Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየታራሚዎች የይቅርታ አሰጣጥ ከሙስና የፀዳ ስለመሆኑ ጥርጣሬ እንዳለው ፓርላማው ገለጸ

የታራሚዎች የይቅርታ አሰጣጥ ከሙስና የፀዳ ስለመሆኑ ጥርጣሬ እንዳለው ፓርላማው ገለጸ

ቀን:

በአገር አቀፍ ደረጃ ለታራሚዎች ይቅርታ የሚደረግበት አሠራርና መሥፈርት ከሙስና የፀዳ ስለመሆኑ ጥርጣሬ እንዳለው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት የፍትሕ ሚኒስቴርን የ2015 ዓ.ም. ሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት፣ የኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ እፀገነት መንግሥቱ፣ ‹‹የተሻለ አቅም፣ ዘመድና ገንዘብ ያለው ሰው ቶሎ ይወጣል፣ በዚህም የተነሳ አሠራራችሁ ከሙስና የፀዳ ነው ብለን አንደፍርም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በተጨባጭ ያገኘነው ጉዳይ ዋና ወንጀለኛው ወጥቶ ተባባሪው በእስር ላይ ይገኛል፣ እንዲያውም ዋናው ወንጀለኛ ከእስር ተለቆ ተባባሪው ካልወጣ ምን ልንለው እንችላለን? አድሎዓዊ አሠራር ካልሆነ?›› ያሉት ዋና ሰብሳቢዋ፣ ‹‹በምን ዓይነት መረጃ ላይ ተመርኩዛችሁ ነው ይቅርታ የምታደርጉት?›› በማለት ጠይቀዋል፡፡

- Advertisement -

ሌላኛው የቋሚ ኮሚቴ አባል በበኩላቸው፣ በይቅርታና በአመክሮ ከእስር ስለሚወጡ ሰዎች ክትትል የሚደረግበት ግልጽ ሥርዓት አለመኖርን በማውሳት፣ በመስክ ምልከታ ወቅት በሁሉም በሄዱባቸው ማረሚያ ቤቶች ያለው የይቅርታ አሠራር ተፈትሾ ይቅረብ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

አቶ መስፍን እርካቤ የተባሉ የቋሚ ኮሚቴ አባል፣ ይቅርታ የሚደረግላቸው ታራሚዎች የይቅርታው አሠራርና አካሄድ ግልጽ ባለመሆኑ፣ አድልኦ አለ የሚል ቅሬታ በማረሚያ ቤቶች በተደጋጋሚ ስለመሰማቱ ተናግረዋል፡፡

ወ/ሮ እፀገነት ‹‹አንዳንድ ወንጀሎች አያስከስሱም›› ተብለው መዝገቦቹ የሚዘጉ መሆናቸውን፣ በዚህ ምክንያት ሕዝብን የሚያስከፉ ወንጀሎች መኖር አለመኖራቸውን እንዴት እንደሚያረጋግጡ ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡

‹‹ለአብነት እንኳ አንድ ሰው ላይ አሲድ የደፋ ግለሰብ ይቅርታ ተደርጎለት ከወጣ በኋላ ተመልሶ በሴቶች ላይ በድጋሚ የሠራው ወንጀል በግልጽ እየታየ፣ ሕዝቡ እንዴት በፍትሕ ተቋማት ላይ እምነት ያሳድር፣ ይቅርታ ሲመዘን የሕዝብ ፍላጎትን እንዴት አትመለከቱም?›› በማለት ለሥራ ኃላፊዎቹ ወቀሳ አቅርበዋል፡፡

በቋሚ ኮሚቴ አባላት የተነሳውን ጉዳይ አስመልክተው ምላሽ የሰጡት የፍትሕ ሚኒስቴር ደኤታ አቶ ፍቃዱ ፀጋ፣ በይቅርታ አሠራሩ ላይ ውስንነቶች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ 2014 ዓ.ም. በተለያዩ ምክንያቶች ይቅርታ ሳይሰጥ ያለፈበት ዓመት እንደነበርም አውስተዋል፡፡

በ2014 ዓ.ም. መጀመሪያ አካባቢ የቦርዱን ጽሕፈት ቤት ይመራ የነበረው ሰው የተለያዩ ሐሜቶች ስለተሰሙበት፣ የወንጀል ምርመራ ለማድረግ ታስሮ መረጃ የማሰባሰብ ሥራ መከናወኑን ሚኒስትር ደኤታው አስረድተዋል፡፡

አቶ ፍቃዱ አሲድ በመድፋት ታስሮ በይቅርታ የተለቀቀውን ግለሰብ አስመልክተው፣ ‹‹እዚህ ላይ ብትገነዘቡ ጥሩ የሚሆነው አሲድ የደፋው ሰው ሲለቀቅ፣ የይቅርታ ቦርዱን ይመራ የነበረውን ሰው ሒደቱ ትክክል አይደለም በማለት ማስተካከያ የወሰደው የእኛ ተቋም ነው፡፡ ስለዚህ ስህተቶች ሲኖሩና መኖራቸውም በተረጋገጠ ጊዜ ማስተካከያ እየወሰድን ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ይቅርታ መብት አይደለም፣ ታይቶ የሚደረግ ምሕረት እንጂ፡፡ በዚህም ቦርዱ እያየ ይቅርታ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው እንደ መብት ይቅርታ ይገባኛል ብሎ ሊጠይቅ አይችልም፤›› ብለው፣ ከአጠቃላይ የቅጣት ጊዜው አንድ ሦስተኛውን በእስር ያጠናቀቀ ይቅርታ ሊጠይቅ ይችላል እንጂ፣ ለእኔ ለምን አልተሰጠም የሚል አስተሳሰብ መስተካከል እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል ታራሚዎች ዝውውር የመጠየቅ መብት ስላላቸው ይህን መብት መሠረት በማድረግ ተዘዋውረው ወደ ሌላ ቦታ ከሄዱ በኋላ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ ማረሚያ ቤቶች በቀላሉ ሊወጡ እንደሚችሉና በተለያዩ ቦታዎች ያለው የይቅርታ አሰጣጥ መርህ የተለያየ በመሆኑ በአሠራሩ ላይ ክፍተት ሊፈጠር እንደሚችል አክለው ገልጸዋል፡፡

በዓላትን ጠብቆ በጅምላ የሚሰጥ ይቅርታ አስተማሪ አይደለም ያሉት አቶ ፍቃዱ፣ አሁን ቦርዱ በየወሩ እየተገናኘ ጉዳይ እያየ ይቅርታ እንዲሰጥ ቢደረግ ይሻላል የሚል አቋም መያዙን አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ይቅርታ የሚደረገው ቦርዱ ውስጥ ባሉ ከተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ አካላት ሊቀርብላቸው በሚችለው ጉዳይ ላይ ተወያይተው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...