Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናተቋርጦ የነበረው የፌዴራል ዳኞች ምዘና በሦስት ወራት ውስጥ እንደሚጀመር ተገለጸ

ተቋርጦ የነበረው የፌዴራል ዳኞች ምዘና በሦስት ወራት ውስጥ እንደሚጀመር ተገለጸ

ቀን:

የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ለሁለት ዓመታት ተቋርጦ የቆየውን የፌዴራል ዳኞች የሥራ አፈጻጸም ምዘና በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሊያስጀምር ነው፡፡

በ2013 ዓ.ም. የፀደቀው የፌዴራል የዳኝነት አስተዳደር አዋጅ በአዲስ እየተዘጋጀ መሆኑን ተከትሎ ቆሞ የነበረውን የዳኞች ምዘናን በድጋሚ ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ ያለው፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዳኞች የሥራ አፈጻጸም ምዘና መመርያ ከፀደቀ በኋላ፣ ከሁለት ሳምንታት በፊት የፀደቀው አዲሱ መመርያ ለምዘናው ተግባራዊነት የሚደረጉ ዝግጅቶች ተጠናቆ በሦስት ወራት ውስጥ ምዘናው እንዲጀመር ማስቀመጡን፣ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘሪሁን ጌታሁን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አዲሱን መመርያ ማዘጋጀት የተጀመረው ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሆነ ያስታወሱት አቶ ዘሪሁን፣ ‹‹የፌዴራል የዳኝነት አስተዳደር አዋጅ ተሻሽሎ በድጋሚ እስከሚወጣ ድረስ እንዲቆይ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ምዘናው በመቆሙ በግለሰብ ደረጃ ካልሆነ በስተቀር፣ አሁን የዳኞች ሥራ አፈጻጸም ምን ደረጃ ላይ እንዳለ አይታወቅም፤›› ብለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እንደ አቶ ዘሪሁን ገለጻ፣ በአዲሱ መመርያ መሠረት ከተደረጉ ለውጦች ውስጥ አንዱ ከዚህ ቀደም የዳኞች የሥራ አፈጻጸም ምዘና ላይ ነጥብ የማይሰጡት የፍርድ ቤት አመራሮች፣ በሥራቸው ላሉ ዳኞች የሚሰጡት ግምገማ የምዘናው አካል እንዲሆን መደረጉ ነው፡፡

ኃላፊው፣ ‹‹ከዚህ ቀደም የፍርድ ቤት ዳኞች ምዘናው ውስጥ የማይሳተፉት ዳኞችን ገለልተኛና ነፃ ናቸው፤›› በሚል ዕሳቤ መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹የትኛው ዳኛ ዲሲፕሊን አለው? የትኛው ዳኛ መዝገቦችን በአግባቡ ያያል? የትኛው ዳኛ በሰዓት በሥራ ገበታው ይገኛል? የሚለውን ፕሬዚዳንቶች ያውቃሉ፤›› በማለት አመራሮች ምዘናው ሒደት ውስጥ የተካተቱበትን ምክንያት አብራርተዋል፡፡

የችሎት አስተባባሪዎች፣ የፍርድ ቤት ተገልጋዮች፣ ጠበቃዎችና የሥራ ባልደረባዎች ስለዳኞች የሥራ አፈጻጸም የምዘና ነጥብ ከሚሰጡት መካከል እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በየዓመቱ የሚደረገው የሥራ አፈጻጸም ምዘና ላይ፣ ዳኞች በተከታታይ ሦስት ዓመታት ውስጥ የሚያገኙት ነጥብ እንደ ውጤቱ የተለያየ ምላሽ ይኖረዋል፡፡ አቶ ዘሪሁን እንደሚያስረዱት፣ ለተከታታይ ሦስት ዓመታት የላቀ አፈጻጸም ያገኙ ዳኞች የሚሸለሙ ሲሆን፣ ዝቅተኛ አፈጻጸም ያላቸው ደግሞ ብቃታቸውን ለማሻሻል ሥልጠና እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ ሥልጠና ወስደው በተከታታይ ሦስት ዓመታት ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘገቡ (Gross Incompetence) ዳኞች ጉዳያቸው የዳኞች ሥነ ምግባርና የዲሲፕሊን ሥነ ሥርዓት ደንብ እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 79 ንዑስ አንቀጽ 4 ዳኞች ከኃላፊነት ሊነሱ ከሚችሉባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ፣ ‹‹የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ዳኛው ጉልህ የሆነ የሥራ ችሎታና ቅልጥፍና አንሶታል፤›› ብሎ ሲያምን መሆኑን አስቀምጧል፡፡

በ2013 ዓ.ም. የወጣው የዳኞች ሥነ ምግባርና የዲሲፕሊን ሥነ ሥርዓት ደንብ አንቀጽ 15 ንዑስ አንቀጽ 2 ደግሞ፣ ‹‹ዳኞች የዳኝነት ሥራ አፈጻጸማቸውን ለማሻሻል የሚሰጣቸውን ሙያዊ ሥልጠና ቢያጠናቅቁም፣ ከዚያ በኋላ የሚያሳዩት የሥራ አፈጻጸም በተከታታይ ከአንድ ዳኛ ከሚጠበቀው በታች የወረደ ከሆነ ከዳኝነት ሥራቸው ሊሰናበቱ ይችላሉ፤›› ሲል ደንግጓል፡፡

እንደ አቶ ዘሪሁን ገለጻ፣ በአዲሱ የሥራ አፈጻጸም መመርያ የምዘና ሥራው በሦስት ወራት ውስጥ መጀመር እንዳለበት የደነገገ ሲሆን፣ በቀጣዮቹ ወራት ጊዜ ውስጥ ደግሞ በመመርያው ላይ ለምዘና መሥፈርትነት እንዲያገለግሉ የተቀመጡ መለኪያዎች ወደ መጠይቅ ተቀይረው ይዘጋጃሉ፡፡ በጉባዔ መመርያው ከፀደቀ በኋላ መጠይቅና ማንዋሎች እንዲዘጋጁ ወደ ባለሙያዎች እንዲመራና የተለያዩ አካላት የሚሞሏቸው መጠይቆች የተለያየ ይዘት ያላቸው እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡ ለምዘና የሚዘጋጀው መጠይቅ በሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት ለዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ቀርቦ መፅደቅ እንዳለበት አክለዋል፡፡

የዳኞችን የሥራ አፈጻጸም ምዘና የሚያስተባብሩት ፍርድ ቤቶች እንደሆኑ የተናገሩት ኃላፊው፣ በሦስት ወራት ውስጥ ከሚደረገው ዝግጅት መካከል አንዱ የሥራ አፈጻጸም ምዘናው የሚመራበት የድርጊት መርሐ ግብር ማዘጋጀት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ለምዘና የሚውለውን መጠይቅ ወደ ፍርድ ቤቶችና ምድብ ችሎቶች የማሠራጨት፣ መልሶ መሰብሰብ፣ ማደራጀትና በጉባዔው የማፅደቅ ሥራዎች አንድ ዓመት እንደሚወስዱ አቶ ዘሪሁን ተናግረዋል፡፡ ዳኞች በተሰጣቸው ነጥብ መሠረት የሚያገኙት ውጤት ወደ ግል ማኅደራቸው ከመግባቱ በፊት ተሰጥቷቸው ቅሬታ ካላቸውም ይግባኝ ማለት እንደሚችሉም ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...