የኢትዮጵያን ጦርነት ለማስቆም የአፍሪካ ኅብረት ዋና አደራዳሪ የሆኑት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ አንድ ጥያቄ አነሱ፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ሰላም መፍጠር ከተቻለ በሌላው የአፍሪካ ክፍልም መፍጠር ይቻላል፤›› (If Peace Can be Achieved in Ethiopia, it Can be Done Elsewhere in Africa) በማለት ነበር ኦሊሴጉን ጥያቄ የሚያጭር ጉዳይ ያነሱት፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ የቆየውን ጦርነት በሰላም ስምምነት መቋጨት መቻሉ ለኢትዮጵያ ትልቅ የፖለቲካ ምዕራፍ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት በሰላም ስምምነት መቋጨት እንደተቻለው ሁሉ በኦሮሚያ ያለውን ግጭትና ዕልቂትስ በሰላማዊ መንገድ መቋጨት አይቻልም ወይ? የሚለው የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ የሆነ ይመስላል፡፡
በኦሮሚያ የሚታየውን ግጭትና ዕልቂት የመንግሥት አካላት ‹የፀጥታ ችግር› እያሉ አቃለው ቢያቀርቡትም ችግሩ ግን በጊዜ ሒደት ሥር እየሰደደና ከፍተኛ ቀውስ እየፈጠረ መሆኑን የሚታዩ ምልክቶች ይናገራሉ፡፡
ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ላይ ብቻ በሁለት አጋጣሚዎች በገርበ ጉራቻ አካባቢ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ካህናት እገታ መፈጸሙ ዋና የዜና ርዕስ ሆኖ ነበር፡፡ ከቢርቢርሳ ማሪያም ቤተ ክርስቲያን አምስት አገልጋዮች ታግተው ቆዩ፡፡ ይህ ችግር በተፈጠረ በሳምንቱ ደግሞ ጥቅምት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ኪዩ ወረዳ ከአንድ ቤተ ክርስቲያን 11 አገልጋዮች መታገታቸውና አንድ ሰው መገደሉ ተሰማ፡፡ ኦነግ ሸኔ በሚንቀሳቀስባቸው የሰሜን ሸዋ አካባቢዎች ሰላማዊ ኑሮን መኖር ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት ተቋማትም አደጋ ላይ መውደቃቸው እየተሰማ ይገኛል፡፡
ኦነግ ሸኔ በሚንቀሳቀስባቸው የምሥራቅ ሸዋ ዞን ወረዳዎች ቦሰትና ፈንታሌ ውስብስብ የፀጥታ ችግር መኖሩ ሲነገሩ ነው የከረመው፡፡ በአርሲ ዞን በተለይ ጀጁና መርቲ ወረዳዎች ኦነግ ሸኔ ተከታታይ ጥቃትና ግድያዎች እየፈጸመ መሆኑም ሲዘገብ ነው የሰነበተው፡፡ በሁለቱ ማለትም ምሥራቅ ሸዋና አርሲ ዞኖች በርካታ አካባቢዎች በኦነግ ሸኔ ጥቃት ሥጋት ውስጥ መውደቃቸው ነው የተነገረው፡፡
በአርሲ ዞን ጀጁና መርቲ ወረዳዎች በጥቂት ቀናት ልዩነት ከደርዘን በላይ ሰዎች ተገድለዋል፡፡ አዲስ ሕይወት በተባለው አካባቢ አምስት ሰዎች የመገደላቸው ዜና ገና ትኩስ ወሬ ሆኖ ሳለ በጥቂት ቀናት ልዩነት ግን አፍሪካ ጁስ ማምረቻ ጀጁ ወረዳ መንበረ ሕይወት አካባቢ ዘጠኝ ሰዎች መገደላቸው ተነገረ፡፡
የእነዚህ ሰዎችን አገዳደል በሚመለከት የተጠየቁ የአካባቢው ሰዎች ከሟቾቹ ብዙዎቹ ከፖለቲካ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ሠርቶ አዳሪ ዜጎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አንዳንዶቹ በጥይት ብቻም ሳይሆን በስለትና በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውም ተነግሯል፡፡
ከኦነግ ሸኔ ጋር የተያያዘው ትኩሳት ግን ከሰሞኑ የበለጠ እየተጋጋለ የመጣ ነው የሚመስለው፡፡ በወለጋ በኦነግ ሸኔ መዘዝ የፀጥታው ችግር ተባብሶ ወደ ድሮን ድብደባ መሸጋገሩ እየተነገረ ይገኛል፡፡ በምሥራቅ ወለጋ መፈናቀልና የዜጎች ደኅንነት አደጋ ላይ የመውደቅ ሁኔታ የቀጠለ ቢሆንም በምዕራብ ወለጋ ያለው ሁኔታ ግን ወደለየለት ጦርነት እያመራ መሆኑ ሲነገር ቆይቷል፡፡
የምሥራቅ ወለጋ ዞን ዋና ከተማ ነቀምቴን ‹‹የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ተቆጣጠሩ›› የሚለው ዜና ብዙ ትኩረት የሳበ ጉዳይ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ታጣቂዎቹ በጥቂት ቀናት ልዩነት ከተማዋን ለቀው መውጣታቸው ተነግሯል፡፡
መንግሥት በወለጋ በተለይም ምዕራብ ወለጋ ዞን የሸመቁ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችን በድሮን ድብደባ በመታገዝ መጠነ ሰፊ ዘመቻ እያካሄደ መሆኑ ተነግሯል፡፡ የኦነግ ሸኔ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢና የተለያዩ የመከላከያ ምንጮች እንዳረጋገጡት ከሆነ መንግሥት መጠነ ሰፊ ጦር ወደ አካባቢው በማንቀሳቀስ ላይ ይገኛል ብሏል፡፡ የወለጋ ሁኔታ በመጪዎቹ ቀናትም የግጭቱ መጠንና አድማስ ከእስካሁኑ እንደሚሰፋ እየተገመተ ይገኛል፡፡
መንግሥት በወለጋና በተለያዩ አካባቢዎች በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ላይ የሚወሰደው የጦር ዕርምጃ መጠናከር ደግሞ የቡድኑን የበቀል ጥቃት እንደሚጨምረው እየተገመተ ይገኛል፡፡ በዚህ የተነሳም የኦሮሚያ ክልል ወደ ውስብስብ ቀውስና ጦርነት እንዳይገባ እየተሠጋ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ለሰሜን ኢትዮጵየ ጦርነት ዕልባት በመስጠት ዕፎይታ አገኘች ስትባል ለሰነበተችው ኢትዮጵያ ሌላ ቀውስ ይዞ እንዳይመጣ እየተሠጋ ይገኛል፡፡ ለዚህም ይመስላል በርካታ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሔና ዕልባት ይፈለግለት ሲሉ ከወዲሁ እየወተወቱ ያሉት፡፡
የኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ (ኦነን) ሊቀመንበር አቶ ደረጀ በቀለ ችግሩን ወደ ሰላማዊ መድረክ ማምጣት እንደሚበጅ ይመክራሉ፡፡ ‹‹እነዚህ ታጥቀው የሚፋለሙ ኃይሎች ምን እንደሚፈልጉ መጠየቅና በሰላም ለመፍታት መሞከር አዋጪ ነው፡፡ በሌላም በኩል የመንግሥት መዋቅር ራሱን በትክክል ማጥራት አለበት፡፡ መንግሥት በራሱ ላይ መጨከን መቻል አለበት፡፡ ግማሽ አጎፍሮ ግማሽ ተላጭቶ አይሆንም፡፡ መንግሥት ራሱን ያጥራ፡፡ ሕዝባችን ሰላም እየተጠማና ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ሠርቶ ለመኖር ስቃይ እየሆነበት ሁልጊዜ መኖር አይቻልም፤›› በማለት ነው ችግሩ ስለሚፈታበት ሁኔታ የተናገሩት፡፡
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት የደኅንነት አማካሪ ኃይሉ ጎንፋ (ብርጋዴር ጄኔራል) ከሰሞኑ የተናገሩትም ይህንኑ የሚያጠናክር ነበር፡፡ ‹‹በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያለው አካል በጫካ ካለው ሸኔ በላይ ሥጋት ነው፤›› በማለት የተናገሩት አማካሪው የኦነግ ሸኔ እንቅስቃሴ የኦሮሞ ሕዝብ ያገኛቸውን ፖለቲካዊ ድሎች የሚቀለብስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ወደ ኤርትራ በረሃ በመግባት ከኦነግ ሠራዊት ጋር በመቀላቀል የኢሕአዴግ መንግሥትን ሲታገሉ ቆይተው በለውጡ ማግሥት ወደ አገር ቤት የገቡት ኃይሉ ጎንፋ (ብርጋዴር ጄኔራል) ስለ ኦነግ ብዙ አነጋጋሪ የሆኑ ነገሮችን በመናገር የሚታወቁ ሰው ናቸው፡፡ በአንድ ወቅት በተለይም ‹‹ኦነግ የኦሮሞ ትግል መንፈስ ነው፡፡ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ለማ መገርሳም ሆነ እኔ ኦነግ ነን›› ሲሉ መናገራቸው ብዙ ሲያነጋግር መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ከሰሞኑ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሰጡት በተባለው አስተያየትም ኦነግ ሸኔን በተመለከተ ‹‹የሚመለሰውን በሽማግሌና በአባ ገዳ መክሮ በመመለስ አልመለስ የሚለውን ደግሞ በሚገባው የኃይል አማራጭ ማናገር ተገቢ ነው፤›› ሲሉ መናገራቸው ተዘግቧል፡፡ ኃይሉ (ብርጋዴር ጄኔራል) ይህን ይበሉ እንጂ የኦነግ ሸኔ ኃይልን ትጥቅ ለማስፈታት በቂ የሰላም ጥረት ተደርጓል ወይ? እንዲሁም ከዚህ ቀደም በአባ ገዳዎች የተሞከረው ሽምግልና ለምን አልሠራም? የሚለው ጉዳይ ብዙ እያጠያየቀ ነው፡፡
‹‹ለሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት የኃይል አማራጭና ጦርነት መፍትሔ እንዳልሆነው ሁሉ በኦሮሚያ ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ችግር ለመፍታትም ጦርነት መፍትሔ አይሆንም፤›› ይላሉ የኦነግ ፓርቲ የፖለቲካ ኦፊሰሩ አቶ በቴ ኡርጌሳ፡፡ በኦሮሚያ ከኦነግ ሸኔ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ቀውስ እንዴት እንደተጀመረ ከመነሻው የሚያስታውሱት አቶ በቴ ‹‹በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ችግር ለመፍታት የተሄደበት የሰላም መንገድ በኦሮሚያስ ለምንድነው የማይተገበረው?›› ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡
መንግሥት በአባ ገዳዎችና በአገር ሽማግሌዎች ችግሩን ለመፍታት ብዙ ርቀት መሄዱን ይናገራል ተብለው የተጠየቁት አቶ በቴ በሰሜን ኢትዮጵያም ቢሆን ተመሳሳይ ትርክት ይነሳ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
‹‹አንዳንዶች እሺ ያለውን ኃይል ትጥቅ አስፈትተናል፡፡ በጫካ ያለው ግን አልመለስም በማለቱ የምታደርጉትን አድርጉ ብለው መናገራቸው የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው፤›› ይላሉ፡፡
‹‹የሰላም ፍላጎት በላከው የሽግማሌ ብዛት አይለካም›› የሚሉት አቶ በቴ አንዴ አድርገናልና ከእኛ ይቅር በሚል ግብዝ ምክንያት የሰላምን መንገድ መተው ፍፁም የተሳሳተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እሳቸውን ጨምሮ በርካታ የኦነግ ታጋዮች ከኤርትራ በረሃ በለውጡ ማግሥት ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን የሚያስታውሱት አቶ በቴ ከገቡ በኋላ ግን በስምምነቱ የተገባው ቃል እንዳልተፈጸመላቸው ይገልጻሉ፡፡ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት አባላት ትጥቅ ፈተው ወደ መደበኛ ሕይወት እንዲመለሱ ለማድረግ የተወሰኑት ጦላይና ወሊሶ ካምፖች መሰብሰባቸውን ያስታውሳሉ፡፡
በተለያዩ መንገዶች የታጣቂዎቹ ሕይወት አደጋ ላይ እንዲወድቅ መደረጉንና ‹‹የጃል መሮ ሁለተኛ ሰው የሆነ ዲን ራስ የተባለ የጦር አዛዥ ቢሾፍቱ ከተማ በሰዎች ጥቃት ተፈጽሞበት በኮሪያ ሆስፒታል ሲታከም ቆይቶ ሞተ፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ በቴ ይህ ሁኔታም የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነግ ሸኔ) አባላትን ትጥቅ አንግበው ወደ ጫካ ትግል እንዲገቡ የበለጠ የሚገፋ ምክንያት እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
‹‹መንግሥት ከኤርትራ ጠርቶ ያስገባቸውን የኦነግ ታጣቂዎች መልሶ ሳያቋቁም ሜዳ ላይ በትኗቸዋል፤›› ሲሉ የሚናገሩት አቶ በቴ ጫካ ከገቡ በኋላም ችግሩን በሰላም ለመፍታት በቂ ጥረት አለማድረጉን ያነሳሉ፡፡
‹‹እነ ጃዋር መሐመድ የተካተቱበት የአባ ገዳዎች ሽምግልና አልተሳካም፡፡ መንግሥት ሽማግሌዎቹንም ወስዶ ካምፕ ውስጥ ነው ያቆያቸው፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ በቴ ከችግሩ ባለቤቶች ጋር በቀጥታ ተገናኝተውና ተነጋግረው ዕርቁን ለመጨረስ አመቺ ሁኔታ እንዳልነበራቸው እንደሚያውቁ ተናግረዋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ተመሳሳይ አስተያየት የሰጡት የኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ (ኦነን) ሊቀመንበር ደረጀ በቀለም ቢሆኑ ‹‹የኦነግ ሸኔ ኃይሎች በሽምግልና ተሞክረው አልታረቅ ብለዋል ወይ?›› የሚለውን መመርመርና ማጥራት ያስፈልጋል ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሽምግልና ባይኬድም በጫካ ያሉት ኃይሎችም ሐሳባቸውን ወይም ፍላጎታቸውን ወደ ሰላም ጠረጴዛ አምጥተው መጠየቅ ይችላሉ፡፡ ዝም ብሎ ሰላማዊ ሰዎችን እየገደሉና እየዘረፉ መኖር አያዋጣም፡፡
በመንግሥት ወገንም እነዚህ ቡድኖች በሽምግና አልመለስ ያሉ ተራ ሽፍታዎች ናቸው ብሎ ማናናቁና ችግሩን ማቅለሉ ተገቢ አይደለም፡፡ ሁለቱም ወደ ትክክልኛ ዕርቅና የሰላማዊ ንግግር መምጣት አለባቸው፤›› ሲሉ አቶ ደረጀ ይናገራሉ፡፡
የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናትም ሆነ የፌዴራል መንግሥት አመራሮች ኦነግ ሸኔ ተብሎ የሚጠራውንና በኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ችግር የሆነውን አካል በተመለከተ ችግሩን ዝቅ አድርጎ ማየት ላይ ሲያተኩሩ ይታያል፡፡ ቡድኑን የሕወሓት ተላላኪ ብለው ሲጠሩትም ተደጋግሞ ይታያል፡፡ የፖለቲካም ሆነ የርዕዮተ ዓለም ግብ የሌለውና በቀላሉ የሚከስም ኃይል ሲሉም ይበይኑታል፡፡ ባለሥልጣናቱ ይህን ቢሉም የኦነግ ሸኔ ጉዳይ ግን በየቀኑ ችግሩ እየሰፋና ሰቆቃው እየበረታ ሲሄድ ነው የታየው፡፡
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ ከአንድ ዓመት በፊት በሰጡት አስተያየት ‹‹ሸኔም ሕወሓትም ከኦሮሞ ሕዝብ በተቃራኒ የቆሙ ጠላቶች ናቸው፡፡ ሸኔ ለምንድነው የኦሮሞን እናት የሚዘርፈው? ሸኔ ለምንድነው የኦሮሞን ወንድ የሚደፍረው? መሳቂያ እንዳንሆን ብለን ነው ብዙ ውርደትን የደበቅነው፤›› በማለት ነበር ኦነግ ሸኔ የሚሉት ኃይል የፈጠረውን ቀውስ የተናገሩት፡፡
የሚዲያ ባለሙያው ጃዋር ኡመር ኦነግ ሸኔ የተባለውን ኃይል በሚመለከት የሰጠው ማብራሪያ ቡድኑ በኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን በተለይ ክልሉን በሚመሩ ኃይሎች በምን መንገድ እንደሚታይ ጠቋሚ ተደርጎ ሊቀመጥ ይችላል፡፡
ጃዋር ኡመር እንደሚናገረው ኦነግ ሸኔ በኦሮሚያ ዋነኛ አሸባሪ ገዳይ ቡድን ነው፡፡ በአራትና አምስት ቦታ እየተቧደነ የሚንቀሳቀስ የኦሮሞን ሕዝብ የሚያጠፋ ኃይል ነው፡፡ የወለጋው የራሱ መሪ ዓለው፡፡ አባላቱም የዚያው አካባቢ ሰው ብቻ ነው፡፡ የሌላ የለም፡፡ ሸዋ ሲመጣም ራሱን የቻለ መሪ ያለው ሌላ የኦነግ ሸኔ ኃይል አለ፡፡ ሁለቱ ቢገናኙ እርስ በርስ የሚገዳደሉና በጠላትነት የሚተያዩ ኃይሎች ናቸው፡፡ ጉጂና ቦረናም አካባቢ ተመሳሳይ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ጉጂ ስም ወጥቶለት በአካባቢው ተወላጆች የተደራጀ ራሱን የቻለ ኃይል አለ፡፡ ቦረናም ልክ እንደዛው የተለየ ኦነግ ሸኔ አለ፡፡ አርሲና ባሌም ልክ እንደዚህ ለማቋቋም ሞክረው ነበር በማለትም ይናገራል፡፡
ይህ የፖለቲካ አሰላለፍ የዛሬ 30 ዓመት በሶማሊያ ተሞክሮ አገሪቱን በጎሳ ክፍፍል ያፈረሳት ሲሆን፣ እስከ ዛሬም አንድ አገር እንዳትፈጥር ያደረገ ምክንያት ነው ይላል፡፡ ወሎ ውስጥ የሚንቀሳቀሱትንና ከወያኔ ጋር ግንኙነት ለመፍጠር የሚሞክሩትን የሼኔ ኃይሎች የሸዋው ሸኔ ሲፈልግ አናቃቸውም ይላል፡፡ ይህ በአንድ አካባቢ ያለው ኦነግ ሸኔ ከሌላው ጋር የተከፋፈለ መሆኑን የሚጠቁም ብቻ ሳይሆን ወለጋ፣ ሸዋና ጅማ እያለ በየቦታው ተበጣጥሶ የሚገኝ ኃይል መሆኑን ያሳያል፡፡ ኦነግ ሸኔ የፖለቲካ ፕሮግራም የሌለው፣ የፖለቲካ ማዕከላዊነት የሌለው፣ የፖለቲካ መዋቅር የሌለውና የተመሰቃቀለ አሠላለፍ ያለው አደገኛ ድርጅት ነው ሲልም አቶ ጃዋር ያብራራል፡፡
ድርጅቱ ዓላማም ሆነ ድርጅታዊ ዲሲፕሊን የለውም፡፡ ሲፈልጉ ኦሮሚያን እንገነጥላለን ይላሉ፡፡ የኦሮሚያ መንግሥትንም እንመሠርታለን ይላሉ፡፡ የኦሮሚያ መንግሥትን ለመመሥረት ግን ከአማራ ጋር መጋጨት ለምን ያስፈልጋል፡፡ ማንም ወገን በመንግሥት ሥልጣን ላይ ካሉ አመራሮች ጋር ሊጋጭ ይችላል፡፡ ያለው መንግሥት አልተስማማኝም ብሎ መቃወምና የራሴን መንግሥት እመሠርታለሁ ማለትም ይችላል፡፡ ይህን ለማድረግ ግን ከሌላው ማኅበረሰብ ጋር መጣላት አያስፈልገውም፡፡ የኦሮሚያን መንግሥት ለመመሥረት ከአዲስ አበባ ሕዝብ ጋር መጋጨት ለምን ያስፈልጋል? ጋምቤላ ሄዶ ካለው መንግሥት ጋር መጋጨት እንዲሁም የጋምቤላ ተቃዋሚዎችን ደግፉኝ ማለት ለምን ያስፈልጋል? በማለትም የሚዲያ ባለሙያው ይጠይቃል፡፡
ኦነግ ሸኔ የተምታታና ዓላማ የለሽ ፖለቲካን ስለሚከተል ለረዥም ጊዜ ውጤት አልባ ድርጅት ሆኗል፡፡ የውጪ መንግሥታትም ሆነ በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ኃይሎች የድርጅቱን ዓላማ ቢስነት ስለተረዱም ነው በዚህ ጉዳይ የተለየ ነገር ከማድረግ የተቆጠቡት፡፡ አሁን ግን ጥቅማችንን ያስጠብቃል ያሉት ሕወሓት ስለተነካና ኢትዮጵያንም መጉዳት ስለሚፈልጉ ኦነግ ሸኔንም ለዚሁ ዓላማቸው ሊጠቀሙበት ይችላሉ ሲልም አቶ ጃዋር ኡመር ሐሳቡን ያጠቃልላል፡፡
በገዥው መደብ ያሉ የኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን ይህን ቢሉም በተቃውሞ ጎራ ያሉ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ግን ይህ ፍፁም የተሳሳተ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡ የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰሩ በቴ ኡርጌሳ ኦነግ ሸኔ (የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት) ‹‹የፖለቲካ ዓላማም ሆነ ግብ ከሌለው ያ የእርሱ ችግር ነው፡፡ ነገር ግን ቡድኑ ዓላማና ግብ ሳይኖረው ነው ወይ ይህን ሁሉ ወጣት ወደ ጫካ እያስገባ ያለው?›› ሲሉ ጥያቄ በማንሳት ነው አስተያየት የሚሰጡት፡፡
የኦነን ሊቀመንበሩ ደረጀ በቀለም ‹‹ማናናቅ የውሸት ዕንባ ነው›› በማለት ይናገራሉ፡፡ ‹‹ቡድኑን የምናናንቅና ተራ ሽፍታ ነው የምንል ከሆነ ቦረና፣ ወለጋም ሆነ ሌላ የኦሮሚያ አካባቢ ሄደን ለምን አናርስም? ሥራስ አንሠራም? ወይም በሰላም አንነግድም ታዲያ?›› በማለት ነው አቶ ደረጀ ችግሩ የገዘፈ መሆኑን የሚናገሩት፡፡
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በሚገኙት ኦነግ በተቆጣጠራቸው ግንደበረትና አቡና ግንደበረት አካባቢዎች ችግር የሚተነትን ዘገባ የሠራ አንድ ጋዜጠኛ የኦነግ ሸኔ ችግር ሁለት ዓይነት ገጽታ እንዳለው ይናገራል፡፡ ልክ እንደ ሽፍታ ሰው እየገደለና እየዘረፈ መኖር የሚፈልግ ኃይል አለ የሚለው ጋዜጠኛው በተቃራኒው በግልጽ የተተነተነ ፖለቲካ አንግቦ የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ቡድን መኖሩንም ያስቀምጣል፡፡
የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መሪ መሆኑን የሚናገረው ጃል መሮ የተባለው የጦር መሪም ቢሆን ‹‹ኦነግ ሸኔ የሚባል የፖለቲካ ኃይል የለም፤›› በማለት ደጋግሞ ተናግሯል፡፡ እሱ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መሆኑን የሚናገረው ጃል መሮ ሰዎች የሚገሉትንና ንፁኃንን የሚያሰቃዩትን ኃይሎች መንግሥት ራሱ ነው የሚያደራጃቸው ሲል ይከሳል፡፡
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ከፍተኛ አመራርና ታዋቂው ፖለቲከኛ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ ከሰሞኑ ስለኦሮሚያ ቀውስ በትዊተር ገጹ ሰፊ መልዕክቶችን አስተላልፏል፡፡ ደም መፋሰሱ በዋናነት እንዲቆም የጠየቀው አቶ ጃዋር ላለፉት አራት ዓመታት በተሄደበት የኃይል መንገድ ጉዳዩን ለመፍታት መሞከር እንደማይሠራ ተናግሯል፡፡
‹‹ባለፈው ሳምንት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በሰላም በመፈታቱ ሁላችንም ደስ ብሎናል፡፡ በኦሮሚያ የሚካሄደው ግጭት ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ ተባብሷል፤›› በማለት ሥጋቱን የገለጸው አቶ ጃዋር፣ ችግሩን በሰላም ለመፍታት ዕድል እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ኅዳር 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል በንፁኃን ዜጎች ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ መጠየቁ ይታወሳል፡፡ በምሥራቅ ወለጋ፣ በምሥራቅ አርሲ፣ በምዕራብ ሸዋ፣ ከአዲስ አበባ ሐዋሳ ፈጣን መንገድ ላይ፣ በምዕራብ ወለጋና በሌሎችም አካባቢዎች በንፁኃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ኢሰመጉ በመግለጫው አትቷል፡፡ የፌዴራል መንግሥትና የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ይህንን ችግር ትኩረት ሰጥተው በአስቸኳይ እንዲያስቆሙም በመግለጫው ጠይቋል፡፡
ለዚህም ሆነ ከኦነግ ሸኔ ጋር ለተያያዙ ሌሎች ጉዳዮች አንድም ጊዜ የተብራራ ምላሽ ሲሰጡ ያልታዩት የፌዴራልም ሆነ የኦሮሚያ አመራሮች ግን በኦሮሚያ ያለውን አሰቃቂ የፖለቲካ ቀውስ ምንጭ ኦነግ ሸኔ ነው ብለው ሲደመድሙ ነው የሚታየው፡፡ በዚህ ሁኔታ ታዲያ ችግሩ እንዴት ይፈታል? የሚለው ጉዳይ የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል፡፡