ብለው ይሞግታሉ፡፡ ባንኮቹ የሚሸጡት ባለቤትነት ስለሆነ በዕድሜያቸው ያፈሩት ሀብት ስለሆነ ዶላሩን እንዳይጠቀሙበትና ለዕድገታቸው የሚሆን ሥራ እንዳይሠሩ በማድረግ መጎዳት እንደሌለባቸው አቶ ኢየሱስወርቅ ተናግረዋል፡፡ 

ባለው ሕግ ከሚገኘው የውጭ ምንዛሪ 70 በመቶው ለብሔራዊ ባንክ ይግባ የሚለው መመርያ ካልተስተካከለ ሼር ገዝተው በሚገቡ የውጭ ባንኮች ጭምር ጥያቄ የሚነሳበት እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡ ባንኮቹ ከብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠው ሕግ ካልተለወጠ የትኞቹ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ ያሳስበኛል ያሉት አቶ ኢየሱስወርቅ የውጭ ባንኮች እንዲህ ያሉ ድንጋጌዎችን የማይሹ መሆኑ ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል፡፡ ባንኮች ሼራቸውን ሸጠው የውጭ ባንኮች ከገቡ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ አሁን ባለው ሕግ ሊስተናገድ ይችላል የሚል ግምት ያላቸው አቶ እሸቱ ደግሞ ከሽያጩ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ለባንኮቹ ቢገባ ይመኛሉ፡፡ ሆኖም አሁን ካለው ችግር አኳያ መንግሥት ይህንን ያደርጋል ወይ? የሚለው ጥያቄ ግን ያሳስባቸዋል፡፡

አቶ እሸቱ የውጭ ባንኮች አሁን ላይ መግባት ችግር ያለው መሆኑን ለማስረዳትና የሀብት አጠቃቀማችን ችግሮች ያሉበት መሆኑን ለማሳየት ምሳሌ ያደረጉት በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ የአገሪቱ ባንኮች የሚጠቀሙ ተበዳሪዎች ለ330 ሺሕ የሚሆኑ ብቻ መሆናቸውን መግለጻቸው ነው፡፡ 

የውጭ ባንኮች የአገር ውስጥ ሀብቱን ሰብስበው የሚያበድሩ ከሆነ ግን በዚህ ሥራቸው በጣም ውጤታማ መሆን ቢችሉ እንኳን አገር የመጨረሻው ውጤት አገርን መጉዳት ነው ይላሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህ ባንኮች የራሳችንን ሀብት ለብድር ማቅረብ አግባብ ስለማይሆን ይግቡ ከተባሉ እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ሁሉ መታሰብ እንዳለባቸው ያመለክታሉ፡፡  

የውጭ ባንኮች መግባት ሲታሰብ የባንክ ባለአክሲዮኖችም ሊታሰቡ እንደሚገባ የሚገልጹት አቶ እሸቱ አንዱ መደረግ አለበት ብለው የጠቀሱት ባለአክሲዮቻችን እንዳይጎዱ የውጭ ባንኮች አገባብ ደረጃ በደረጃ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ እንደ ህንድ እንደ ሲሪላንካ ያሉ አገሮችም የውጭ ባንኮችን ያስገቡት ደረጃ በደረጃ በመሆኑ ስለዚህ በኢትዮጵያም በፖሊሲ ስህተት አገርና ባንኮችን የፈጠሩ ባአክሲዮኖችም እንዳይጎዱ ማድረግ ተገቢ ይሆናል ይላሉ፡፡ 

አቶ ኢየሱስወርቅ አሁን እንዲህ ላለው የተዘበራረቀ አካሄድ መፍትሔ የሚሆነው ግን መንግሥት ከኢኮኖሚው እጁን በማውጣት ሥራው በባለሙያዎች ቢሠራ ነው ይላሉ፡፡ 

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው ቴዎድሮስ መኮንን (ዶ/ር)፣ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ ከቀረቡ የተለያዩ አማራጮች ውስጥ ከኢትዮጵያ ባንኮች ጋር በሽርክና መሥራት የሚለው የተሻለ ፋይዳ ያለው መሆኑን ይገልጻሉ። ይህ አማራጭ የአገር ውስጥ ባንኮችን ከማበረታታት አንፃር በሽርክና መሠራቱ የተሻለ ነው ይላሉ፡፡ ውድድርን ከማበረታታት አንፃር ግን የውጭ ባንኮች ቅርንጫፍ ከፍተው ወይም ራሳቸውን ችለው በመምጣት መሥራታቸው የተሻለ ሊሆን የሚችልበት ዕድል እንዳለም ገልጸዋል፡፡

ከቀረቡ አራት አማራጮች እንደየሁኔታቸው ፋይዳቸው የተለያዩ በመሆናቸው የተሻለ የሚባለውን በመምረጥ እንዲገቡ ሊደረግ የሚችል ቢሆንም እስካሁን ግን በግልጽ የተቀመጠ ነገር የለም ብለዋል፡፡ 

ከዚህ ቀደም ባንኮች እንዳይገቡ ይከለከል የነበረው የውጭ ባንኮችን መቆጣጠር ስለማንችል ነው ይባል እንደነበር ያስታወሱት ቴዎድሮስ (ዶ/ር) ይህ ትክክለኛ ነጥብ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ የውጭ ባንኮች ከመግባታቸው በፊት የቁጥጥር አቅምን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ ከገቡ በኋላም ራስን ማጠናከር ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ከዚያም በኋላ ራስን የማጠንከሩ ሥራ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ብዙ የአውሮፓ አገሮች ጠንከር ያለ የቁጥጥር ሥርዓት እንዳላቸው የገለጹት የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው ለምሳሌ የአውሮፓ ባንኮች ቢመጡ እዚያ ያለውን የቁጥጥር ሥርዓት ይዘው ነው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እነሱ ከመጡበት አገር ጋር ግንኙነት ፈጥሮ ቁጥጥሩን ሊያጠብቅ የሚችለበት ዕድል ይፈጥራል፡፡ ይህ ከቁጥጥር አንፃር ከአውሮፓ የሚመጡ ባንኮች እንዲሳቡ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን በአብዛኛው እነዚህ የአውሮፓ አገሮች የሚያገለግሉት በቂ መረጃ ያለባቸው ድርጅቶችን ነው፡፡ ለፕሮዳንስ ሲሉ ይህንን ያደርጋሉ፡፡ ወደ ኢትዮጵያም ሲመጡ ሊያገለግሉ የሚችሉት በጣም ሀብታም የሆነውን ወይም መረጃ ሊያቀርብ የሚችለውን የኅብረተሰብ ክፍል ሊሆን ይችላል፡፡

ከዚህ አንፃር ሲታይ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ የሚመረጡት የአፍሪካ ባንኮች ሊሆኑ እንደሚችሉ ቴዎድሮስ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱም ከታዳጊ አገሮች የሚመጡ ባንኮች ዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍል ያገለገሉ እንዲህ ባለው አሠራራቸው የሚታወቁ ስለሆነ እዚህ ሲመጡ ይህን የኅብረተሰብ ክፍል ለመድረስ ሲሉ የሚፈጥሯቸው አገልግሎቶች እንደሚተገብሩ ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ከአፍሪካ ወይም ከታዳጊ አገሮች የሚመጡ ባንኮች እንዲህ ያለው አገልግሎት ስላላቸው ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ 

ለምሳሌ እንደ ሞባይል ባንኪንግ ያሉ ተደራሽነትን የሚፈጥሩ አገልግሎቶችን ይዘው ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የሚመጡ ባንኮች እንደሚመጡበት ፋይዳቸው የተለያየ ሊሆን ስለሚችል ከሁለቱም ባላንስ አድርጎ መወሰን ያስፈልጋል የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች ግን በተለያዩ መድረኮች እየቀረቡ ያሉትን ሐሳቦች በግብዓትነት የሚጠቀምባቸው መሆኑን በመግለጽ፣ እንደ አደጋ የታዩ በረቂቁ የተገለጹ ድንጋጌዎችንም በመፈተሽ ማሻሻያ የደረሰባቸው እንደሚችል አስታውቀዋል። 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች