Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየጥቅምት 23 የሰላም ስምምነት የታሪክ ሥፍራ

የጥቅምት 23 የሰላም ስምምነት የታሪክ ሥፍራ

ቀን:

በአንዳርጋቸው አሰግድ

የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር የመስተዳድሩን ወንበር ከጨበጠበት ከ2010 ዓ.ም. አንስቶ በርካታ የውጭ ጫናዎችን ለመቋቋም ተገዶ እንደነበር ይታወቃል። አስተዳደሩ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መጠበቅና መከበር እንዳለበት በየአጋጣሚው ከማሳወቅ ቦዝኖ አያውቅም፡፡ መስተዳድሩ ከዚህ አኳያ ከህዳሴ ግድብ እስከ ደቡብ አፍሪካው ድርድሮች ድረስ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ልዕልናና ግዛታዊ አንድነት ለማስከበር ለወሰዳቸው አቋሞችና ዕርምጃዎች ዕውቅና ሊሰጠውና በየምዕራፉም በፅኑ ሊደገፍ ይገባል።

አሁን ይህ ጽሑፍ በሚዘጋጅበት ሰዓት ስለፕሪቶሪያው ስምምነት ለመግለጽ የሚቻለው አደራዳሪውን ኦባሳንጆን ተከትሎ፣ ‹‹ከባዱ ሥራ  ገና ከፊት ያለ እንደሆነ ብቻ ነው››፡፡ እንደዚሁም ተስማሚዎቹ ወገኖች የስምምነቱን አንቀጾች እንደሚያከብሩ ተስፋ እንደሚደረግ ነው፡፡ ከውስጥና ከውጭ በሚያርፉባቸው አሰናካይ ጫናዎች ምክንያት ከስምምነቱ ውጭ ያሉ ጉዳዮችን እየሸነቆሩ እንዳያሰነካክሉት ነው። ከዚህ አኳያ፣ አዲሱ የሕወሓት አመራር ከውስጡና በተለይም የትግራይ ዳያስፖራ ከሚባለው ክፍል የሚነሱበትን የቀድሞው ሕወሓት ናፋቂያን ግፊቶችን ለመቋቋም እንደሚበቃ ተስፋ ይደረጋል። የዓብይ (ዶ/ር) አስተዳደርም ጣልቃ ገብነታቸውና ጫናቸው የማይነጥፈውን የውጭ ኃይሎች በመቋቋምና በማምከን እንደሚቀጥል፣ ነገር ግን ደግሞ ከስምምነቱ በኋላ የተስተዋሉትን አንድ ሁለት ታሪካዊ ጉዳዮችንም ላለማስታወስ አይቻልም።

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከሁሉም ከሁሉም በፊት ከኢትዮጵያ አስተዳደርም ሆነ ከኢትዮጵያ ሕዝብ በኩል ምንም ዓይነት የአሸናፊነት ቡረቃ (Triumphalism) አልታየም፣ አልተሰማም። ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አንስቶ እስከ መንገደኛው ተጠያቂ ድረስ  ተደጋግመው የተነገሩትና የተሠራጩት አመለካከቶች፣ በተቃራኒው ‹‹አሸናፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው›› እና ‹‹ያሸነፈው ሰላም ነው›› የሚሉ አርቆ አስተዋይነት የተሞላባቸው አስተውሎቶች ናቸው። ይህ በራሱ የመስተዳድሩንና የሕዝቡን የፖለቲካ ብስለት በአደባባይ ያስመሰከረ ነው። እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለስምምነቱ መተግበርና ለሰላም መስፈን ያለውን ከፍተኛ ፍላጎትና ናፍቆት አጠንክሮ ያመለከተ የአደባባይ አዋጅ ነው። በተጨማሪም የኢትዮጵያን የፖለቲካ ዓለም ከግዳጅ ጣይ ፎካሪዎች ባህል አላቆ በአርቆ አስተዋይነትና በፖለቲካ ትህትና (Modesty) ባህል ወደ መተካት ያቀና በመሆኑ፣ ከፍተኛ የፖለቲካ ትምህርትን የሰጠና ያስተዋወቀ ነው።

ይሁንና ይህ ሁሉ የተቻለው ተደራዳሪዎቹ በአንድ ወገን የሚገኙበትን ነባራዊ ሁኔታ በውል ለማስተዋል በመብቃታቸው ነው። ሰላም የሚያስገኘውን ጥቅም በመገንዘባቸው ነው። በሌላው ወገን፣ የአፍሪካ ኅብረትና በተለይም መሪው ሙሳ ፋቂ ከአሜሪካ አስተዳደር፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ሠፈር የሚደረግባቸውን ጫና ስለተቋቋሙ ነው። አደራዳሪዎቹ ኦባሳንጆ፣ ኡሁሩና ምላልምቦ (ዶ/ር) አገሮቻቸውን በፕሬዚዳንትነት የመሩና ከፍተኛ ተሞክሮ ያላቸው ግለሰቦች በመሆናቸው ነው። እዚህም ላይ ከድርድሩ መጀመር በፊት በርካታ እሳት ለኳሽና አቀባይ የወሬ ነጋዴዎች ስለፕሬዚዳንት ኡሁሩ ብዙ ብዙ አውርተው እንደነበር መታወስ ይኖርበታል፡፡ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ተደራዳሪዎቹን በመምከርና በማግባባት በብዙ የደከሙ አደራዳሪ እንደነበሩ ከእርግጠኛ ምንጭ እንደሰማሁ መግለጽ ይኖርብኛል፡፡  

ስምምነቱ ሁለተኛና ከመጀመርያው ባላነሰ ደግሞ፣ ‹‹ለአፍሪካ ችግሮች የአፍሪካውያን መፍትሔ›› በሚለው መርሆ መሠረት በመጠራቱና በመመራቱ ከአኅጉራዊ ፖለቲካ አንፃር ለአፍሪካ አዲስ ምዕራፍን የከፈተ ሆኗል። አንደኛ በአፍሪካ ምድር ተከናወነ። ሁለተኛ በአፍሪካ ኅብረት አማካይነትና የአፍሪካ ኅብረት በሰየማቸው ዋና አደራዳሪና በአፍሪካዊ ተባባሪዎቻቸው ብቻ ተመራ። ሦስተኛ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትንና የአሜሪካ መንግሥትን ተሳታፊዎች በታዛቢነት ወሰናቸው። አራተኛና በመጨረሻም የአውሮፓ ኅብረትን ከተሳትፎ ውጪ አደረገ። የፕሪቶሪያው ድርድርና ስምምነት በዚህም ለዛሬዎቹና ለመጪዎቹ የአፍሪካ ፖለቲካ ችግሮች መፍትሔዎች ከፍተኛ ትርጉም ያለውን የድርድር አካሄድና ሥርዓት አጠንክሮ የቸከለ መመርያ (Precedence) ነው። የኮንጎ፣ የቻድ፣ የመካከለኛው አፍሪካ፣ የሶማሊያና ሌሎቹም የአፍሪካ ችግሮች የፕሪቶሪያው መንገድ ተረኞች እንዲሆኑ እመኛለሁ።

የፕሪቶሪያው ስምምነት በተጨማሪ ኢትዮጵያ ከዓድዋ ድሏ፣ ለአፍሪካውያን ፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግል ካደረገቻቸው ተከታታይ ድጋፎችና ከአፍሪካ ኅብረት መሥራችነቷ በኋላ በአፍሪካ ምድር የቸከለችው አራተኛው የታሪክ ዓምዷ ነው። የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓትና የአገሪቱ የመገናኛ አውታሮች በዚህ ረገድ ገና ብዙ ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፣ ይገባቸዋል። የኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ደራሲያንም የእነ ዮፍታሔ ንጉሤን፣ ፀጋዬ ገብረ መድኅንን፣ ብርሃኑ ዘሪሁንና በዓሉ ግርማን ፈለግ ተከትለው በቴአትር፣ በፊልም፣ በሙዚቃ፣ በድርሰቶች፣ ወዘተ. ብዙ ብዙ እንዲዘምሩለት ያስፈልጋል። ምክንያቱም ይህችው ኢትዮጵያችን የአፍሪካ ምሁራንና የፖለቲካ ልሂቃን ለተመለከቱት መሠረታዊ ጉዳዮችና ለሌላ ሌላውም የኢትዮጵያ ግዙፍ ንብረቶች የሚሰጡትን ከፍተኛ ሥፍራ በውል የማያስተውሉና የሚያንኳንስሱ አንዳንድ ጥራዝ ነጠቅ ኢትዮጵያውያንን ያበቀለችም አገር ናት። የዛሬውና መጪው ትውልድ የእንዲህ ዓይነቶቹ ኢትዮጵያውያን ትረካ ሰለባ እንዳይሆን በብዙ መሠራት ይኖርበታል።

ሦስተኛና ተደጋግሞ እንደተከሰተው፣ በመንግሥትና በታጠቁ ቡድኖች መካከል የድርድር  ሐሳብ ሲነሳና ድርድር ሲካሄድ በተለይም ታጣቂው ቡድን ወደ መከፋፈልና እርስ በርሱ ወደ መናቆር ያቀናል። ምክንያቶቹ የተለያዩ ቢሆኑም ክስተቱ ለምሳሌ ያህል በአየርላንዱ ሺንፌን፣ በስሪላንካው ታሚል ታይገርስ፣ በኮሎምቢያው ፋርክና በሌሎቹም ደርሷል፡፡ ስለዚህም ብንል ያስኬዳል፡፡ በሕወሓት ውስጥ መከፋፈል ተከስቶ መታየቱ ሊያስደንቅ አይገባም፡፡ ወዴት አምርቶ በምን እንደሚያበቃ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ይመሰክራል፡፡ ከሰሞኑ ከተሰማው ክስተት ለአሁኑ በእጅግ የሚያስገርመው ይልቁኑም የትግራይ ምሁራን የሚባሉ ያወጡት ከአንድ የተራ አክቲቪስት ትረካ የማይለየው መግለጫ ነው። ለታሪክ ፍርድ የሚተው መግለጫ ብለን ልናልፈው እንችላለን። ይሁንና ግን የተባሉት ምሁራን በመግለጫቸው ውስጥ ሕዝባችን ለሚሉት የትግራይ ሕዝብ የዓመታት ሰቆቃና የሰላም ጥማት፣ አንዲትም ቃል እንኳን ሳይጭሩ ያለፉ ምሁራን መሆናቸው ሲስተዋል አለመገረም አይቻልም።

ሌላው አስገራሚ መግለጫ፣ የአብኑ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር)  በአንድ የቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው የወልቃይት ጉዳይ በፕሪቶሪያ ባለመወሰኑ ምክንያት የሰጡት መግለጫ ነው። ደሳለኝ (ዶ/ር) ድርጅታቸውን አብንን በሕገ መንግሥቱ መሠረት ያስመዘገቡ ግለሰብ ናቸው፡፡ የምክር ቤቱን ወንበር በሕገ መንግሥቱ መሠረት ተወዳድረውና ተመርጠው የጨበጡ ግለሰብ ናቸው። ይህ ሲታወስ  ደሳለኝ (ዶ/ር) የፕሪቶሪያው ስምምነት በአንቀጽ 1 እና 2 የዘረዘራቸውን ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች አለማስተዋላቸው አነሰ ሲባል በእጅግ ያስተዛዝባል። ሲበዛም፣ በእጅጉ ያስገምታል።

ኦፌኮ የሚባለው የመረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) ድርጅት በበኩሉ ስምምነቱን አልደገፈም እንዳይባል፣ ደግፎና ተቃውሟል እንዲባልም የኦነግ ሸኔን ነገር ሸንቁሮ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ይሁንና በዚህ የኦፌኮ አመራር የተለመደ ብልጣ ብልጥና አድርባይ ‹‹መግለጫ›› ላይ መቆየት የሚያስፈልግ አይመስለኝም። ኦፌኮ ነገ ጠዋት ወደ ኤምባሲዎች ሮጦ የለመደውን የተማፅኖ ድበዳቤዎች ሲያስገባ ቢታይም የሚያስደንቅ አይሆንም።

በተረፈ ከቀድሞው የሕወሓት አመራር አሻሻጮች መካከል አሌክስ ደዋል የሚባለው እንግሊዛዊና መሰሎቹ፣ በአሻሻጭነት ተግባራቸው ተሰማርተው መቀጠላቸው የሚያስገርም አይደለም። አሌክስ ደዋልም እንደተጠበቀው በሚከረፋ ዘረኝነት በታጨቀው ድርሰቱ፣ ‹‹ስምምነቱ ከሕወሓት ጋር እንጂ፣ ከትግራይ መንግሥት ጋር አልተደረገም። ኤርትራ አልተወሳችም። ክትትሉንና ቁጥጥሩን የሚያደርጉት አፍሪካውያን ብቻ ናቸው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንኳን አልተካተተም። ሪፖርቶችንና ጥሰቶችን የሚዳኙትም ኦባሳንጆና ሙሳ ፋቂ ብቻ ናቸው። የአፍሪካ ኅብረት ለታዛቢነት የጋበዘው ደግሞ የተባበሩት መንግሥታትን፣ የምሥራቅ አፍሪካ ድርጅትንና የአሜሪካ ተወካዮችን ብቻ ነው። የአውሮፓ ኅብረት ከታዛቢነት ታግዶ አልተሳተፈም፤›› እያለ በስምምነቱ ላይ ወደ መዝመት ተሻግሮ ተነቧል (Alex de Waal, Ethiopia civil war: Tigray truce a triumph for PM Abiy Ahmed, November 3, 2022)። ለአፍሪካ ችግሮች የአፍሪካውያን መፍትሔ የሚለው መርሆ የተጠናከረውን ያህል ራሳቸውን የአፍሪካ ሊቅ አድርገው የሚወናኙት አሻሻጭና ዘረኛ ፈረንጆች ከጨዋታ ውጪ እየሆኑ ይሄዳሉ ብዬ አምናለሁ።

ይህ በዚህ ቢሆን ማይመር መናሰማይ (ፕሮፌሰር) በአንድ አጭር ጽሑፋቸው ያመለከቱትን ቁም ነገር ወደ አዕምሮ መጥራትና መተገበር ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ። ይህችን አጭር ማስታወሻ የእሳቸውን ጽሑፍ በረዥሙ በመጥቀስ አጠቃልላለሁ።

‹‹ከታሪክ አንፃር ያለፉት ዘመን ድሎቻችንን የታሪክ ሥፍራ አበጥረን አልገላለጥናቸውም፡፡ በመሆኑም ለፖለቲካ፣ ለማኅበራዊና ለኢኮኖሚያዊ ድሎችና ለምሁራዊ ለውጥ (Transformation) አልበቃንም፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ስለዚህም ድሎችን ወደ ማምለክና በሽለላና ቀረርቶ ወደ ማዳነቅ እናጋድላለን። ወይም ድል ማኅበራዊ ድል እስካልሆነ ድረስ፣ ዕድሜው እጅግ አጭር እንደሆነ እንዘነጋለን። የኢትዮጵያ ያለፉት ዘመን ድሎችም የተከታዩን ዘመን በሮች ለሽንፈቶች በርግደው የከፍቱ ሆኑ፡፡ ይህንኑ በሁለት ምሳሌዎች ለማሳየት ይቻላል።

‹‹አፄ ምንሊክ ከ1888 ዓ.ም. የዓድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያን ወደ ማዘመን አቀኑ፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያን ለመጪው ትንቅንቅ ሊያዘጋጅ ይችል የነበረውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ሪፎርም ሳይፈጽሙ ቀሩ። አፄ ኃይለ ሥላሴም በተሻለ ሳይሠሩ አለፉ። ስለዚህም ጣሊያን በ1928 ዓ.ም. ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ፣ ኢትዮጵያ ራሷን ለመከላከል ሳትበቃ ቀረች። የ1988 ዓ.ም. ድል የኢትዮጵያን የ1933 ዓ.ም. ሽንፈት ፀነሰ። ማይጨውን ወለደ…

‹‹…አሁን በ2015 ዓ.ም. ያለፉት የ1888 እና የ1933 ዓ.ም. ታሪካዊ ስህተቶች መደገም የለባቸውም፡፡ የ2015 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ድል፣ ኢትዮጵያን ወደ ፖለቲካ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ሪፎርሞችና ምሁራዊ ለውጥ አስፈንጣሪ መሣሪያ እንዲደረግ ያስፈልጋል፤›› (Maimire Mennasemay፤ Victory… And the Day After፣ November 2022)።

የማይምርን (ፕሮፌሰር)  ጽሑፍ የተረዳሁት፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ነፃነትና የግዛት አንድነት ታግሎ አኩሪ ድሎችን ተቀዳጅቷል። በሽለላና በቀረርቶ አድምቋል። ይሁንና ገዥዎቹ አንድም ጊዜ የሰላምን ትሩፋት ወይም ድርሻ (Peace Dividend) ለብሔራዊ ነፃነቱና ለግዛት አንድነቱ ለተዋደቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለግሰውት አያውቁም፤›› በሚል ነው። የዛሬዎቹ ገዥዎች፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ተዋናዮችና ልሂቃን ከፕሪቶሪያ ስምምነት ባሻገር አጅግ አተኩረው ሊመዝኑት የሚገባቸው መሠረታዊ ሀቅና ጉዳይ ነው።

ለማጠቃለል የፕሪቶሪያው ድርድር የፖለቲካ ድርድር ተሰጣጥቶ የመቀባበል ክንዋኔ የሚካሄደበት መድረክ ነው የሚባለውን በውል አሳይቷል። በጥሩ አስተምሯል። ስለሆነም መንግሥት ለታጣቂው ቡድን የሚገባውን ሰጥቶ እንደ መንግሥት ማስጠበቅና ማስከበር የሚገባውን መንግሥታዊ ሥልጣን አስረግጧል። ታጣቂው ቡድንም የመንግሥት የሆነውን ለመንግሥት ሰጥቶ፣ እንደ ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ማግኘት የሚገባውን ተቀብሏል፡፡ የዛሬዎቹ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተዋናዮችና ልሂቃን ከፕሪቶሪያው ስምምነት የፖለቲካ ጥበብ ተገቢውን ትምህርት ለመቅሰም የበቁ እንደሚሆኑ ተስፋ ይደረጋል።

በ2015 ዓ.ም. አገራዊ ምክክር የሚጀምርበት ዓመት ነው። በሌላ አባባል ብንገልጸው፣ የኢትዮጵያና የመላው ሕዝቧ መሠረታዊ የፖለቲካ፣ የአስተዳደራዊ፣ የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚያዊ ሪፎርሞችና የምሁራዊ መለወጥ የሚጀምርበት ዓመት ነው። በተለይም የአገሪቱ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ልሂቃንና ምሁራን ወደፊት ተመልካች ተሳትፎ ያደረጉትን ያህልና አገራዊ ምክክሩ የተሳካውን ያህል ኢትዮጵያን ለማስፈነጥር የሚያስችል የታሪክ አጋጣሚ ነው። ከዶጋሊ እስከ ዓድዋና ከዓድዋ እስከ ትናንቱ ፕሪቶሪያ ብሔራዊ ልዕልናዋንና የግዛት አንድነቷን ሲፈታተኑ የኖሩትን የቅርብና የሩቅ ጠላቶች የመመከት አቅሟን ለማጎልበት የሚያስችል የታሪክ አጋጣሚ ነው። ኢትዮጵያ የራሷን ዕድል በራሷ የምትወስን አገር ሆና የምትደምቅበትን የታሪክ ምዕራፍ የሚከፍት የታሪክ አጋጣሚ ነው። ሪፎርሞቹ የተከናወኑትንና ምሁራኖቿና ልሂቃኖቿ ራሳቸውን የለወጡትን ያህል፣ ኢትዮጵያና ሕዝቧ የሰላም ትሩፋቶቿ ተቋዳሽ የሚሆኑባት ዘመን ይቀዳል፡፡ ‹‹ለአፍሪካ ችግሮች የአፍሪካውያን መፍትሔ›› የሚለውን መርሆ ለኢትዮጵያ ችግሮች የኢትዮጵያውያን መፍትሔ በማለት ብናውለው፣ የወደፊቱ የጋራ ሰላምና የጋራ ብልፅግና የሚወስደው የጋራ የፖለቲካ ጎዳና አምሮ ይከፈታል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...