Tuesday, February 27, 2024

ስለሰላም ስምምነቱ ምን ተባለ?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በፊት በኢትዮጵያ ይታይ የነበረው ነባራዊ ሁኔታ አሥጊ እንደነበር፣ የጊዜውን ሁኔታ የታዘቡ ወገኖች ይገልጹታል፡፡ አንድ ታዋቂ ፖለቲከኛ፣ ‹‹ይህ ሁሉ የጦር ድግስ የእኔን ሠርግ ለማጀብ ነው ወይ?›› ሲሉ በትዝብት እንደተናገሩት፣ በግራም በቀኝም የሚሰማው ወደ ጦርነት የሚገፋ ነገር ነበር፡፡

አገሪቱ ወደ ጦርነት እንዳትገባ የሚለው የብዙዎች ውትወታ ሰሚ አልነበረውም፡፡ በመንግሥት ወገን በሰላማዊ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች ብዙ እንደነበሩ በርካታ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ የሽማግሌዎች ወደ መቀሌ መመላለስ ብቻውን ግን የጦርነቱን መጀመር አላስቀረውም፡፡ የሕወሓት ሰዎች በራሳቸው አንደበት እንደተናገሩትም፣ በሰሜን ዕዝ ላይ የተሰነዘረው ከባድ ጥቃት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የጦርነት ማስጀመርያ ፊሽካ ሆነ፡፡

ጦርነቱ ኢትዮጵያን ለሁለት ዓመታት ከባድ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት አደረሰባት፡፡ የኢትዮጵያውያን መጨፋጨፍ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ዋነኛ ርዕስ ሆነ፡፡ በዓለም አደባባዮች የኢትዮጵያ ስም ጎደፈ፡፡ ወትሮም ከድህነትና ከግጭት ተላቃ የማታውቀው አገር ዳግም ከዕልቂት ጋር ስሟ ይነሳ ጀመር፡፡

ኢትዮጵያውያን ይህን የዕልቂት አዙሪት ለማስቆም ‹‹ሁለት ዓመታት ፈጀ›› ሲሉ አንድ ታዛቢ በማኅበራዊ ሚዲያ እንደከተቡት ሁሉ፣ አሰቃቂውን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ለማብረድ ብዙ ውጣ ውረድ መታለፍ ነበረበት፡፡ ይህ ሁሉ ታልፎ የጦርነቱ መነሻ ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ሁለተኛ ዓመቱን ሲደፍን በጎ ወሬ ከደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ተሰማ፡፡

ረቡዕ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት፣ ከሰሜን ኢትዮጵያ አልፎ ለመላው አገሪቱ የሰላም አየር እንዲነፍስ የሚያደርግ ዕርምጃ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ የሰላም ስምምነቱን መፈረም ተከትሎ ከተለያዩ ወገኖች የተሰሙ አስተያየቶችም ቢሆኑ ይህንን ተስፋ የሚያጎሉ ነበሩ፡፡

የሰላም ሒደቱን በዋናነት የመራው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ሙሳፋቂ ማህማት የሰላም ስምምነቱን የተፈራረሙትን ሁለቱን ወገኖች በማመሥገን ነበር፣ በኢትዮጵያ ሰላም እንደሚሰፍን ያላቸውን ተስፋ የተናገሩት፡፡

መንግሥትን በመወከል የስምምነቱ ፈራሚ የነበሩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ የደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር)፣ መላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡

‹‹ከተቃጠልንም በኋላ ቢሆን ተምረናል፡፡ ልናስወግደውና ልናስቀረው ይገባ የነበረ ቀውስን ማስቆም ችለናል፡፡ በአስቸጋሪ መንገድም ቢሆን ተምረናል፡፡ አሸናፊዎቹም ሰላም ራሱና ኢትዮጵያ ሆነዋል፡፡ ሁላችንም ቁስላችንን ማከክ አቁመን ወደፊት መጓዝ ይኖርብናል፤›› በማለት ነበር ሬድዋን በትዊተር ገጻቸው መልዕክት ያስተላለፉት፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን አገራቸው አሜሪካ የሰላም ስምምነቱ መፈረሙን በደስታ እንደምትቀበል ሲገልጹ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሜሪካ ቋሚ መልዕክተኛ ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ አገራቸው የስምምነቱን ተግባራዊነት እንደምታግዝ ቃል ገብተዋል፡፡

በጃፓን የኤርትራ አምባሳደር እስጢፋኖስ አፈወርቂ (አምባሳደር) የሰላም ስምምነቱ መፈረም እንዳስደሰታቸው ከገለጹት መሀል አንዱ ነበሩ፡፡ ‹‹በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኤርትራ፣ የኢትዮጵያ፣ የሶማሊያና የሱዳን ዜጎች የአፍሪካ ቀንድን ለመቆጣጠር ልዕለ ኃያላን አገሮች በሚያካሂዱት የተልዕኮ ጦርነት ብዙ ደም፣ ላብና ዕምባ ከፍለዋል፤›› ሲሉም ነበር የተናገሩት፡፡

ጸሐፊና ጋዜጠኛ ሎውረንስ ፍሪማን የሰላም ስምምነቱ መፈረም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ ለአፍሪካም ጭምር ታላቅ ድል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጸሐፊና ጋዜጠኛ ጄፍ ፒርስ በበኩላቸው፣ ‹‹ስምምነቱ በአሜሪካ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወይም በአውሮፓ ኅብረት ሳይሆን በራሳቸው በአፍሪካውያን ጥረት የተካሄደ መሆኑ ዘላቂ የሰላም ዕርምጃ እንደሚሆን  ተስፋ አለኝ፤›› በማለት ነበር ሐሳባቸውን ያጋሩት፡፡

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዛዎ ዚዩዋን (አምባሳደር)፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ ለሰላም ስምምነቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡ የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለስምምነቱ ያለውን ድጋፍ አስታውቋል፡፡ የጂቡቲ ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ ስምምነቱን ሲያደንቁ፣ የሴኔጋል ፕሬዚዳንት ማኪ ሳሊም በተመሳሳይ ድጋፋቸውን ገልጸዋል፡፡

ዓለም አቀፍ ዕውቅና የሌላት የሶማሌላንድ ምክትል ፕሬዚዳንት አብዱራህማን ሳይሊሲ በአማርኛ ጭምር ነበር፣ ‹‹በምሥራቅ አፍሪካ ሰላም ይኑር፤›› ሲሉ በስሜት የተሞላ የደስታ መግለጫ ያወጡት፡፡

የላይቤሪያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ፣ ከአደራዳሪዎቹ አንዷ የነበሩት የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ፉምዚሌ ምላምቦ ንጉካ፣ እንዲሁም ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦችና ፖለቲከኞች ስምምነቱን አድንቀዋል፡፡ የአውሮፓ ኅበረት የውጭ ግንኙነት አገልግሎት ተወካዩ ጆሴፍ ቦሬል ደግሞ ስምምነቱን በበጎ እንደሚቀበሉት በመጥቀስ፣ በአስቸኳይ በተግባር መተርጎም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ይህ ሁሉ ሲነገርለትና ሲባልለት የከረመው የሰላም ስምምነት ምን ይዟል? እንዲሁም በተጨባጭ በተግባር መተርጎም እንዴት ይችላል? የሚለው ጉዳይ ደግሞ አሁን ጎልቶ እየተነሳ ያለ ጥያቄ ሆኗል፡፡

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር እምቢአለ በየነ (ረዳት ፕሮፌሰር) እንደሚናገሩት፣ የሰላም ስምምነቱ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን የጂኦ ፖለቲካ ተፅዕኖ ይቀንሳል፡፡

‹‹ምዕራባውያኑ ሕወሓትን በኢትዮጵያ አጀንዳቸውን ለማስፈጸሚያነት ለመጠቀም የሚችሉበትን ዕድል ያሳጣቸዋል፤›› ሲሉ ያክላሉ፡፡ ‹‹ሕወሓት ትጥቅ ለመፍታት ከተስማማ ከሰመ ማለት ሲሆን፣ ይህም ምዕራባውያኑ ለተልዕኮ ጦርነታቸው ሊጠቀሙበት አይችሉም ማለት ነው፤›› በማለትም ይናገራሉ፡፡ ሕወሓት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ችግሬን እፈታለሁ ብሎ ከተስማማ፣ እንዲሁም ትጥቁን ፈቶ ለመኖር ዝግጁ ከሆነ እሱን መጠቀሚያ የሚያደርጉ ኃይሎች፣ ‹‹ጣልቃ ገብነታቸውንና የእጅ አዙር ጦርነታቸውን ባያቆሙ እንኳን ሕወሓትን የሚጠቀሙበት ዕድል አይኖርም፤›› በማለት ነው ያስረዱት፡፡

ሕወሓት ስምምነቱን ከመፈረም ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለው የሚናገሩት የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ምሁሩ አሰፋ አዳነ (ዶ/ር)፣ ቡድኑ ከመጥፋት እንደሚሻል አስቦ ያደረገው መሆኑን ያወሳሉ፡፡ ‹‹ስምምነት መደረጉ ትልቅና በጎ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ያኔ ድሮ ቢደረግ ኖሮ ስንት ንብረትና ሕይወትን ከጥፋት መታደግ ይቻል ነበር፤›› ሲሉ በቁጭት ይናገራሉ፡፡ በሌላም በኩል ሕወሓቶች ወደ ስምምነቱ የመጡት ራሳቸውን ከተጠያቂነት ለማውጣትና ለረዥም ዘመን በተለያየ መንገድ ያካበቱትን ሀብት ያለጠያቂ ለመጠቀም በማሰብ ነውም ይላሉ፡፡

‹‹በስምምነቱ ግጭት መቆሙ ደስ የሚል ቢሆንም፣ ነገር ግን ለብዙ ውድመትና ዕልቂት ምክንያት የሆነ ኃይል ከተጠያቂነት እንዳያመልጥ ሥጋት አለኝ፡፡ በስምምነቱ ደስ ቢለኝም ለግጭት መንስዔና የፖለቲካ ውዝግቦች ምንጭ የሆኑ ጥያቄዎች ሳይመለሱ እንዳይታለፉ ሥጋት አለኝ፤›› ብለዋል፡፡

በእሳቸው እምነት እንዲህ ያለ ስምምነት ዋና ዋና ወይም ጥቅል ጉዳይ የሚቀመጥበት ቢሆንም፣ ነገር ግን አፈጻጸሙን በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮች በሀቀኝነት በቶሎ ለሕዝብ መገለጽ ይኖርባቸዋል፡፡

‹‹‹መንግሥት ሳይፈራ፣ ሳይደብቅም ሆነ ሳይሸማቀቅ ከእስካሁኑ በተሻለ ግልጽነት የስምምነቱን ምንነትና ዝርዝር ሒደት ካላስቀመጠ ግርታን በሚፈጥሩ ጉዳዮች የተነሳ ምናልባትም ስምምነቱን እንዳናጣ ያሠጋል፤›› በማለትም የፈጠረውን በጎ ተስፋ ከእነ ሥጋቱ አጋርተዋል፡፡

የሕግ ባለሙያው አቶ አንዷለም በዕውቀቱ በበኩላቸው፣ ከስምምነቱ ኢትዮጵያ አገኘቻቸው ያሉትን መሠረታዊ ጥቅሞች በመግለጽ ነው አስተያየታቸውን የሚሰጡት፡፡

‹‹ሕወሓት በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ትጥቅ አልባ የሆነ ኃይል ሊሆን ነው፡፡ በታሪኩ ሁሉንም ዓይነት የፖለቲካ ፍላጎቱን በትጥቅና በኃይል ለማስመለስ ሲንቀሳቀስ የኖረ ኃይል ትጥቅ መፍታቱ ትልቅ አጋጣሚ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል፣ ‹‹ሕወሓት የፌዴራል መንግሥቱን ሥልጣንና የፌዴራል ሥርዓቱን በራሱ ምርጫ በማድረግ ሲገዳደር ነበር፡፡ በዚህ ስምምነት ግን ይህ የሕወሓት ፍላጎት እንዲገደብ ተደርጓል፤›› ሲሉም ያስረዳሉ፡፡ ይህ ብቻም አይደለም በስምምነቱ መሠረት ሕወሓት ከውጭ ኃይሎች ጋር በራሱ ግንኙነት በመፍጠር ለአገር ሰላምና መረጋጋት ችግር የሚሆኑ እንቅስቃሴዎች ማድረግ እንደማይችል ነው አቶ አንዷለም የጠቆሙት፡፡

ከግራም ከቀኝም ብዙ ስሜቶችና አስተያየቶችን እያስተናገደ የሚገኘው ስምምነት አንዳንድ ሥጋት የሚያጭሩ ግምቶችንም አላጣም፡፡

የግጭት ምክንያት ስለሆኑ ጉዳዮች በሕገ መንግሥቱ ይፈታሉ ከሚል ጥቅል ድምዳሜ ውጪ፣ ዝርዝር ማዕቀፎች አለማስቀመጡ የስምምነቱ ጎዶሎ ተብሎ እየተነሳ ነው፡፡ የሽግግር ጊዜ ፍትሕን በተመለከተ የጦርነቱ መነሻና የግጭት ምንጭ የሆኑ አካላት ተጠያቂነት ስለሚሆኑበት ሁኔታም ስምምነቱ የዘረዘረው ነገር የለም የሚል ጥያቄም ይነሳል፡፡ በስምምነቱ ላይ የሕወሓት ትጥቅ መፍታት፣ እንዲሁም ከማኅበረሰቡ ጋር የመቀላቀል ጉዳይ በግልጽ ቢሰፍርም የሕወሓት ህልውና መቀጠል አለመቀጠልን በሚመለከት ምንም ውሳኔ አለመቀመጡ እንደ አንድ ጉድለት እየተጠቀሰም ነው፡፡

ከዚሁ የስምምነት ጉዳይ ጋር በተያያዘ ስምምነቱ ተፈጻሚነት የሚኖረው ስምምነቱን በፈረመው ሕወሓት ላይ ወይስ በመላው ትግራይ የሚለው አለመመለሱን አንዳንዶች በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ስምምነቱ የተደረገው በሁለት የፖለቲካ ኃይሎች (ማለትም መንግሥትን በሚመራው ብልፅግናና ሕወሓት) መካከል? ወይስ በሕዝቦች መካከል? ሲሉም የሚጠይቁ ወገኖች አሉ፡፡

አንዳንዶች በበኩላቸው የአፍሪካ ኅብረት ምን ዓይነት የማስፈጸም አቅምና ብቃት ኖሮት ይህን ውስብስብ ስምምነት በተግባር ለመተርጎም ይችላል? ሲሉ ጠንካራ ጥያቄ እያነሱ ነው፡፡

ሌሎች ደግሞ በሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ ይፈታሉ የተባሉ የሕግ ትርጓሜ የሚሹ አጨቃጫቂ ነጥቦች ሄደው፣ ሄደው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ላይ ቢወድቁ ምክር ቤቱ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ያለውን አቅምና ብቃት ከወዲሁ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ያስገባሉ፡፡

የተዘለለ፣ በዝርዝር ያልተቀመጠ፣ መልስ ያላገኘም ሆነ ያልተብራራ ጉዳይ በስምምነቱ ውስጥ አለ የሚለው ክርክር የቀጠለ ቢሆንም ሆኖም ከስምምነቱ ኢትዮጵያ ብዙ አትርፋለች የሚለው ግን ሚዛን የደፋ ይመስላል፡፡

የግራካሱ ተራራዎች ከጥይት ድምፆች ይገላገላሉ፣ የወልቃይትና ተከዜ ሸለቆዎች የሰላም አየር ይነፍስባቸዋል የሚሉ በጎ አስተያቶች በስምምነቱ ዙሪያ እየተደመጡ ነው፡፡ ልጆች ያለ ፍርኃት ወደ ትምህርት ቤት መሄድ የሚችሉበት ዕድል ይፈጠራል የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ አርሶ አደሩ የዘራውን ይሰበስባል የሚሉም በርካቶች ናቸው፡፡ ስምምነቱ ከሁሉም በላይ በጦርነት ለሁለት ዓመታት የማቀቁትን ትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎችን ዕፎይ የሚያሰኝና ለመላው ኢትዮጵያም እረፍት የሚያስገኝ እንደሆነ የሚገምቱት በርካቶች ናቸው፡፡

የኮተቤ ዩኒቨርሲቲው አሰፋ (ዶ/ር)፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በጦርነት ሲደቅ መቆየቱን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ወንጀል የሠሩ፣ ለግጭትና ለበርካታ ጭፍጨፋ ምንጭ የሆኑ ወገኖች በሰላም ስም ከወንጀል ነፃ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ሥጋት አለኝ፡፡ ይሁን እንጂ የሁሉም ጦርነቶች ማብቂያ መጨረሻው ስምምነት ነው፤›› ይላሉ፡፡ ስምምነቱን በተመለከተ አሻሚ የሆኑና ግርታን የፈጠሩ ጉዳዮችን መንግሥት ማጥራት እንዳለበት ግን ያሳስባሉ፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ሁልጊዜ በታሪኳ ስምምነት በተደረገ ማግሥት ግጭትና ቁርሾ ሲፈጠርባት ይታወቃል፡፡ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በስምምነት በተቋጨ ማግሥት የሆነውን እናስታውሳለን፡፡ አሁንም ቢሆን በስምምነቱ ማግሥት ሌላ ዓይነት ክፍፍልና ውዝግብ እንዳይፈጠር መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በመንግሥት ብቻ ሳይሆን በሕወሓት ወገንም ቢሆንም በስምምነቱ ማግሥት ሌላ የግጭትና የልዩነት በር እንዳይከፈት ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፤›› በማለትም አሰፋ (ዶ/ር) ምክራቸውን አስቀምጠዋል፡፡ ለዚህ ነው ይህ ሁሉ ግጭት የተደረገው? በሚል ቁጭት ወደ ሌላ ንትርክ እንዳይገባ ሁሉም ወገን ከአላስፈላጊ ድርጊት እንዲቆጠብም ያሳስባሉ፡፡

ይህን ሐሳብ የሚጋሩት የሕግ ባለሙያው አቶ አንዷለም፣ ስምምነቱ ለሁሉም ወገን ጥቅም የሚያስገኝ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡ የሕወሓት አለመክሰም ቅሬታ ቢፈጥርም በአንዴ ሊሳካ የማይችል ጉዳይ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በአንድ የስምምነት ሰነድ ብቻ ሁሉም ችግር ይፈታል ብሎ መጠበቅ ተገቢ አይደለም ያሉት አቶ አንዷለም የሕወሓት መክሰም ጉዳይ፣ አጨቃጫቂ አካባቢዎች፣ ሌሎች ጉዳዮች በስምምነቱ በተሻለ መንገድ ተቀምጠዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሕወሓት ይህንን የሰላም ስምምነት ለመፈረም የመጣው ከምን ሁኔታ እንደሆነ እናስታውስ፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ሲደረግ የነበረውን ጫናም አንርሳ፡፡ ኢትዮጵያ ከተደገሰላት ብዙ ጥፋት በዚህ ስምምነት አምልጣለች ነው የምለው፤›› በማለትም ሐሳባቸውን ያጠቃልላሉ፡፡

ይህን የሚጋራ ሐሳብ የሚሰነዝሩት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ እምቢአለ (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ ለኢትዮጵያ እስከ መንግሥት ግልበጣ ሴራ ተደግሶ እንደነበር ነው የተናገሩት፡፡ ‹‹ኢትዮጵያን መቆጣጠር ዓባይን መቆጣጠር ነው፡፡ ዓባይን መቆጣጠር ሱዳንና ግብፅን መቆጣጠር ነው፡፡ ሱዳንና ግብፅን መቆጣጠር ደግሞ የስዊዝ ቦይን መቆጣጠር ነው፡፡ የስዊዝ ቦይን መቆጣጠር ደግሞ ዓለምን መቆጣጠር ነው በሚለው በቆየ የጂኦ ፖለቲካ ዕሳቤ ኢትዮጵያ በጦርነት ተማግዳ መከራዋን ስታይ ቆይታለች፤›› የሚሉት ምሁሩ፣ ይህ ስምምነት ሕወሓትን ለእጅ አዙር ጦርነት የመጠቀም ዕድልን እንደሚያስቀር ነው የተናገሩት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -