Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹መሬት የደላሎችና የሌባ ሹመኞች ሆኗል›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

‹‹መሬት የደላሎችና የሌባ ሹመኞች ሆኗል›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

ቀን:

በሕገ መንግሥቱ መሠረት መሬት የሕዝብና የመንግሥት እንደሆነ ቢገለጽም፣ አሁን ላይ ‹‹የመንግሥትም የሕዝብም ሳይሆን የደላሎችና የሌባ ሹመኞች›› መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡  

በመሆኑም መሬትን መንግሥትም ሆነ ሕዝብም እያዘዙበት ባለመሆኑ፣ ሥር ነቀል ማስተካከያ እንደሚያስፈልገው አስታውቀዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮችና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማክሰኞ ኅዳር 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ከፓርላማ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ፣ ‹‹ሕገ መንግሥቱ የሚለው መሬት የሕዝብና የመንግሥት እንጂ የደላሎች አይደለም፣ ነገር ግን ደላሎች ወስደውታል፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም ይህንን ማስተካከል የሚቻለው ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ምክክር የተባለውን ሒደት በትክክል መነጋገር ሲቻል መሆኑ አስረድተዋል፡፡

‹‹በከተሞች መሬት የግለሰብ መሆን ቢኖርበትም እየታየ ያለው ግን መሬቱን ወይ ባለቤቱ አይሸጠው፣ ወይ መንግሥት አይሽጠው፣ ወይም ራሱ ባለቤቱ ሳይጠቀምበት መከራ ሆኗል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በአጭሩ እንድትገነዘቡት በአዲስ አበባ የጀመርናቸውን የልማት ሥራዎች እንደ መንግሥት መሥራት አልቻልንም፡፡ በመሆኑም የመንግሥት መሬት፣ የጋራ መሬት፣ የመንግሥትና የሕዝብ መሬት እንዲሁም የግለሰቦች መሬት በመኖሩ ይህን ለይቶና አርሶ አደሩን እንዳይጎ ተደርጎ ካልተቀረፀ በስተቀር፣ አርሶ አደር የማያዝበትና አንድ ከንቲባ እየተነሳ በሚያዝበት አካሄድ ገበሬውን ያንተ ቦታ ነው እየተባለ ጊዜ መባከን የለበትም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል በኢንቨስተሮች አካባቢ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው ብዙ እውነታዎች እንዳሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸው፣ ኢንቨስተሮች እንዳይቸገሩ አዲስ አበባ ቦሌ ለሚ ኢንዳስትሪያል ፓርክ ውስጥ የፈለገ ባለሀብት የፈለገውን ሼድ እንዲሠራ በማሰብ መንገድ ተሠርቶ መብራት ገብቶለት ከተማ ቢመስልም ነገር ግን አንድም ኢንቨስተር እንደማይፈልገው ተናግረዋል፡፡ ባለሀብቱ የሚፈልገው የአንድ ሰው ቦታ ወስዶ ያንን ቦታ አስይዞ ገንዘብ ተበድሮ የሕንፃ መሠረት አውጥቶ መገንባት ካልቻለ መሸጥ ወይም ባንክ አስቸገረኝ፣ መንግሥት አስቸገረኝና ከንቲባ አስቸገረኝ ብሎ ብሩን ወስዶ እንደሚያቆም ገልጸዋል፡፡ ይህ አሠራር የውጭ ባለሀብቶችን ጨምሮ የብዙዎች ምክንያት መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፌዴራል መንግሥቱ ከሕወሓት ታጣቂዎች ጋር እያካሄደ ያለውን ድርድር በተመለከተ፣ ሰላምና ብልፅግናን ለማስቀጠል ሲባል ጦርነት ማቆም በእጅጉ ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡

ውጊያ ከአንድ ግንባር ብቻ ለአንድ ሳምንት ወይም ለአንድ ወር የሚካሄድ ባለመሆኑ፣ ጦርነቱ እየቀጠለ ከሄደ እንደ አገር መድቀቅን ስለሚያመጣ ለሰላምና ለብልፅግና ሲባል መንግሥት ጦርነትን ማቆም ቀዳሚ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን በግል የሚሰማን ስሜት ብዙዎቻችሁ እንደምትሉት ነው፤›› ብለዋል፡፡

በመሆኑም ለኢትዮጵያ ሰላም፣ አንድነትና ዕድገት የሚደረግ ድርድር እንኳን አፍሪካ ውስጥ ሌላም ቦታ ካለ ‹‹እንሄዳለን›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹ብዙ ጊዜ ከድርድር በኋላ በመተማመን ዕጦትና ቃል የተገባን ባለመፈጸም ምክንያት ድርድሮች ይበላሻሉ፡፡ ለአብነት እንኳን በዓለም ላይ 154 ድርድሮች የከሸፉት ከተስማሙ በኋላ የተስማሙ ወገኖች ቃላቸውን መጠበቅ ባለመቻላቸው ነው፤›› በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኛ የሚጠበቅብን የገነባነውን ቃል በተዓማኒነት መፈጸምና ያ ችግር እንዳያጋጥም አበክረን መሥራት ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የፌዴራል መንግሥት ከአሸባሪ ድርጅት ጋር ተደራደረ ይባላል፡፡ ነገር ግን ምክር ቤቱ ያወጣውና ሕወሓትን በአሸባሪነት የፈረጀው አዋጅ አሸባሪ አታሠልጥን፣ አታስታጥቅና አትደግፍ እንጂ ከአሸባሪ ጋር አትደራደር አይልም፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡ ‹‹ይሁን እንጂ አልደገፍንም፣ አላሠለጠንም፤›› ብለዋል፡፡

ወልቃይትን በተመለከተ የሚነሱ ሐሳቦች በተለይም መንግሥት ደቡብ አፍሪካ ሄዶ ወልቃይትን ወደ አማራ ይሁን ወይም ወደ ትግራይ ይሁን? የሚለውን ለመወሰን ሥልጣን የለውም ብለዋል፡፡ አክለውም፣ ‹‹ምን አገባውና የኢትዮጵያን መሬት እዚያ ይሂድ እዚህ ይሂድ የሚለው? እኛ እዚያ የሄድነው እነዚህን ችግሮቻችንን እንዴት እንፍታ ለማለት ነው እንጂ የወልቃይት ጉዳይ እዚህ ውስጥ ለምን ተስቦ እንደሚገባ አላውቅም ብለዋል፡፡ በመሆኑም የተደረሰው ስምምነት በኢትዮጵያ ሕግና ሥርዓት ይፈጸም በሚል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የወልቃይት መሬት ሕገ መንግሥት ከመፅደቁ በፊት የተወሰደ ነው ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄ፣ ‹‹እኔ የምፈልገው ያ ስህተት እንዳይደገም ነው፣ በመሆኑም ዛሬ እኔ በጉልበት ነገ ሌላው ደግሞ በጉልበት ከሆነ ዘላቂ ሰላም አያመጣም፤›› ብለዋል፡፡  

ወልቃይት የተወላገደ አማርኛና የተወላገደ ትግርኛ የሚናገር የሁለቱ ሕዝቦች ድልድይ መሆኑን፣ ሕዝቡ ወልቃይትነቴን አትንኩብኝ ነው እንጂ ከትግራይ ሕዝብ ጋር አልገናኝም ወይም አልነጋገርም አለማለቱን አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ያን ቢልም አይችልም ብለው፣ በመሆኑም ይህ በሕግና ሥርዓት ቢፈጸም ለትግራይም ሆነ ለአማራ ይጠቅማል እንጂ የሚጎዳ ነገር እንደማይኖር በመግለጽ፣ መንግሥት ያለው አቋም በምክክርና በሕግ አግባብ ይፈታ የሚል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹በመሆኑም በወልቃይት ከዓድዋም የሄደ፣ ከደብረ ማርቆስም የሄደ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን ወልቃይትነቴ ይታወቃል፡፡ ይህ ሕዝብ ስለዚህ ቦታ ሐሳብ እንዲሰጥ ዕድል ካልተሰጠው በስተቀር ዘላቂ ሰላም አያመጣም፡፡ ጉዳዩ ወደዚያ ስለሄደ ወይም ወደዚህ ስለመጣ ሳይሆን፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ እንዲወስን ዴሞክራሲያዊ ዕድል እንዲያገኝ ከተደረገ ብቻ መፍትሔ ይመጣል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

‹‹ያ ካልሆነ ግን ከሕገ መንግሥት በፊት ሕወሓት በግድ ስለወሰደው አሁን እኛ ደግሞ በግድ ወስደን እዚህ ቦታ ወታደር ልናቆም አንችልም፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲፈታ የሚነገሩት ተንኮሎች ቢቀሩ መልካም እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ስላላው ብልሹ አሠራር ፓርላማው ጠንከር ያለ ክትትል ማድረግ እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡

በፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ዳኛ፣ ዓቃቤ ሕግና ፖሊስ ሆኖ በገንዘብ ፣ ቃለ መሃላ ፈጽሜያለሁ ቃሌን ጠብቄያለሁ እምነት አለኝ የሚሉ ቢኖሩም፣  እነዚህ ሰዎች ግን በተቋሞቻቸውና በቤተሰቦቻቸው እንደ ሞኝ እንደሚቆጠሩና በእውነት ላይ ተመርኩዞ የሚሠራ አካል ሞኝ፣ ያልገባውና ያልሠለጠነ ተደርጎ በጓደኛው እንደሚሰደብ አስረድተዋል፡፡

በ2014 ዓ.ም. በፓርላማው ቀርበው ስለዳኞች ብልሹ አሠራር ያደረጉት ንግግር አንዳንዶችን እንዳላመማቸው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ሌብነት አለ ሲባል ዝም ብሎ ሳይሆን በቴሌግራም ግሩፕ ከፍተው ጉቦ የሚቀባበሉ ዳኞች›› በመኖራቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ የፍትሕ ሥርዓቱ በጀት ከአስፈጻሚው ወጥቶ ለፓርላማ የገባው አሁን መሆኑን በመግለጽ፣ ተቋማቱ በብዙ ተደግፈዋል መሻሻል ካለባቸው አሁን ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን አሁን ነገሩ ከተናጋ መቼም የማይቃና በመሆኑ እውነተኛ የሆኑ አገርን የሚወዱና ቃላቸውን የሚያከብሩ ሰዎች ተባባሪ ሆነው ጠንካራ ሪፎርም መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ሌብነት በጣም አታካች ጉዳይ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹የገጠመንን አገራዊ ፈተናና ችግር እንደ ዕድል የወሰዱ ሰዎች ቀይ መስመር ያልነውን ሌብነት ቀይ ምንጣፍ አድርገውት በነፃነት የሚንሸራሸሩበት ሰዎች በዝተዋል፤›› ብለዋል፡፡ በአዲስ አበባም ሆን በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ፋይል በእግሩ አይሄድም የሚባል ንግግር እየተለመደ የመጣ ስለመሆኑ በመግለጽ፣ ሌብነት ልምምዱ ብቻ ሳይሆን እንደ መብት መወሰዱ አደገኛ  እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

‹‹ሌብነት የኢኮኖሚ ነቀዝና የዕድገት ነቀርሳ ነው፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሌብነት ባለበት ማደግም መኖርም አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም ሌቦች መስረቃቸው ብቻ ሳይሆን፣ ከሰረቁ በኋላ ገንዘቡ ባንክ ስለማይሄድ ከሰረቁ በኋላ ወደ ሕገወጥ የንግድ ሥርዓት ውስጥ እንደሚገቡ አስረድተዋል፡፡ ለዚህም ማሳያው በአዲስ አበባ በርካታ ሕንፃዎች ባለቤት አልባ ሆነው መገኘታቸውን በመጠቆም፣ ‹‹ሌብነትን እንደ ብልፅግና ሳይሆን እንደ ማኅበረሰብ እየተለማመድነው በመሆኑ በየሁሉም ተቋማት ውስጥ መፍትሔ ካልተበጀ ጉዳቱ ያመዝናል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ድሮ ሳይሠሩ የሚበሉ ይባል ነበር፣ አሁን የመጡት ደግሞ የሚሠራውን መርጠው የሚበሉ ወይም እየሠራ የሚንቀሳቀስን ሠራተኛና ሥራውን የሚበሉ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለኑሮ ውድነት በሰጡት ማብራሪያ የሸቀጦች የዋጋ መናርና የፍትሕ ሥርዓት መበላሸት ለኢትዮጵያ ትልቅ ስብራት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣምና በጦርነት ምክንያት ምርቶች ወደ ገበያ መግባት እንዳይችሉ በመስተጓጎላቸው፣ የሸቀጦች ዋጋ መጨመሩን አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በርከት ያሉ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ፈተናዎች ገጥመውት እንደነበር የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአገር ውስጥ ጦርነት፣ ድርቅና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ እንዲሁም በውጭ የዩክሬንና የሩሲያ ጦርነት ተዳምሮ ኢኮኖሚውን ደቁሰውት እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የማይሰበር መሆኑን ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚስቶች ብቻ ሳይሆን ይህንን ጉዳይ የሚገመግሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ ላሉ ሰዎችም ጭምር ግራ እስኪያጋባቸው ድረስ ኢኮኖሚው ያጋጠመውን ፈተና ተቋቁሞ መሻገር መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ2014 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ 6.16 ትሪሊዮን ብር ወይም 126.7 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የነፍስ ወከፍ ገቢ 1,212 ዶላር መድረሱንና ከምሥራቅ አፍሪካ አንደኛ፣ እንዲሁም ከሰሃራ በታች ከሚገኙ አገሮች ሦስተኛ ግዙፍ ኢኮኖሚ መሆኑን የዓለም ባንክ መረጃን ጠቅሰው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...