Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሦስተኛውን የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ለመስጠት ለአንድ ወር የሚቆይ ምክክር ተጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ጨረታውን የሚያሸንፍ ኩባንያ በ08 መነሻ ቁጥር አገልግሎት ይጀምራል

የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ቀጥሎ፣ ሁለተኛውን አዲስ የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ፈቃድ (License B) ለመስጠት በሚያወጣው የፍላጎት መግለጫና ጨረታ ላይ የባለድርሻ አካላት ምክክር አስጀመረ፡፡

እስከ ታኅሳስ 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ለአንድ ወር በሚቆየው ምክክር፣ በጨረታው ላይ ሊሳተፉ የሚችሉ ዓለም አቀፍ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች የሚሳተፉ ሲሆን፣ ኩባንያዎቹ ባለሥልጣኑ ፈቃድ በሚሰጥባቸው ሁኔታዎች ላይ ሐሳባቸውን እንደሚገልጹ እንደሚጠበቅ፣ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሬባ (ኢንጂነር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ እንደሚያስረዱት፣ ባለሥልጣኑ ያስጀመረው የባለድርሻ አካላት ግብዓት ማሰባሰቢያ ምክክር ለሁለተኛ የቴሌኮም ኦፕሬተርነት ፈቃድ የሚወጣው የፍላጎት መግለጫ ማስታወቂያ ምን ዓይነት መሆን እንዳለበት ለመወሰን፣ በጨረታው አካሄድ ላይ ሊሳተፉ ከሚችሉ ኢንቨስትሮች ጋር መግባባት ላይ ለመድረስ ያለመ ነው፡፡

ለዚህም ሲባል ባለሥልጣኑ በአገሪቱ ያሉ አገልግሎት ሰጪዎችን ሦስት የሚያደርሰውን ሁለተኛ ፈቃድ ለመስጠት ስላሰበባቸው መንገዶችና ተያያዥ ጉዳዮች የሚያስረዳ፣ ባለ አሥር ገጽ የባለሥልጣኑ የሕዝብ ማስታወቂያ ሰነድ ይፋ አድርጓል፡፡ ባለድርሻ አካላት አስተያየቶቻቸውን የሚሰጡት በሰነዱ ላይ በቀረቡት ጉዳዮች ላይ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ለምክክር የቀረበው የባለሥልጣኑ የሕዝብ ማስታወቂያ ሰነድ እንደሚያስረዳው፣ ሁለተኛውን ፈቃድ የሚወስድ የቴሌኮም ኦፕሬተር በሌሎቹ ኦፕሬተሮች የሚሰጡትን አገልገሎቶች በሙሉ የመስጠት ፈቃድ ይኖረዋል፡፡ ፈቃዱ የሚቆይበት ጊዜም እንደ ሳፋሪኮም ሁሉ 15 ዓመት ነው፡፡

ባለሥልጣኑ ለምክክር ካቀረባቸው ጉዳዮች ውስጥ የመጀመርያው፣ ሁለተኛው ፈቃድ ከተሰጠ በኋላ ሦስተኛ የቴሌኮም ኦፕሬተር ፈቃድ እስከሚሰጥ ድረስ ምን ያህል ጊዜ ይጠበቃል የሚለው ነው፡፡ የምክክር ሰነዱ በጨረታው ላይ ሊሳተፉ የሚችሉ ባለድርሻ አካላት ምን ያህል የዕፎይታ ጊዜ መሰጠት እንዳለበት ሐሳብ እንዲያቀርቡ የሚጠይቅ ሲሆን፣ ባለሥልጣኑ በአንፃሩ በራሱ የያዘው የዕፎይታ ጊዜ እንዳለ ባልቻ (ኢንጂነር) አስረድተዋል፡፡ ይሁንና የዕፎይታ ጊዜው የሚወሰነው ከባለድርሻ አካላት በኩል ከሚቀርበው ሐሳብ በኋላ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

በኅዳር 2013 ዓ.ም. በወጣው የመጀመርያው የቴሌኮም ፈቃድ ጨረታ ሁለት ፈቃዶችን ለመስጠት ታስቦ የነበረ ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ ሦስተኛ ፈቃድ ከመሰጠቱ አሥር ዓመት የዕፎይታ ጊዜ እንደሚሰጥ ተገልጾ ነበር፡፡ አሁን በድጋሚ ጨረታ የወጣው ሁለተኛ ፈቃድ የመስጠት ሒደቱ ከተቋረጠ አሥር ዓመት ሳይጠበቅ ሌላ ጨረታ እንደሚወጣ በመቀመጡ ነው፡፡

ሦስተኛ የቴሌኮም ኦፕሬተር ለመሆን ፈቃድ የሚያገኘው ኩባንያ ከ2ጂ እስከ 5ጂ አገልግሎት መስጠት የሚችል ሲሆን፣ ለዚህም የሚያገለግሉ ስድስት ስፔክትረም ባንዶች ተመድበው ቀርበዋል፡፡ ጨረታ አሸናፊው ፈቃዱን ካገኘ በኋላ ተጨማሪ የማይክሮዌቭ ሊንክ ስፔክትረም ምደባ ሊያገኝ ይችላል፡፡

በሰነዱ ውስጥ የተካተተው ሌላኛው ጉዳይ ሦስተኛው ቀድመው ፈቃድ ያገኙት ከሁለቱ ቴሌኮም ኦፕሬተሮች ሦስተኛው ባለፈቃድ፣ አገልግሎት ባልጀመረባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ደንበኞቹ የነባሮቹን ሲግናል ተጠቅሞ መደወልና ሌሎች አገልግሎቶችን እንዲያገኝ (Roaming) የሚችል መሆኑ ነው፡፡ ይህ ግዴታ ባለሥልጣኑ ከዚሀ ቀደም ባወጣው የብሔራዊ ሮሚንግ የጅምላ ሽያጭ መመርያ የተቀመጠ ሲሆን፣ የሚገቡ ኩባንዎች ‹‹የራሳቸውን የኔትወርክ መስመር ሳይዘረጉ መቆየት ስለሌለባቸው››፣ በ36 ወራት ጊዜ የተገደበ መሆኑን ባልቻ (ኢንጀነር) አስረድተዋል፡፡

ይሁንና ሮሚንግ በአዲሱ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያና ኢትዮ ቴሌኮም መካከል አለመከናወኑን ጠቅሰው፣ ‹‹አስገዳጅ በሆኑት መሠረተ ልማት መጋራትና ኢንተርኮኔክቲቪቲ ላይ ተስማምተው እየሠሩ ነው ያሉት፡፡ ሮሚንግ ላይ ሁለቱም ፍላጎት አላሳዩም፣ ስለዚህ አላስገደድናቸውም፤›› ብለዋል፡፡ 

ሦስተኛ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ለመሆን ጨረታውን የሚያሸንፈው ኩባንያ፣ በሳፋሪኮም ኢትዮጵያና በኢትዮ ቴሌኮም የአገልግሎት መስጫ መነሻ ቁጥር መካከል ያለው “08” መነሻ ቁጥር በመውሰድ አገልግሎት እንደሚጀምር ባልቻ (ኢንጂነር) ተናግረዋል፡፡

አክለውም፣ ‹‹የመጀመርያውን ጨረታ ስናወጣ በ07 እና 08 የሚጀምሩ ቁጥሮች ለጨረታ አሸናፊዎች ለመስጠት መድበን ነበር፤›› ሲሉ የቁጥር ምደባው ከመጀመርያ አንስቶ የተወሰነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የአገሪቱ የሕዝብ ብዛትና የቆዳ ስፋት “በማያሻማ ሁኔታ” እስከ አራት የቴሌኮም ኦፕሬተሮችን ማስተናገድ እንደሚችል ጠቁመው፣ ለዚህ የሚሆን የቁጥር ሀብት መኖሩን ገልጸዋል፡፡ ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ ያለውና አሥር ዲጂቶችን የያዘው የቁጥር አሰጣጥ ዕቅድ እስከ ቀጣይ 40 ዓመት ድረስ ማስጠቀም የሚችል መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ መሠረት እስከ 15 ቁጥር መጠቀም እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የቴሌኮም ዘርፉን ክፍት ለማድረግ ውሳኔ ላይ ከደረሰ በኋላ፣ ሁለት የቴሌኮም ፈቃዶችን ለመስጠት ጨረታ አውጥቶ 850 ሚሊዮን ዶላር ያቀረበው በኬንያው ሳፋሪኮም የተመራው ጥምረት ግንቦት 2013 ዓ.ም. የመጀመርያውን ፈቃድ መውሰዱ ይታወሳል፡፡ በጨረታው ላይ ተሳትፎ የነበረው ሌላኛው የቴሌኮም ኩባንያ የደቡብ አፍሪካው ኤምቲኤን ግሩፕ (MTN Group) ፈቃድ ለማግኘት 600 ሚሊዮን ዶላር አቅርቦ ነበር፡፡ በጊዜው በኤምቲኤን ግሩፕ ቀርቦ የነበረው ገንዘብ በሳፋሪኮም ከቀረበው አንፃር “ልዩነቱ ትንሽ ሰፋ” በማለቱ ሁለተኛው ፈቃድ ሳይሰጥ መቅረቱን ባልቻ (ኢንጂነር) ጠቅሰዋል፡፡

ባለሥልጣኑ መስከረም 2014 ዓ.ም. ሁለተኛ ፈቃድ ለመስጠት ጨረታ አውጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ በታኅሳስ ወር ሒደቱን ሰርዞታል፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ በድጋሚ እየተጀመረ ባለው የጨረታ ሒደት ሁለተኛውን ፈቃድ እ.ኤ.አ. በ2023 መጀመርያ ላይ ለመስጠት ታቅዷል፡፡

ባልቻ (ኢንጂነር) አሁን ሊወጣ በዝግጅት ላይ ባለው የጨረታ ሒደት ለፈቃድ የሚቀርበው ዋጋ ከጊዜውና ከመሬት ላይ ካለው የገበያ ዋጋ ጋር እንደሚያያዝ ጠቅሰው፣ አሁን ያለው ሁኔታ ባለፈው ዓመት ጨረታው በወጣበት ጊዜ ከነበረው የተሻለ አንደሆነ አንስተዋል፡፡

የመጀመርያው ፈቃድ ጨረታ በወጣበት ጊዜ የውጭ የቴሌኮም ኩባንያዎች የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎት ፈቃድ ማግኘት እንደማይችሉ መገጹን ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከብሔራዊ ክፍያ ሥርዓት አዋጅ እየተሻሻለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ‹‹የቴሌኮም ፈቃድ አገኙ ማለት የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎት ፈቃድ የማግኘት ዕድላቸው ከፍ ይላል ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ይህም የፈቃድ ጨረታ ሒደቱ በጥሩ ጎኑ የሚታይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ወደ ሥራ ከገባበት ሁኔታ በተለየ ቀጣዩ ኩባንያ ጨረታውን ሲያሸንፍ፣ የ5ጂ ኢንተርኔት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ፍሪኩዌንሲ ምደባ ከፈቃዱ ጋር ያገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም የ5ጂ ምደባ የሚደረገው ፈቃዱን ካገኙ በኋላ በሚያቀርቡት ጥያቄ እንደሆነ መገለጹን አስታውሰዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በ2014 ዓ.ም. የ5ጂ ፍሪኩዌንሲ ምደባ የተደረገለት በጊዜያዊነት ለአንድ ዓመት ያህል በሦስት ከተሞች ሙከራ ለማድረግ ሲሆን፣ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ደግሞ የ5ጂ ፍሪኩዌንሲ ምደባ ጥያቄ አቅርቦ በሒደት ላይ ነው፡፡ ባለሥልጣኑ ለሦስተኛው ኩባንያ የሚከተለው አካሄድ ከዚህ የተለየ መሆኑ፣ ለፈቃድ ጨረታው የሚቀርበው ዋጋን ከፍ ሊያደርግ የሚችል ሌላ ምክንያት እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች