Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትበድሬዳዋ ዝናብ ከቀጠለ ውድድሩን ለማስቀጠል የሚያስችል አማራጭ ስታዲየም እንደሌለ ተገለጸ

በድሬዳዋ ዝናብ ከቀጠለ ውድድሩን ለማስቀጠል የሚያስችል አማራጭ ስታዲየም እንደሌለ ተገለጸ

ቀን:

ከስድስተኛ ሳምንት ጀምሮ በድሬዳዋ ከተማ ሲከናወን የነበረው የቤቲኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በአየር ንብረት ምክንያት ከተቋረጠበት መርሐ ግብር እንደሚቀጥል ቢገለጽም፣ የሚጥለው ዝናብ ከቀጠለ አማራጭ ስታዲየም እንደሌለው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር አስታወቀ፡፡

ከመስከረም 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በባህር ዳር ሲከናወን የቆየው የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ከስድስተኛ ሳምንት ጀምሮ በድሬዳዋ ቢቀጥልም፣ በከተማዋ በጣለው ከፍተኛ ዝናብ መቋረጡና መገለጹ ይታወሳል፡፡ ፕሪሚየር ሊጉ የሰባተኛ ሳምንት አራት ጨዋታዎች ብቻ የተደረጉ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ አራት ጨዋታዎች በከተማዋ በጣለው ከፍተኛ ዝናብ የመጫወቻ ሜዳ ለማጫወት ምቹ ባለመሆኑ ማካሄድ አልተቻለም፡፡

በዚህም ምክንያት የሊጉ መርሐ ግብር  ላልተወሰነ ጊዜ  ማራዘሙን አክሲዮን ማኅበሩ አስታውቆ ነበር፡፡

- Advertisement -

ሆኖም አክሲዮን ማኅበር የስምንተኛ ሳምንት ጨዋታዎችን ረቡዕ ኅዳር 7 ቀን 2015 ዓ.ም. እንደሚከናወኑ ይፋ አድርጓል፡፡

ከጥቅምት 25 ቀን ጀምሮ የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ለማስተናገድ ዝግጅት ሲያደርግ የሰነበተው ድሬዳዋ ከተማ፣ በሰባተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ወልቂጤ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ድሬዳዋ ከመቻል፣ ኢትዮጵያ መድን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ሲዳማ ከሐዋሳ ያደረጉት ጨዋታዎች በጨቀየ ሜዳ ላይ ለማስተናገድ ተገደዋል፡፡ በዚህም የሜዳው መጨቅየት በርካቶችን ሲያነጋገር ሰንብቷል፡፡  

የፕሪሚየር ሊግ ውድድርን የማሰናዳት ዕድሉን ለሦስተኛ ጊዜ ያገኘው የድሬዳዋ ከተማ የስታዲየም ዕድሳት ሲያደርግ መቆየቱ ቢጠቀስም፣ የመጫወቻ ሜዳ ዕድሳት ጥራት ላይ ግን ጥያቄ ተነስቶበታል፡፡

በአሸዋማ ሜዳው የሚታወቀው ድሬዳዋ ስታዲየም ዕድሳቱ ሲከናወን በቂ ጥናት ሳይደረግ የሳር ተከላው መከናወኑ ጥራቱን የጠበቀ ሜዳ ማሰናዳት አለመቻሉን ባለሙያዎች ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የሳር ተከላውን ለማከናወን አሸዋማ ሜዳው ላይ ሌላ አፈር በመጨመሩና በዝናብ ወቅት እንዲጨቀይ ምክንያት መሆኑ ተነስቷል፡፡

በድሬዳዋ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን አማካይነት ዕድሳት ሲደረግለት እንደነበር የተጠቀሰው ስታዲየሙ የመጫወቻ ሜዳ፣ የመልበሻ ክፍል፣ የመፀዳጃና የሚዲያ ክፍሎች እንዲሁም አዲስ የማስታወቂያ ዲጂታል መሣሪያዎች መካተታቸው ተገልጾ ነበር፡፡

ሆኖም ሊጉ አመቺ የሆነ የመጫወቻ ሜዳ ባለመኖሩና በኢትዮጵያ አማራጭ ስታዲየሞች ባለመኖራቸው አክሲዮን ማኅበሩ ሥጋት ውስጥ መግባቱ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ክፍሌ አስተያየት ከሆነ፣ በኢትዮጵያ አማራጭ ውድድር ማስኬጃ ስታዲየሞች አለመኖራቸው የሊጉን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ አሳሳቢ አድርጎታል ይላሉ፡፡

ምንም እንኳን በድሬዳዋ ተቋርጦ የነበረው የሁለተኛው ዙር ውድድር የዝናብ ትንበያ ውጤትን ተከትሎ ከተቋረጠበት እንደሚቀጥል ቢገለጽም፣ የአየር ሁኔታ ካልተስተካከለ አማራጭ ስታዲየም አለመኖሩንና ውድድሩን ለማቋረጥ እንደሚገደዱ አቶ ክፍሌ ያስረዳሉ፡፡

በ2015 ዓ.ም ውድድር ዓመት በባህር ዳር፣ በድሬዳዋ፣ በአዳማ፣ በሐዋሳና በአዲስ አበባ ጨዋታዎቹን በዙር ለማከናወን ዕቅድ የያዘው ሊግ ካምፓኒው፣ ዕድሳታቸው ካልተጠናቀቀ አንድም ዝግጁ የሆነ ስታዲየም እንደሌለ ገልጿል፡፡

በዙር ውድድሩን የማስተናገድ ዕድል አግኝተው የነበሩት የአዳማና የሐዋሳ ዩኒቪርሲቲ ስታዲየሞች ዕድሳት እንዲሁም በግንባታ ላይ ያለው የአዲስ አበባ ስታዲየም ዕድሳት ባለመጠናቀቃቸው ችግሩን አሳሳቢ እንዳደረገው አቶ ክፍሌ ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

‹‹ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ሳምንት መርሐ ግብሩን ሲያስተናግድ የነበረው የባህር ዳር ስታዲየም፣ ለሁለተኛ ዙር ዕድሳት ላይ በመሆኑ አክሲዮን ማኅበሩ አማራጭ ስታዲየም እንዳይኖረውና አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገባ ዳርጎታል፤›› ሲሉ አቶ ክፍሌ ያክላሉ፡፡

ደረጃውን የጠበቀ ወይም የካፍን መሥፈርት ማሟላት የቻለ ስታዲየም የሌለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ችግር፣ አሁን ደግሞ አንድ ለእናቱ ወደሆነው ፕሪሚየር ሊግ  መምጣቱ አሳሳቢ መሆኑን በበርካቶች ዘንድ እየተነሳ ይገኛል፡፡

በክልሎች እንዲሁም በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ስታዲየሞች ተገንብተው ቢገኙም፣ ሕንፃቸው ለይስሙላ ከመቆም በዘለለ አንድም ጥራቱን የጠበቀ የመጫወቻ አለመኖሩና የድሬዳዋ ስታዲየም መጫወቻ ሜዳ ዕድሳቱ የይድረስ ይድረስ መሆኑ ዋነኛ ምክንያት መሆኑ ችግሩን እንዳባባሰው ጠቅሰዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...