ለውጥና ተለዋዋጭነት የመጀመርያው የኑሮ ሀቅ ነው። ሁሉም በውልደት በዕድገት በበስባሽነት በሟችነት ተከታታይና ተቀጣጣይ አካሄድ ውስጥ የሚያልፍ ነው። ከለውጥ የሚቀር የለም። ሕይወትም እንዲያ ናት። አዲስ መልክና ቅርፅ እያስፈለጋት ወደፊት ትጓዛለች። እንዲያውም ‹‹ሕይወት ድልድይ ናት፤ ስለዚህ ምንም ቤት አትገንባባት›› ይህን ነው መገንዘብ። ሕይወት የለውጥ ፍሰት ናት። አብሮ ነው መፍሰስ። ለውጡን በብልጠት እታገላለሁ ባይ፤ የለውጡ ሰላባ ነው የሚሆን።
ታዲያ ወዳጄ ሆይ የለውጥ ሕግ ‹‹ነፍስም›› ላይ ይሠራል። ከሰውም ሆነ ከምንም ነገር ውስጥ የማይለወጥ ነገር የለም። ያ ‹‹ስም አልባው›› አንድዬና ባለ እውነታው ብቻ ነው የማይለወጥ። እሱ ከለውጥ በላይ ነው። ግን የሕይወት ሁሏ ነገር፤ ሰውም ሆነ ሌላው የለውጥ ተጋላጭና ተገዥ ነው።
- ሪፖርተር መጽሔት (1991 ዓ.ም.)