Saturday, July 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ውሳኔዎችን ማስፈጸም ላይ ተግዳሮት እያጋጠመው መሆኑን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከታክስ ጋር የተያያዙ አቤቱታዎችን የሚመለከተው የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን፣ በሚሰጣቸው ውሳኔዎች ላይ የአፈጻጸም ተግዳሮቶች እያጋጠሙት መሆኑን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች በፍርድ ቤት ዕግድ ካልተጣለባቸው በስተቀር በ30 ቀናት ውስጥ መፈጸም ያለባቸው ቢሆንም፣ በተለይ የተሻሻሉ ውሳኔዎች በተባለው የጊዜ ገደብ ውስጥ እየተፈጸሙ አለመሆኑ ተገልጿል፡፡ የኮሚሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አያሌው፣ ‹‹አብዛኛውን አቤቱታ እየተቀበልን ያለነው ከዋናው ሥራችን በላይ የአፈጻጸም መዝገብ መክፈት ነው፤›› ሲሉ ማክሰኞ ጥቅምት 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡

የኮሚሽኑን የ2015 ዓ.ም. የመጀመርያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ፕሬዚዳንቱ፣ በሩብ ዓመት ውስጥ ይግባኝ የቀረበባቸው 202 መዝገቦች ውሳኔ እንደተሰጠባቸው ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህ መዝገቦች ውስጥ 128 መዝገቦች ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋር በተያያዘ የቀረቡ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ 74 መዝገቦች በጉምሩክ ከተጣለ ታክስ ጋር የቀረቡ ይግባኞች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ በአራት ወራት ውስጥ ውሳኔ የተሰጠባቸው መዝገቦች 1.26 ቢሊዮን ብር የገንዘብ መጠን እንዳላቸውም ጠቅሰዋል፡፡

ውሳኔ ከተሰጠባቸው መዝገቦች ውስጥ 141 የሚሆኑት ባሉበት የፀኑ መሆናቸውን ለሪፖርተር የተናገሩት አቶ ሙሉጌታ፣ ቀሪዎቹ ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ውሳኔ መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡ ይሁንና በኮሚሽኑ ውሳኔ መሠረት ጉዳያቸው ተፈጻሚ ያልሆነላቸው 55 መዝገቦች፣ በሩብ ዓመቱ ለኮሚሽኑ ቅሬታ ማቅረባቸውን ያስረዱት ፕሬዚዳንቱ፣ ታክስ ይግባኝ ኮሚሽኑ 31 ያህሉ ተፈጻሚ እንዲሆኑ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡ ቀሪዎቹ 24 መዝገቦች ደግሞ አሁንም በሒደት ላይ መሆናቸውን አክለዋል፡፡

የታክስ ይግባኝ ኮሚሽንን ያቋቋመው የ2008 ዓ.ም. የፌዴራል የታክስ አስተዳደር አዋጅ፣ ኮሚሽኑ አቤቱታ በቀረበለት በ120 ቀናት ውስጥ ውሳኔ እንደሚያሳልፍና የውሳኔው ግልባጭ በሰባት ቀናት ውስጥ ለሁለቱም ወገኖች እንደሚቀርብ ደንግጓል፡፡ ኮሚሽኑ የሰጠው ውሳኔ ለይግባኝ አቅራቢው የወሰነ ከሆነ ገቢዎች ሚኒስቴር፣ ወይም ጉምሩክ ኮሚሽን የውሳኔው ማስታወቂያ በደረሳቸው በ30 ቀናት ውስጥ የማስፈጸም ግዴታ እንዳለባቸው አስቀምጧል፡፡

በታክስ ሒደት ቅሬታ ያላቸው ይግባኝ ባዮች አቤቱታቸውን ለኮሚሽኑ የሚያቀርቡት፣ አቤቱታቸው በቅርንጫፍና በዋና መሥሪያ ቤቶች ታይቶ የውሳኔ ማስታወቂያ በደረሳቸው በ30 ቀናት ውስጥ ነው፡፡ ይሁንና አቤቱታቸውን ለኮሚሽኑ ከማቅረባቸው በፊት አከራካሪ የሆነው የገንዘብ መጠን፣ የገቢዎች ከሆነ 50 በመቶ፣ የጉምሩክ ጉዳይ ከሆነ ደግሞ 100 በመቶ መክፈል አለባቸው፡፡

የኮሚሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ እንደሚያስረዱት፣ አፈጻጸም ላይ ጉድለት የታየባቸው መዝገቦች፣ በፍርድ ቤት ዕግድ ያልተጣለባቸውና ተቋማቱ እስከ ሰበር ድረስ ሄደው አቤቱታ አቅርበው የተሸነፉባቸው ናቸው፡፡

ጉዳዩን አስመከልክቶ ከገቢዎችና ጉምሩክ አመራሮች ጋር ንግግር መደረጉን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ በታክስነት የተከፈለው ገንዘብ ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር መተላለፉና ከኮሚሽኑ ውሳኔ በኋላ እስኪመለሱ ጊዜ የሚወስድ መሆኑ በምክንያትነት መጠቀሱን አውስተዋል፡፡ ተሽከርካሪዎች ሲወረሱ ለመንግሥት ተቋማት የሚተላለፉ መሆናቸው፣ ወርቅ ሲያዝም ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባ መሆኑና የዕቃዎቹን የገበያ ዋጋ ግምት ለመስጠት ጊዜ የሚወስድ መሆኑም ለአፈጻጸም መዘግየት ምክንያቶች እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

‹‹ይህ ሒደት ጊዜ ስለሚወስድብን እንጂ፣ ላለመፈጸም አይደለም የሚል ምላሽ ሰጥተውናል፤›› ሲሉ፣ ከሁለቱ ተቋማት የተገኘውን ምላሽ ገልጸዋል፡፡

የታክስ ይግባኝ ኮሚሽኑ በ2015 ዓ.ም. የመጀመርያ ሩብ ዓመት ውስጥ ውሳኔ ከሰጠባቸው 202 ጉዳዮች ውስጥ፣ 132 ግለሰቦች በኮሚሽኑ ውሳኔ ቅር በመሰኘት፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማቅረባቸውን አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ከእነዚህ መዝገቦች ውስጥ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በድጋሚ እንዲታዩ ወደ ኮሚሽኑ የመለሳቸው 11 መዝገቦች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ የእነዚህ መዝገቦች ጉዳይ በሒደት ላይ መሆኑንና በተጀመረው ሩብ ዓመት ምላሽ እንደሚያገኝ አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች