Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየፈነጠቀው በኩር ድምፃዊ አሊ ቢራ (1940 - 2015)

የፈነጠቀው በኩር ድምፃዊ አሊ ቢራ (1940 – 2015)

ቀን:

በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ታሪክ ለስድስት አሠርታት በድምፃዊነት፣ በዜማና ግጥም ደራሲነት በመዝለቅ ስመ ጥር መሆን ብቻ አይደለም፣ ከፈር ቀዳጆች ተርታ ለመሠለፍ በቅቷል፡፡ ማን ቢሉ በኦሮምኛ፣ አማርኛ፣ ሶማሊኛ፣ ሐረሪ፣ ዓረቢኛ፣ አፋርኛ ዘፋኝነቱ የሚታወቀው በኩር ድምፃዊ አሊ ቢራ ነው፡፡ ከባህር ማዶ ቋንቋዎችም በስዊድሽ፣ በስፓኒሽና እንግሊዝኛም እንደሚጫወት ይነገርለታል፡፡

ስለ ፍቅር፣ ስለ ትምህርት፣ ስለ ባህልና ፎክሎር፣ ስለ ዕርቅና ሰላም፣ ስለ ሰብዓዊ መብትና እኩልነት ወዘተ በዳሰሳቸው ሥራዎቹ በተለያዩ ቋንቋዎች ማቀንቀኑ የብዙዎችን ቀልብ እንዲገዛ አስችሎታል፡፡

ወላጆቹ ካወጡለት አሊ መሐመድ ሙሳ ከሚለው መጠርያው ወደ አሊ ቢራ የተቀየረው ለከያኒነት ሕይወቱ ፈንጣቂ በሆነው የመጀመርያው ዘፈኑ ‹‹ቢራ ዳ በሪኤ›› ተቀባይነት በማግኘቱ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ቢራ በአማርኛ ብራ ከባዱ ክረምት አልፎ የአዲስ ዘመን ብርሃን የሚጠባበት አበቦች የሚፈኩበት የመፀው ወቅት የሚገባበት ነው፡፡ በገጸ ታሪኩ እንደተወሳው ‹‹ቢራ ዳ በሪኤ›› – የብራ ወቅት መጣ፣ አበባው አወደ የሚል ትርጉም አለው፡፡

አሊ ቢራ በ1954 ዓ.ም. በትውልድ ከተማው ድሬዳዋ ከተማ አፍረን ቀሎ አማካይነት በተቋቋመው ባህላዊ የሙዚቃ ቡድን በመግባት ድምፃዊነቱን አሐዱ ብሎ ጀምሯል፡፡

ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ በታዋቂውና እነ ጥላሁን ገሠሠ፣ ብዙነሽ በቀለ መሐመድ አህመድ፣ ተፈራ ካሳ በነበሩበት የክብር ዘበኛ ኦርኬስትራን በመቀላቀል ለዓመታት ሠርቷል፡፡ አይቤክስ ባንድን በመቀላቀል ለስምንት ዓመታት የሙዚቃ ሥራዎቹን በዲ አፍሪክ ሆቴል ሲያቀርብ መቆየቱ፣ በተለያዩ ክለቦች ምሽቶችንም ጨምሮ መጫወቱ ይወሳል፡፡  

ከ267 በላይ ሙዚቃዎች ያበረከተው ድምፃዊው 13 አልበሞችን አውጥቷል፡፡ ከተወዳጅ  ሥራዎቹ መካከል  ዋ መሊ ኑ ዲቤ፣ ጃላሉማ ቴቲ፣  በርኖታ፣ ዑሹሩሩ ያ ቡርቱካኔቶ፣ ከራን መና አባ ገዳ፣ ኒን ዴማ፣ ደባለ ኬሰን፣ አማሌሌ ይጠቀሳሉ፡፡ ቀደም ሲል ከማህሙድ ጋር፣ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ከሔለን በርሔ (ሲያዴን) እና አብርሃም በላይነህ (ዳርም የለው ላፍታ) ጋር የተጫወታቸው ዘፈኖችም በተወዳጅነታቸው ይጠቀሳሉ፡፡

ከ1960ዎቹ አጋማሽ በኋላ በአገር ውስጥ የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ቀውስ ተከትሎ ባወጣው ዘፈኑ ‹‹ሃቲ ቴኛ ታካ ማልቱ አዳን ኑባሴ?› – እናታችን አንድ ነች ምንድነው ያለያየን?- በማለት አጥብቆ ጠይቋል፡፡

ከድምፃዊነቱና ዜና ደራሲነቱ ባሻገር የተለያየ የሙዘቃ መሣሪያዎች ሊድና ቤዝ ጊታር፣ ፒያኖ፣ ኦርጋን፣ አኮርዲዮና ኡድ ይጫወት እንደነበር ይወሳል፡፡

ለዜማ ከሰጣቸው ድምፃውያን መካከል ጥላሁን ገሠሠና መሐሙድ አህመድ ይገኙበታል፡፡

በ1970ዎቹ መገባደጃ በስደት በስዊድን፣ ሳዑዲ ዓረቢያና አሜሪካና ካናዳን የኖረው ድምፃዊው በተለያዩ አኅጉሮች በመዘዋወር የሙዘቃ ሥራዎቹን በተለያዩ መድረኮች አቅርቧል፡፡

ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ ከሙዚቃዊ ሥራው ባለፈ ‹‹ቢራ የሕፃናት ትምህርት ፈንድ የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ማቋቋሙና ለሕፃናት ትምህርት ድጋፍ መስጠቱ ይወሳል፡፡

አሊ ቢራ በሙዚቃ ላበረከተው ታላቅ አስተዋጽኦ  የድሬዳዋና ጅማ ዩኒቨርሲቲዎች  የክብር ዶክትሬት የሰጡት ሲሆን፣ የአገር ውስጥና የውጭ ተቋማትም ሽልማቶችን አጎናፅፈውታል፡፡

በድሬዳዋ ከተማ ፓርክ፣ በአዳማ መንገድ በስሙ የተሰየሙለት አሊ ቢራ ካገኛቸው የውጭ ሽልማቶች አንዱ በካናዳ ቶሮንቶ ‹‹የአፍሪካ የምንጊዜም አንጋፋ ሙዚቀኛ›› ሽልማትን ነው፡፡

በድሬዳዋ ከተማ ገንደ ቆሬ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከአባቱ አቶ መሐመድ ሙሳና ከእናቱ ወ/ሮ ፋጡማ አሊ በ1940 ዓ.ም. የተወለደው አሊ፣ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቱን በድሬዳዋ ከተማ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአዲስ አበባ ካቴድራል ትምህርት ቤት ተከታትሏል። የአሜሪካ በሚገኘው የሳንታ ሞኒካ ኮሌጅም የሙዚቃ ትምህርት ተምሯል።

አሊ ቢራ ባደረበት ሕመም ምክንያት ሕክምና ሲከታተል ቆይቶ ጥቅምት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ በ75 ዓመቱ ያረፈ ሲሆን፣ ሥርዓተ ቀብሩ ጥቅምት 29 ቀን በድሬዳዋ ከተማ በለገሀሬ የሙስሊም መካነ መቃብር ተፈጽሟል፡፡

ሥርዓተ ቀብሩ ከመፈጸሙ በፊት በአዲስ አበባ ወዳጅነት አደባባይ የክብር ሽኝት ተደርጎለታል፡፡  

ማን ምን አለ?

‹‹አሊ ቢራ ብሩህ አዕምሮ የነበረው፣ ታላቁንም ታናሹንም የሚያከብር፣ ተግባቢና ቀልደኛ ሰው ነበር፡፡ በክብር ዘበኛ ውስጥ ቢያንስ ሰባት ዓመት አገልግሏል፤ ወደ ክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ሲመጣ የተቀበልነው እኛ ነበርን፤›› ያለው በአሸኛኘቱ ላይ የተገኘው በኩር ድምፃዊ ማህሙድ አህመድ ነው፡፡

‹‹ናፍቆት ነው የጎዳኝ›› የተሰኘ አንድ ዜማ እንደሰጠው፣  ማንዶሊን ይዞ ‹‹ትዝ፣ ትዝ እያለኝ›› እያለ ሲያስጠናው እንደነበር ትዝታውን ያወጋው ማህሙድ፣‹‹እሳቱ ተሰማ፣ ተዘራ ኃይለ ሚካኤል፣ ተፈራ ካሳ፣ ጥላሁን ገሠሠ፣ ብዙነሽ በቀለ እና እኔ አንድ ቡድን ነበርን፤ በመሃል ከተቀመጥንበት ልውጣ ያልኩ እንደሆነ ቆይ እኔ ይዤህ እወጣለሁ ይለኝ ነበር፤›› ብሏል፡፡

‹‹ሙዚቃ የቋንቋን እና የአመክንዮን ድንበርን ትሻገራለች፤ የማንሰማው ሙዚቃ በስሜት፣ በተመስጦ እንድናዳምጥ የምታደርገን ልዩ ባለሙያዎችና ጥበበኞችን ስታገኝ ነው፡፡ በዚህም ሳሊፍ ኬታ፣ ዩሱን ዱሩን እና ማሪያም ማኬባን መጥቅስ እንችላለን፡፡ ልክ እንደነዚህ ሁሉ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በጣም በሚገርም ለዛ በሚያስደንቅ የአዛዚያም ስልት የማንሰማው ቋንቋ በተመስጦ እንድናዳምጥ ያደረገ ታላቅ የሙዚቃ ሰው  አሊ ቢራ ነው፤›› ያሉት በወዳጅነት አደባባይ በተደረገው አሸኛኘት ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት ናቸው፡፡

የሙዚቃ ባለሙያው አክለውም ‹‹በክህሎት መጫወት አንድ ነገር ነው፣ ከክህሎት በላይ ዕውቀት መጨመር በጣም ረጅም ጉዞ የሚያስኬድ ነው፤›› ብለዋል።

ሠዓሊና ቀራፂ በቀለ መኰንን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ በኩር ድምፃዊውን እንደሚከተለው ገልጾታል፡፡

‹‹የአሊ ጥልቁ የድምፃዊነት ስጦታው በድምጹ ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ድምፃዊነት የሚጠይቀውን ጥበብ ብልሃት ስልት ልምድና በተለይም በልዩነት የምትሰጥ በቃል የማትተነተን ስፍራዋ እንደነፍስ ተለይቶ የማይታይ የተሰጥዖ ቅመሙ ጭምር ናት፡፡… የአሊ ሃይልና ጉልበቱ ተሻጋሪ (transcendental) ያደረገው የድምፃዊነት ርቅቀቱ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ያቺን ከፍ ያለች ዜማና ዜመኝነት ነው ሊቃውንቱ የጥበባት ሁሉ ቁንጮ ናት የሚሏት። ያዜመ ሁሉ አይታደላትም የተሰጠው ብቻ እንጂ። ሌላ ሌላው ሁሉ ብዙዎች ዘንድ ሊገኝ ይችላል።

‹‹በርግጥ እሱንም ማንሳት ካስፈለገ የአሊ የዘፈን ግጥሞች (ሊሪክስ) ካገራችን ድምፃውያን በግጥሞቿ ለኔ ወደር ከሌላት ከሜሪ አርምዴ (ሥዕሎች ልበል መሰለኝ) ግጥሞች ትይዩ መቆም የሚችል ነው። ከሚያነሳው ቁም ነገር በላይ ፖኤቲክ ጉልበቱ አጃኢብ የሚያሰኝ ሥራ ነው። ለኔ አሊን ማዳመጥ ሜሪን ከማዳመጥ የሚለየው በሥነ ግጥሙ ጥልቀትና ውበት አማልሎ በድምፃዊነቱ ምትሃት ከዘመንና ከአድማስ በላይ የማንሳፈፍ አቅሙ ነው። ያለን እስካለን እናደምጠዋለን፤ ገና የሚፈጠሩትም ያለጥርጥር ተማርከው ሲያደምጡት ይኖራሉ። አሊ አንድ ቋንቋና አንድ መልክዓ ምድር ብቻ ሳይሆን አንድ ዘመንም ብቻውን ሊሸከመው የማይቻለው ከላይ እንዳልኩት ተሻጋሪ ድምፃዊ ነው፡፡››

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...