Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዘመን ባንክ ጠቅላላ ጉባዔ የባንኩን ካፒታል ወደ 15 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዘመን ባንክ ጠቅላላ ጉባዔ የባንኩን ካፒታል ወደ 15 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ በባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ የቀረበውን ሐሳብ ተቀብሎ አፀደቀ።

የባንኩ ባለአክሲዮኖች ይህንን ውሳኔ ያሳለፉት ባለፈው ቅዳሜ ባካሄዱት ድንገተኛ ጠቅላላ ጉባዔ የባንኩን ካፒታል ወደ 15 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ የቀረበው ሐሳብ ላይ ተወያይተው ውሳኔ አሳልፈዋል። በአሁኑ ወቅት የባንኩ የተፈረመ ካፒታል አምስት ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ የተከፈለው ካፒታል መጠን 3.64 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ከባንኩ የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

እስከ 2014 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ድረስ ባንኩ የተከፈለ ካፒታሉም 3.64 ቢሊዮን ደርሶ የነበረ ሲሆን ሆኖም ባለፈው ቅዳሜ የባንኩ ባለአክሲዮኖችን ካፒታሉን በአሥር ቢሊዮን ብር ለመጨመር የቀረበውን ሐሳብ ተቀብለው በተስማሙት መሠረት ቀሪውን ካፒትልና በዕለቱ የፀደቀውን ተጨማሪ ካፒታል በአምስት ዓመት ውስጥ ከፍሎ ለመጠናቀቅ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ 

የባንኩን ካፒታል በዚህን ያህል ደረጃ ለማሳደግ የተፈለገበትን ዋነኛ ምክንያት በአሁኑ ወቅት መንግሥት ከፍተኛ የፋይናንስ ዘርፍ ሪፎርም መተግበር መጀመሩ ሲሆን፣ ዘመን ባንክም ይህንን ሪፎርም ያገናዘበ አቅምና ዝግጁነት መፍጠር እንዳለበት በመታመኑ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ 

እየተካሄደ ባለው የፋይናንስ ዘርፍ ሪፎርም ዝግ የነበረው የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የሚከፈት በመሆኑ፣ ዘመን ባንክም መጪውን ውድድር ታሳቢ ያደረገ አቅም ለመፍጠር ከሚያስችሉት ጉዳዮች አንዱና መሠረታዊው የባንኩን ካፒታል ማሳደግ እንደሆነ ተጠቁሟል። ይህንን በማድረግ የባንኩ መሠረታዊ መዋቅርን ማጠናከር ተገቢ መሆኑ ስለታመነበት በዚሁ አግባብ ውሳኔው መተላለፉን የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ኤርሚያስ እሸቱ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ 

ባለፈው ቅዳሜ በተካሄደው የባንኩ ጠቅላላ ጉባዔ እንደተገለጸው፣ ዘመን ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ አግኝቷል። በዚህም ባንኩ ዓመታዊ የትርፍ መጠኑን ለመጀመሪያ ጊዜ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ማሻገር መቻሉን አስታውቋል፡፡ 

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ኤርሚያስ እንዳመለከቱት ዘመን ባንክ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት አገኛለሁ ብሎ በዕቅድ የያዘው የትርፍ መጠን 2.21 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ያስመዘገበው ትርፍ ግን 2.1 በመሆኑ የዕቅዱን 95 በመቶ ማሳካት መቻሉን አመልክተዋል፡፡ 

በ2014 የሒሳብ ዓመት ያስመዘገበው የትርፍ መጠን ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ ደግሞ የ675 ሚሊዮን ብር ወይም የ48 በመቶ ብልጫ የታየበት ነው። ባንኩ በ2013 የሒሳብ ዓመት አግኝቶት የነበረው የትርፍ መጠን 1.4 እንደነበር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ባንኩ ከፍተኛ አፈጻጸም ካሳየባቸው ክንውኖች ውስጥ ዓመታዊ ገቢውን በ43.3 በመቶ ወይም በ1.25 ቢሊዮን ብር ማሳደግ መቻሉ ነው፡፡ በመሆኑም ባንኩ በ2014 የሒሳብ ዓመት 4.1 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ እንዳገኘ የገለጹት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ ለገቢው ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው ከብድር የተገኘው ወለድ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ከተገኘው ጠቅላላ ገቢ ውስጥ ከብድር ወለድ የተገኘው ገቢ 2.4 ቢሊዮን ብር ወይም ከአጠቃላይ ገቢው ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነውን እንደሚሸፍን ተገልጿል፡፡ 

ከዓለም አቀፍና ከተዛማጅ የባንክ አገልግሎቶች የተገኘው ገቢ ደግሞ 1.67 ቢሊዮን ብር እንደነበር አቶ ኤርሚያስ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ዘርፍ የተገኘው ገቢ ከቀዳሚ ዓመት የ55 በመቶ ብልጫ እንዳለውም በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡ 

ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎትና ተያያዥ አገልግሎቶች የተገኘው ገቢ ከፍተኛ ቢሆንም፣ ባንኮች ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ ገቢ ውስጥ 70 በመቶውን ለብሔራዊ ባንክ እንዲያስረክቡ የሚያስገድድ መመርያ ባይወጣ ከዚህ ዘርፍ የተገኘው ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር የሚችልበት ዕድል እንደነበር ጠቅሰዋል።

‹‹በዚህ አስገዳጅ መመርያ ምክንያት ባንካችን በበጀት ዓመቱ 218 ሚሊዮን ዶላር ለብሔራዊ ባንክ ገቢ አድርጓል፡፡ ይህ ገንዘብ በባንኩ በኩል ሥራ ላይ ቢውል ኖሮ ሌሎች ተጓዳኝ ጥቅሞች ሳይጨመሩበት ከ1.1 ቢሊዮን በላይ ገቢ ማግኘት ያስችል ነበር›› ብለዋል። አክለውም፣ ባንኮች ከዓመታዊ የውጭ ምንዛሪ ግኝታቸው 70 በመቶውን ለብሔራዊ ባንክ እንዲያስገቡ የሚያስገድደው መመርያ በባንኮች ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳረፈ መሆኑን አመላክተዋል።

የባንኩን የ2014 የሒሳብ ዓመት ሌሎች አፈጻጸሞችን በተመለከተ የቦርድ ሊቀመንበሩ እንዳብራሩት በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ባንኩ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው ብድር መጠን 21.4 ቢሊዮን መድረሱን ገልጸዋል፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ50.2 በመቶ ወይም የ7.2 ቢሊዮን ብር ዓመታዊ ዕድገት የታየበት ነው፡፡ የብድሮችን ጤናማነት ለማረጋገጥ በተሠራው ተከታታይ ሥራ የተበላሹ ብድሮች አምና ከነበረበት 2.25 በመቶ ወደ 1.51 በመቶ ዝቅ ለማድረግ መቻሉንም በመጥቀስ ይህ አፈጻጸም የባንኩን ብድር ጤናማነት የሚያረጋግጥ መሆኑን ነው፡፡ 

የአንድን ባንክ ጤናማነት ከሚያረጋግጡት ዋና ዋና ባህሪያት ውስጥ የብድር ጤናማነት በመሆኑ በተለይም የምጣኔ ሀብት ዕድገት መቀዛቀዝ በሚያጋጥምበት ጊዜ የተበላሹ ብድሮች ሊጨምሩ የሚችሉበት ዕድሉ ሰፊ መሆኑን የገለጹት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ በዚህ ረገድ ዘመን ባንክ የተሻለ አፈጻጸም አሳይቷል ብለዋል፡፡ በቀጣይም ቦርዱ የባንኩ ብድሮችን ጤናማነት እንዲሁም የተበላሹ ብድሮች በሚመለሱበት ሁኔታ ላይ የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚከታተል ጠቁመዋል፡፡

ከውጭ ምንዛሪ ግኝት ጋር በተያያዘ በአገር አቀፍ ደረጃ ችግር ቢኖርም ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ከቀዳሚው ዓመት የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ግኝት አስመዝግቧል፡፡ የቦርድ ሊቀመንበሩ ባቀረቡት ሪፖርታቸው ላይ እንዳመለከቱትም በዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ 502 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ተችሏል፡፡ ይህም የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ83.7 ሚሊዮን ዶላር ወይም የ20 በመቶ ዕድገት እንደነበረው ታውቋል፡፡

የዘመን ባንክ አጠቃላይ ሀብት መጠኑ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 35.1 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ39.6 በመቶ ወይም በብር 9.97 ቢሊዮን ዕድገት ማስመዝገቡን ታውቋል፡፡ የተቀማጭ ገንዘብ በማሳሰብ ረገድም የተሻለ አፈጻጸም የታየበት ዓመት ነው ተብሏል፡፡ ከሪፖርቱ መረዳት እንደሚቻለውም ባንኩ በ2013 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ የነበረው 18.9 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ በ2014 መጨረሻ ላይ የ41.5 በመቶ ዕድገት በማሳየት 26.9 ቢሊዮን ብር መድረሱን ሪፖርቱ አመላክቷል።

ባንኩ በ2014 ሒሳብ ዓመት አጠቃላይ ወጪው 2.91 ቢሊዮን ብር የደረሰ መሆኑን የሚገልጸው ሪፖርቱ ከባለፈው የሒሳብ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 522 ሚሊዮን ብር ወይም የ33 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተጠቅሷል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ወጪ ከፍተኛውን ድርሻ የወሰደው ለተቀማጭ ገንዘብ የተከፈለ ወለድ ሲሆን ይህም 938 ሚሊዮን ብር ወይም የ45 በመቶ ድርሻ አለው፡፡ ሌሎች ለወጪው መጨመር ቀዳሚ ምክንያቶች ተብለው የተጠቀሱት ደግሞ የባንኩ የሰው ኃይል ቁጥር መጨመር ይህም ከቅርንጫፎች ዕድገት ጋር ተያይዞ የሚመጣ መጨመር፣ የሠራተኞች ደመወዝና ጥቅማ ጥቅሞች ማደግ ቀዳሚ ምክንያቶች ናቸው ተብሏል፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባንኩ በአዲስ አበባ ‹‹የፋይናንስ መንደር›› እየተባለ በሚጠራው ሠንጋ ተራ አካባቢ የገነባው ባለ 33 ወለል ሕንፃ ግንባታው ከጥቃቅን ሥራዎች በስተቀር በመጠናቀቁ የዋና መሥሪያ ቤቱን አገልግሎቶች ወደዚህ አዲስ ዘመናዊ ሕንፃ ማዛወር መጀመሩን አስታውቋል፡፡ የባንኩ ለዋና መሥሪያ ቤትነት በኪራይ ከሚጠቀምባቸው ሕንፃዎች መካከል ቦሌ አካባቢ የሚገኘው አንደኛው ሕንፃ ውስጥ ያሉትን አገልግሎቶች ወደ አዲሱ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ካሳንቺስ የሚገኘውም ባንኩ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ በዋና መሥሪያ ቤትነት የሚገለገልበትን ሕንፃ በሁለት ወር ውስጥ ለቆ ወደ አዲሱ ሕንፃ የሚገባ ስለመሆኑና ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ ባንኩ ራሱ ወዳስገነባው ሕንፃ መዛወሩ ለዓመታት ለዋና መሥሪያ ቤትነት ሲያወጣ የነበረውን ከፍተኛ የኪራይ ዋጋ ያስቀርለታል ተብሏል፡፡ 

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ደረጃ ለሪፖርተር እንደገለጹትም ባንኩ ወደ አዲሱ ሕንፃ ሲገባ ለኪራይ በዓመት ያወጣ የነበረውን እስከ 40 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ወጪ ያስቀርለታል ብለዋል፡፡ 

ዘመን ባንክ ይህንን ሕንፃ ለማስገንባት ኮንትራት የተፈራረመው 1.2 ቢሊዮን ብር እንደነበር የሚታወስ ሲሆን አሁን ላይ የዋጋ ንረትና በሕንፃው የታከሉ ተጨማሪ ሥራዎች የግንባታውን ወጪ ከፍ ሊያደርጉት እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ከዚህ ሕንፃ ሌላ አዲስ ሕንፃ ለመገንባት ዕቅድ ያለው መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህም ሕንፃ ከአዲሱ ዋና መሥሪያ ቤት አጠገብ ከተረከበው በተለይ የሚገነባ እንደሚሆን ከአቶ ደረጀ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ይህ አዲስ ሕንፃ አሁን ወደ አገልግሎት እየገነባ ካለው ሕንፃ የሚበልጥ መጠን ያለው ሕንፃ እንደሚገነባም ይኸው ከባንኩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች