በጥቅምት ወር ላይ የታየው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበትን በመስከረም ወር ከነበረበት አኃዝ ከፍ እንዲል እንዳደረገው የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
በተጠናቀቀው ወር ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክስ ክፍሎችን ጨምሮ አጠቃላይ ዋጋ ግሽበት መጠነኛ ጭማሪ እንደታየበት ያስታወቀው አገልግሎቱ፣ የምግብ ኢንዴክስ ክፍሎች ላይ ግን የ0.3 ከመቶ ቅናሽ መመዝገቡን ይፋ አድርጓል፡፡
በመስከረም የተመዘገበው የ30.7 በመቶ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት በጥቅምት ወደ 31.7 ከፍ እንዲል ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ በነዳጅ ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ዋነኛው መሆኑ ታውቋል፡፡
ሪፖርተር ሰሞነኛውን የምግብና ምግብ ነክ ሸቀጦች የዋጋ ሁኔታ አስመልክቶ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንዳስታወቁት፣ የእህል ሰብሎች በሚባሉት ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ በቆሎና ማሽላ ዋጋ ላይ ከቀደመው ወር የተለየ ለውጥ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን በአትክልት ምርት ውጤቶች ላይ በተለያዩ የገበያ ቦታዎች መጠነኛ ቅናሽ መታየቱን ሸማቾች ተናግረዋል፡፡
የፋብሪካ ውጤቶች በሆኑት ስኳር፣ የፉርኖ ዱቄት፣ የምግብ ዘይት፣ የንፅህና መጠበቂያ ግብዓቶች ላይ የሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ በየዕለቱ እያሻቀበ እንደሚገኝ የሚናገሩት ሸማቾች፣ ለአብነትም አንድ ኪሎ ስኳር በ120 ብር፣ ዘይት ከ1,000 እስከ 1,200 ብር፣ አምስት ኪሎ ፉርኖ ዱቄት 280 ብር እንዲሁም ሳሙና በፍሬ ከ45 ብር በላይ በሆነ ዋጋ እንደሚሸጥ አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ትላንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ምላሽ ከሰጡባቸው ጉዳዮች ውስጥ፣ መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ምን እየሰራ ይገኛል? የሚለው ይገኝበታል፡፡ ጥያቄቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት የምክር ቤት አባላት በፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን ምክንያት ለተከሰተው የዋጋ ግሽበት በተለይም ደግሞ ምግብ ነክ ባልሆኑ ግብዓቶች የዋጋ መናር ላይ መንግስት ምን እየሰራ እንደሚገኝ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የዋጋ ንረት የዓለም ሁሉ ፈተና መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በማክሮ ኢኮኖሚው ካልተሳኩ ጉዳዮች ውስጥም የዋጋ ግሽበት እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
መንግሥት የበዓልና የሰንበት ገበያዎችን በማቋቋም፣ የማዕድ ማጋራት እንዲሁም የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ ችግሩን ለመቅረፍ ያደረገውን ጥረት ያስረዱት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ይህም ሆኖ በግሽበት ላይ የተገኘው ውጤት የሚቀረው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ብቸኛው አማራጭ ምርትን ማሳደግ ነው ያሉት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ በዚህ ወቅት እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር ብክነትን መቀነስን፣ ማዕደ ማጋራትን፣ ባሉ ክፍት ቦታዎች ሁሉ ምርት በበቂ መጠን ማምረትን፣ ከሌብነትና ከስንፍና መታቀብ እንዲሁም ከግጭት ሰላምን፣ ከስንፍና ትጋትን፣ ከሌብነት ሃቀኝነትን መምረጥ ቁልፍ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡