Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊቤቶች ኮርፖሬሽን የመኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሪ ሊያደርግ ነው

ቤቶች ኮርፖሬሽን የመኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሪ ሊያደርግ ነው

ቀን:

  • የመንግሥት ኃላፊዎችና ተቋማት የሚጠቀሙባቸውን ቤቶች ኪራይ እንዲከፍሉ ተጠይቋል

በተያዘው በጀት ዓመት የነባር መኖሪያ ቤቶች የኪራይ ዋጋ ክለሳ በማድረግ፣  ጭማሪ ሊያደርግ መሆኑን የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡

የኪራይ ቤቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ ጥናት ማድረጉን የገለጹት የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይለ ብርሃን ዜና፣ ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ በተከሰቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግሮች ምክንያት ዕቅዱ ሳይተገበር መቆየቱን  ተናግረዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከጥቂት ዓመታት በፊት በንግድ ቤቶች ላይ ጭማሪ ባደረገበት ወቅት፣ ከተከራዮች በገጠመው ተቃውሞ ሳቢያ የፓርላማው ዕገዛ ትልቅ እንደነበር ያወሱት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በተያዘው ዓመት ዕቅዱን ለማሳካት የምክር ቤቱን ዕገዛ እንደሚፈልግ ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከ1967 ዓ.ም. ጀምሮ በመኖሪያ ቤት ኪራይ ላይ የማስተካከያ ጭማሪ ባለመደረጉ፣ በቀጣይ በሚካሄደው ጥናት ላይ ከቤት ባለቤቶችና ከሚመለከታው አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበት በኮርፖሬሽኑ ሥራ አመራር ቦርድ ፀድቆ እንደሚተገበር ተነግሯል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በባለቤትነት ከሚያስተዳድራቸው ቤቶች ውስጥ የመንግሥት ተቋማትና ኃላፊዎች ኪራይ ሳይከፍሉ እየተጠቀሙባቸው ስላሉ፣ ምክር ቤቱ ዕገዛ እንዲያደርግና የገንዘብ ሚኒስቴር በጀት ይዞላቸው ተቋማቱ ኪራይ እንዲከፍሉ እንዲደረግ አቶ ኃይለ ብርሃን ጠይቀዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከአሁን በፊት ባለበጀት መሥሪያ ቤት በነበረበት ወቅት ቤቶቹን የተከራዩ ተቋማት በነፃ እንዲጠቀሙባቸው ተፈቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን ኮርፖሬሽኑ በልማት ድርጅትነት ተመዝግቦ ሕንፃዎችን ለማደስና አዳዲስ ግንባታዎች ለማካሄድ የራሱ የሆነ የፋይናንስ ምንጭ የሚያስፈልገው በመሆኑ ተቋማቱ ኪራይ መክፈል እንደሚጠበቅባቸው ለሪፖርተር የገለጹት የኮርፖሬሽኑ የቤት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ይርጋለም ኩመሊት ናቸው፡፡

በመሆኑም የሃይማኖት ተቋማትና የተወሰኑ የመንግሥት ተቋማት ሙሉ ሕንፃ ጭምር ለዓመታት ያለ ምንም ኪራይ ይጠቀሙባቸው የነበሩ ቤቶችን፣ ከሐምሌ 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ኪራይ ተተምኖ እንዲከፍሉ በኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ምንም እንኳ ተቋማቱ በጀት አስይዘው ኪራይ እንዲከፍሉ ለተቋማቱ ደብዳቤ የደረሳቸው በየካቲት 2014 ዓ.ም. ቢሆንም፣ የተወሰኑት መንግሥት ቤቶቹን በነፃ ስለሰጠን አንከፍልም የማለት አዝማሚያ እያሳዩ ስለሆነ የፓርላማው ዕገዛ እንደሚያስፈልግ ጠይቀዋል፡፡

ቤቶቹን ያለ ክፍያ ከሚጠቀሙት ተቋማት መካከል የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ የፍትሕ ተቋማት ኢንስቲትዩት፣ እንዲሁም ስማቸው ያልተጠቀሱ የሃይማኖት ተቋማት ይገኙበታል ተብሏል፡፡

ኮርፖሬሽኑ አብዛኛውን ቤቶች የሚያከራየው እጅግ አነስተኛ በሆነ የኪራይ ተመን በመሆኑ፣ ከዚህ አቅሙ ላይ ለቤት ልማት ከፍተኛ ወጪ እያደረገ የሚገኝ ስለሆነ፣ የሚያጋጥመው የፋይናንስ እጥረት በቤት ልማቱ ላይ ተፅዕኖ በማስከተሉ፣ ከመንግሥት ለቤት ልማት ሥራዎች የሚውል የፋይናንስ ድጋፍ እንዲደረግለት ቋሚ ኮሚቴው ድጋፍ እንዲሰጥ ተጠይቋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት በአራት ቢሊዮን ብር ወጪ 1,600 ቤቶችን ለመገንባት ዲዛይን አውጥቶ በመንግሥት ድጋፍና ከውጭ በሚገኝ ፋይናንስ፣ እንዲሁም ስድስት የቤት ፕሮጀክቶችን በግልና በመንግሥት አጋርነት ለመገንባት ኮርፖሬሽኑ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡

የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽንም በገበያ ፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተት ለማጥበብ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ፣ በሒደትም ተወደዳሪና አትራፊ እንዲሆን ታስቦ በ33 ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል የተቋቋመ የመንግሥት የልማት ድርጅት መሆኑ ይታሰባል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ኮርፖሬሽኑ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች የቤት ፍላጎት ለሟሟላት እያደረገ ያለው ጥረት አስደሳች አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በ2010 ዓ.ም. አካሄድኩት ባለው የቤቶች ቆጠራ ውጤት መሠረት በአጠቃላይ 18,456 ቤቶች ሲኖሩት፣ ከእነዚህ ውስጥ 11,861 የመኖሪያ ቤቶች፣ 6,595 የድርጅት ቤቶችና 1,752 ሽንሽኖች ናቸው፡፡ ከእነዚህ አጠቃላይ ቤቶች ውስጥ 125 ቤቶች በዶላር ሲከራዩ፣ 100 ቤቶች ከኪራይ ነፃ አገልግሎት እንደሚሰጡ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በብር የሚከራዩ ናቸው ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...