Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹ሁላችንም በጋራ ሕገወጥ የባህል ንብረት ዝውውርን መዋጋት አለብን›› ዩኔስኮ

‹‹ሁላችንም በጋራ ሕገወጥ የባህል ንብረት ዝውውርን መዋጋት አለብን›› ዩኔስኮ

ቀን:

ዓለም አቀፉ የባህል ተቋም ዩኔስኮ በየዓመቱ ኖቬምበር 14 ቀን (ኅዳር 5) ቀን በሕገወጥ መንገድ የሚደረጉ ባህላዊ ንብረቶች (ቅርሶች) ዝውውርን የመከላከል ቀን አድርጎ ማክበር ከጀመረ ሦስተኛ ዓመቱ ላይ ደርሷል፡፡

በየአገሮቹ የሚገኙ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ላይ ስርቆት፣ ዘረፋና ሕገወጥ ዝውውር እየተፈጸመ መሆኑ በየጊዜው የሚሰማ ነው፡፡

የሕዝቡ ባህል፣ ማንነትና ታሪክ እየተዘረፈ በመሆኑ ሁሉም ይህንን ወንጀል ለመዋጋት በጋራ መሥራት እንዳለበት ዩኔስኮ ቀኑን አስመልክቶ ባስተላለፈው መልዕክት ጥሪ አቅርቧል፡፡

‹‹ሁላችንም በጋራ በመሆን ሕገወጥ የባህል ንብረት ዝውውርን መዋጋት አለብን፤›› ሲልም አስገንዝቧል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕወጥ የባህላዊ ንብረት ዝውውር የሚፈጸምባቸው በርካታ ምክንያቶች ያሉ ሲሆን፣ አንዱ አለማወቅ ወይም አለመገንዘብ ሌላው በጥንታዊ ቅርስ አሰባሳቢ ደላሎች የሚፈጸም ነው፡፡ ይህም ኢንተርኔትን ጨምሮ በጨረታ የሚሸጥበት ነው፡፡

በሌላ በኩልም በአገሮች ውስጥም ሆነ በአገሮች መካከል በሚደረጉ ጦርነቶች ተንቀሳቃሽ ዝርፊያ መንስዔዎች ናቸው፡፡

ዩኔስኮ ይህንን ሕገወጥ ድርጊት ለመቋቋም እ.ኤ.አ. በ2019 ባካሄደው 40ኛው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ኖቬምበር 14 ቀን ሕገወጥ ዝውውርን ለመከላከል ዓለም አቀፍ ቀን አድርጎ መርጦታል፡፡

የ1970 ኮንቬንሽን አፈፃፀምን ለማጠናከር፣ ሕገወጥ ዝውውርን ለመዋጋት ሞዴል ድንጋጌዎችን በማዘጋጀት፣ ባህላዊ ንብረቶችን የተመለከተ የሥነ ምግባር ደንብን ለማሻሻል እየሠራ መሆኑን ያስታወቀው ዩኔስኮ፣ ለዓመታት የሚዘልቅ የአቅም ግንባታ መርሐ ግብር ለመጀመር ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ እገኛለሁ ብሏል።

በዚህ ረገድ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ በስዊድን መንግሥት ድጋፍ   በምሥራቅና በመካከለኛው አፍሪካ ወደ አንድ መቶ የሚጠጉ የሙዚየምና የሕግ አስከባሪ ባለሙያዎች የሚሳተፉባቸው ሁለት ዓውደ ጥናቶችን ማዘጋጀቱን ይፋ አድርጓል፡፡  

ከዩኔስኮ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያላት ኢትዮጵያ ከሦስት ዓመት በፊት የተወሰነውን ዓለም አቀፍ ቀንን በተከታታይ ሁለት ዓመታት ስታከብር ቆይታ ዘንድሮ ግን አስባ ውላለች፡፡

በአዲሱ ስሙ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን በአዳራሹ ቀኑን ኅዳር 6 ቀን 2015 ዓ.ም. ያከበረው ‹‹ሕገወጥ የቅርሶች ዝውውር መከላከል ቀን›› በማለት ነው፡፡ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንደገለጸው፣ ሕገወጥ የቅርስ ዝውውርና ሽያጭ ለአገሪቱ ቅርሶች መጥፋት ምክንያት ከሆኑ በርካታ ሰው ሠራሽ ችግሮች መካከል አንዱ ነው፡፡

ቅርሶችን ከስርቆትና ከዘረፋ መከላከል የሁሉም ግዴታ መሆኑም በመድረኩ ተወስቷል፡፡

ለዝርፊያና ለስርቆት ተጋላጭ የሆኑት ብራናዎች

ኢትዮጵያ የዓለም ቅርስ ከሆኑት ከ12ቱ ጥንታውያን መጻሕፍት ባሻገር  የበርካታ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶች ባለቤት ናት፡፡ የእምነት ተቋሞች የቅርሶቹ ቀዳሚ መገኛ ሥፍራ ናቸው፡፡ ጥንታውያኑ መጻሕፍት አገር በቀል ዕውቀትን አምቀው እንደመያዛቸው ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላው መረጃ የሚሸጋገርባቸው ድልድዮችም ናቸው፡፡

በጥንታውያን ገዳማትና መስጊዶች የሚገኙ የጽሑፍ ቅርሶች ምዝገባ ሒደትም ብዙ ክፍተት አለው፡፡ ምን ዓይነት ይዘት ያላቸው መጻሕፍት፣ በምን ያህል መጠን፣ በየትኛው ተቋም፣ እንደሚገኙ አለመታወቁ ቅርሶቹ ለስርቆት ከሚዳረጉባቸው ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳል፡፡ ለጉብኝት፣ ለጥናትና ምርምርና ሌሎችም ምክንያቶች ወደ አገሪቱ የሚመጡ ግለሰቦች ለስርቆቱ ቀዳሚ ተጠያቂ ሲሆኑ፣ ዜጎችም የቅርስን ዋጋ ባለመገንዘብና በገንዘብ በመደለል ይተባበራሉ፡፡

በ19ኛውና በ20ኛው ምዕት ዓመት በቀዳሚነት በእንግሊዙ ጄኔራል ናፒርና በፋሺስት ኢጣልያ ወረራ ወቅት የጽሑፍ ቅርሶችን ጨምሮ በርካታ ቅርሶች ከአገሪቱ ተዘርፈው ተወስደዋል፡፡

 የኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶች በአውሮፓ ሙዚየሞች፣ በቤተ መጻሕፍትና ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞችም ይገኛሉ፡፡ በጦርነት ወቅት ቅርሶች እንዳይዘረፉና ከተሰረቁም ለባለቤት አገሮች የሚመለሱበት ዓለም አቀፍ ድንጋጌ ቢኖርም፣ ቅርሶችን የማስመለስ ሒደቱ አልጋ በአልጋ አይደለም፡፡ በእርግጥ ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ያስመለሰቻቸው ቅርሶች ቢኖሩም፣ ከኢትዮጵያ ውጪ ካለው የቅርስ ክምችት አንፃር እምብዛም አይደሉም፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 ቅርሶችን መጠበቅ አገራዊ ግዴታ መሆኑ ተደንግጓል፡፡ በ2008 ዓ.ም. የታተመው የባህል ፖሊሲም ዓለም አቀፍ ደረጃውንስ ለጠበቀ የቅርሶች አመዘጋገብ ያትታል፡፡ ጥንታዊ የዋሻ ሥዕሎች አጠባበቅ፣ የመጻሕፍት አጠራረዝ  (ድጎሳ)፣ የአጻጻፍ ሥልትን የመሰነድና የማጥናት ኃላፊነቱም ተገልጿል፡፡

የአብያተ ክርስቲያናት፣ የገዳማት፣ የመስጊዶችና ሌሎችም ቤተ እምነቶችን የቅርስ ሀብት ጠብቆ ለትውልድ ከማስተላለፍ በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት ከአገር የወጡ ቅርሶችን ለማስመለስ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንደሚደረግም በፖሊሲው ተመልክቷል፡፡ አዋጅ ቁጥር 209/1992 የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንን ቅርሶችን የመመዝገብ፣ የመንከባከብ፣ የመጠበቅ፣ ስለ ቅርሶች መረጃ የመስጠት እንዲሁም በልዩ ልዩ ሕገወጥ መንገድ ወደ ውጪ የተወሰዱ ቅርሶች ወደ አገር ውስጥ የሚመለሱበትን መንገድ የማመቻቸት ግዴታ ጥሎበታል፡፡

የብራና ጽሑፎች፣ የድንጋይ ላይ ጽሑፎችና ሥዕሎች ለሕገወጥ ዝርፊያ ተጋላጭ ከሆኑ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ከሌሎች የዩኔስኮ ስምምነት ፈራሚ አገሮች ጋር በጦርነትና በሌሎችም ምክንያቶች የተወሰዱ ቅርሶቿን የማስመለስ መብትን ብትጋራም፣ ምን ያህል ቅርሶችን ለማስመለስ ተጠቅመንበታል? የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...