የፋይናንስ የደኅንነት አገልግሎት ተቋም በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር የተሳተፉ ባለሥልጣናት፣ ኢንቨስተሮችና ግለሰቦችን የመለየት ሥራ እየተሠራ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ከሪፖርተር ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የተቋሙ የፋይናንስ ወንጀሎች ትንተና ኃላፊ አቶ ዮናስ ማሞ እንደተናገሩት፣ ሰሞኑን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ሲያንቀሳቅስ ተደርሶበታል ተብሎ በቁጥጥር ሥር የዋለው ተጠርጣሪ በሥሩ እጅግ በጣም በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ በአካውንቱ ዶላር ያስገቡለታል፡፡ እሱም በጥቁር ገበያ ክፍያ ይፈጽማል፡፡ ለጊዜው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ቢኖሩም፣ የመለየት ሥራ እየተሠራባቸው የሚገኙ ባለሥልጣናት፣ ኢንቨስተሮችና ግለሰቦችም መኖራቸውን አብራርተዋል፡፡
‹‹በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ተሳትፈዋል የተባሉ ግለሰቦች ኢንቨስተሮችንና የመንግሥት ባለሥልጣኖችን እየለየን ነው››
አቶ ዮናስ ማሞ፣ በፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት የፋይናንስ ወንጀሎች ትንተና ኃላፊ
የፋይናንስ ዘርፉ በኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሥጋቶች ያደረበት መሆኑ በተደጋጋሚ ይገለጻል፣ ለዚህም በማስረጃነት የሚቀርበው ሰርክ በተለያየ መገናኛ አውታሮች የሚቀርበው በፋይናንስ ወንጀል የተሰማሩ አካላት የረቀቀ ድርጊት ነው፡፡ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብና ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ፣ ሕገወጥ የሐዋላ ዝውውር፣ በፍራንኮ ቫሉታ ተጠቃሚነት የሚፈጸም ሕገወጥ ሥራ፣ የስፖርት ውርርድን ተገን ተደርጎ የሚደረግ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ በአገሪቱ ላይ እየፈጠሩት ያለው ቀውስ ግዝፈቱ ይጠቀሳል፡፡ ለመሆኑ እየተበራከተ ነው የሚባለው የፋይናንስ ወንጀል ለአገሪቱ ምን ያህል ፈተና ሆኗል? እንዴትና በምን መልኩ ነው የሚፈጸመው? ከድርጊቱ ጋር ተያይዞ በሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት የሚደረጉ ምርመራዎችና ወንጀለኞችን ለሕግ የማቅረብ ሒደት ምን ይመስላል? የሚለውንና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ኤልያስ ተገኝ በፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት የፋይናንስ ወንጀሎች ትንተና ኃላፊ ከሆኑት አቶ ዮናስ ማሞ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
ሪፖርተር፡– የፋይናንስ ወንጀሎች እየተበራከቱ መሆኑ ይነገራል፣ የዚህን የወንጀል ድርጊት ደረጃና በአገሪቱ ላይ የደቀነው ሥጋት ካለ ቢነግሩኝ?
አቶ ዮናስ፡- በዚህ ሰዓት በዚህች አገር ላይ እጅግ በጣም በርካታ የፋይናንስ ወንጀሎች እየተፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ እየተፈጸሙ ካሉ ወንጀሎች ውስጥ ቀዳሚው ሕገወጥ የሐዋላ ዝውውር ወንጀል ሲሆን፣ ሁለተኛው በሕገወጥ መንገድ የውጭ አገር ገንዘብ ማዘዋወር ነው፡፡ የተለያዩ አገር ገንዘቦች ዶላር፣ ፓውንድ፣ ዩሮ እንዲሁም የዓረብ አገሮች ገንዘብ ወደ ባንኮች መግባት ሲገባቸው በሕገወጥ መንገድ ወይም ከብሔራዊ ባንክ ዕውቅና ውጭ ወደ ባንክ ሥርዓቱ ሳይገቡ ኢኮኖሚው ውስጥ የሚዘዋወሩበት ሁኔታ በስፋት ይታያል፡፡ ሌላው ሙስና ሲሆን፣ እነዚህ ሦስቱ ወንጀሎች በከፍተኛ ሁኔታ አገሪቷን እየፈተኑ ናቸው። ለምሳሌ የእነዚህ ሁሉ ወንጀሎች ዋናውና አንዱ ምክንያት ሊሆን የሚችለው ሙስና ነው፡፡ ባንኮች ላይ የሚፈጸም የሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር አለ፣ ያ ደግሞ የሚሆነው ወደ ባንኮች የገቡትን ገንዘብ በትክክል ለተባለለት ዓላማ ወይም (ከውጭ ለገባ ዕቃ አስመጪዎች ጠይቀውና ፕሮሰሰ አድርገው ሕጋዊ ወደሆነ ነገር እንዳያደርጉ) እንዳይውል የሚደረግበት መንገድ አለ፡፡ በባንክ ያሉ ሁሉም ግለሰቦች ማለት ሳይሆን አንዳንዶች በሙስና ወይም ኮሚሽን በመቀበል ወደ ባንክ የገባው የውጭ አገር ገንዘብ ለተባለለት ዓላማ እንዳይውል ያደርጋሉ። ሌላው በተለያየ መንገድ የውጭ ምንዛሬ ወደ አገር እንዳይገባ የሚደረግበት መንገድ አለ፡፡ የእያንዳንዱ መንስዔ ቢለያይም ተሳታፊዎች ብዙ ናቸው፡፡ በሕገወጥ ሐዋላ ላይ ትልቁን ድርሻ የሚወስዱትና የመጀመሪዎቹ አስመጪዎች ናቸው፡፡ አገሪቱ ውስጥ ያለውን የዶላር እጥረት እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ውጭ አገር በሚሰብሰብ፣ በአገር ውስጥ ብሔራዊ ባንክ የሚያወጣውን የውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ ጭማሪ በማድረግ ወደ አገር ውስጥ ገንዘቡ ከሚላክ ወደ እነሱ የሚመጣበትን መንገድ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ገንዘቡን ሰብስበው ዕቃ ወደ አገር ውስጥ በማምጣት የጨመሩትን ጭማሪ የሚያካክሱት ማኅበረሰቡ ላይ ገንዘብ በመጨመር ነው፡፡ ያስመጡት ዕቃ ላይ እጥፍ ገንዘብ ይጨምራሉ፡፡ በዚህ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ላይ አስመጪዎች ትልቁን ሚና ይይዛሉ። ይህ ሲባል ግን ሕጋዊና ትክክለኛውን ቅድመ ሁኔታ የሚከተሉ አስመጪዎች እንዳሉም መታወቅ አለበት፡፡ ሕገወጥ አስመጪዎች ለሕጋዊዎቹ ፈተና የሆኑበት ሁኔታ የሚስተዋል ሲሆን፣ አንድ አስመጪ በርካታ የውጭ ምንዛሪ ከጠየቀ አገሪቱ ውስጥ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ስላለ በቶሎ አይሰጠውም፣ ስድስት ወር አንድ ዓመት እንዲጠብቅ በባንኮች ይገደዳል፡፡ እነዚህ ሰዎች ግን ሕጋዊ ቅደም ተከተሉን ለማሟላት ብቻ በጣም ትንሽ በሆነ ብር የባንክ ኤልሲ በመክፈት ስድስትና ሰባት ዙር የሚያመጡበት ሁኔታ አለ፡፡ በዚህ ምክንያት በሕጋዊ መንገድ የሚሄዱትን ነጋዴዎች ወደ እነሱ እንዲሄዱ ነው የሚያደርጓቸው፡፡
ሌላው የፍራንኮ ቫሉታ ተጠቃሚ የሆኑ ግለሰቦችም በተመሳሳይ፣ መጀመሪያ ሕጉ ሲወጣ እንደሚታወቀው የመሠረታዊ ፍላጎት የሆኑ ዕቃዎችን ወደ አገር ውስጥ ዶላር ያለው በውጭ አገር የሚኖር ግለሰብ ወደ አገር ውስጥ እንዲያስገባ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ የፍራንኮ ቫሉታ መብት የተሰጣቸው አካሎች ከውጭ አገር ገንዘቡን በማሰብሰብ በሕገወጥ ሐዋላ ዘይትና የመሳሰሉት ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ አድርገዋል፡፡ ስለዚህ ወደ አገር ውስጥ መግባት የነበረበት የውጭ ምንዛሪ በፍፁም አይገባም ማለት ነው፡፡ ይህም አንድ ተግዳሮት ነው፡፡ ለምሳሌ የዘይት ችግር ኢትዮጵያ ውስጥ ባይኖርም ዋጋው ግን አልቀነሰም፡፡ ምክንያቱም እዚያ ከፍ አድርገው የገዙበትን ዋጋ ጨምረው ለማኅበረሰቡ ስለሚያቀርቡ ነው፡፡ ያ ደግሞ በማኅበረሰቡ ላይ የኑሮ ወድነት ያመጣል፣ ይህም የአገሪቱን የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሁላ እንዲፈተን ያደርጋል፡፡ በሌላ በኩል በዚህ ጉዳይ የሚሳተፉት ውጭ አገር የሚገኙ ደላሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በተለያየ መንገድ ገንዘቡን በመሰብሰብ ይሳተፋሉ ፣ ከሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር የሚገናኝ እንቅስቃሴም ያደርጋሉ።
አገር ውስጥ ሆነው የሚያሠራጩ ግለሰቦች ሌላው ትልቁን ቦታ የሚወስዱ ናቸው። እኛም እነዚህ ላይ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ያለንበት ነው፡፡ ለምሳሌ ከውጭ አገር የመጣውን ወይም በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ለቤተሰቦቻቸው መላክ የነበረባቸውን (በዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ) ገንዘብ እዚያው በማስቀረት የአገር የዶላር ገቢና ክምችት እንዲቀንስ አድርገዋል፡፡ በውጭ አገር የተሰበሰበ ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው የሚሰሩ በርካታ ግለሰቦች አሉ፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ የውጭ አገር ዜጎች የሚሳተፉበት ነው፡፡ በኢንቨስትመንት ስም የመጡ አካሎች በዚህ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ስለሚሳተፉ፣ ስለዚህ የእኛ ተቋም እንደ መሥሪያ ቤት እያደረገ ያለው የመጀመሪያው ነገር እዚህ አገር ውስጥ ሆነው ገንዘቡን የሚበትኑ ሰዎች ላይ ዕርምጃ መውሰድ ነው፡፡ ዕርምጃው እነሱ ላይ ብቻ ሳይሆን ከእነሱ በስተጀርባ ሆነው የገንዘቡ ምንጭ የሆኑትን የአገር ውስጥም ባላሀብቶች ጭምር ላይ ነው፡፡ ብዙኃን ኢትዮጵያኖች ዕቃ ለማስመጣት ፍጆታ ሲጠቀሙት፣ የውጭ አገር ዜጎች ደግሞ ገንዘብን ከአገር ለማሸሽ (ካፒታል ፍላየት) የሚጠቀሙበት ነው፡፡ የውጭ አገር ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ መጥተው ኢንቨስት በሚያደርጉበት ሰዓት የሚያገኙትን የኢትዮጵያ ብር ዶላሩን በሕገወጥ መንገድ በውጭ አገር ሰብስበው ያስቀሩትና እዚህ በምትኩ ግን ካመረቱት ምርት የሚሸጠውን ኢትዮጵያ ውስጥ ይላክልን ላሉ ሰዎች ወይም የቤተሰብ አባላት የግለሰቦች አካውንትን በመጠቀም ይበትኑታል፡፡ በዚህ የሚሳተፉት በኢንቨስትመንት ስም የተሰማሩ የወጭ አገር ዜጎች ናቸው፡፡ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት አንደኛ የገንዘቡ ምንጭ የሆነው ግለሰብ የውጭ አገር ዜጋ፣ ኢትዮጵያዊ የሆነ አስመጪ፣ አስተማሪ በሆነ መንገድ ጥናቶችን በማካሄድ ዕርምጃ እንዲወሰድ እያደረገ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ በዚህ ድርጊት (በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ በሐዋላም ሆነ በዶላር) ላይ ተሳትፈዋል የሚባሉ የአቋማሪ ድርጅቶች፣ አስመጪዎች፣ የውጭ አገር ኢንቨስተሮች፣ ደላሎች ጭምር ዕርምጃ እያስወሰድን ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋር እየሰራን ነው የምንገኘው፡፡
ሪፖርተር፡– እንደዚህ ዓይነት ወንጀሎች ከዕለት ወደ ዕለት እንዲባባስ የሚያደርጉት ምክንያቶች ምንድናቸው? የቁጥጥር ሥርዓት መላላት ነው? ወንጀሉን በሚፈጽሙ አካላት ላይ አስተማሪና ጠንካራ ዕርምጃ አለመወሰዱ ነው? ወይስ ሌላ?
አቶ ዮናስ፡- አንደኛ በአገሪቱ ውስጥ ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያመጣው ነገር አለ፡፡ ሁለተኛ የሕገ አስከባሪውና በየደረጃው የሚገኝ አካል የቅንጅት ችግር፣ አጥፊዎች ላይ የሚወሰድ ዕርምጃ አስተማሪ አለመሆን እንደ ክፍተት የሚታዩ ናቸው፡፡ ብሔራዊ መታወቂያ አለመኖር ዋነኛው ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም አብዛኛው ገንዘብ የሚንቀሳቀሰው ሐሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም ነው፡፡ ባንኮች የተለያዩ አሠራሮችን እየዘረጉ ቢሆንም፣ ውጤቱ ያን ያህል አመርቂ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ሌላው የሚወጡ ሕጎች በራሱ ለዚህ ሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር ክፍተት አላቸው፡፡ ለምሳሌ የዳያስፖራ አካውንት ሲታይ ራሱን የቻለ ጥቅምና ጥሩ ጎኖች ቢኖሩትም ግለሰቦች ያንን ሕግ ለሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ዕሳቤው ግለሰቦች በዶላር አካውንታቸው ውስጥ ገንዘብ ማስቀመጥ እንዲችሉ ነው፡፡ አሁን ግን እየተደረገ ያለው ግለሰቦች ውጭ አገር ባልሄዱበት ሁኔታ ከጥቁር ገበያ ዶላር በመግዛት ወደ ዶላር አካውንታቸው የሚያስገቡበት ሁኔታ በተቋማችን ተረጋግጦ ከፍተኛ የሆነ ሥራ እየሠራን እንገኛለን፡፡ በሌላ በኩል ግለሰቦች ውጭ አገር ሄደው ሲመጡና በጉምሩክ ሲያፀድቁ፣ ይዘውት የመጡት አንድ ሺሕ ዶላር ከሆነ የዲክለራሲዮኑን ሙሉ ቁጥር በመጠቀምና ሰነዱን ተጠቅመው ሌላ ሐሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት 200 ሺሕ ዶላር ነው ይዘን የመጣነው በማለት ቀሪውን ከጥቁር ገበያ በመሰብሰብ ወደ ዶላር አካውንታቸው የሚያስገቡ በርካታ ግለሰቦች አሉ፡፡ ስለዚህ የሚወጡ ሕጎች ላይ ራሱ ያሉትን ክፍተቶች በመጠቀም የሚፈጸም የጥቁር ገበያ መንስዔ አለ፡፡ ይህ ወንጀል የሚፈጸመው በሰንሰለት ነው፡፡ ውጭ አገር የሚሰበስብ አለ፣ አስመጪዎች አሉ፣ እዚህ የሚበትን አለ፣ ከእነሱ ጀርባ ሆኖ ገንዘብ የሚያስገባ አለ፡፡ ይህ ሁላ ሲሆን አብዛኛው ምርመራችን ከፊት ለፊት ያሉ ግለሰቦች ላይ ብቻ ትኩረት ማድረጉ አንድ መንስዔ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ከጀርባ ያሉት ግለሰቦች ራሳቸውን ደብቀው ስለሚሠሩ፣ በውጭ አገርም የሚኖሩ ስላሉ አንድ ግለሰብ ዛሬ ቢታሰር ሌላው ነገ ከሌላ ጋር ይሠራል፡፡ ባለድርሻ አካላት በሚባለው ልክ በጥምረት አለመሥራት ሌላው እንደ ምክንያት ሊወሰድ ይችላል፡፡ አሁን ላይ በተለይ ከብሔራዊ መረጃ ደኅንነት፣ ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች፣ ፍትሕ ሚኒስቴር፣ ብሔራዊ ባንክ እንዲሁም የእኛ ተቋም በጋራ እየሠሩ ነው፡፡ ነገር ግን ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ንረቱ ከመጨመሩ በፊት ሁሉም ተቋማት የየራሱን ስለሚሠራ ጥምረቱ ብዙም የጠነከረ አልነበረም፡፡ በአጠቃላይ ለሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውሩ በከፍተኛ ደረጃ መጨመር መንስዔ ከሆኑት አንዱ የሕግ ክፍተቶች፣ ሁለተኛ ብሔራዊ መታወቂያ አለመኖሩ ሲሆን፣ ሦስተኛው ባለድርሻ አካላት በጋራ በሚፈለገው ልክ ተቀናጅቶ አለመስራት ሲሆን፣ በተጨማሪም ወንጀሉን ለመመርመር ጠንካራ ሥርዓት አለመኖሩ ራሱን የቻለ ተግዳሮት ነው ማለት ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡– የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በቅርቡ የስፖርት ጨዋታ ውርርድ (ቤቲንግ) በሚሠሩ አካላት ላይ ዕርምጃ መውሰዱ ይታወሳል፡፡ ምን ዓይነት ወንጀሎች ናቸው በእነዚህ ተቋማት የተፈጸመው?
አቶ ዮናስ፡- የቤቲንግ ድርጅቶች በዚህ ወንጀል (በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር) ላይ ከሚሳተፉት የተለየ ነገር የለውም፡፡ በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ላይ ወይም ዶላር ገዝቶ ከአገር ማሸሽ ላይ ወይም ቅድም እንደተገለጸው በኢትዮጵያ ብር የሚያገኙትን ገንዘብ በአገር ወስጥ ለሚገኝ የላኪዎች ተወካይ በማስተላለፍ የተሰበሰበው የውጭ ምንዛሪ እዚያው እንዲቀር ያደርጋሉ፡፡ አብዛኞቹ የቤቲንግ ካምፓኒዎች መሠረታቸው (ኦሪጅናቸው) ኢትዮጵያ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ቅርንጫፍ አላቸው እንጂ ከውጭ አገር ጋር የሚገናኙ ናቸው። በስፖርት ውርርዱ (ቁማር) በርካታ ገንዘብ ይመነጫል፡፡ ስለዚህ እነዚያ ግለሰቦች በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ላይ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ አካሎች ናቸው፡፡ በሕገ ሒደት ላይ ያለ ጉዳይ እንደመሆኑ ይህን ይህን አድርገዋል ለማለት ጊዜው አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡– በሕገወጥ መንገድ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ ሲያንቀሳቅስ የነበረ ግለሰብ ከሰሞኑ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ብዙዎችን ሲያነጋግር የነበረ ክስተት ነው፡፡ ምርመራው በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ዮናስ፡- የፍተሻና ትንተናው ተሠርቶ ለፌዴራል ፖሊስ የተላለፈው በእኛ ተቋም ተለይቶ ነው፡፡ በሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር የሚሳተፉ ግለሰቦች እንለያለን፡፡ ተቋማችን ታች ከሚበትነው ግለሰብ ጀምሮ ኔትወርኩን በማጥናት ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ አገር ድረስ ያጠናል፡፡ ሳሚ ዶላር ተብሎ በቅፅል ስም የሚጠራው ይህ ግለሰብ በሥሩ እጅግ በጣም በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ ወደ አካውንቱ የሚያስገቡ ግለሰቦች፣ እሱ ደግሞ ወደ አካውንቱ የገባውን ገንዘብ በጥቁር ገበያ ዶላር በመግዛት በሕገወጥ የውጭ አገር ዝውውር ላይ ተሰማርቷል ተብሎ ነው የተጠረጠረው፡፡ ዋና ወንጀል ፈጻሚውን ጨምሮ ከእሱ በላይ ያሉ ግብረ አበሮች ከሥሩ ሆነው ከ20 በላይ ግለሰቦች (ወደ እሱ አካውንት ገንዘብ ሲያስገቡና አብረው በጋራ ሲሠሩ የነበሩ) ታስረው ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው፡፡ ለምንሠራው ሥራ አንዱ ይኼ ምሳሌ ነው፡፡ ተያያዥነት ያላቸው ሌሎች ግለሰቦች፣ ድርጅቶች፣ አስመጪዎች፣ ኢንቨስተሮች፣ የመንግሥት ባለሥልጣኖች፣ በዚህ ድርጊት ተሳትፈዋል የሚባሉትን ሁሉ እየለየን እየሠራን ነው፡፡ ቀኑ ሲደርስ ሌሎቹንም ይፋ እናደርጋለን፡፡
ሪፖርተር፡– በተመሳሳይ ባለፈው ወር 665 የባንክ ሒሳቦች እንዳይንቀሳቀሱ አግዳችሁ ነበር፡፡ ይህን ያደረጋችሁት ከምን ወንጀል ጋር በተያያዘ ነበር?
አቶ ዮናስ፡- እሱ ብቻ አይደለም በተደጋጋሚ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ድርጊቱ ከወንጀል ጋር የተገናኘ ነው ብሎ ሲያስብና ያ ገንዘብ መውጣት የለበትም ብሎ በሚያምን ሰዓት ወደ ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ ከመድረሱ በፊት ገንዘቡ ቢወጣ ችግር አለው ሊሸሽ ይችላል፣ ገንዘቡ ወጥቶ ለሽብር ዓላማ ሊውል ይችላል ብሎ ካሳበ የባንክ አገልግሎቱን ያቋርጣል፡፡ አገልግሎቱ ይኼ ሥልጠን አለው፡፡ በርካታ አካውንቶች ለሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ዓላማ ሊውል ነው ብለን ካሰብንና ለዚያ የሚያበቃ ምክንያት ካለን በተጨማሪ ሽብርተኝትን በገንዘብ ለመርዳት ሊውል ይችላል ብለን ካሰብን በየጊዜው ያገድናቸው በርካታ አካውንቶች አሉ፡፡ ከ600 ውጪ 391 እንዲሁም በተለያየ ጊዜና በየቀኑ የሚታገዱ አሉ፡፡ ይህን የምናደርገው ከወንጀል ጋር ግንኙነት አላቸው ብለን የምናስባቸውን ድርጅቶች፣ ግለሰቦች አካውንት እናግዳለን፣ ከዚያ ትንተና እየሠራን በምን ጉዳይ እንዳገድን፣ የእነ ሳሚ ዶላር ጭምር ከእነሱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች አካውንት አግደን አስፈላጊውን የትንተና ሥራ ሠርተን ወደ ፖሊስ አስተላልፈናል፡፡ በተመሳሳይ ሁሉም ሰው በዚያ ውስጥ ተሳትፎ አድርጓል ብለን ስናስብ አካውንቱን ዘግተን ትንተና ሠርተንም፣ ማስረጃዎችን አጠናቅረን ለሚመለከተው አካል እንልካለን፡፡ ግለሰቡ በወንጀል ግንኙነት አለው ብሎ ከታሰበና በምርመራ ከተረጋገጠ ገንዘቡ የሚወረስበት ሁኔታ አለ፡፡ በምርመራ ሒደት ግለሰቡ ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት ከሌለው ደግሞ ገንዘቡ የሚለቀቅበት አሠራር ነው ያለው፡፡
ሪፖርተር፡– በወንጀል የሚገኝ ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ከሚቀርብባቸው ነገሮች ውስጥ በተደጋጋሚ እንደሚገለጸውም፣ በኢንቨስትመንት ስም የሚደረጉ የሪል ስቴት ግንባታዎች ይገኙበታል፡፡ በዚህ ዙሪያ በምርመራችሁ ያገኛችሁት ነገር ካላ ቢያስረዱን?
አቶ ዮናስ፡- እውነት ለመናገር የሪልስቴቱን ኢንቨስትመንት ሕጋዊ መንገድ ተከትለው የሚሠሩ ድርጅቶች አሉ፡፡ ግን ደግሞ ከዚህ ውጭ የሚሳተፉ እጅግ በጣም በርካታ ድርጅቶች አሉ፡፡ ምክንያቱም በሙስና የተገኘ፣ በሕገወጥ ሐዋላ የተገኘ፣ በማጭበርበር ወይ ደግሞ በታክስ የተገኘ ገንዘብ ሊቀየር የሚችለው የመጀመሪያው ውድ የሆነ ንብረቶችን መግዛት ነው፡፡ በሙስና የተገኘ ገንዘብ በእጅ ላይ ማስቀመጥ አደጋ እንደሆነ ስለሚያውቁ የመጀመሪያ የሚያደርጉት ወርቅና የመሳሰሉ ውድ የሆኑ ንብረቶችን መግዛት ነው፡፡ ሁለተኛው ኢንቨስትምንት ላይ መሳተፍ ነው፡፡ በቤተሰቦቻቸው፣ በቅርብ ሰው፣ ታማኝና ገንዘባችንን ያንቀሳቅሳል ብለው በሚያስቧቸው ሰዎች በበርካታ ኢንቨስትመንት፣ በሪልስቴት ሊሆን ይችላል ይሳተፋሉ፡፡ ሦስተኛው ሼሮችን መግዛት ነው፡፡ አሁን በርካታ ሼር የሚሸጥባቸው የፋይናንስ፣ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ሌሎችም በዝተዋል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ግለሰቦች በቤተሰቦቻቸውና እነሱ በሚያምኑት ሰው ሼሮችን ይገዛሉ፡፡ ሰለዚህ እኛ ውድ ንብረት የሚሸጥባቸው ቦታዎች፣ የኢንቨስትመንት አካባቢዎች የትኩረት አካባቢዎቻችን ናቸው፡፡ በብዙ ሚሊዮን የሚሸጡ ቅንጡ አፓርትመንቶች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ የኑሮ ደረጃ እነዚያን ማን ነው የሚገዛው? ተብሎ ቢታሰብ ሁለተና ሦስት ከፍ ብሎ ሲታይ፣ በዚህ በሙስና ወይም በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ወይም ደግሞ በታክስ ማጭበርብር ላይ በወንጀል የሚሳተፉ ግለሰቦች ከጀርባ ሆነው የሚፈጽመት ግብይት ነው፡፡ ሌላው ቁማርና ውርርድም ከዚህ ጋር ይገናኛል፡፡
ሌላው ትላልቅ ግንባታዎችን ማከናወን ነው፣ አዲስ አበባ ትልቅ ከተማ ነች በርካታ ግንባታዎች በዚህ ወቅት እየተገነቡ ነው፡፡ ከእያንዳንዱ ፉክክር በስተጀርባ የሕንፃው ባለቤት ተብሎ የሚታወሰው ሰው ነው ወይ ያለው? ተብሎ ቢታሰብ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ወይ በአንድ ድርጅት ስም ነው ያለው፡፡ የደርጅቶቹን ባለቤት ሄደህ ስታየው ከተለያዩ ወንጀሎች ጋር የሚገናኙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ትላልቅ ግንባታዎች ላይ መሳተፍ አለ፡፡ በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስለው የሚጠቀሙበት ነው፡፡ በተጨማሪም ዋናው ከአገር ገንዘቡ እንዲወጣ ማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያን በሚያዋስኑት አምስቱ አቅጣጫ ድንበሮች ገንዘቡ በዶላር ተሰብስቦ ከአገር እንዲወጣ ይደረግና ከሌላ አገር ገንዘቡ እንዲገባ ይደረጋል፡፡ ይህ ማለት ሕጋዊ ሰነድ ይዘው ይቀርባሉ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ በሞያሌ በኩል ወደ ኬንያ በብላክ ማርኬት እዚህ አሰብስበው ቢያስወጡና ኬንያ ቀደም አድርገው የላኩት ቤተሰብ ቢኖር፣ በእሱ አማካይነት እንዲላክ ቢደረግ ሕጋዊ ሰነድ ይዘው ይቀርባሉ ማለት ነው፡፡ ቤት፣ ሕንፃ ይሠራሉ ከየት አመጣችሁት ቢባሉ አንኳን ‹‹ኬንያ ያለው ቤተሰቤ›› በዚህ ቀን ልኮልኝ ነው ለማለት ይጠቀሙበታል፡፡ እንደተናገርኩት ከላይ በተጠቀሱት ቦታዎች ሁሉ አገልግሎት መሥሪያ ቤታችን እንፈትሻለን (ትሬስ እናደርጋለን)፣ ሼሮች ላይ እነማን ነው እየተሳተፉ ያሉት?፣ ሪልስቴት ግዥው ላይ እነማን ናቸው እያደረጉ ያሉት? ኢንቨስትመንቱ ላይ እነማን ናቸው ያሉት? ከትላልቅ ኮንስትራክሽን ጀርባ እነማን ናቸው ያሉት? እያንዳንዱ ትራንዛክሽን መጨረሻ ላይ ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ አገር ያለው ኔትወርክ ምን ይመስላል? የሚለውን ዝርዝር ጥናት ሠርተን ለሚመለከተው የሕግ አስፈጻሚ አካል እናስተላልፋለን፡፡
ሪፖርተር፡– ምን ያህል መዝገቦች ላይ ምርመራ አድርጋችኋል? ዕርምጃስ የተወሰደባቸውስ አሉ?
አቶ ዮናስ፡- የእኛ አገር የፋይናንስ ደኅንነት አወቃቀር አስተዳደራዊ ነው፡፡ ይህ ቅርፅ ሲኖር ሊደረግ የሚችለው ሥራ መረጃ ሰብስቦ የኢንተለጀንስ ሥራ ከሠራን በኋላ ለሚመለከተው የሕግ አስከባሪ አካል መላክ ወይም ማሠራጨት ነው፡፡ ስለዚህ እኛ ሠርተን ለፖሊስ የላክናቸውን ሒደታቸውን በጋራ እንገመግማለን፣ የሚያስቸግሩ የአሠራር ችግሮች ካሉ እነሱን ለመፍታት እንሞክራለን፣ ተጨማሪ ማሰረጃ የሚያስፈልጋቸው ካሉ ተጨማሪ እንሰጣለን፡፡ በየጊዜው ስለሚሄድ በዚህ ወቅት ምን ያህል መዝገብ ነው ያለው የሚለውን በትክክል መናገር ያዳግታል (እያወራንበት ባለው ቅፅበት ሁላ ከባንኮች፣ በስልክ እንዲሁም ከበርካታ አቅጣጫ የሚመጣ ጥቆማ አለ)፡፡ ዓምና ግን ከህገወጥ የገንዘብ ዝወውርና ወደ ተቋሙ ከመጡ የወንጀል ጥቆማዎች ጋር ተያይዞ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለማዳን ተችሏል፡፡
ሪፖርተር፡– ከአዲስ አበባ አንስቶ እስከ ድንበር መውጫ በሮችና አልፎም ውጭ አገር ባሉ ግለሰቦች የሚፈጸሙት የፋይናንስ ወንጀሎች የተራቀቁ መሆናቸው ይታወቃል፣ በዚያው ልክ አገሪቱ ጉዳዩን የምትከታተልበት የምርመራ አቅም በዚያው ልክ አድጓል ወይ? ያለንበት ደረጃ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ዮናስ፡- ወንጀለኛ በየቀኑ አዳዲስ ነገር ክፍተት እየፈጠረ ወንጀል ይፈጽማል፡፡ እንደ ፋይናንስ ደኅንነት ጊዜውን የሚመጥን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ተቋማችን በማስመጣት የትንተና መንገዶችን (አናሊስስ ቱሎችን)፣ ሶፍትዌሮችን በማምጣት፡፡ እንደሚታወቀው ባንኮች በዚህ ሰዓት በዝተዋል፣ ሥራ የጀመሩ ባንኮች በጣም በርካታ ናቸው፡፡ ስለዚህ የፋይናንስ ሥርዓታችን፣ የትራንዛክሽን መጠኑ እየጨመረ ነው የመጣው፡፡ ያንን መሸከም የሚችል የሕግ አስከባሪ (ሎው ኢንፎርስመንት)፣ የደኅንነት ተቋም፣ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረነዋል ባይባልም እውነት ለመናገር እጅግ በጣም ብዙ ለውጦች አሉ፡፡ ግን ደግሞ የሚቀሩ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ወንጀሉ ውጭ አገር ድረስ መሠረት የዘረጋ ስለሆነ ከባድ ያደርገዋል፡፡ ኔትወርኩ በጣም ጠንካራ ነው፡፡ በተጨማሪም በገንዘብ አቅማቸው በጣም ክፍ ያሉ ሰዎች የሚሳተፉበት ነው፡፡ ያም ብቻ ሳይሆን እነሱን በምክር የሚደግፉ የተለያዩ ተቋማት ሠራተኞች አሉ፡፡ እያንዳንዱ ሕግ ሲወጣ ክፍተቱን የመጠቀም ዝንባሌ አለ፡፡ ቅድም ከዳያስፖራ አካውንት ጋር ተያይዞ እንደተነሳው ማለት ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ዝም ብሎ የሚመጣ አይደለም የወንጀል አማካሪ (አድቫይዘር) አላቸው፡፡ ለምሳሌ ባንክ ላይ እያንዳንዱ የምትወጣን ሕግ በምን ዓይነት መንገድ ነው የምንቀለብሰው (ካውንተር) በሚል የሚያማማክሯቸው ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ባንክ ላይ፣ በሕግ አስፈጻሚ (አስከባሪ) አካባቢ የሚያስቀምጧቸው በዚህ ሕገወጥ ዓላማ ላይ የተሳተፉ አንዳንድ ግለሰቦች አይጠፉም፡፡ ስለዚህ ያንን ተገን በማድረግ ነው ይህንን ወንጀል የሚያባብሱት፡፡ እንደኛ ተቋም አንዱ ጥሩ ነገር ምንድነው ከሌሎች 164 አገሮች ላይ ካሉ መሰል የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ተቋሞች ጋር መረጃ እንሰበስባለን፡፡ ያ እንደ አገር ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡ ምክንያቱም ውጭ አገር ገንዘብ የሚያሸሹ ባለሥልጣኖች ገንዘቡን ለማሸሽ የግዴታ የሚጠቀሙት ሕገወጥ ሐዋላን ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ግለሰብ እዚህ አገር በሙስና ገንዘብ ከሰበሰበ በኢትዮጵያ ብር ምንም ሊያደርገው አይችልም ውጭ አገር ማስወጣትና ፎቅ መገንባት ካለበት ሊያደርግ የሚችለው በሙስና የተቀበለውን ገንዘብ ኢትዮጵያ ውስጥ መበተንና በዚያው እኩሌታ የሆነ ገንዘብ በውጭ አገር ማሰብሰብ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ በተባለው አገር መኖሪያ ቤት፣ አክሲዮን (ሼር) ሊገዛ ይችላል፡፡ በምትኩ ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ዓይነት ገንዘብ ባልገባ መንገድ ባለሥልጣኖች ጭምር እየበተኑ ነው፡፡ ገንዘብ ሊያሸሹ የሚችሉበት መንገድ እሱ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እንደ ተቋም ይህን መረጃ የማግኘት ዕድል (አክሰስ) ስላለን በከፍተኛ ሁኔታ እየሠራንበት ነው፡፡ የትኞቹ ኢትዮጵያውን ናቸው? በዚህ ድርጊት የተሰማሩት፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት አሉበት ወይስ የሉበትም? የውጭ ኢንቨስትሮች በዚህ ልክ እየተሳተፉበት ነው ወይ? የሚሉትንና ሌሎችንም እየሠራን ስለሆነ እሱም እንደ መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ ከዚያ ባለፈ ለማዘመን ሒደት አለ፡፡ ወንጀሉ ከመፈጸሙ በፊት ግንዛቤ ለመስጠት፡፡ ነገር ግን ወንጀሉ እንደተፈጸመ ስናውቅ ሌላ የማስተካከያ ሕጎችን ለማድረግ ይሞከራል፡፡
ሪፖርተር፡– ለፋይናንስ ወንጀሎች መስፋፋት በተቋማት መካከል ያለው የቅንጅት ችግር ብቻ ሳይሆን፣ በተቋማት ውስጥ ከአመራር ጀምሮ እስከ ታች መዋቅር የሚገኙ የተለያዩ ግለሰቦች የወንጀለኞቹ ተባባሪ ሆነው መገኘታቸው ነው ይባላል፡፡ ባደረጋችሁት ወይም በምታደርጉት ምርመራ ላይ ፋይናንስ ዘርፉን መሠረት አድርገው የሚሠሩ ተቋማት ላይ ያገኛችሁትን ነገር ቢገልጹልን?
አቶ ዮናስ፡- የፋይናንስ ዘርፉ ይበልጥ የሚጎዳውም፣ ከፍተኛ ተሳትፎ የሚያደርገውም እንዲሁም የገንዘቡ መነሻ ባንኮች ናቸው፡፡ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ላይ በተለይም ወደ ባንኮች አካባቢ ሙያቸውን አክብረው የሚሠሩ እንዳሉ ከግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል፡፡ ባንኮች ላይ በእንደዚህ ዓይነት ሕገወጥ ሥራ ላይ የሚሳተፉ እንዳሉ ታውቆ ለምሳሌ ዶላር አፈቃቀድ ላይ በኮሚሽን የሚሠሩ ግለሰቦች ተገኝተው ዕርምጃ የተወሰደባቸው፣ በእኛ ተቋም ክትትል የተደረገባቸው ግለሰቦች አሉ፡፡ ድንበር አካባቢ የሚገኙ የባንክ ቅርንጫፎች ውስጥ የሚሠሩ አንዳንድ ግለሰቦች የሕገወጥ የዶላር ዝውውሩ ላይ ተሳታፊ ሆነው ትንታኔ ተሠርቶባቸው ለፖሊስ ምርመራ የተደረገባቸው ግለሰቦችም አሉ፡፡ ግለሰቦቹ አንደኛ የባንኩን አሠራር በማየት ለወንጀለኞቹ ምክር ይሰጧቸዋል፡፡ በተጨማሪም ገንዘቡን እነሱ ተቀብለው ለዶላር መግዣ የሚሆነውን ወደ መሀል አዲስ አበባ እስከ መላክ ጭምር ማለት ነው፡፡ የባንክ ቤት ሠራተኛ ሆነው በመቶ ሚሊዮኖች ወደ መሀል አገር ገንዘብ እንዲተላላፍ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ለእኛ ጥቆማውን የሚሰጡን ባንኮች ስለሆኑ ያንን ሪፖርት አለማድረግ፣ ለእነሱ ከለላ መስጠት ጭምር የፈጸሙ ግለሰቦች እንዳሉ ተለይቶ ዕርምጃ የተወሰደባቸው አሉ፣ ሕግ አስከባሪዎች (ሎው ኢንፎርስመንት) አካባቢ በዚህ ሁኔታ ላይ ተሳትፍዋል የሚባሉና የሚጠረጠሩ ግለሰቦች በተለያየ ጊዜ ዕርምጃ እየተወሰደ ነው የሚገኘው፡፡
ሪፖርተር፡– የትኞቹ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ወይም ተቋማት ላይ ዕርምጃ ተወስዷል?
አቶ ዮናስ፡- አሁን ስለ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር እያወራን ስለሆነ ነው፡፡ በሙስና በተለያየ መንገድ አንደ ፋይናንስ አገልግሎት ተቋም፣ ለምሳሌ ከመሬት ጋር በተያያዘ የሠራነው በርካታ ሥራ አለ፡፡ ከሕገወጥ የመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ በክፍለ ከተሞች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች በሙስና ተጠርጥረው በሚዲያ እንደሚሰማው በርካታ አመራሮች ሁላ የታሰሩበት ሁኔታ አለ፡፡ እነዚህ ግለሰቦ ብቻቸውን አይደለም ተሳትፎ ያደረጉት (መሬቱን የወረሩት) እዚያ ውስጥ ባለ ሠራተኛ ታግዘው ነው፡፡ በዚያም ዕርምጃ የተወሰደባቸው ሠራተኞች አሉ፡፡ ሌሎችም በመገናኛ ብዙኃን የምንሰማቸው ይኖራሉ፡፡
ሪፖርተር፡– ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታላዜሽ የምታደርገው እንቅስቃሴ ከዕለት ወደ ዕለት ለውጦች የሚታዩበት ነው፡፡ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር ከተጀመረ ዓመት አልፎታል፣ የውጭ ቴሌኮም ኩባንያ ገብቷል፣ በቀጣይ ደግሞ የፋይናንስ ዘርፉ ሊበራላይዝ ሊደረግ በዋዜማው ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህ ነገሮች ሥጋትነታቸው እንዴት ይገለጻል?
አቶ ዮናስ፡- እያንዳንዱ ቴክኖሎጂ የራሱ የሆነ ጉዳት (ድሮባክ) አለው፡፡ የዲጂታል ኢኮኖሚ ሲገነባ የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን የሚቀንስ፣ ሰዎች ስልካቸውን፣ የወረቀት ገንዘብ በሌለበት ሁኔታ ግብይት መፈጸም የሚችል አሠራር ነው፡፡ ያንን ለመጥፎ ነገር የሚጠቀሙበት እጅግ በጣም በርካታ ናቸው፡፡ ስለዚህ ሕጎቹ ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት ጠንካራ አሠራር መዘርጋት እንዳለበት እኔ በግሌ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም ለምሳሌ ሞባይል ባንኪንግን ለሕገወጥ የሐዋላ ዝውውር ትልቁን ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ ከቴሌ ምዝገባ ውጭ ያሉ ስልኮች ለወንጀል መፈጸሚያ እየዋሉ ነው ያሉት፡፡ ምክንያቱም በስም የተፈጸምን ስልክ ለሕገወጥ ዓላማ መጠቀም ስለማይቻል ሌሎችን በገንዘብ በመደለል ለሕገወጥ ዓላማ ያልተመዘገቡ የሲም ካርዶችን የሚጠቀሙ አሉ፡፡ ሐሰተኛ መታወቂያ በመጠቀም አካውንት ይከፈታል፣ ከዚያ በኋላ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ገቢ ይደርግበታል፡፡ አንድ ግለሰብ ቤቱ ቁጭ ብሎ በሞባይል ባንኪንግ ሕገወጥ ሐዋላ በቀን ለበርካታ ሰዎች ባልተመዘገቡት ስልኮች ያስተላልፋል፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን ሞባይል ባንኪንጉን፣ አካውንቱን የከፈተን አንድ ሰው የሞባይልና ኢንተርኔት ባንኪንግ ኮድ ጭምር ለሌላ ሰው ሰጥተው የተሰጠው ሰው ከአገር ወጥቶ ገንዘቡን በሄደበት አገር የሚያሰባስብ ሲሆን፣ አገር ውስጥ ሆነው በዚህ በማሠራጨት ሥራ ላይ የተሰማሩ እጅግ በጣም በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ እነሱን እንከታተላለን (ትሬስ እደረግን) ዕርምጃ የተወሰደባቸው አካሎች አሉ፡፡ ስለዚህ ዲጂታል ቴክኖሎጂው ራሱን የቻለ ጠንካራ ጎን ቢኖረውም፣ በጣም ግን ጥንቃቄ የሚፈለግና ከሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር አንፃር መቃኘት አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ መጀመሪያ ሕጉ ራሱ ሲወጣ እያንዳንዱ ፕሮዳክት ሲተዋወቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ፕሮዳክቶቹ ከመኒ ላውንደሪንግ፣ ሽብርተኝነትን በገንዘብ ከመደገፍ ወንጀል ጋር እንዲሁም ፋይናንስ ወንጀሎችን ከማባባስ አንፃር በደንብ ታይተውና ተገምግመው፣ እነዚያ ክፍተቶች ተሞልተው ቢወጣ የተሻለ ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡– በዚህ ወቅት እየሠራችኋቸው ስላሉ የምርመራ ሥራዎች ቢገልጹልን?
አቶ ዮናስ፡- በጣም በርካታ ባለድርሻ አካላት በጋራ እየሠራን ነው የምንገኘው፡፡ ለምሳሌ ይህንን የሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር አገር ላይ ከሚያመጣው ጉዳት አንፃር እሱን ለመፍታት ከብሔራዊ ባንክ፣ ብሔራዊ መረጃ አገልግሎት፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ኢንሳ፣ የእኛ ተቋም፣ ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግ፣ አዲሰ አበባ ፖሊስ፣ ክልሎችም ጭምር በጋራ ሆነን ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በጋራ ሥራዎች እየተገመገሙ እየተሠራ ነው፡፡ ባንኮችም ጭምር እስከዛሬ ከሚሠሩት በተለየ መንገድ ትኩረት ሰጥተው መረጃ በመስጠቱ፣ ሌሎች ሥራዎችን በጋራ እየሠራን ነው የምንገኘው፡፡ እኛም ከዚህ በፊት ስንሠራ ከነበረው በተለየ መንገድ ለዚህ ተብሎ የተለየ ቡድን በማቋቋም በከፍተኛ ሁኔታ እየተሠራ ነው፡፡
ሪፖርተር፡– ፍራንኮ ቫሉታን ጨምሮ ለፋይናንስ ወንጀሎች መንስዔ የሆኑ ጉዳዮች ተነስተዋል፣ ይህንን ለማስተካካል መደረግ ይገባል የምትሏቸው ምክረ ሐሳቦች ምንድናቸው?
አቶ ዮናስ፡- እኛ አንደ ተቋም ከምናቀርባቸው ምክረ ሐሳቦች አንደኛው በሕጎች ዙሪ ያሉ ክፍተቶች ጊዜ ስለሚወሰዱ በቅርብ ጊዜ ባይሆንም ታይተውና ተገምግመው ከፍተት ያለባቸው ሕጎች መስተካከል መቻል አለባቸው፡፡ የዳያስፖራ አካውንት ሊሆን ይችላል፣ ከፍራንኮ ቫሉታ ጋር ሊሆን ይችላል፣ ሌሎችም ሕጎች በሙሉ ለሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ቀዳዳ ከፍተዋል የሚባሉ ሕጎች መስተካካል አለባቸው ብለን እናስባለን፡፡ ብሔራዊ መታወቂያ ብዙ ነገርን ስለሚፈታ አሁን ለማስጀመር የተጀመሩት ሒደቶችና የሙከራ ሥራዎች ተጠናክሮ ሁሉም ብሔራዊ መታወቂያ መጠቀም መቻል አለበት ብለን እናስባለን፡፡ ሁለተኛ ምንጮቹን ማድረቅ ላይ ትኩረት ማድረግ አንዱ መሠራት ያለበት ነገር ነው ብለን እናስባለን፡፡ የጥቁር ገበያ ምንጮችን ማድረቅ አንዱ ነው፡፡ የጥቁር ገበያ ምንጮች የሚባሉት አንደኛ ቀጥተኛ የጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ የሚባል አለ፡፡ ይኼ አንደኛ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ቱሪስቶች ይዘውት የሚገቡትን ገንዘብ ወደ ባንክ የሚሄድበትን ሙሉ በሙሉ ማቋረጥ ነው፡፡ ከየት ነው ገንዘቡ የሚመጣው? ተብሎ ሲታሰብ ከእነዚህ ምንጮች ነው የሚመጣው (ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ቱሪስቶች ይዘውት የሚመጡት ገንዘብ)፡፡ ስለዚህ እነዚህ ዜጎች ይዘውት የሚመጡትን ለሆቴሎች፣ ለጉብኝት፣ ለሌሎች ወጭያቸው የሚጠቀሙት ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ወደ ባንኮች እንዲገባ አሠራር መዘርጋት አለበት ብለን እናስባለን፡፡ ምክንያቱም ግለሰቦቹ በቱሪስት ስም ይመጣሉ ገንዘቡን ወደ ጥቁት ገበያ ይዘው ይሄዳሉ፡፡
ሁለተኛው በኢትዮጵያ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ በኤምባሲዎችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለደመወዝ፣ ለሥራ ማስኬጃ የሚሰጧቸው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ በባንኮች ማለፍ አለበት ብለን እናስባለን፡፡ ምክንያቱም በተለያዩ የውጭ አገር ኤምባሲዎችና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚሠሩ ኢትዮጵያኖች ደመወዛቸው የሚከፈላቸው እንደሚታወቀው በባንክ ነው፡፡ እዚያ ውስጥ የሚገኙ የውጭ አገር ዜጎች በዶላር የሚከፈላቸው አሉ፡፡ ለተለያየ ሥራ በዶላር የሚፈጸም ክፍያ አለ፡፡ ይኼ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ብር ብቻ እንዲሆንና የውጭ አገር ገንዘቡ ወደ ባንክ እንዲገባ ማድረግ አንድ መፍትሔ ነው፡፡ ከውጭ አገር ወደ አገር ውስጥ ሳያስመዘግቡ የሚገቡም ግለሰቦች ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ ሰዓት ሁሉም ሰው ዲክሌር አድርጎ ያመጣውን ገንዘብ ወደ ባንክ የሚወስድበት እንጂ ወደ ጥቁር ገበያ የማይወስድበትም አሠራር መዘርጋትም መቻል አለበት፡፡ ለሥልጠናና ኮንፍረንስ ወደ ውጭ አገር የሚሄዱ ግለሰቦችም በተመሳሳይ ከኮንፍረንስ የሚያገኙት ገንዘብ በአግባቡ መሥሪያ ቤቶች ወይም የሚልኳቸው አካሎች ስለሚያውቁት ያንን ገንዘብ ወደ ባንክ መግባት አለመግባቱን መረጋጋጥ መቻል አለበት፡፡ በተለያየ መንገድ ከአገር ውስጥ ወደ ውጭ የሚሄዱ ግለሰቦች ለሥልጠናና ሌላም ይዘውት የሚመጡት ገንዘብ ወደ ጥቁር ገበያ ነው ይዘውት የሚሄዱት ይህን ወደ ባንክ የሚሄድበትን አሠራር መዘርጋት መቻል አለበት፡፡
ኢትዮጵያ እንደሚታወቀው ዶላር የምታገኝበት የተለያዩ ዕድሎች አሉ፣ ስላልተጠቀምንባቸው፣ አሠራር ክፍተት ስላለ ነው እንጂ፡፡ ለምሳሌ የአፍሪካ ኅብረት ስብስባ በሚደረግበት ሰዓት የሚመጣው ያ ሁላ ደንበኛ የሚጠቀመው በዶላር ነው፣ ገንዘቡን ግን አፍሶት የሚሄደው በሆቴሎች ለተለያየ ወጭ ነው፡፡ እነዚያ ሆቴሎች ላይ የሚሰበሰቡ ገንዘቦች በሙሉ በአግባቡ ተሰብስበው ወደ ባንክ የማይገቡ ከሆነና የተወሰነው ወደ ጥቁር ገበያ የሚሄድ ከሆነ ይህም ጠንከር ያለ አሠራርና ክትትል ሊደረግበት ይገባል፡፡ አስጎብኝ ድርጅቶችና ሠራተኞች ከጉብኝት የሚያገኙትን ገንዘብ እንዲሁ፡፡ እነዚህንና መሰል ነገሮች ተግባራዊ ቢደረጉ ከዚህ በተሻለ መንገድ የዶላር ክምችታችንን መጨመር ይቻላል፡፡ ሌላውና ዋናው ነገር ውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያኖች ከምን ጊዜው በላይ በሕገወጥ የሐዋላ ዝውውር የሚሳተፉ ሰዎች የሚሰጧቸውን የተወሰነች ትርፍ ትተው በዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላለፊ ድርጅቶች በኩል ቢልኩ ለአገር ትልቅ ጥቅም ነው፡፡ በዚህ ልክም መሠራት አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡
ኢንቨስተሮችና የውጭ አገር ዜጎች በዚህ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ላይ የተሳተፉ አገሮች አስተማሪ የሆነ ዕርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል፡፡ ጠንከር ያለ ቁጥጥር መደረግ አለበት ብለን እናስባለን፡፡ በኢንቨስትምንት ስምና በተለያየ መንገድ ወደ አገር የሚገቡ የውጭ አገር ዜጎች በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ላይ እየተሳተፉ ስለሆነ እነሱ ላይ ከሚመለከታቸው አካሎች ጋር በጋራ በመሆን ዕርምጃ መወሰድ አለበት፡፡ ከዚያ ባለፈ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚታወቀው በርካታ የማጭበርበር ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ በተለይ የማኅበራዊ ሚዲያ በመጠቀም የሚፈጸም የማጭበርበር ወንጀል ከቀን ወደ ቀን የማኅበረሰቡን የኑሮ ሁኔታ እያዛባ ነው የመጣው፡፡ በዚህ ደግሞ የሚሳተፉት አብዛኞቹ የምዕራብ አፍሪካ ዜጎች ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ የውጭ አገር ዜጎች አብዛኞቹ በቱሪስት ቪዛ ነው የሚገቡት፣ በዚህ መንገድ ገብተው ለጉብኝት ሳይሆን ለማጭበርበር ዓላማ የመጡትን በመለየት፣ በተጨማሪም ጊዜያቸውን ጨርሰው በወንጀል ድርጊት የሚሳተፉ የአፍሪካ፣ የእስያ፣ የሌሎች አገሮች ዜጎች ላይ አስተማሪ የሆነ ዕርምጃ መወሰድ አለበት፡፡
ሕግ አስፈጻሚ አካላት አሁን በተጀመረው መንገድ በጋራ መሥራት አለባቸው፡፡ ሌላው የሕግ አስከባሪ አካላት በደኅንነት፣ በፖሊስ፣ ፋይናንስ ደኅንነት ሊሆን ይችላል፣ በባንኮችም አካባቢ ያሉ በሕገወጥ ደርጊት ላይ ተሰማርተው በዚህ ወንጀል ላይ ድጋፍ አድርገዋል ተብለው የሚታሰቡ ሰዎች በሚለዩ ሰዓት እነሱ ላይ አስተማሪ ዕርምጃ መውሰድ አለበት ብለን እናስባለን፡፡