Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በጦርነቱና በተያያዥ ክስተቶች የግብይት ሥርዓቱ ምን ያህል እንደተጎዳ ከሸማች በላይ መስካሪ የለም !

በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል ሰላም ለማውረድ የተደረሰው ስምምነት በወረቅት ላይ እንደሰፈረው የሚተገበር ከሆነ አገር ብዙ ያተርፋል፡፡ ዜጎች የሰላም አየር ይተነፍሳሉ፡፡ በተለይ የጦርነቱ ወላፈን የለበለባቸው አካባቢዎች የዚህ ስምምነት የበለጠ ተጠቃሚዎች ይሆናሉ ብቻ ሳይሆን ዳግም ወደ ጦርነት እንዳይገባ የየበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ የሚችሉበትን ዕድል ፈጥሯል፡፡

መጨረሻውን ያሳምርልን እንጂ የሰላም ስምምነቱ መፈረሙ ከተሰማበት ማግሥት ጀምሮ ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የነገን ተስፋ እንዲሰንቁ አድርጓል፡፡ 

የሰላም ስምምነቱ ከተሰማ በኋላ የብዙዎች ከጦርነት ወጥተን ወደተሻለ ጎዳና ለመጓዝ ዕድል ይሰጠናል የሚል ስሜታቸውን እያንፀባረቁ ነው።

ይህ የሰላም ስምምነት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ላለፉት ሁለት ዓመታት የነበረውን ደም መፋሰስ ያስቀራል የሚል ተስፋን ቢያጭርም፣ በመሀል የአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች እየተሰማ ያለው ዜና ደግሞ የብዙዎችን ደስታና ተስፋ የሚያደበዝዝ ሆኗል። ታጣቂዎች ሰዎችን እየገደሉ ነው፡፡ ንብረት እየወደመ ነው፡፡ መንገድ በመዝጋት እንቅስቃሴዎችን እያስተጓጎሉ ነው፡፡ ሕገወጥ ተግባራትንም እያስፋፋ ነው፡፡ ዜጎች ታግተው ገንዘብ እየተጠየቀባቸው ነው፡፡ ከባንክ ያለ ገንዘብ እየተዘረፈም ነው፡፡ ከሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ጦርነት እልቂት እንጂ ማንም አሸናፊ ያልሆነበት ፣ በኋላም ልዩነቶችን ለመፍታት ሰላማዊ ብቸኛው አማራጭ ሆኖ ገሃድ እየታየ ይህንን ነባራዊ ሃቅ ማስተዋል ያልቻሉ ነፍጥ ያነሱ ሌሎች ኃይሎች ማኅበረሰቡን እረፍት እየነሱ ነው። መንግስትም ሆነ ማኅበረሰቡ በአጠቃላይ በመሐል አገር እየተሽሎከሎከ ሰላም እያሳጣ የሚገኘውን ‹‹የሸኔ እንቅስቃሴ›› ማስቆም ካልቻሉ በሙሉ ልብ ኢኮኖሚውን ለማከም ከባድ ይሆናል፡፡ በሰሜኑ የተገኘው ዕፎይታ ይህንንም ማርገብ ካልቻለ አሁንም ከችግር አዙሪት ላንወጣ እንችላለን፡፡ 

በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች የሚሰሙት የጥይት ድምፆች ማስቆም ከዚህ በኋላ በመንግሥት ትኩረት የሚገባው ጉዳይ እንዲሆን ይፈለጋል፡፡ አሁን በሰሜን የተገኘው መልካም ነገር ልንጠቀምበት የምንችለውም በመሀል አገር በተለያዩ አካባቢዎች በሸኔ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃትና ውድመት ማስቆም ሲቻል ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ሰላም ለማውረድ የተደረገው ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ኢኮኖሚዊውን ለማከም ሊሠሩ ከሚገባቸው ጉዳዮች አንዱ በአቅርቦትና በፍላጎት መካከል ያለውን ልዩነት በማጥበብ ገበያውን ማረጋጋት ሁነኛ ቦታ ሊሰጠው ይገባል፡፡

በጦርነቱም ሆነ ተያያዥ በሆኑ ክስተቶች የግብይት ሥርዓቱ ምን ያህል እንደተጎዳ ከሸማች በላይ መስካሪ የለም፡፡ የተዛባውን ኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የተበለሻሸውን ሥርዓት ለማስተካከል እንዲሁም የዋጋ ንረቱን ለማርገብ በአገር ውስጥ አቅም ብቻ የሚገፋ ባለመሆኑ ሌሎች አማራጮች መታሰብ አለባቸው፡፡ ከዚሁ ውስጥ አንዱ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች ሊያመርቱ የሚችሉ የውጭ ኩባንያዎችን መጋበዝ እንደ አንድ መፍትሔ ማሰብ ግድ የሚል ይሆናል፡፡ የውጭ ኩባንያዎችን ችግር በሚታይባቸው ቦታዎች ይግቡ ሲባል ሸቀጦቻቸው እዚህ ያራግፉ ሳይሆን ለዘለቄታው ጨቀሜታ ሲባል ማምረቻ ተክለው የሚፈለጉ ምርቶችን እንዲያመርቱ ማድረግ ነው፡፡ ቀና የውጭ ኩባንያዎችንም ማሰብ አሁን የተፈጠረው አጋጣሚ መልካም ዕድል ተደርጎ መወሰድ አለበት፡፡

ከተዳከመው ኢኮኖሚያችን ጎን ለጎን በገበያ ውስጥ ያለውን የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ለማቃለል የተሞከሩ ሙከራዎች በሙሉ ዘላቂ የሆነ መፍትሔ አላመጡም፡፡

ስለዚህ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የተሻለ መሆኑ ስለሚታሰብ ይህም በገበያ ውስጥ የምርት ፍላጎት ስለሚጨምር ይህን ከፍ እያለ የሚሄደውን ፍላጎት ለማርካት ወይም አቅርቦትን መጨመር ግድ ይላል፡፡ በመሆኑም ይህንን ፍላጎት አሁን በአር ደረጃ ባለን አቅም ብቻ ማርካት አይቻልም፡፡

ይህንን ሃቅም እስካሁን የመጣንበት መንገድ ያሳየናል፡፡ ገበያውም ቢሆን የሚነግረን ይህንን ነው፡፡ ነጋ ጠባ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶችም ሆኑ ሌሎች ምርቶች በየጊዜው ዋጋቸው እየጨመሩ መምጣታቸው የሚመሰክርልን ገበያው የሚፈልገውን ያህል ምርት ያለመኖር ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ደግሞ እንቅስቃሴዎች ከቀድሞ የተሻለ ከሆነ ሰዎች የመግባት ፍላጎት መጨመሩን በማሰብ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

ይህ እጥረት የበለጠ ትርጉም የሚኖረው ደግሞ አንገብጋቢ ሊባሉ የሚችሉ ምርቶችን እንዲያመርቱ የምሻቸው የውጭ ኩባንያዎች ከአገር ውስጥ ኩባንያዎች ጋር ተሳስረው እንዲሠሩ ከተደረገ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ የሰላም ስምምነት ያለ ችግር ማምረት የሚቻልበትን ዕድል የፈጠረ መሆኑን በማስረዳት ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት ዕርዳታ ሳይሆን ኢንቨስትመንት የምንሻ ስለመሆኑ ማሳወቅ አሁንም የአንባሳደሮቻችን ብርቱ ጥረት ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከዚህ የተሻለ ጊዜ ስላለ አጋጣሚውን መጠቀም የግድ ሊሆን ይገባል፡፡

ለዚህ ደግሞ በጦርነቱ ሰበብ ያለ አግባብ እንደተበዳይ ተቆጥረን ለኢትዮጵያ የተሰጠውን ስም መቀየር ቀዳሚ ሥራ ሆኖ ጉድለት ባለበት የአገራችን ገበያ ውስጥ የውጭ ኩባንያዎች ገብተው እንዲሠሩ ማድረግ ከፍተኛ ጥቅም ሊያስገኝ ይችላል፡፡ በዚህ ዘርፍ የአገራችን ኩባንያዎች ተሳታፊ ሆነው ውጤት ቢያመጡ የሚደገፍ ቢሆንም አሁን ካላቸው አቅም የአገሪቱን ችግር ለማቃለል አቅም የሌላቸው በመሆኑ ቢያንስ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ተጣምረው እንዲሠሩ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠር ካለንበት ችግር አንፃር ብቻ ሳይሆን ለዘለቄታውም ጠቀሜታ ይሆናል፡፡

በአራቱም አቅጣጫ ባሉ የዓለማችን ክፍሎች ያሉ ኤምባሲዎቻችን ከዚህ በኋላ ቁጥር አንድ ሥራቸው መሆን የሚገባው የተጎዳ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ሊያሻሽሉ የሚችሉ ኢንቨስትመንቶች ወደ አገር እንዲገቡ ማድረግ ነው፡፡ በተለይ በተለይ ዘወትር እጥረት የሚፈጠርባቸውን ምርቶች በአገር ውስጥ የሚያመርቱ ኩባንያዎችን በማፈላለግ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ማበረታታት የዲፕሎማቶቻችን ወቅታዊ አጀንዳ መሆን ይገባዋል፡፡

ኢትዮጵያ ትልቅ ገበያ ያላት በመሆኑ ወደ አገር የምናስገባቸው ኢንቨስተሮች መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች ላይ ከኢትዮጵያውያን ጋር በሽርክና በመሥራት የገበያ ጉድለታችንን ለመሙላት የሚያስችሉ አሠራሮች እንዲኖሩን በማድረጉ ረገድ መሥራቱ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ገበያን ሊያረጋጋ ይችላል፡፡

ገበያችንን ለማረጋጋት የውጭ ኩባንያዎቻችን የምንፈልገው አማራጭ በማጣት ጭምር ሊሆን ስለሚችል የውጭ ፋይናንስ ተቋማትን ለማስገባት እየተደረገ ካለው ጥረት ባልተናነሰ ሁኔታ ገበያን ሊያረጋጉ የሚችሉ ሥራ ሊሠሩ የሚችሉ የውጭ ኢንቨስትመንቶችን በጥንቃቄ በመምረጥ ቢሠራ ብዙ ለውጥ ሊመጣ ይችላል፡፡ ካልሆነ ግን እያደገ የመጣውን ገበያ ፍላጎት ማቀራረብ እስካልተቻለ ድረስ የዋጋ ንረቱ እየከበደ ይሄዳል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት