Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየጎዳና ሕፃናትን ይታደጋሉ የተባሉት አማራጮች

የጎዳና ሕፃናትን ይታደጋሉ የተባሉት አማራጮች

ቀን:

የቤተሰብ፣ የአካባቢና ከጦርነት ጋር የተያያዙ የእርስ በርስ ግጭቶች ሕፃናት ከወላጆቻቸው እንዲለዩና ከአካባቢያቸውም እንዲፈናቀሉ ያደርጋል፡፡ እነዚህም ሕፃናቱን ለጎዳና ሕይወትና ለከፋ የጤና ችግር ከሚያጋልጡ ምክንያቶች ግንባር ቀደሙን ይይዛሉ፡፡

ድህነት፣ አቅም ማጣት፣ ቁጥሩ ጎልቶ ባይታይም የአቻ ግፊቶች፣ ቤት ውስጥ ለሕፃናት በቂ የሆነ የደኅንነትና ጥበቃ መጓደል፣ ሕፃናትን ሆን ብሎ መጣል ሕፃናትን ለከፋ ችግር ከሚዳርጋቸው በርካታ ምክንያቶችም ይጠቀሳሉ፡፡

አቶ አንዱዓለም ታፈሰ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሕፃናት መብትና ደኅንነት ማስጠበቅ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ፣ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ሕፃናት ድጋፍና እንክብካቤ ማግኘት የሚያስችላቸው አምስት አማራጭ ፕሮግራሞች ተዘጋጅተው ለመተግበር እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡

ከአማራጮቹም መካከል የመጀመርያው ማኅበረሰብ አቀፍ ድጋፍና እንክብካቤ  ሲሆን፣ ፕሮግራሙ ሕፃናት በወላጆቻቸው፣ በማኅበረሰቦቻቸውና በቅርብ ዘመዶቻቸው ሊረዱ የሚችሉበት ሥርዓት ነው፡፡

ለዚህም ዕውን መሆን ቢሮው የተለያዩ ሐሳቦችን በማፈላለግ፣ በጎ ፈቃደኞችንና ባለሀብቶችን በማስተባበር ሕፃናት እዚያው ባሉበት ከወላጆቻቸው ጋር እየኖሩ የሚረዱበትን ሁኔታ የማመቻቸት ተግባር በመከናወን ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሁለተኛው አማራጭ ፕሮግራም በልዩ ልዩ ምክንያት ከወላጆቻቸው የተለዩ ሕፃናትን ከተፈጥሮ ወላጆቻቸው ጋር ማገናኘት መሆኑን ገልጸው፣ በዚህ ዓመት ብቻ ከ5000 ያላነሱ የጠፋ ሕፃናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ከተፈጥሮ ወላጆቻቸው ወይም ከቤተሰቦቻቸው መቀላቀል ያልፈቀዱት ደግሞ የተሃድሶ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ሥራ መከናወኑን ከዳይሬክተሩ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ሦስተኛው አማራጭ ፕሮግራም የአደራ ቤተሰብ የሚባል ሲሆን፣ ተጥለው የተገኙን ሕፃናትን ወደ ማሳደጊያ ማዕከል ከመውሰድ ይልቅ እነሱን ለመቀበል ዝግጁ ለሆኑ የአደራ ቤተሰቦች የሚሰጥበት ነው ብለዋል፡፡

በአደራ የመቀበሉ ሁኔታ ለአጭር፣ ለመካከለኛና ለረዥም ጊዜ ሊሆን እንደሚችል፣ የአጭር ጊዜው ከአንድ ሳምንት እስከ አንድ ወር፣ መካከለኛው ጊዜ ከአንድ ወር እስከ ስድስት ወራት፣ የረዥም ጊዜው ደግሞ ከስድስት ወራት በላይ ማለትም ሕፃናት ለወግ ማዕረግ እስከሚበቁና ተምረው እስከሚጨርሱ ድረስ ሊዘልቅ እንደሚችል ተገልጿል፡፡

በቆይታው ወቅት ከአደራ ቤተሰቦች ተገቢውን የወላጅ ፍቅርና እንክብካቤ የሚያገኙ ቢሆንም፣ ንብረት መወረሰ ላይ መብታቸው ላይጠበቅ ይችላል፡፡

የአደራው ዓይነት ይለያያል፡፡ አንደኛው ዓይነት አቅም ኖሯቸው ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ ምንም ዓይነት ድጋፍ ሳይፈልጉ የተረከቧቸውን ሕፃናት በእንክብካቤ የሚያግዙ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ አቅማቸው አነስተኛና መካከለኛ ሆኖ የተወሰነ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ የሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የአቅም ውስንነት  ላለባቸው አደራ ተቀባዮች በየወሩ የምግብ አስቤዛና 2,000 ብር ወርሃዊ ክፍያ እንደሚያደርግ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

አራተኛው አማራጭ የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ ፕሮግራምን ማራመድ ሲሆን፣ በዚህም ወደ 1150 ሕፃናት የፕሮግራም ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ የውጭ አገር ጉዲፈቻ ከ2007 ዓ.ም. ወዲህ መቅረቱንና በአንፃሩም የአየር ውስጥ ጉዲፈቻ እየተስፋፉና በዚህም የኅብረተሰቡ ግንዛቤ እያደገ መምጣቱን አክለዋል፡፡

ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ 139 ወንዶችና 113 ሴቶች በድምሩ 252 ሕፃናት የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ ተጠቃሚ መሆናቸውን ፕሮግራሙም ሕፃናቱ ጎዳና ላይ እንዳይወጡና ለከፋ ችግር እንዳይጋለጡ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡

አራቱ አማራጮች ከታጡ እንደ መጨረሻ አማራጭ ተደርጎ የተወሰደው አምስተኛው ፕሮግራም የተቋም ማለትም አገልግሎትን ማሳደጊያ በማስግባት የሚሰጥ ነው፡፡ ማዕከላቱን መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ያቋቋማቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

በማሳደጊያ ማዕከላት ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ከ2000 በላይ ሕፃናት ገብተው ድጋፍና እንክብካቤ እየተደረገላቸው ቢሆንም፣ ማሳደጊያ ማዕከላት የመጨረሻ አማራጭ እንደሆነ ነው ያመለከቱት፡፡

‹‹የወደፊት አገር ተረካቢና ተስፋዎች የሆኑ ሕፃናትን ደኅንነት፣ ምቹ ኑሮና ፍቅር የማግኘት ሁኔታን ማስጠበቅ ኃላፊነት ያለበት ኅብረተሰቡ ነው›› ያሉት ደግሞ በቢሮው የሕፃናት መብትና ደኅንነት ማስጠበቅ ቡድን መሪ አቶ አናንያ ያዕቆብ ናቸው፡፡

እንደ ቡድን መሪው፣ ይህ ሁኔታ መሬት ላይ ያልወረደና ወሬ ብቻ ሆኖ የቀረ በመሆኑ ሕፃናቱን ለመጥፎ ነገሮች የሚዳርጉ ማንኛቸውም ዓይነት ክፉ ነገሮች እየተስፋፉና እየበዙ መጥተዋል፡፡ እነዚህ ክፉ ነገሮች ሥር ከመስደዳቸው በፊት ማኅበረሰቡ ራሱን ሊፈትሽና መጥፎ ነገሮችን ሊያስወግድ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

ከወላጆቻቸው ጋርም ሆነ ከወላጆቻቸው ተለይተው በተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ ሕፃናትን ለመታደግ በሚካሄደው ጥረት ላይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ተሳትፎ፣ ዕገዛና ድጋፍ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ዕድሜው ከ18 ዓመት በታች ወይም ያልሞላው ሁሉ ሕፃን ተብሎ ይፈረጃል፡፡ ስለሆነም በተጠቀሰው ዕድሜ የሚገኙ ሕፃናት አካላዊ፣ አዕምሮአዊና ሥነ ልቦናዊ ዝግጅታቸው ገና ነው፡፡ በመሆኑም ተንከባካቢው ይህን ታሳቢ ያደረገ ድጋፍ ማድረግ አለበት፡፡

እንደ ቡድን መሪው፣ ሕፃናት ሊመሰገኑ፣ ሊበረታቱና ሊሸለሙ ይገባል፡፡ በተለይ ዕድሜያቸው 12 እና 13 ዓመት ሲሆናቸው በወላጆቻቸው ወይም በቤተሰቦቻቸው የምክር ድጋፍና አድናቆት ሊቸራቸው ይገባል፡፡

በቤተሰብ መካከል በሚካሄድ ውይይት ላይ ሕፃናት እንዲሳተፉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም በአዕምሮና በሥነ ልቦና ገና ያልዳበሩ ስለሆነ የሚያወጧቸው ሐሳቦች ራሳቸውን መልሶ የሚጎዳና ለቤተሰቡም የማይጠቅም ሊሆን ይቻላል፡፡ በዚህ ጊዜ ቤተሰብ ጣልቃ እየገባ መምከር፣ መደገፍና የሰነዘሩት ሐሳብ ጉዳት ያለው መሆኑን በመግለጽ ትክክለኛውን ሐሳብ እንዲያንፀባርቁ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመገረም እየተመለከቱ አገኟቸው]

ምንድነው እንዲህ ቀልብሽን የሳበው? ስለሰላም ኖቤል ሽልማት ዜና እየተመለከትኩ ነበር። እና...

የወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መመሥረትና የአማራ ክልል ጥያቄ

አማራ የኢሕአዴግ አንዱ መሥራችና አጋር ከሆነው ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ...

የሽንኩርት ዋጋ ሰማይ የነካበት ምክንያት ምንድነው?

ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት የሸማቾችን ኪስ ካስደነገጡ መሠረታዊ ከሚባሉ...

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ኤግዚቢሽን ማዕከልን እንዲያስተዳድር የተሰጠው ኮንትራት ለምን ተቋረጠ?

በአዲስ አበባ ከተማ ለንግድ ትርዒት ዝግጅት ብቸኛ በመሆን የሚጠቀሰው...