Tuesday, April 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በመንግሥትና በሕወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ዋነኛ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ያሳረፈው በትር የከፋ በመሆኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውን ለረሃብና ለስቃይ እንዲሁም ለስደትና እንግልት ተዳርገዋል። ማንም አሸናፊ ባልሆነበት በዚህ ሁለት ዓመታትን ባስቆጠረ ደም አፋሳሽ ጦርነት ደረጃው ይለያይ እንጂ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ማኅብሰብ ተጎጂ ሆኗል። አገሪቱ ኢኮኖሚም ከፍተኛ ፈተና ውስጥ መውደቁ የማይካድ ሀቅ ነው።

የሰሜኑ ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰባቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል አንዱ የፋይናንስ ዘርፉ ነው፡፡ በትግራይ ክልል የሚገኙ ከ600 በላይ የፋይናንስ ተቋማት ቅርንጫፎች ከአገልግሎት ውጪ ሆነዋል፡፡ በዚህም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተገልጋይ በባንኮቹ ያስቀመጠውን ሀብት እያለው መጠቀም ሳይችል በረሃብና በችግር ተጎድቷል። የአገሪቱ ባንኮችም በቅርንጫፎቻቸው አማካይነት የተሰጡትን ከፍተኛ መጠን ያላቸው ብድሮች ላለፉት ሁለት ዓመታት ለማስመለስ አልቻሉም፡፡

አሁን ግን ይህ የሰላም ስምምነት መልሰው አገልግሎታቸውን ለመጀመር ዕድል እንደሚሰጣቸው ያነጋገርናቸው የተለያዩ ባንኮች የሥራ መሪዎች ገልጸዋል፡፡ 

በሰሜኑ ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው ወጋገን ባንክ ነው፡፡ የባንኩ የማርኬቲንና ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አፈወርቅ ገብረ ጻዲቅ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሰለሳም ስምምነቱ ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን ነው፡፡ የሰሜኑ የኅብረተሰባችን ክፍል ወደ ቀድሞ ሕይወቱ መመለስ የሚችልበት ዕድል የሚፈጥርም ስለመሆኑ አመልክተዋል፡፡ ወጋገን ባንክ ባለፉት 25 ዓመታት በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ሲሠራ የቆየ ሲሆን፣ በጦርነቱ ምክንያት ግን በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ብቻ 112 ቅርጫፎቹ ከሥራ ውጪ ሆኖ በመቆየቱ ባንካቸው ከፍተኛ የሚባል ጉዳት ገጥሞት እንደቆመ ዳይሬክተሩ ይገልጻሉ፡፡ እነዚህ ተዘግተው የቆዩት ቅርንጫፎች ለወጋገን ባንክ አጠቃላይ እንቅስቃሴ የ28 በመቶ ድርሻ የነበራቸው በመሆኑ ባንኩም ሆነ ደንበኞቹ በእጅጉ መጉዳታቸውን አቶ አፈወርቅ ገልጸዋል፡፡ 

አሁን ግን የሰላም ስምምነት መደረጉ ለባንኩ ትልቅ ፋይዳ ያለው በመሆኑ፣ እነዚህን ቅርንጫፎች መልሶ ሥራ ለማስጀመር ባንኩ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ቅርጫፎቹን ሥራ ለማስጀመር ደግሞ ይህንኑ ሥራ የሚሠራ አንድ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን፣ ቅርንጫፎቹ ያሉበት ሁኔታ በመገምገምና በማጥናት በፍጥነት እንዲከፈቱ እንደሚደረግ ከአቶ አፈወርቀ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ይህ ዕርምጃ ለኅብረሰተቡም ሆነ ባንኩን የሚያግዝ ይሆናል፡፡ የባንክ ሥራ በአንድ ኅብረተሰብ ውስጥ ወሳኝ ሚና ስላለው የእነዚህ ቅርጫፎች መከፈት ኢኮኖሚውን ከማነቃቃቱም በላይ አገልግሎት አጥቶ የነበረውንም የኅብረተሰብ ክፍል የሚያግዝ ጭምር በመሆኑ፣ ከዚህ የሰላም ስምምነት ሁሉም ተጠቃሚ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ 

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከ100 በላይ ቅርንጫፎችን በጦርነቱ ምክንያት ከሥራ ውጪ የሆኑበት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ቅርጫፎቹ መልሶ ለማስጀመር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቢ ሳኖ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ከሰሞኑ አገልግሎት ያስጀመራቸው ቅርንጫፎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይልና የቴሌ ኮሙዩኒኬሽን መሠረት ልማት የተሟሉባቸው አካባቢዎችን እየተለዩ በየዲስትሪክቱ አስተባባሪነት ቅርንጫፎቹ ኦዲት እየተደረጉ ወደ ሥራ የሚገቡ መሆኑንም አቶ አቤ ሳኖ አመልክተዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ሆነ ከወጋገን ባንክ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ ጦርነቱ በትክክል በባንካቸው ላይ ያሳረፈውን ተፅዕኖ ለመግለጽ በመስክ የሚደረገው መረጃ ከተሰበሰበ በኋላ የሚገለጽ እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡ 

በመንግሥትና በህወሓት መካከል የተረሰው የሰላም ስምምነት ለባንኮች ብቻ ሳይሆን ለበርካታ ኢትዮጵያን የእረፍት ስሜትን የፈጠረ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚንም ከገባበት ቅርቃር ሊያወጣ የሚችል በጎ ዜና አንደሆነ ያነጋገርናቸው የተለያዩ ባለሙያዎችና የኅብረተሰብ ክፍሎች ይገልጻሉ።

በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ያልጠበቁት፣ ግን እጅግ አስደሳች ከሆነባቸው በርካታ ዜጎች መካከል የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አንዱ ናቸው፡፡ ፕሬዚዳንቱ አቶ ካሳሁን ፎሎ እስከ ዛሬ ከሰማኋቸው ክስተቶች በሙሉ ከዚህ ዜና የበለጠ ያለ እንደማይመስላቸውም ገልጸዋል፡፡ በዚህ ጦርነት አገር የከፈለችው ዋጋ ቀላል ያለመሆኑን የጠቆሙ አቶ ካሳሁን፣ ‹‹በእርግጥ የማንኛውም ጦርነት መጨረሻው ድርድር ወይም ስምምነት ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ደረጃ በዚህ መልኩ ተስማምተው ይወጣሉ የሚል ግምት አልነበረኝም፤›› ብለዋል፡፡ በወንድማማች መካከል ተከፍቶ የነበረውን ጦርነት በድርድር ለመፍታት የተወሰነው ውሳኔ ትልቅ ነገር ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡   

ከሁኔታዎች አንፃር ሰላም ለማውረድ እንዲህ አጭር ጊዜ ስምምነት ላይ ይደርሳል ብለው ያልጠበቁት ነገር ቢሆንም፣ ስምምነቱ ዕውን ሆኖ ሰላም ለማውረድ የተጀመረው እንቅስቃሴ እንደ ዜጋ ትልቅ ዕፎይታ የሚሰጥና መነቃቃትን የሚፈጥር ስለመሆኑም አመልክተዋል፡፡  

እንደ አቶ ካሳሁን ሁሉ የሕግ ባለሙያው አቶ ፈቃዱ ጴጥሮስ በበኩላቸው፣ የሰላም ስምምነቱ እንዲህ በቀላሉ በእነዚህ ሁሉ ነጥቦች ላይ ስምምነት ይደረሳል ብለው ያልጠበቁት መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡  

‹‹ነገር ግን በፈጣሪ ዕገዛ ታክሎበት የሰላም ስምምነቱ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረሱ ደግሞ የአደራዳሪዎችንም ተግባር ማድነቅ ይገባል፤›› በማለት፣ ለዚህ ስምምነት መፈረም አደራዳሪዎች ላበረከቱት አስተዋጽኦ ተገቢውን ምሥጋና ማቅረብ እንደሚገባም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ ዘጠኝ ቀናት ሙሉ እጅግ ከፍተኛ በሆነ ድካም የሠሩትና በሁለቱም ወገን እየተወቀሱ፣ በጥርጣሬ እየታዩ ያስገኙት ውጤት ስለሆነ ትልቅ ቦታ እንደሚገባቸው አመልክተዋል፡፡  

ታዋቂው የፋይናንስ ባለሙያው አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ፣ እንዲህ ያሉ ጦርነቶች መጨረሻቸው ይህ እንደሚሆን ይጠብቁ እንደነበር አመልክተዋል፡፡ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ መሰባሰቡ ጠቃሚ መሆኑን፣ በተደጋጋሚ ሲገልጹ እንደነበር በማስታወስ፣ ይህ በመሆኑ እጅግ ተደስቻለሁ ብለዋል፡፡ ብዙዎቻችን ሲያስጨንቅ የነበረው ጦርነት ቆሞ ወደ ሰላም ጉዞ መጀመሩ ለአገር ዕፎይታ ጭምር መሆኑን የገለጹት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ የደረሰው ጉዳት እንደ አገር ብዙ ዋጋ ያስከፈለ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ በአንፃሩ ግን በዚህ የጦርነት ዘመን ይህንን ያህል ጫናና ጉዳት ደርሶብን የህዳሴ ግድብን ያለማቋረጣችን፣ ሌሎች የልማት ሥራዎችን መቀጠላችንና ለዛሬ መድረሳችን በራሱ ተዓምር እንደሚሆንባቸው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡  

ጦርነቱ ካስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ ባሻገር ኢኮኖሚ ላይ ያደረሰውን ውድመትን በተመለከተ እኚሁ ያነጋገርናቸው አስተያየት ሰጪዎች ወድመቱን በቀላሉ ለመግለጽ የሚከብድ መሆኑንና እንደ አገር ብዙ ዋጋ የተከፈለበት ስለመሆኑ አውስተዋል፡፡ 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ በበኩላቸው፣ ጦርነቱ ኢኮኖሚው ላይ ብዙ ጫና ፈጥሮ እንደነበር ገልጸው፣ በጦርነቱ ምክንያት የተፈጠሩ ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች በርካታ ናቸው ይላሉ፡፡ ለውጭ ምንዛሪ እጥረትና ለዋጋ ንረቱ ማባባስ ይህ ጦርነት የነበረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር፡፡ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ፋይዳ የነበረና እንደ ዓለም ባንክ ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንሰጣለን ያሉትን ድጋፍ ብድር ላለመልቀቃቸው አንዱ ምክንያት ይኼው ጦርነት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ 

የዓለም ባንክ ለአገራዊ ኢኮኖሚው እሰጣለሁ ብሎ ቃል ከገባው ሦስት ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ሦስት መቶ ሚሊዮን ዶላር ብቻ ከሰጠ በኋላ ቀሪው ገንዘብ ያልተለቀቀበት ዋናው ምክንያት የሰሜኑ ጦርነት ስለሆነ ጦርነቱ ኢኮኖሚ ላይ የፈጠረውን ጫና በቀላሉ መገመት እንደሚቻል አመልክተዋል፡፡  

ጦርነቱ ያስከተለው ጉዳት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ጓዳ ውስጥ ገብቶ እንደነበር የገለጹት አቶ ካሳሁን ደግሞ፣ የኑሮ ውድነት እንዲባባስም ጦርነቱ የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለው በመጥቀስ የአቶ ተክለወልድን ሐሳብ አጠናክረዋል፡፡  

እንደ ሠራተኛ መሪነታቸው በዚህ ጦርነት ሰበብ ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ሥራ አጥ ሆነዋል፣ ሞተዋል፣ ቆስለዋል፣ አካል ጉዳተኛ ሆነዋል፡፡ ሌላውን ሁሉ ትተን ይህንን ጦርነት ሰበብ በማድረግ የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያ የአጎዋ ዕድል ተጠቃሚ እንዳትሆን የተላለፈው ውሳኔ ብቻ አገር ካጣችው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ባሻገር የሠራተኞችን የሥራ ዋስትና እስከ ማሳጣት መድረሱን ገልጸዋል፡፡ 

በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ በአጎዋ ዕድልን ተጠቅመው ምርታቸውን  ለአሜሪካ ገበያ ያቀርቡ የነበሩ ፋብሪካዎች 5,600 ሠራተኞች የተባረሩት በዚሁ ጦርነት ሰበብ መሆኑን በማስታወስ ጦርነቱ ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ ቀውሶችንም አስከትሏል ይላሉ፡፡ 

ከዚህ ባሻገር በአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ፋብሪካዎች ውስጥ አሁንም ድረስ ሥራ ያልጀመሩ ሠራተኞችን አባረዋል፡፡ ሥራ ያልጀመሩ አሉ፡፡ በአፋርም ተመሳሳይ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ስለዚህ የጦርነቱ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የተለያዩ መገለጫዎች እንደነበራቸው ያመለክታሉ፡፡ 

በትግራይ ክልልም ያሉ ፋብሪካዎች መቆም፣ ምን ያህል ሠራተኛ ሥራ አልባ እንዳደረገ መገመት እንደማያቅት ያስታወቁት አቶ ካሳሁን፣ እነዚህ ፋብሪካዎችም ይሰጡ የነበረው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲታጣ አድርጓል፡፡ በተለይ በትግራይ ክልል በሚገኙ ተቋማት ውስጥ ብቻ ከ70 ሺሕ በላይ አባላት እንዳሏቸው የገለጹት አቶ ካሳሁን፣ እነዚህ ሠራተኞች ያሉበትን ሁኔታ ምን እንደሆነ እንኳን አለማወቃችን ሌላው ሕመም እንደሆነ በመግለጽ፣ ጦርነቱ ያስከተለውን ጉዳት ዘርዝሮ ለመጨረስ የሚከብድ እንደሚሆንባቸው ጠቅሰዋል፡፡ 

አቶ ፈቃዱም ይህ ጦርነት በዚህች አገር ላይ ያደረሰው ጉዳት፣ በርካታ መገለጫዎች እንዳሉት ገልጸው፣ አንዱና ትልቁ ጉዳት ለዚህ ጦርነት የሚወጣው ወጪ ከፍተኛ ስለነበር ኢኮኖሚውን በእጅጉ ጎድቷል፡፡ የጦር መሣሪያ በውጭ ምንዛሪ ተገዝቶ ጦርነቱ የሚካሄድ እንደመሆኑ መጠን በውጭ ምንዛሪ የሚገቡ ሌሎች ምርቶችን ለማስገባት እስካለመቻል መድረሱንም አስታውሰዋል፡፡ ከበጀት አንፃርም  ከሌላው ልማት ላይ እየተቀነሰ ለጦርነት ይውል ስለነበር ኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጫና ያደርሳል፣ አድርሷል፡፡ ጦርነቱ ያስከተለው ጉዳት በጥቅል የሚያሳይ መረጃ ይፋ ባይሆንም፣ የአማራ ክልል ባደረገው የዳሰሳ ጥናት በክልሉ ብቻ ከ290 ቢሊዮን ብር በላይ ውድመት ደርሷል ማለቱ ይታወሳል።

ከአቶ ተክለወልድ ገለጻ መረዳት እንደተቻለው ደግሞ፣ የዓለም ባንክና ሌሎች አጥኚዎች ባደረጉት ጥናት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተደረገው ጦርነት የወደመውን ንብረት ለመተካትና በጦርነቱ ሰለባ የሆኑትን ለማቋቋም ከ20 እስከ 23 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ለሚደረገው የመልሶ ማቋቋምና የመሠረተ ልማት ግንባታ ያስፈልጋል ተብሎ የሚገመተው ይህ የገንዘብ መጠን፣ እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ይህ ገንዘብ በኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ የማይሸፈን ባለመሆኑ የውጭ ረጅ ተቋማትና አገሮችን እንዲሳተፉበት በተደራጀ ሁኔታ ሥራ የሚሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ጦርነቱ የሰዎችን ሕይወት ከመቅጠፍ ባሻገር በንብረት ላይ የደረሰው ውድመት ከፍተኛ ስለመሆኑ እንዲህ ያሉ አኃዛዊ መረጃዎች ማሳያ ይሆናሉ ተብሏል፡፡

ጦርነቱ ሌላው አስከፊ ገጽታ ተደርጎ መገለጽ ያለበት ጦርነቱ የበላው በአብዛኛው ልማታዊ የሚባለውን ወጣቱን ክፍል በመሆኑ ነው የሚሉት አቶ ፈቃዱ፣ ይህም ጉዳቱ የአሁኑን ብቻ ሳይሆን ወደፊትንም ተስፋ እንደሚጎዳ ገልጸዋል፡፡ ቤተሰብን ያለ ረዳት፣ ልጅን ያለ ረዳት፣ ወላጅን ያለጧሪ የሚያስቀር ስለሆነ፣ ይህም ራሱን የቻለ ኢኮኖሚዊ ጉዳት ተደርጎ መወሰድ አለበት ብለዋል፡፡

ጦርነት ወይም የሰላም ዕጦት ሲከሰት ኢንቨስትመንት ይጎዳል በተለይ አስተማማኝ ሠላም መኖርን መሠረት አድርጎ የሚፈሰው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በጦርነቱ ምክንያት በእጅጉ መዳከሙንና ይህም በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ የሚያስከተልው ጉዳት ቀላል እንደማይሆን ገልጸዋል፡፡

የጦርነቱ ጉዳት በአኃዝ ለመግለጽ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ የጉዳቱ ስፋት ግን በተጨባጭ መረጃዎች መግለጽ እንደሚቻል የጠቆሙት አቶ ፈቃዱ፣ ለምሳሌ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተወሰነ ግነትም ቢኖረው፣ አንዳንድ የኢንቨስትመንት አማካሪዎች ‹‹ኢትዮጵያ ኢንቨስት ሊደረግባት የማትችል አገር ብለው በየሚዲያው እስከ መግለጽ ለመድረሳቸው ዋናው ምክንያት ይኼው ጦርነት ነው፤›› ይላሉ፡፡ 

እንዲህ ያለው አመለካከት ደግሞ ኢትዮጵያ ብድር የመመለስ አቅሟ ዝቅተኛ ነው በሚል ‹‹ሲሲሲ›› የሚባለውን ደረጃ እንዲያሰጣት ማድረጉን አቶ ፈቃዱ አብራርተዋል፡፡ ይህ ደረጃ ደግሞ የኢትዮጵያ የዕዳ ሰነድ (ቦንድ) ተፈላጊ እንዲሆን እንዳደረገው ጠቁመው፣ ጦርነቱ የዚህ ሁሉ ነገር ብቸኛው ምክንያት ነው ባይባልም ተያያዥነትና ተፅዕኖ እንዳለው ግን አይካድም ብለዋል። 

ችግሩ በዚህ ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ባንኮች ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ሥርዓት ጋር እንዳይተሳሰሩ፣ ብድር እንዳይሰጥ ሁሉ ያደረገው ይህ ጦርነት መሆኑን አቶ ፈቃዱ ገልጸዋል፡፡ ስለዚሀ ጦርነቱ ያደረሰው ኢኮኖሚዊ ጉዳት እንዲህ በቀላሉ የሚገመት አይደለም የሚለውን ምልከታ ይጋራሉ፡፡ ጦርቱ ኢትዮጵያ  የተለያዩ ማዕቀቦችም ውስጥ እንድትገባ ያደረገ እንደነበር የሚጠቅሱት አቶ ፈቃዱ፣ አሁን ላይ የሰላም ስምምነቱ ግን እንዲህ ያሉ ጫናዎችንና ማዕቀቦችን የሚያስቀርና የሚያነሳ በመሆኑ፣ ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ ያደርጋል የሚል እምነታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ 

በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ብዙ ተስፋ የተጣለበት የመሆኑን ያህል ዝርዝር አፈጻጸሙ ደግሞ ጥንቃቄና ብዙ ሥራ የሚጠይቅ መሆኑን ማሰብ እንደሚገባ አቶ ፍቃዱ ያሰምሩበታል። 

የሰላም ስምምነቱ የሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ምንድነው? በሚለው ጥያቄ ዙሪያ አቶ ፈቃዱ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ አሁን የተፈጸመውን ስምምነት ወደ ተጨባጭ ዘላቂ ሰላም ለመውሰድ መተማመን ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ነው፡፡ ‹‹እምነት መታመንን ይወልዳል›› እንደሚባለው፣ እያንዳንዱ ወገን ጥርጣሬን ከሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎች፣ ድርጊቶችና መግለጫዎች መቆጠብና ሁሉም የቀደመውን ረስቶ ወደፊት መሄድ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ ይህ ሲሆን ኢኮኖሚም እንደታሰበው ከሚገኘው ሰላም የሚጠቀም ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ግን ‹‹ይህ ጦርነት ያስተማረን ነገር አለ›› የሚሉት አቶ ፈቃዱ፣ ‹‹ከዚህ በኋላ ጦርነትን እንዳናምነው፣ ጦርነትን ተስፋ እንዳናደርግ የሚያደርግ ይመስኛል፡፡ ምክንያቱም የምንፈልገውን ነገር ከጦርነት አናገኝም፤›› በማለት፣ ይህንን አጋጣሚ መማሪያ ማድረግ ብልህነት እንደሆነ ይመክራሉ፡፡ 

ከዚሁ አንፃር በዚህ መራር መንገድ ውስጥ ማለፋችን ምናልባት እንደ አገር ትውልዱ ከዚህ ተምሮ ለወደፊት ከጦርነት እንዲርቅ ያደርጋል ብለው ተስፋም ያደርጋሉ፡፡ ባንፈልገውም የደረሰው ደርሷል፡፡ ከዚህ ስምምነት በኋላ ምናልባት እንደ ጀርመንና ጃፓን ከጦርነቱ በኋላ ታላቅ የበለፀገች አገር መሆን የሚቻልበትም ዕድል ሊኖር ይችላል የሚልም ተስፋቸውን አክለዋል፡፡ 

ከዚህ የሰላም ስምምነት ማግሥት የሚመጡ የኢኮኖሚ ትሩፋቶች እንደሚጠበቁና የኢኮኖሚ ማዕቀቦችና ጫናዎች እንደሚረግቡ የገለጹት አቶ ካሳሁና አቶ ፈቃዱ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ፣ የአውሮፓና የአሜሪካ የዕርዳታ ተቋማት የመተባበርና የማገዝ ፍላጎትና ዝግጁነት እያሳዩ መሆኑን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ በጦርነት ወቅት አገሪቱን የጎዳት አንዱ ነገር ማዕቀቡ ነውና ይህ ማዕቀብ መነሳቱ ኢኮኖሚን ለማነቃቃት አጋዥ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡ 

የስምምነቱ ሌላው ጠቀሜታ ደግሞ ለኢንቨስትመንትና ማኅበረሰቡም ተስፋ የሚሰጥ መሆኑ ነው፡፡ የጦርነቱ መቆም ኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ያሉት አቶ ተክለወልድ ደግሞ፣ በአበዳሪና በለጋሽ አገሮች የተያዘው ብድርና ዕርዳታ የሚለቀቅበትን መልሶ የማመቻቸት ሁኔታ በር ከፋች በመሆኑ ነው፡፡ ከእነዚህ አካላት በተጨማሪ ሌሎች ተቋማትም ድጋፍ እንዲሰጡ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር በመሆኑ ከኢኮኖሚ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለማቃለል የሚቻልበትን በር እንደሚከፍት ተቁመዋል፡፡ ሰላም ከመጣ የልማት አጋሮቹ እንደገና ወደ ቀደመው ድጋፋቸው የሚመለሱ ስለመሆናቸው የሚያምኑት አቶ ተክለወልድ፣ የጦርነቱ መቆም የሰው ሕይወት እንዳይቀጠፍ ከማድረጉ በተጨማሪ፣ ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው አመልክተዋል፡፡ በአንፃሩ ግን በጦርነት የተጎዳው ብዙ ነገር ስላለ ለጦርነት የሚውል ገንዘብ ቆመ ማለት ከጦርነቱ በኋላ ምንም ወጪ የለም ማለት እንዳልሆነም አቶ ተክለወልድ ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱም ለመልሶ መቋቋሙና ለተያያዥ ሥራዎች ብዙ ወጪ ይጠይቃሉ፡፡ እንዲያውም ለመልሶ መቋቋምና ለመሠረተ ልማት ግንባታው የሚወጣው ወጪ ለጦርነት ከሚወጣው በላይ ሊሆን እንደሚቻልም  አስረድተዋል፡፡ ይህ የመልሶ ግንባታና መልሶ የማቋቋም ግን ኢኮኖሚው ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው የገለጹት አቶ ተክለወልድ፣ በመልሶ ግንባታ የሚከናወኑ እያንዳንዳቸው ፕሮጀክቶችና የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ የመሆኑን ያህል ሰፊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ አስረድተዋል፡፡ 

መልሶ የመገንባትና የማቋቋም ሥራው እየሰፋ በሄደ ቁጥር ገንዘብ እንቅስቃሴን ያሳድጋል ገበያን በማስፋት ብዙ ሸማቾችን እንደሚጥር በመግለጽ የመልሶ ግንባታው ሥራ ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ የሚያስችል ይሆናል ይላሉ፡፡ ስለዚህ መልሶ የማቋቋም ሥራ ራሱ ኢኮኖሚ መነቃቃትን ከመፍጠር በላይ ለኢኮኖሚው ዕድገቱም አጋዥ ይሆናል ተብሎ እንደሚታመን አብራርተዋል፡፡ 

ጦርነቱ በሰላም ስምምነት መፈታት በራሱ ብዙ ነገሮችን ያፍታታል ያሉት አቶ ካሳሁንም፣ አሁንም ምሳሌ አድርገው ያነሱት አጎዋን ነው፡፡ ‹‹ከአጎዋ ተጠቃሚነታችን የተገደብነው ሰብዓዊ ዕርዳታ መድረስ አለበት፤›› በሚልና የመሳሰሉ ምክንያቶች ተደርድረው ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ተጠቃሚነት ተገለን የምንቆይበትን ምክንያት ሊያቀርቡ አይችሉም፡፡ እኛም እንደ ሠራተኛ ማኅበር ዕገዳው እንዲነሳ እንጥራለን፡፡ በአጎዋ ተጠቃሚነታችን ይቀጥላል፡፡ ስለዚህ ይህ ስምምነት የአጎዋ ተጠቃሚነታችንን ይመልሳል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የተዘጋው ገበያ ይከፈታል፣ የሠራተኛው የሥራ ዋስትና የሚያረጋግጥ በመሆኑ በጦርነት ያጣነውን የሰላም ድርድሩ ውጤት መልሰን እንድናገኘው ያደርጋል ይላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ግብና ላይ የተመሠረተ እንደመሆኑ መጠን ጦርነቱ ያስተጓጎለው እርሻ ይታረሳል፣ የተሻለ ምርትም እንዲመረት ዕድል ስለሚሰጥ የሰላም ስምምነቱ ለአገር ኢኮኖሚ የሚበጅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡ የሰላም መገኘት የቱሪዝም ዘርፉ እንዲነቃቃና በጦርነት ምክንያት ተገድቦ የቆየው ቱሪዝም እንቅስቃሴ ሊያግዝ ይችላል ብለዋል፡፡  

አቶ ተክለወልድ የሰላም ስምምነት መደረጉ በአጭር ጊዜ የተጎዳውን ኢኮኖሚ ለመመለስ ትልቅ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን አመልክተዋ፡፡ ሰላሙ በአገር ደረጃ የተፈጠረውን ዋጋ ንረት ለማውረድ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን ሁሉ ለመቅረፍ ያግዛል፡፡ በመሆኑ ያለ ምንም ጥርጥር ኢኮኖሚውን ለማሳደግ እየተደረጉ ያሉ ወቅታዊ ጥረቶች ሰላም ከሚያስገኝልን ጥቅም ጋር ተዳምሮ ኢኮኖሚውን እንደሚቀይረው የጠነከረ እምነት አላቸው፡፡

ከአቶ ተክለወልድ አጥናፉ ገለጻ መረዳት እንደተቻለው፣ ከ20 እስከ 23 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ይጠይቃል ከተባለው የመልሶ ማቋቋም የመሠረተ ልማት ግንባታ በሻገር፣ አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙን ለማስቀጠል የሚረዱን የፋይናንስ ድጋፎችን ለማግኘት ተጨማሪ ሥራዎች የሚሠሩ መሆኑን ነው፡፡ በተለይ የዓለም ባንክና አይኤምኤ እሰጣለሁ ብለው ቃል የገቡትን ድጋፍ እንዲለቁ ይህ የሰላም ስምምነት ጥሩ አጋጣሚ ከመሆኑ ባሻገር፣ መንግሥት ከነዚህ ተቋማት ኢኮኖሚውን የሚደግፍ የተሻለ ድጋፍ ለማግኘት አዲስ ፕላን አደራጅቶ ለማቅረብ ተጨማሪ ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል። 

ይህ የሰላም ስምምነት የሚያስገኘው ጥቅም በብዙ መንገድ የሚገለጽ ቢሆንም፣ በተለያዩ ሚዲያዎች የሚሰሙ አንዳንድ ዘገባዎችና የሰላም ሒደቱን የማደናቀፍ አቅም ያላቸው መረጃዎች በርካቶች ላይ ሥጋትን እየጫሩ ነው። ከነዚህም መካከል አቶ ካሳሁን አንዱ ናቸው። 

‹‹የተጀመረው ስምምነት ይህ ይጎለዋል›› በማለትና የመሳሰሉትን አደናቃፊ ምክንያቶች በማቅረብ የሚሰጡ አስተያየቶች ተገቢ ነው ብለው አያምኑም፡፡ ስምምነቱ መሬት ላይ ሳይወርድ ሌሎች ጥያቄዎችን ማቅረብ አግባብ እንዳልሆነ፣ ሁሉም ጥያቄዎች በአንድ ጊዜ እንዲመለሱ ከመወትወት ይልቅ በደረጃ እንዲታዩ ማድረግ ሰላምን እንደሚያጸና ይመክራሉ። በተለይ የሲቪክ ማኅበራት ሕዝብ እንዲቀራረብ ካላደረጉ፣ ምሁራንና ሚዲያዎችም ይህንን የሰላም ስምምነት ለማስጠበቅ የማይሠሩ ከሆነ ዳግም ወደ ጦርነት የመግባት ጉዳይ ዝግ እንዳልሆነ በመጥቀስ ሁሉም በማስተዋል ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ብለዋል።

ይህንን የሰላም ስምምነት በአግባቡ መሬት ላይ ማውረድ ከተቻለ ኢኮኖሚውን ለማንሳት ዕድሎች እንዳሉ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ በተለይ አቶ ተክለወልድ ይህ የሰላም ስምምነት ኢኮኖሚውን ይጠቅማል ይላሉ፡፡ 

ከሕወሓት ጋር በተደረገው ድርድር በሚፈጠረው ሰላም ኢኮኖሚውን ለመታደግ የሚያስገኘው ጥቅም የማይሳት ቢሆንም፣ በመሐል አገር አሁንም ሰው እየሞተና ንብረት እየወደመ የሚቀጥል ከሆነ ኢኮኖሚውን በታሰበው ደረጃ ለማነቃቃት እንቅፋት መሆኑ እንደማይቀርና እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል፡፡ 

የሰላም ድርድሩ ከኢኮኖሚ አንፃር የሚያስገኘውን ውጤት በተመለከተ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ትናንት በፓርማ ቀርበው በሰጡት ማብራሪያም፣ ሰላም መሥፈኑ የአገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገቱን እስከ 7.5 በመቶ ሊያደርሰው የሚችል መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ይህንንም ምልከታቸውንም ‹‹ባለፈው ዓመት ጂዲፒ 6.4 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ በዚህ ዓመት ያለን ዕቅድ ቢያንስ 7.5 በመቶ ነው፡፡ በተለይ አሁን የተፈጠረው የሰላም ሁኔታ ማስጠበቅ ከቻልን ቢያንስ 7.5 በመቶ እናድጋለን ብለን እናስባለን፤›› በማለት ገልጸውታል፡፡.

   

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች