Sunday, May 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት በመጋዘን ውስጥ ለመጠባበቂያ የሚሆን የስኳር ክምችት እንደሌለው ገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በፓርላማ ስብሰባዎች ላይ ሻይ ቡና ያለ ስኳር መቅረብ ጀምሯል

በመጀመርያ ሩብ ዓመት በ2015 ዓ.ም. ከውጭ ተገዝቶ መግባት የነበረበት የስኳር ምርት ወደ አገር ባለመግባቱ፣ በመንግሥት መጋዘኖች ለመጠባበቂያ የሚሆን ምርት እንደሌለ ተገለጸ፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች የተቋማቸውን የ2015 ዓ.ም. የመጀመርያ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም በተጠናቀቀው ሳምንት ለንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርበዋል፡፡

መንግሥት በሩብ ዓመቱ ከ835 ሺሕ በላይ ኩንታል ስኳር ለማሠራጨት አቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ ማሠራጨት የቻለው 284 ሺሕ ኩንታል ስኳር ብቻ መሆኑን፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትሩ አቶ ገብረ መስቀል ጫላ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በፍራንኮ ቫሉታ ከታክስና ከቀረጥ ነፃ 1.8 ሚሊዮን ኩንታል የስኳር ምርት ወደ አገር ውስጥ እንደገባ ተጠቅሷል፡፡ ይሁን እንጂ በገበያው ላይ ለሕዝቡ ሲቀርብ የነበረው የስኳር ምርት በከፍተኛ ዋጋ ከመሸጡም በላይ፣ ‹‹በአገር አቀፍ ደረጃ የስኳር አቅርቦት እጥረት ለምን አጋጠመ?›› ሲሉ የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጠይቀዋል፡፡

ወ/ሮ ሉባባ ኢብራሂም የተባሉ የምክር ቤት አባል በኅብረተሰቡ ውስጥ የበዛ እሮሮና ቅሬታ እየተነሳ ስለመሆኑ፣ በተለይም ከመሠረታዊ ሸቀጣ ሸቀጥ አቅርቦቶች ጋር በተገናኘ ሲናገሩ፣ ስኳርን ገበያ በሕጋዊ መንገድ ካለው ይልቅ በሕገወጥ መንገድ የሚሸጠው ገበያውን እንደተቆጣጠረው ተናግረዋል፡፡

‹‹ስኳር በየሱቆቹ በጣም ውድ በሆነ ዋጋ ይቸረቸራል፡፡ ከየት መጣ ብለን ስንጠይቅ ስኳሩ ከየትም አልመጣም፣ መንግሥት ገበያውን ለማረጋጋት ብሎ በሕጋዊ መንገድ ገዝቶ ሲያከፋፍል ወደ ሕገወጥ ሥርዓት ገብቶ ሲሸጥ ይታያል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በተወሰነ መልኩ አዲስ አበባ ውስጥ ስኳሩን በማንኪያም ሆነ በስኒ እናገኛለን፡፡ ነገር ግን ከከተማ ውጪ ያለው ማኅበረሰብ ግን እያገኘ አይደለም፡፡ የመረጠንን ማኅበረሰብ ስናወያይ የሚሰማው ነገር መንግሥትና ሕዝብ ሆድና ጀርባ እንደሆነ ነው፤›› ይህንን በመንግሥትና በሕዝብ መካከል የተፈጠረ መሰናክል መፈታት አለበት፡፡ ይህ ተቋም በመሆኑ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን አቅዶ መንቀሳቀስ እንዳለበት አክለው አሳስበዋል፡፡

አክለውም ተቋሙ ያወጣው ዕቅድ ውጤት ሊያመጣ ይቻላል ወይ? ብለን ስናገላብጥ ዕቅዱ ምንም ነገር እንደሌለው ዓይተናል ብለዋል፡፡

‹‹መንግሥት የገበያ ሁኔታውን ማረጋጋት ባለመቻሉና ጠንካራ የንግድ ክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት ባለመፈጠሩ የከፋው ማኅበረሰብ ነው የያዝነው፤›› ያሉት ደግሞ አቶ አስቻለው አላምሬ የተባሉ የምክር ቤት አባል ናቸው፡፡

ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት ሚኒስትሩ፣ ስኳር ኮርፖሬሽን ባለፉት ወራት ማስገባት የነበረበትን ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ወደ ገበያ ማስገባት ባለመቻሉ፣ ገበያ ላይ እጥረት መፈጠሩንና ለሕዝቡ መድረስ የነበረበት መጠን ሊደርስ አለመቻሉን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ወራት በፍራንኮ ቫሉታ 1.8 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ቢገባም፣ መንግሥት እጁን አስገብቶ ዋጋ መተመን የማይችል ባለመሆኑ ገበያው ውስጥ አለመረጋጋትና የዋጋ ንረት ሊፈጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡፡

ይሁን እንጂ በመንግሥት የተሠራጨውን 835 ሺሕ ኩንታል ስኳር ለዝቅተኛ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንዲሆን ታስቦ በኮታ እንዲሠራጭ ወደ ተለያየ የኢትዮጵያ ክፍሎች ቢሠራጭም፣ ስኳሩን ለመውሰድ ኩፖን ለማይገባው ሁሉ በመስጠቱ ስኳሩን ሲወስደው የነበረው የማይገባው ሰው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ ስኳር እጥረት በማጋጠሙ ለዩኒቨርሲቲዎችና ለትምህርት ቤቶች የሚፈለገውን ስኳር ማቅረብ የተቻለው ኮርፖሬሽኑ ከነበረው ክምችት ውስጥ አሟጦ መሆኑን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡  

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች በተጠናቀቀው ሳምንት በርካታ ስብሰባዎችን ያካሄዱ ሲሆን፣ በእነዚህ ስብሳባዎች ለተሰብሳቢዎች ሲቀርብ የነበረው ሻይ፣ ቡናና ወተት ያለ ስኳር እንደነበር ሪፖርተር መታዘብ ችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች