Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉሰላማችን ከፖለቲከኞች ፍላጎት በላይ ናት!

ሰላማችን ከፖለቲከኞች ፍላጎት በላይ ናት!

ቀን:

በፍሬሕይወት ተሰማ

‘በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል ዕርቀ ሰላም በደቡብ አፍሪካ ተፈረመ’ ሲባል እንደ ብዙ ኢትዮጵያዊ ወገኖቼ ግራ ተጋባሁ፡፡ ምክንያቱም ከሁለት ሦስት ቀናት በፊት ምዕራባውያን ማስፈራሪያ የሚመስሉ አስተያየቶች ሲሰጡ ስለተመለከትኩ ነው፡፡ እንዴት ሁሉም ጉዳይ እንዲህ በቶሎ በስምምነት አለቀ ብዬ ተገረምኩ፡፡ አምላኬን የማይቻለውን ስላስቻለ እንደገናም ጣልቃ ስለገባ ከቤተሰቤ ጋር ተንበርክከን አመሠገንነው፡፡

ለወትሮው በእንዲህ ያለ ሁኔታ የቅርብ ወዳጆቼ ጋር ደውዬ ደስታዬን የማካፍል ቢሆንም፣ በዚህ ጊዜ ግን ለራሴም ለመረዳትና በጥያቄ የተሞላውን አዕምሮዬን ለማሳመን ጊዜ ወሰድኩ፡፡ በዚያ ሁኔታ እያለሁ ጓደኛዬ ደወለችልኝ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹ፍርዬ፣ ሰማሽ አይደል?!››

‹‹…እግዚአብሔር ይመሥገን! አምላካችን ይመሥገን!›› ከማለቷ የደስታ ዕንባ ሲቃ ሲያንሰቀስቃት ስሰማ ደነገጥኩ፡፡ እውነት ነው ይህች እህቴ የትግራይ ክልል ተወላጅ ናት፡፡ የቤተሰቧን፣ በተለይ የወንድም የእህቷን ወሬ ከሰማች ሁለት ዓመታት ሊሞላት ነው፡፡ ነገር ግን ያስለቀሳት፣ የደስታ ሲቃ የያዛት፣ ተስፋም የሰጣትና ከዚህ በላይ የሆነ ምክንያቷን አስታወስኩ፡፡ ስልኩን ከዘጋሁ በኋላ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያሳለፈችውን ውጣ ውረድና መከራ አስታውሼ፣ እኔም በሐዘንና በለቅሶ በአዲስ ምሥጋናና ተስፋ ተሞላሁ፡፡

ጦርነቱ እንደተጀመረና መንግሥት መቀሌን እንደተቆጣጠረ እንደ ማንኛውም ሰው ዕረፍትና ተስፋ አድርጋ፣ ነገር ግን ሁሉም ቤተሰቧ ሰላም መሆኑን ለመስማት ወሬ ትጠብቅ ነበር፡፡ እውነትም ራያ አካባቢ ያሉት ወንድሞቿም ሆኑ ሄዋኔ ያለችው እህቷ ሰላም መሆናቸውን መስማታችን ለጊዜው እረፍት ሰጠን፡፡ መቀሌ አካባቢ ወንድምና እህት ቢኖራትም በወቅቱ በዚያ ጦርነት ስላልነበረ እጅግም አልሠጋችም ነበር፡፡

ከዚህች ጓደኛዬና እህቴ ጋር በተለያዩ ጊዜያት በትግራይ ክልል ያሉ ቤተሰቦቿንና ዘመዶቿን ተዋውቄ፣ በፍቅርና በደግነት አስተናግደውኝ ስለሸኙኝ ደህና መሆናቸውን ስሰማ እኔም እረፍት አገኘሁ፡፡ በተለይ ከዚህች ትግራዋይ ጓደኛዬ ጋር ‹‹መኾኒ›› የሚባለው ቦታ ሄደን ከአሥር በላይ የሚሆኑ ቤተሰቦቿ ሊያገኟት ከገጠር መጥተው ሲጨዋወቱ፣ እኔ መካከላቸው ካለሁ እኔም ጨዋታቸው እንዲገባኝ ወዲያውኑ ቋንቋቸውን ወደ አማርኛ ይቀይሩት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡

ከእነሱ ውስጥ አንዳንዶቹ አማርኛ መናገር የማይችሉ መሆናቸውን ስረዳ፣ እንዲጫወቱ ብዬ ከአጠገባቸው ዞር ስል እንደገና በቋንቋቸው ማውራት ይጀምራሉ፡፡ እኔም፣ ‹‹እባካችሁ በሚመቻችሁ ቋንቋ አውሩ፡፡ ደግሞ እኮ ትግርኛን ለመስማት ቀላል ነው፣ አማርኛ ማለት ነው፤›› ስላቸው፣ ‹‹ከመቼ ወዲህ ነው ቋንቋችንን የማይናገር እንግዳ አጠገባችን አስቀምጠን በቋንቋችን የምናወራው?!›› ያሉኝን በፍፁም አልረሳውም፡፡ ከዚህ ደግነትና ፍቅራቸው የተነሳ ደኅንነታቸውን መስማቴ እረፍትና ደስታን ሰጥቶኝ ነበር፡፡

ነገር ግን በሳምንቱ አካባቢ መቀሌ ይኖር የነበረ በግል ሥራ የሚተዳደር የዚህች ጓደኛዬ/እህቴ ወንድሟ በተባራሪ ጥይት ተመትቶ ማረፉን ተረዳች፡፡ ይህ ወንድሟ እንደ ልጇ ያሳደገችው ሲሆን፣ የግል ድርጅቷን በኃላፊነት የሚመራ ነው፡፡ እኔም በተለያየ ጊዜ ከዚህች ጓደኛዬ ጋር ትግራይ ስንሄድ ያገኘሁት ሲሆን፣ በተለይ ጓደኛዬ ከዘመዶቿ ጋር ስትጫወት እኔና እሱ ወጣ ብለን በየከተማው አንዳንድ ቦታዎች ያስጎበኘኝና ታሪክም ያጫውተኝ ስለነበር በብዙ እንቀራረብ ነበር፡፡ ቀልድና ጨዋታ የሚወድ ስለሆነ በተለያዩ ነገሮች ስደናበር ‹‹ሙድ›› ይዞ ስቆ ያስቅብኝ ነበር፡፡

የዚህን ወንድሟን መሞት የሰማችው ጓደኛዬ ሐዘኗ እጅግ ከባድ በመሆኑ፣ የሆነውን ማመን አቃታት፡፡ መንግሥት ገብቶ መቀሌ ሲረጋጋ ከቤቱ ወጥቶ ትልቅ እህቱ ቤት እየሄደ ነው የተተኮሰበት፡፡ ከሁሉ የሚገርመው ሐዘንተኞች ዕርማቸውን ሊያወጡና ሊያፅናኗት ሲመጡ የመንግሥት ወታደር እንደገደለው በእልህና በንዴት ሲናገሩ ስትሰማቸው እንዲህ ነበር ያለቻቸው፣ ‹‹የሞተው አንድ ኢትዮጵያዊ ወንድሜ፣ ወገናችን ነው፡፡ ከዚህም ከዚያም ወንድም ወንድሙን ገድሏል፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን የኢትዮጵያ እናትና እህት ታልቅስ!›› ነበር ያለችው፡፡

ይህች ጓደኛዬ አብዝታ ስታዝን የነበረው ጦርነቱ በኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ ባስከተለው ጉዳት፣ ሞት፣ መፈናቀል፣ ውድመት… እንጂ፣ ‹‹የወንድሜ ገዳይ እከሌ ነው›› በሚል አልነበረም፡፡ በእርግጥ ከዚህ ማንነቷ የተነሳ በዘመናት ውስጥ ብዙ ወዳጆች በዙሪያዋ ቢኖሩም፣ በዚህ ሁኔታዋ ግን ሰው ሁሉ እጅግ ተደነቀ፣ ማመን ያልቻለው ብዙ ነው፡፡ ብዙዎች ለቅሶ ሊደርሱ መጥተው፣ ‹‹ልናፅናናሽ መጥተን አፅናንተሽ መለስሽን፤›› ብለዋታል፡፡

ይህች ጓደኛዬ ጠንካራ የቢዝነስ ሰው ከመሆኗም በላይ አንባቢ፣ አሳቢ፣ ለኅብረተሰብ መልስ በመስጠት የምታምን፣ ለውጥ የምትናፍቅ፣ ተስፋ የምታደርግ፣ በነገር ሁሉ መልካሙን ማየት የምትመርጥ ናት፡፡ ለውጡ መጥቶ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሥራ ፈጣሪዎችን ማበረታታት የሚል ሐሳብ ሲያፈልቁ የድርጅቷን ሠራተኞች ሰብስባ፣ ምሳ ጋብዛና አዲስ ተስፋ፣ አዲስ ጅማሬ እንዳለ አብሥራ ከሥራው በተጨማሪ በግል የራሱን ፈጠራ ይዞ የሚመጣን ሠራተኛ በፋይናንስ እንደምታግዝ ቃል ገባች፡፡ ለውጡን በሙሉ ልቧ ተቀብላ ሠራተኛውንም በአዲስ ተስፋ በግል ሕይወቱ፣ በሥራው፣ እንዲሁም ለአገሩ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ላይ እንዲበረታ አሳሰበች፡፡

በአስተሳሰብ ላይ በተለይ ወጣቱ ላይ መሥራት ይገባል በሚል ‹‹ህልዮተ ዓምባ›› የሚል ስብስብ ፈጥራ ወጣቱ በመነጋገር ችግርን በውይይት መፍታት፣ እንዲሁም ትውልዱ ከተዘፈቀበት የሞራል ዝቅጠት እንዴት መውጣት ይችላል? በሚል በትምህርት ጥራት፣ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂና በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በየሳምንቱ ተገናኝቶ ሐሳብ የሚያነሳ፣ የሚወያይ፣ የሚከራከርና የሚጽፍ ቡድን መሠረተች፡፡ ይህ ስብስብ ኮሮና መጥቶ እስኪቀዛቀዝ ድረስ ለሁለት ዓመት አካባቢ ዘልቋል፡፡

ለአብነትም በዚህ ቡድን ውስጥ ከተነሱ የውይይት አጀንዳዎች መካከልም፣ በትምህርት ጥራት ዙሪያ ለስድስት ሳምንታት የዘለቀው ውይይት አንዱ ነበር፡፡ በዚህ ውይይት ላይ በወቅቱ የዚህ ስብስብ መሪና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ትምህርት ምሁር፣ ከትምህርት ሚኒስቴር የሥነ የትምህርት ምሁራንና ኤክስፐርቶችን በመጋበዝ የተለያዩ የቡዱኑ አባላት ሰፋ ያለ ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦች እንደተነሳበት አስታውሳለሁ፡፡

በዚህ ውይይታችን መጨረሻ ላይም በወቅቱ የትምህርት ሚኒስቴር ደኤታ የነበሩት ወ/ሮ ፅዮን ተክሉ በመካከላችን ተገኝተው በትምህርት ጥራት ጉዳይ ላይ በህልዮተ ዓምባ የተነሱ ሐሳቦችን ካካፈልናቸው በኋላ፣ እነዚህ የተነሱ ሐሳቦቹን ወደሚመሩት ተቋም በመውሰድ በግብዓትነት እንደሚጠቀሙባቸውና እንዲህ ዓይነቶቹ አገራዊና ለትውልድ ጠቃሚ የሆኑ ውይይቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስተያየታቸውን ሰጥተውን ነበር፡፡

የዚህ ስብስብ ህልዮተ ዓምባ መሥራች የሆነችው ለአገርና ለትውልድ በጎ ራዕይ የሰነቀችው ይህቺ እህቴ በመንግሥትና በሕወሓት ኃይሎች በኩል ጦርነቱ ለሁለተኛ ጊዜ ሲጀመር፣ የትግራይ ተወላጆች በጥቆማ ይታሰሩ ነበርና እሷም ከቤቷ ተወሰደች፡፡ ማንነቷን የምናውቅ ሰዎች ልባችን ቢደማም፣ ሁኔታው ለእሷና ለቤተሰቧ አስደንጋጭ ነበር፡፡ የጠቆመባት ሰው ደግሞ ‹ባለ ተራ ነኝ› የሚል፣ ይህች ጓደኛችን ለውጡን መደገፏና ተስፋ ማድረጓ ያላስደሰተው የድርጅቷ ሠራተኛ መሆኑን ማመን ከብዷት ነበር፡፡

ነገር ግን ጓደኛችን ነፃ መሆኗ ተረጋግጦ ከ20 ቀናት እስር በኋላ ስትወጣ፣ ሊያፅናኗት የሚመጡ ወዳጅ ዘመዶቿ በመኪናዋ ቁልፍ መያዣ ላይ ያለውን የዓብይን (ዶ/ር) ፎቶ አሁንም ይዛ መታየቷን ማመን አልቻሉም፡፡ አንዳንዶች ጓደኞቿም፣ ‹‹አሁንም በዓብይና በአስተዳደሩ ላይ ተስፋ አልቆረጥሽም ማለት ነው እንዴ?! ለመሆኑ ከዚህ በላይ በአንቺም ሆነ በሕዝባችን ላይ ምን እንዲደርስብን ፈልገሽ ነው…? አይ እሷንስ ይበላት!›› ለሚለው አስተያየታቸውን ያዘንቡባት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታዬ ነው፡፡

እሷ ግን በምላሿ የምትሰጠው መልስ፣ ‹‹መንግሥት ምን አደረገኝ? ይህንን አላስፈላጊ ጦርነት ያመጣብን ድኅነታችን፣ ከአገራዊ የሞራል እሴቶቻችን መፈናቀላችን፣ ፈጣሪያችን/አምላካችን አብዝቶ ከቸረን ፍቅርና በጎነት መጉደላችን ነው እንጂ!?›› ነበር፡፡ ብዙዎቻችን ጓደኞቿ እንዲህ እንል ነበር፣ ‹‹እንዴት ቂም አትይዝም? እንዴት አትማረርም? እንዴት አይከፋትም?›› እውነትም ለማመን የሚከብድ ነው፡፡ ነገር ግን እሷ ማሰብና ማመዛዘን የምትችል፣ ላመነችበት እውነት በፅናት የምትቆም፣ ነገሮችን ከራሷ አንፃር ብቻ የማታይ በሳል፣ ባለ ራዕይ፣ ለአገሯና ለወገኖቿ የምትቆረቆር ሴት ናት፡፡

ይህም እንዳይበቃ ያው የጠቆመባት ሰው በሥራ ቦታዋ የመንግሥት ተቆጣጣሪዎችን እየላከ ይህንና ያንን ማስረጃ እያስጠየቀ ቁም ስቅሏን አሳያት፡፡ ከጭንቀቷ የተነሳ ጤናዋን ማጣት ጀመረች፡፡ ዳግም እንዳያሳስራት በፍርኃት ራደች፡፡ የዛሬ ሰላሳ ዓመት ሥራዋን አገሯ ለመሥራት ጠቅልላ የመጣች፣ አገሯ ውስጥ ብዙ ደክማ የተሳካላት ሴት፣ ከዚህ የተነሳ ተማራ ሳትወድ በግድ ከአገሯ እንደገና ለመሰደድ ተገደደች፡፡

ለዚህም ነው ይህ አሁን የተፈረመው ‹‹የሰላም ስምምነት›› ከፖለቲከኞች ፍላጎት በላይ ነው በሚል፣ ይህ የጓደኛዬን አሳዛኝ ገጠመኝ ለማካፈል የፈለግሁት፡፡ በየጦር ቀጣናው ያሉት ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ፣ ከዚህና ከዚያ ዘር ብቻ ስለሆኑ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ያሉ ወገኖችም በእጅጉ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ሕይወታቸውን፣ ጤናቸውን፣ ሥራቸውንና ቤተሰባቸውን አጥተዋል፡፡ ለዚህ ነው ይህ የሰላም ውል ሲፈረም ብዙዎች በዕፎይታ በደስታ ያነቡት፡፡

እነዚህ ወገኖች ዕፎይታቸውና ደስታቸው ትልቅ ምክንያት አለው፡፡ ይኼውም በሞት የተለዩዋቸውን ወገኖቻቸው መቃብር ላይ ሄደው ዕርማቸውን ለማውጣት ከመፈለግ፣ የአዛውንት እህት፣ ወንድም፣ እናት አባትን ትከሻ አቅፎ ለመሳም ከመጓጓት፣ በረሃብና በጦርነት የተጎዱትን ወገኖች ለመደጎም ከመፈለግ የተነሳ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ ዘመናቸውን በሙሉ የደከሙበትን ሥራ በሰላም ለማስቀጠል ከመፈለግ፣ በወንድማማችነትና በመተማመን እንደ ወትሮው ከሌላው ሕዝብ ጋር በሰላም ለመኖር፣ ዳግም ‹‹የውሾን ነገር ያነሳ …›› ብሎ ምሕረትና ይቅርታ አድርጎ የሰላም ኑሮን ለመኖር ከመፈለግ የተነሳ ነው፡፡ እናም እባካችሁን ሰላማችንን አታቃሉብን፣ አታወሳስቡብን፣ ለእኛ ሰላማችን የግል ጉዳያችን ነውና!!

ሰላም ለኢትዮጵያ! ሰላም ለምድራችን!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ (ክፍል አንድ)

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...