Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፓርላማው በማረሚያ ቤቶችና በፖሊስ ጣቢያዎች ተፈጸሙ የተባሉ የመብት ጥሰቶችን ሊመረምር ነው

ፓርላማው በማረሚያ ቤቶችና በፖሊስ ጣቢያዎች ተፈጸሙ የተባሉ የመብት ጥሰቶችን ሊመረምር ነው

ቀን:

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ‹‹ተዘዋውሬ የመስክ ምልከታ አካሄድኩባቸው›› ባላቸው ማረሚያ ቤቶች፣ ከታራሚዎች ‹‹ደረሱኝ›› ያላቸውን አቤቱታዎች፣ በአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ጣቢዎች ተፈጸሙ ተብለው ‹‹በተደጋጋሚ ቀረቡልኝ›› ያላቸውን የመብት ጥሰት አቤቱታዎች አጣሪ ቡድን አዋቅሮ ለመመርመር መገደዱን አስታወቀ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ጥቅምት 26 ቀን 2015 ዓ.ም. የፍትሕ ሚኒስቴርንና የተጠሪ ተቋማትን የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድና የአንደኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላት የሰብዓዊ መብት አያያዝን በተመለከተ በቂሊንጦ፣ በድሬዳዋ፣ በዝዋይና በሌሎች ማረሚያ ቤቶች በርካታ ታራሚዎች ግርፋትና ወጣ ያሉ የመብት ጥሰቶች እንደተፈጸመባቸው በመስክ ምልከታ ከታራሚዎች መስማታቸውን ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በአዲስ አበባ ከተማ በወንጀል ተጠርጥረው የሚያዙ ሰዎች በአጭር ጊዜ ለፍርድ እንደማይቀርቡ፣ ለብዙ ጊዜያት በፖሊስ ማቆያ የሚሰቃዩ መኖራቸውንና ሌሎችም በርካታ አቤቱታ እየደረሷቸው እንደሆነ የቋሚ ኮሚቴው ስበሳቢ ወ/ሮ እፀገነት መንግሥቱ አስረድተዋል፡፡

‹‹ጉዳዩን ተዟዙረን እንድናይ ከሕዝብ ተደጋጋሚ ቅሬታ እየቀረበልን ነው፤›› ያሉት ሰብሳቢዋ፣ ‹‹በቀጣይ አጣሪ ቡድን አደራጅተን የምንመለከተው ጉዳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ቀድሞ ማዕከላዊ ይባል ነበር፣ አሁን ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ ባሉ የፖሊስ ማቆያ ቤቶች የሚታየውን ሕዝቡ በተደጋጋሚ ቅሬታ እያቀረበልን ነው፤›› ያሉት ወ/ሮ እፀገነት፣ በማቆያዎች ይካሄዳል የሚባለውን ከፍተኛ የሆነ የመብት ረገጣ ለምን ማስተካከል አይቻልም? ቶሎ ምርመራ ተደርጎ ውሳኔስ ለምን አይሰጥም? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል አቶ መስፍን እርካቤ የተባሉ የቋሚ ኮሚቴው አባል፣ ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶችን የሚመለከቱ በርካታ ዓለም አቀፍ ሕጎችን ያፀደቀች ቢሆንም፣ ከሰብዓዊ መብቶች ጋር በተገናኘ እየተሰማና እየታየ ያለው ሁኔታ ጥሩ አለመሆኑን በመግለጽ፣ ‹‹በአዲስ አበባ ከተማ እስረኞች በግልጽ እንደሚደበደቡ ተደጋጋሚ መረጃ ይደርሰናል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ይህ እየሆነ ያለው የአገሪቱ ድንበር ላይ ሳይሆን፣ ዋና ከተማዋ ላይ በተለይም የተመድ ድርጅቶች፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ በርካታ ዲፕሎማቶች ባሉበት ርዕሰ ከተማ ውስጥ በመሆኑ፣ እንዲህ ዓይነት አሠራር የመንግሥታችንን ዴሞክራሲዊ አካሄድ ጥላ ሊያጠላበት ይችላል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

‹‹የሚሰማው ጫጫታ ብዙ ነው፤›› የሚሉት አቶ መስፍን፣ ይህ ድርጊት የሕገ መንግሥቱን አንቀጾች አይፃረርም ወይ በማለት ጠይቀዋል፡፡

የፍትሕ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ፍቃዱ ፀጋ ለተነሱት ጥቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ፣ ‹‹ሰዎች ለቀናት ይታገታሉ ተብሎ በቋሚ ኮሚቴ የተነሳው ጉዳይ ሪፖርት አልቀረበልንም፣ ነገር ግን በማኅበራዊ ሚዲያ ያለውን ከሆነ ምንም ማድረግ አንችልም፤›› በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹በመሆኑም ታግቶ ነገር ግን ሪፖርት ተደርጎ ምርመራ ያልተደረገበት ካለ እንጠይቃለን፤›› ብለዋል፡፡

በየማኅበራዊ ሚዲያው ታግቻለሁ የሚል ሰው ለፖለቲካ ፍጆታና ለተለያየ ነገር ሊሆን ስለሚችል ሁኔታው ከባድ ነው ያሉት አቶ ፍቃዱ፣ ‹‹ጉዳዩን ከአሉባልታ ለይተን አናየውም፡፡ ይሁን እንጂ  በሕጋችን ውስጥ እገታ ወንጀል ነው፡፡ በተለይ ደግሞ እገታው የሚፈጸመው በመግሥት ሠራተኛ ሲሆን ከባድ ነው፣  ነገር ግን ከአሉባልታ አልፎ ጥቆማ መጥቶ ካልተመረመረ የማይሆን ነገር ነው፤›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ከሰብዓዊ መብት አንፃር ከቋሚ ኮሚቴው የተነሳው ቅሬታ አስደንጋጭ ነው ያሉት አቶ ፍቃዱ፣ የዚህ ለውጥ የሚያኩራራ ትሩፋት ነው ተብሎ የሚነሳው በማረሚያ ቤቶችና በፖሊስ ጣቢያም በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ የመጣው ለውጥ  መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹አቤቱታ ካለ በደንብ እናያለን፣ እናንተ በምትሉትና በሚያማርር ደረጃ  የቱ ጋ ነው የሳትነው የሚለውን ወስደን አንናያለን፡፡ ነገር ግን በአካል ላይ ደረሰ የተባለ የመብት ጥስት ካለ የለም ብዬ አልክድም፡፡ ነገር ግን ሪፖርት አልተደረገልንም፣ መሬት ላይ ያለውን ተመልስን እናያለን›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...