Tuesday, March 5, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግብርናና የኢንዱስትሪ ዘርፉ ትስስር በጣም ደካማ መሆኑን  ጥናት አመላከተ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ በግብርናና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያለውን ትስስር ለማጠናከር የተለያዩ ዕርምጃዎች ቢተገበሩም በክፍለ ኢኮኖሚዎቹ መካከል ያለው ትስስር በጣም ደካማ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ያጠናው ጥናት አመላከተ፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ባዘጋጀው የፖሊሲ ውይይት መድረክ ላይ ለውይይት የቀረበው ጥናት፣ በኢትዮጵያ የግብርና ኢንዱስትሪው ትስስር በተለይም ከሥራ ፈጠራና የኢኮኖሚ ለውጥ ከማስገኘት አኳያ ምን ይመስላል? የሚለውን አመላክቷል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዴቬሎፕመንት ስተዲስ ኮሌጅ መምህርና በኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ተመራማሪ ሰለሞን ፀሐይ (ዶ/ር) ባቀረቡት ጥናት፣ በተለያየ ወቅቶች አገሪቱ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን ከአምራች ዘርፉ ለማስተሳሰር የተለያዩ ዕቅዶችን ተግባራዊ ብታደርግም፣ በተግባር ያለው የክፍለ ኢኮኖሚዎቹ ትስስር ዳካማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የጥናቱ ግኝት እንደሚያሳየው፣ በኢትዮጵያ ያለው የግብርናና አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ትስስር በጣም ደካማ በመሆኑ፣ አገሪቱ ልታሳካ የምትችለውን የዕድገት ምኞት ግቡን እንዳይመታ ሊያደርገው ይችላል የሚል ሐሳብ ተያይዞ ቀርቧል፡፡

የአገር ውስጥ ኢንዱሰትሪ ዘርፎች በአብዛኛው ከግብርናው ዘርፍ ጋር የተሳሰረ አይደለም የሚሉት ሰለሞን (ዶ/ር)፣ ጥናቱን በሚደረግበት ወቅት ከፖሊሲ አውጪዎች፣ ከኢንዱስትሪ ባለቤቶች ጋር ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ እያንዳንዱ ዘርፍ የተለያየ ችግር እንዳለበት መረዳታቸውን አመላክተዋል፡፡

ለአብነትም የእንስሳት ሀብት ዘርፉ ላይ የሕገ ወጥ ንግድ አንዱ ሳንካ ከመሆኑም ባሻገር፣ ዘርፉ ዘመናዊ አለመሆኑ በተለይም በሥጋና የሥጋ ውጤቶች ምርት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ ተገልጿል፡፡

በዚህ ወቅት ያለው የአምራች ኢንዱስትሪው ከአጠቃላይ ኢኮኖሚው ድርሻ 6.8 በመቶ ብቻ መሆኑን የሚናገሩት ተመራማሪው፣ ይህም የዘርፉን ደካማነት የሚሳይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የአምራች ዘርፉ ካላደገ ሥራ አጥነትን ከመቀነስ አንፃር፣ አገሪቱ ካጋጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረት አንፃር ትልቅ ጉድለት የሚፈጥር መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ለግብርናው ዘርፍ ከየትኛውም ዘርፍ በተሻለ የፊትና የኋልዮሽ ትስስር የሚፈጥረው የአምራች ዘርፉ እንደመሆኑ መጠን፣ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራበት ይገባል ተብሏል፡፡

አንድ ዘርፍ ብቻውን ሳይሆን በውስጥ ያሉ ተዋንያኖችን ያማከለ የኢንቨስትመንት አቅጣጫ መሰጠት አለበት የሚሉት ሰለሞን (ዶ/ር)፣ ይህም ከዕቅድ እስከ አፈጻጸም እንዲሁም ቁጥጥርን ጨምሮ ውጤት መምጣት አለበት የሚለውን የሚዳስስ ነው፡፡

ለአብነትም ‹‹ግብርና የዘርፉን ዕቅድ ሲያቅድ ብቻውን ሳይሆን ለማን ነው የማቅደው?›› ተብሎ ሊነደፍ የሚገባው ሲሆን፣ ለምሳሌ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆን ነገር አቅዶ መስጠት መቻል አለበት ተብሏል፡፡ የአምራች ዘርፉ በተመሳሳይ በሚያቅድበት ወቅት ከየት፣ ምን አገኛለሁ? ተብሎ ከግብርናው ዘርፍ ጋር ተሳስሮ መሠራት እንደሚገባው ጥናቱ አሳይቷል፡፡

በሌላ በኩል የተለያዩ ዘዴዎችን የሚያስተዋውቁ እንዲሁም በግብርናና አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ መካከል ዘላቂ የሆነ ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል ውጤታማ ፖሊሲ አለመኖሩ ጥናቱ ያመላከተው ጉዳይ ነው፡፡

በአገሪቱ የአገልግሎት ዘርፉ ከአምራች ኢንዱስትሪ በበለጠ የፋይናንስ አቅርቦት ማግኘቱ አንዱ በማነቆነት የሚነሳ ጉዳይ መሆኑ ተገልፆ፣ በቀጣይም አገሪቱ የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ክፍት ስታደርግ ልብ ሊባል ከሚገባቸው ጉዳዮች ውስጥ ለኢንዱስትሪዎች የሚቀርብ የፋይናንስ አቅርቦት መሆኑን የውይይቱ ታዳሚያን ገልጸዋል፡፡

ሰለሞን (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪውን ለማስፋፋት የዕድገት ኮሪደር ሲመረጥ ያለውን አቅም መሠረት ተደርጎ መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የተለያየ የአየር ንብረት መልክዓ ምድር ስላላት የት ጋር ምን ቢመረት?፣ ከየቱ ጋር ቢተሳሰር ውጤታማ ሊሆን ይችላል የሚለው መታየት አለበት፡፡

ስለግብርና ዘርፍ ደጋግሞ ማውራት ብቻ ሳይሆን በግልፅ የተለየ፣ የትኛውን የግብርና ንዑስ ክፍል፣ የትኛውን የሰብል እህል ላይ ነው የምናተኩረው? የሚለው ተነጥሎ መታየት አለበት የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች፣ ስለአምራች ኢንዱስትሪው ሲገለጽ በተመሳሳይ የቱ ላይ እስከ መቼ ይተኮር? የሚለው በግልፅ መቀመጥ አለበት ብለዋል፡፡

የግብርናና ኢንዱስትሪ ትስስር ፊትና ኋላ የሚሄድ ሳይሆን አብሮ ተያይዞ የሚሄድ፣ አንዱ ከሌላኛው ተነጥሎ የማይሄድ በመሆኑ አስተሳስሮና አያይዞ መሄድ ተገቢነቱ በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች